Saturday, 06 October 2018 10:05

“ከውፍረት ተጠቂዎች 16 ከመቶ ያህሉ የስኳርና የደም ግፊት በሽታ እንዳለባቸው እንኳን አያውቁም”

Written by  መንግስቱ አበበ
Rate this item
(5 votes)

ልጆች ትኩረታቸው ሞባይል ጌም ላይ ስለሆነ፣ የሰውነት እንቅስቃሴ አይሰሩም
ወላጆች፤ ለልጆቻቸው አትክልትና ፍራፍሬ በመመገብ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው

የኢትዮጵያ የምግብና ሥነ ምግብ ባለሙያዎች ማኅበር፤ ከአፍሪካ የሥነ ምግብ ባለሙያዎች ማኅበርና ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር፣ ከመስከረም 21-25 ቀን 2011 ዓ.ም ሲያካሂድ የቆየው 8ኛው የአፍሪካ ሥነ ምግብ ኤፒዲሞሎጂ ኮንፈረንስ ትናንት ተጠናቀቀ፡፡
“ባለድርሻ አካላት ለተቀናጀ ሥነ ምግብ ትግበራ፣ ጥናቶች ለውጤታማ ፖሊሲና ፕሮግራም ቀረፃ ያላቸው ሚና” በሚል መሪ ቃል፤ በካፒታል ሆቴልና ስፓ የተካሄደው ኮንፈረንስ፤ በየሁለት ዓመቱ በደቡብ፣ በሰሜን፣ በመካከለኛ፣ በምሥራቅና በምዕራብ አፍሪካ የሚካሄድ ትልቁ የሥነ ምግብ ጉባኤ ሲሆን በኮንፈረንሱ ላይ በመላው ዓለም የሚገኙ በምግብ ዙሪያ የሚሰሩ ሳይንቲስቶች፣ ተመራማሪዎች፣ ተማሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎችና የዘርፉ ባለሙያዎች መሳተፋቸው ታውቋል፡፡
የኮንፈረንሱ ዓላማ፣ ሳይንሳዊ ጥናቶችን ለማጋራትና ለማሰራጨት፣ የፕሮግራምና የመስክ ጥናቶች ምርጥ ተሞክሮዎችን ማጋራት፣ የሥነ ምግብና የጤና ፖሊሲ ልምድ ልውውጥና ተከታታይ ትምህርት ለጤና ባለሙያዎች ማቅረብ መሆኑን የጠቀሱት የአፍሪካ ሥነ ምግብ ሶሳይቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አምስ ላር፤ በኮንፈረንሱ ወቅት የአፍሪካ ዋነኛ ችግር በሆነው በሥነ ምግብ እጥረት (በተመጣጠነ ምግብ እጥረት) ላይ መነጋገራቸውን፤ ሲምፖዚየምና የማኅበራዊ ኔትዎርክ ትስስር መፈጠሩንም ገልጸዋል፡፡
ሙያተኞች፤ የየአገሮቻቸውን የሥነ ምግብ ፕሮግራም ተግባራዊ እንዲያደርጉ ኮንፈረንሱ አቅም ይፈጥርላቸዋል ያሉት የኢትዮጵያ የምግብና የሥነ ምግብ ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት የሆኑት የምግብ ሳይንስና ሥነ ምግብ ተባባሪ ፕሮፌሰር አቶ ቀልቤሳ ዑርጋ፤ ከአፍሪካ ሥነ ምግብ ሶሳይቲና ከኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር፣ ማኅበራቸው፤ ኅብረተሰቡ፣ የሥነ ምግብ ሳይንስን እንዲያውቅ፣ የሥነ ምግብ ሳይንቲስቶች የአገር ውስጥ ባለሙያዎችን ማግኘት እንዲችሉና አዲስ አበባ የአፍሪካ ከተማ ስለሆነች፣ ሕዝቡ ይህን ተገንዝቦ ጤናማ ምግብ እንዲያዘጋጅ እንደሚያግዙ አስታውቀዋል፡፡
የምናወጣቸው የጥናትና ምርምር መረጃዎች ጥራት ያላቸው ስለሆኑ ፖሊሲዎችን ማስቀየር እንችላለን ያሉት የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ፅጌረዳ ክፍሌ፤ ፕሮግራሞች ፈር ይዘው እንዲሻሻሉና በአገር ደረጃ የተሻለ ውጤት ይዞ እንዲወጣ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ውሳኔዎችን ለመተግበር የሚረዱ መረጃዎችን እንደሚያወጡና በአጠቃላይ በኮንፈረንሱ ላይ ትልልቅ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት እንደሚካሄድባቸው ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር ፅጌረዳ ስለ “ሰቆጣው ቃል ኪዳን (ዲክላሬሽን)” ሲያስረዱ፤ ቃል ኪዳኑ በመቀንጨር ላይ ስለሚያተኩርና የመቀንጨር ችግር በብዛት የሚታየው በሰቆጣ አካባቢ ስለሆነ፣ ሰነዱ የሰቆጣ ዲክላሬሽን መባሉን ጠቅሰው፣ ችግሩ የሚታየው በአማራና በትግራይ ክልሎች ስለሆነ ሁለቱ ክልሎች በፕሮግራሙ መታቀፋቸውንና በ2030 የመቀንጨር ችግርን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የመቀንጨር ችግር ያለባቸው ልጆች፤ በቁመት፣ በክብደት፣ በአዕምሮ ንቃት … ችግሩ ከሌለባቸው ጤነኛ ህፃናት ጋር ሲነጻጸሩ፣ አነስተኛ ቁመት፣ ክብደትና የአዕምሮ ንቃት እንዳላቸው ጠቅሰው፤ መቀንጨር የሚመጣው ከተወለዱ በኋላ ተመጣጣኝ ምግብ ስለማይመገቡ ሲሆን ይህ ችግር ሆድ ውስጥ እያሉም፣ እናትየው የተመጣጠነ ምግብ የማትመገብ ከሆነ፣ ህፃኑ የችግሩ ሰለባ ሊሆን ይችላል ብለዋል፡፡
አገራችን የምትታወቀው በምግብ እጥረት (መቀንጨር) ችግር ነው፤ አሁን ግን በከተሞችና በአንዳንድ የገጠር አካባቢዎች ከመጠን ያለፈ ውፍረት እየታየ ነው ያሉት ዶክተሯ፤ በየትምህርት ቤቱ በተለይም በግል ት/ቤት የሚማሩ ተማሪዎችን ብታዩ፣ ችግሩ ምን ያህል ስር እየሰደደ መሆኑን መገንዘብ ትችላላችሁ፡፡ ከወዲሁ መላ ካልተመታለት፣ እየቆየ ሲሄድ ብዙ ዋጋ ያስከፍለናል፤ ሲሉ አሳስበዋል፡፡
በኢንስቲትዩታችን በሰራነው ጥናት፣ ከመቶ ሰዎች 16ቱ የስኳር፣ የደም ግፊት በሽታ እንዳለባቸው እንኳ አያውቁም፡፡ ሕፃናት ብዙ ጊዜ ጣፋጭ ነገር ስለሚያዘወትሩ፣ የስኳር በሽታ እየታየባቸው ነው፡፡ ወላጆች፤ ይህን ችግር ተገንዝበው ጥንቃቄ በማድረግ፣ አትክልትና ፍራፍሬ መመገብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ልጆች ብዙ ጊዜ ትኩረታቸው ሞባይል ጌም ላይ ስለሆነ፣ የሰውነት እንቅስቃሴ አይሰሩም፡፡ በዚህ የተነሳ የስኳር፣ የልብ፣ የኮሌስትሮል … ችግር ሊከሰት ይችላል፡፡ በሽታው ሲከሰት ህክምናው ውድ ነው፤ ገንዘቡ ኪስ ያራቁታል፡፡ ስለዚህ ጠንቀቅ ማለት ይበጃል ብለዋል- ዶ/ር ፅጌረዳ ክፍሌ፡፡


Read 4545 times