Sunday, 07 October 2018 00:00

አዲሱ የምርጫ ህግ ማሻሻያ ምን ይላል?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(11 votes)

· ምርጫ ቦርድ፤ በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚዎች እኩል ውክልና ይመራል
· ቅሬታዎችን የሚያስተናግድ የምርጫ ፍ/ቤት ይቋቋማል
· በአዲሱ ህግ፤ ጠ/ሚኒስትሩ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢን የመምረጥ ስልጣን የላቸውም

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከገዥው ፓርቲና ከተቃዋሚ ፓርቲዎች በእኩል መጠን በተውጣጡ አባላት እንደሚመራ አዲሱ የምርጫ ህግ ሪፎርም ሰነድ አመልክቷል፡፡
በምርጫ ውጤት ቅሬታ የሚያቀርቡ ተወዳዳሪዎችን ለመዳኘትም በምርጫ ቦርድ ጊዜያዊ “የምርጫ ፍ/ቤት” ይቋቋማል ተብሏል፡፡
የሀገሪቱን የምርጫ ስርአት ለመቀየር የግድ ህገ መንግስቱ መሻሻል እንደሚገባውም ይኸው ለፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት የቀረበው የምርጫ ህግ ሪፎርም ይጠቁማል፡፡
ባለፉት 27 ዓመታት በሀገሪቱ በተደረጉት 5 ብሔራዊ ምርጫዎች ላይ በህገ መንግስቱ ተደንግጎ ያገለገለው የአብላጫ ምርጫ ስርአት፣ ህገ መንግስቱ ተሻሽሎ በቅይጥ ትይዩ አሊያም
በተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ስርአት መተካት እንዳለበት ረቂቅ ሰነዱ ያመለክታል፡፡ ምርጫን በበላይነት የሚያስፈፅመው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ቀደም ሲል ዘጠኝ አባላት የነበሩት ሲሆን በአዲሱ ማሻሻያ ቁጥራቸው ወደ 15 ከፍ ብሏል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቦርዱን ሰብሳቢና ምክትል ሰብሳቢ መርጦ ለሹመት ያቀርባል የሚለውን የቀድሞ ህግ በማሻሻል የቦርዱ ሰብሳቢና ምክትል ሰብሳቢ ከቦርዱ አባላት መካከል በቀጥታ እንደሚመረጡም ይጠቁማል - ረቂቁ፡፡ የቦርድ አባላት የሚመረጡበት የቀድሞ መመዘኛ፤ “ታታሪነት፣ ታማኝነትና ስነ ምግባር እንዲሁም ስራውን ለመስራት የተሟላ ጤንነትና ፍላጎት ያለው” የሚል ብቻ ነበር፡፡ በተሻሻለው ረቂቅ ህግ ግን እነዚህ መመዘኛዎች እንዳሉ ሆነው፤ ምርጫው ከእያንዳንዱ ባለድርሻ አካል በኮታ እንደሚከናወን ይገልፃል፡፡ በዚህ መሰረት፤ ከገዢው ፓርቲ የሚመረጡ አራት አባላት፣ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች በጋራ ስምምነት የሚመረጡ አራት አባላት እንዲሁም ከሲቪክ ማህበራት ሁለት አባላት ይመረጣሉ ይላል፡፡ ከገዢው ፓርቲና ከተቃዋሚዎች የተመረጡ አስሩ የምርጫ ቦርድ አባላት አምስት ተጨማሪ አባላትን ተመካክረው ይመርጣሉ የሚለው ረቂቅ ሰነዱ፤ ከአምስቱ ውስጥ ሦስቱ የግድ ሴቶች መሆን አለባቸው፤ ሁለቱ ደግሞ የህግ ባለሙያ እንዲሆኑ ይጠበቃል ይላል፡፡በዚህ የሪፎርም ሰነድ የቀድሞ የምርጫ ህግ 36 አንቀፆች እንዲሻሻሉ ሀሳብ የቀረበ ሲሆን ከቀረቡት የማሻሻያ ሃሳቦች መካከል በእያንዳንዱ የምርጫ ጣቢያ የሚስተናገደው መራጭ ከ1 ሺህ መብለጥ የለበትም የሚለው፣ ከ4 ሺህ በሚል እንዲሻሻል፤ በምርጫ ክልሉ ቢያንስ 6 ወር የኖረ በመራጭነት መሳተፍ ይችላል የሚለው ቢያንስ አንድ ዓመት በምርጫ ክልሉ የኖረ በሚል እንዲሻሻል የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡ አንድ እጩ ለምርጫ በግል ለመወዳደር አንድ ሺህ የድጋፍ ፊርማ ማሰባሰብ ይኖርበታል የሚለው የቀድሞ ድንጋጌ፤ ሁለት ሺህ በሚል እንዲሻሻልም ሃሳብ የቀረበ ሲሆን፤ በምርጫ ውጤቱ ቅሬታ ያለው፤ አካል ቅሬታውን የሚያቀርብበት “የምርጫ ፍ/ቤት” በምርጫ ቦርድ በረቂቅ ሰነዱ ላይ ተገልጿል፡፡ የምርጫ ፍ/ቤቱ ዳኞችም የሚመረጡት በምርጫ ቦርድና በተወዳዳሪ ፓርቲዎች ስምምነት ሲሆን ሹመታቸው በፓርላማው ይፀድቃል ተብሏል፡፡ በምርጫ ፍ/ቤቶቹ ውሳኔ ቅሬታ ያለው ወገን ለመደበኛው ጠቅላይ ፍ/ቤት አቤቱታውን ማቅረብ እንደሚችልም በረቂቁ ህግ ተደንግጓል፡፡




Read 8876 times