Saturday, 29 September 2018 14:47

ተዝካር

Written by  ከቃል ኪዳን
Rate this item
(13 votes)

ትናንትና የእናቴን ሁለተኛ ሙት ዓመት ተዝካር አወጣሁ፡፡ ከዚህ ወር መግቢያ ጀምሮ በተደጋጋሚ በህልሜ እየመጣች ስታስጨንቀኝ ነበር፡፡ ተዝካሯን እንዳወጣላት ማስታወሷ እንደሆነ ገብቶኛል!፡፡ ግና የሙት ዓመቴን ይረሳዋል ብላ በማሰቧ በጣም ተናድጃለሁ፡፡ እናቴ ትሙት በጣም ታዝብያታለሁ። በርግጥ እናቴም ቢሆን እውነት አላት፡፡ ደሞዜን የተቀበልሁ ዕለት ኪሴ ካልጎደለና ሰዓቱ ካልነጎደ በቀር ወደ ቤት እንደማልመለስ ጠንቅቃ ታውቅ ነበር፡፡ ሞታም አልረሳችውም ማለት ነው፡፡
እናቴ ተዝካሬን ማውጣቱን ይረሳዋል ብላ በማሰቧ ብናደድባትም፤ የሙት ዓለም አጣዳፊ ጉዳዮችን እርግፍ አድርጋ ጥላ እኔን ስለተዝካሩ በማስታወስ በመጠመዷ አዘንሁላት፡፡ መቼም የእኔ እናት ሆኗ መፈጠሯ ፈርዶባታል!፡፡ በህይወት እያለችም ለቤት ወጪ፤ ሞታም ለተዝካሯ የእኔን ደሞዝ ቀን እየጠበቀች ማስታወስ ዕጣ ክፍሏ ሆኗል ማለት ነዉ፡፡
እናቴ አሳዘነቺኝ፡፡ ሰባት ዓመቷ እስኪሞላ ተዝካሯን ማውጣት እንደማልረሳና ስለ ተዝካሯ ሳታስብ እንድትቀመጥ መንገር ብችል ፈቃዴ ነበር። በህልም መታየት፤ ህልም እንደ ማየት ቀላል ሥራ አይመስለኝም። በተለይ ደግሞ ለእንደኔ ዓይነቱ ወደ ቤት መግቢያውና መኝታ ሰዓቱ በቅጡ ለማይታወቅ አውደልዳይ ጎረምሳ፤ በህልም ለመገለጥ መሞከሩ አድካሚ ሥራ ይመስለኛል፡፡
በነገራችን ላይ የቅርብ ዘመዳቸውን በህልም እየመጡ በሚጎበኙ ሙታኖችና በተዝካር መካከል ስላለሁ፣ ዝምድና የነገረችኝ አያቴ ናት፡፡ አያቴ እየሱስ የሚለዉ ፊልም ላይ ያለችውን ‹ሁሉም ከትርፉ ሰጠ፤ ይህቺ እመበለት ግን ከችግሯ ሰጠች› የተባለችውን ሴት ትመስለኛለች፡፡ በርግጥ አያቴ ፊልሙ ላይ ካለችው ሴትዮ አንጻር ንቁና ቀልጣፋ ናት፡፡ ወንጌል ላይ ያለችውን እውነተኛ ሴትዮን ስላላየሁ፤ ከእሷ ጋር ማነጻጸር ግን አልችልም፡፡
የሆነ ወቅት ላይ በጣም እወደው የነበረ አጎቴ፤ በእርግጥ አጎትነቱ ለእናቴ ነው፤ ከሞተ ከዓመታት በኋላ ድንገት በህልሜ እየመጣ እንቅልፌን አስጨናቂ አደረገው፡፡ አጎቴ በህይወት እያለ በጣም የተረጋጋና እግሩን እንኳን በልክ እየሰነዘረ የሚራመድ ሰው ነበር። አረማመዱን ያያ ሰው፣ መድረሻዎቹ ሁሉ በእርምጃ ተሰፍረው የተሰጡት ሊመስለው ይችላል፡፡ በዛን ሰሞን በማያቸው ህልሞች ግን አጎቴ በሆሊውድ ፊልም ላይ ዓለምን እራሳቸው አጥፍተው፤ እራሳቸው ሊያድኗት እንደሚሯሯጡት ልዕለ ኃያላን፣ ፈጣንና ቀልጣፋ፤ ሲያሻው አንድ አጁን ደረቱ ላይ ለጥፎ፤ ሌላኛውን ወድሮ አየር እየሰነጠቀ መብረር የሚችል ሆኖ ነበር፡፡
ህልሙ ሲደጋገምብኝ፣ ለአያቴ ሄጄ፣ ወንድሟ በህልሜ እየመጣ አላስተኛ እንዳለኝ ነገርኋት፡፡ አያቴ ከት፣ ከት ብላ ሳቀች፡፡ አነጋገሬ ድሮ አጥፍቼ ሲቆነጥጠኝ መጥቼ፣ ለእሷ ነግሬ እንደማስቆጣው፤ አሳርፊልኝ የሚል ድብቅ መልዕክት ነበረው። ሳቋን ሳይ ህልሙን በስሞታ መልክ ማቅረቤ ትንሽ አሳፈረኝ፡፡ እውነት ለመናገር የአጎቴ እንደዛ መለወጡ በጣም አስፈርቶኛል። በጣም ሥነ-ሥርዓት ያለውና የተረጋጋ ሰው ከመሆኑ የተነሳ፣ ከጦሩ በጡረታ ተገልሎ እንኳን፣ በሲቪል ልብስ ወታደራዊ አካሄድ የሚሄድ ምስኪን ሰው ነበር፡፡ በአነጋገሬ ባፍርም፣ አያቴ እንደዛ መሳቋ አናደደኝ። ቆይ ወንድሟ ጡረታ ወጥቶ እንኳን በወታደርኛ ይራመድ ከነበረ፣ እኔ እሱ ከሞተ በኋላ እንደ ልጅነቴ፣ እሷ ጋ መጥቼ፣ ስለሱ ስሞታ ባቀርብላት ምን ይገርማል?
ህጻን እያለሁ ህልም ሳይ ትልልቆቹ እንደሚያደርጉት፣ ሮጬ ሄጄ፣ እንድትፈታለኝ ህልሙን እነግራት ነበር። የምነግራትን ከመጀመርያ እስከ መጨረሻ በጥሞና ሰምታ ከጨረሰችና አንዳንድ ጥያቄዎችን ጠይቃኝ ሁሉን ካጣራች በኋላ፤
‹‹ሂድ! አንተ እራስህ ህልም ነህ፡፡›› ብላ ታባርረኝ ነበር፡፡ ያሁኑ ሳቋ ግን ‹ሂድ!› ብሎ ከማባረሩ በላይ ይከፋል፡፡
‹‹እርቦት ነው!›› አለችኝ፤ ሳቋን ገትታ፡፡
እርግጠኝነቷ አጎቴ እርቦት ሆዱን ሲፎክት ያየችው ያስመስልባታል፡፡ አያቴ፤ ሙታንን ወይ መናፍስትን የተመለከተ ጥያቄ ከተጠየቀች፣ ግማሽ ደቂቃ እንኳን ያህል ሳታስብ፣ እርግጠኛ የሆነ ምላሽ ነው የምትሰጠው፡፡
‹‹ማህበሬን ባወጣሁ በአሥራ አምስት ቀኑ…..ኧ! በስድስት ነብሱ ወጣች….በሰባት ተቀበረ!…ሰባት ነገም አይደል?›› አለችኝ፤ ጣቷን እየቆጠረች፡፡
አያቴን ጨምሮ የድሮ ሰዎች ትምህርት ሳይማሩ ቁጥር መቁጠር መቻላቸው በጣም ያስገርመኛል፡፡ በተለይ ገንዘብ ሲደምሩና ሲቀንሱ ሳይ እደነቃለሁ። ምናልባት ማንበብና መጻፍ ያን ያህል አስፈላጊ ስላልሆኑ ይሆን እንዴ እንደ ቁጥር ዕውቀት በተፈጥሮ ያልተሰጡን?
‹‹ነው እንዴ?›› አልኋት፤ በጥያቄ ዓይን እያየኋት።
እኔ አጎቴ መሞቱን እንጂ የሞተበት ቀንን አላስታውስም፡፡ በርግጥ እሱ የሞተ ቀን ያፈሰስኩትን ያህል እንባ ለእናቴ እንኳን አላፈስስኩም፡፡
‹‹ቆይ ነገ ሰባትም አይደል እንዴ?›› በጥያቄ አፈጠጠችብኝ፡፡
‹‹አዎ ሰባት ነው፤ ግን እሱ በሰባት መሞቱን አላውቅም›› አልኳት፡፡
እኔ ጥሎብኝ የሰውን የልደት ቀንም ሆነ የሞት ቀንን ማስታወስ አይሆንልኝም፡፡ ቆይ እናቴ፤ ይሄን አመሌን ስለምታውቅ ይሆን እንዴ፣ ሰሞኑን በህልሜ እየተመላለሰኝ፣ ዕለተ ሞቷን ልታስታወሰኝ የሞከረችዉ? የእሷን የሞት ቀን ግን እንዴት እረሳዋለሁ?
የእናቴን ዕለተ ሞት ከድንገተኛ ህልፈቷ በተጨማሪ የሚያስታውሰኝ፤ በዛች ዕለት ከሶስና ጋር ተጣልተን ከሁለት ወር በላይ መኳረፋችን ነዉ፡፡ ሜንጦዋ ፍቅረኛዬ፤ የዛን ዕለት ምሽት ሰፈሯ አካባቢ እንድንገናኝ ቀጥራኝ ስለነበር ወደዛ አመራሁ፡፡ ከቤቴ ስወጣ እናቴ ትንሽ ህመም ስለተሰማት ወደ መኝታ ቤቷ ገብታ አረፍ እንዳለች አስታውሳለሁ፡፡ ወደ ሶስና ሠፈር ስቃረብ ደውዬ መድረሴን ነግርኋት፡፡ እሷ ግን መፍጠኔን ነግራኝ፣ የጀመረችዉን ዮጋ ሠርታ እስክታበቃ፤ ለአሥራ አምስት ደቂቃ ያህል በትዕግስት እንድጠብቃት ነገረችኝ፡፡ ደግሞ እንዲህ በማለቷ እንዳልናደድ፣ ሦስቴ በረጅሙ ተንፍሼ በመረጋጋት፣ ስሜት ውስጥ ሆኜ እንድጠብቃት አሳሰበችኝ፡፡ ይሄ ዮጋ የምትለውን ነገር እና ቅጠል በሊታነቱን ከጊዜ ወዲህ ያመጣችው ነገር ነዉ፡፡
በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ሆኜ ከእነሱ ግቢ አልፎ ካለች ሱቅ ሄጄ፣ ማስቲካ ገዝቼ እያላመጥኩ ቆምኩ፡፡ ማስቲካውን የገዛሁት ባለ ሱቁ ዝም ብሎ በራፌ ላይ ቆመ እንዳይለኝ ይሁን ወይ የአፌን ጠረን ለመቀየር፣ ዛሬም እርግጠኛ አይደለሁም። ወዲያው ከየት መጣ ሳይል ከባድ ዝናም ጣለ። እንዳረጋገጥሁት ከሆነ፣ እናቴ ያረፈችው በዛች ቅጽበት ነው፡፡ እናቴ መልካም ሰው ነበረች፡፡ እግዚሀሩ መልካም፣ መልካም ሰዎችን ሲወስድ፣ ለምን የሰማዩን መስኮት እንደሚከፍት እንጃ። ክፉዎቹ አይተው እንዳያዝኑ፤ ደጋጎቹ በመስኮት በኩል ይሆን እንዴ የሚገቡት?
ዝናብንና የመልካም ሰዎችን ሞት፣ ምን እንደሚያገናኘዉ እስከ ዛሬ ድረስ መልስ ማግኘት አልቻልኩም፡፡ አያቴን ብጠይቃት የሆነ መልስ እንደማታጣለት እርግጠኛ ነኝ፡፡ የድሮ ሰዎች አላውቅም ማለት ሞታቸዉ ነዉ፡፡ የድሮ ሰዎች የሚያውቁት አለማወቃቸውን ሳይሆን አላውቅም አለማለትን ነው። አንድን ጥያቄ በተለያየ ጊዜ ቢጠየቁ የተለያየ ዓይነት መልስ ሊመልሱ ይችላሉ። ደግሞ እኮ መልሱም ይይዝላቸዋል፡፡ ሳስበው መልሱን ከሚመልሱበት የራስ መተማመንና ከእምነታቸው ጽናት የተነሳ የሚሰጡትን ግምታዊ ምላሽ፤ ትክክለኛ መልስ እንዲሆን የሚያስገድድ አንዳች ኃይል አላቸው፡፡
የዝናቡ ወጨፎ ከጫማዬ አንስቶ እጉልበቴ ድረስ አበሰበሰኝ፡፡ ዝናብ እንደመታኝ ግን አልተሰማኝም፡፡ ሰው ግን አናቱ በዝናብ ካልራሰና ፎረፎሩ ካላሳከከዉ በስተቀር ዝናም የመታው የማይመስለው ለምንድን ነዉ? ሶስናንም የወቀስኳት አቁማኝ ስለጠፋች እንጂ ዝናብ ስላስመታችኝ አልነበረም፡፡ ሶስና ሳትመጣ ቀረች። ደጋግሜ ብደውልላትም ስልኬንም አላነሳችም። እናቴ በሞተች በሰማንያዋ፤ ሃውልት ምርቃቱ ላይ መጥታ፣ ከታረቅን በኋላ ቢያንስ ለምን ስልኳን እንዳላነሳች ስጠይቃት፣ በጊዜው ጥልቅ ተመስጦ ውስጥ እንደነበረችና ስልኳ ሲጠራ እንዳልሰማችው ነገረችኝ፡፡
በሶስና መቅረት እንደተናደድኩ ወደ ቤት አመራሁ። ንዴቱን ሶስና እንደመከረችኝ፣ ሦስቴ በረጅሙ በመተንፈስ ለማስለቀቅ ብሞክርም እንዳሰብኩት አልሆነልኝም፡፡ ምናልባት ይሄ ነገር የሚሠራው፣ ንዴትን ለመከላከል እንጂ፣ንዴትን ለማጥፋት ባይሆንስ? ምናልባት ደግሞ ሦስቴ በረጅሙ ከመተንፈስ በላይ የሆነ ንዴት ተናድጄ ይሆናል፡፡
ከመኖርያ ቤቴ አቅራቢያ ስደርስ እናቴ አርፋ ኖሮ፣ ሰው ሲላቀስ አገኘሁ፡፡ በፍቅረኛዬ የተፈጠረብኝ ንዴት ስላልበረደለኝ፣ በእናቴ መሞት ደግሞ ይበልጥ ተናደድኩ፡፡ ህልፈቷ ድንገተኛ ቢሆንም ሀዘንና ድንጋጤው፣ ሶስና ከሰጠችኝ ንዴት በላይ ሆነው መውጣት አልቻሉም፡፡ ደግነቱ ዘመድ አዝማድ የዛን ምሽት ያላለቀስኩት፣ በድንጋጤ መስሏቸው አልታዘቡኝም፡፡ በነጋታው ወደ ራሴ ስመለስና በለቅሶ ብዛት እራሴን ስስት ደግሞ ሁሉ ለኔ አዛኝና አሳቢ ሆኖ ቁጭ አለ፡፡ ከሰው አፍ ተረፍኩኝ፡፡
አንዳንዴ እውነቱን አውቀውት ቢሆን ኖሮ፣ ስለኔ ምን ዓይነት ስሜት ይሰማቸው ነበር ብዬ እራሴን እጠይቃለሁ? እርግጠኛ ነኝ፤ እናቱን ካገባው ይሁዳ በላይ ሊጠሉኝና እርም ሊያደርጉኝ ይችሉ ነበር፡፡ እናቴ ግን ትረዳኛለች፡፡ በአጸደ ሞት ያሉ ነብሳት፤ በአጸደ ሥጋ እንዳሉት እውነትን እንዳይረዱ የሚያግዳቸው አካል የላቸውም፡፡ እሷ በወቅቱ ያደረብኝ የንዴት ስሜት፤ ሀዘኔን መግለጽ እንዳልችል አድርጎኝ እንጂ ሞቷ ሳይሰማኝ ቀርቶ እንዳልሆነ ጠንቅቃ ታውቃለች። ምናልባትም ነገ ከንዴቴ ስመለስና እሷን ከጎኔ ሳጣ የሚፈጠረዉን አስባ አዝናልኝም ይሆናል፡፡ እኔ ለእሷ ማልቀስ ሳልጀምር እሷ ለኔ አልቅሳልኝም ይሆናል። ምድራውያኑ ዘመድ አዝማዶቼ ግን ሊወቅሱኝና እንባቸውን ተገን አድርገው፣ የመጀመርያዋን ድንጋይ ሊወረውሩብኝ እንደሚሽቀዳደሙ እርግጠኛ ነኝ፡፡
ሀዘን ሁሉ በእንባ ይገለጻል የሚል እምነት የለኝም። ደግሞ ለእናቴ ባላለቅስስ እንኳን ለምን ይወቅሱኛል? እናቴ ከኔ የበለጠ ለማን ትቀርባለችና ነዉ ሌላው ለማሽቃበጥ የሚሰናዳው? ደግሞ ማነው ለሞተ የግድ መለቀስ አለበት ያለው? የእንባስ ትክክለኛ ትርጉሙ ምንድነው? ሴቶችና ወንዶች ለምን እኩል የማልቀስ ተሰጥዖ አልተሰጣቸውም? ሴቶች በእልልታ፣ ወንዶች በጭብጨባ እንደሚባለው፤ ሴቶች በእንባ፣ ወንዶች በምንድን ነው የሚባለው? እዉነተኛውና የአዞው እንባስ እንዴት ነው የሚለየው?
የሰው ልጅ በተፈጥሮ እራስ ወዳድ ነው፡፡ የሚያለቅሰው ለሚያጎድልበት እንጂ ለሞተ ሁሉ አይደለም፡፡ ምናልባት ሙታን በሞታቸው ቅጽበት ለኛ ለምንኖረው፣ እንደማያለቅሱልንስ በምን እናውቃለን? እኛም ለእነሱ ስናለቅስ፤ እነሱም ለእኛ ሲያለቅሱ እግዜሩ፣ እንደማይስቅስ ማን ያውቃል?
አያቴ ሙታኖች ሲርባቸው፣ የሚወዱትን ሰው በህልም እየመጡ እንደሚታዩና ተዝካር እንዲያወጣላቸው እንደሚያሳስቡ አስረዳችኝ። ለወንድሟ ስንቅ ይሆን ዘንድ እሷ ንፍሮ ልትቀቅልለት፣ እኔ ደግሞ በስሙ ምጽዋት እንድሰጥ ተስማምተን፣ ለንፍሮ እህል መግዣ የሚሆን ገንዘብ ሰጥቼአት ሄድኩ። አንድ ያልገባኝ ነገር ግን አጎቴ በህይወት እያለ ንፍሮ እንደማይወድ እያወቀች፣ ንፍሮ ልትቀቅልለት ማሰቧ ነዉ። ቢቀቀልም እሱ አይበላው ብላ ይሆን? እንዲህ ከሆነ ዝክሯ እንደቃየን መስዋዕት ቁጣ እንዳያስነሳ ያሰጋል!፡፡ ለነገሩ እሷ ምናለባት፤ ዞሮ ዞሮ፣ ወንድሟ አላስተኛ የሚል እኔኑ ነዉ፡፡ ወይንስ የዚህ ዓለም ንፍሮ በሞት ዓለም ውስጥ ምስር ወጥ ማለት ነው? አጎቴ ሲበዛ ምስር ወጥ ይወድ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡
ደግነቱ አጎቴ ንፍሮውንም ምጽዋቱንም አድርገን ተዝካሩን ካወጣንለት በኋላ ጠፋ። አያቴ ያለችው ነገር በቀላሉ እውነት መሆኑን ማመን ስላልፈለግሁ፣ ለአጎቴ ተጨማሪ ዕድል ለመስጠት በሚል አብዝቼ መተኛት ያዝኩ፡፡ አጎቴ ግን የለም። የአያቴ እውቀቶች መገኛ ምን እንደሆነ ሳስብ ይገርመኛል፡፡ በጣቷ ቁጥር ከማስላት ውጪ ማንበብና መጽሐፍ አትችልም፡፡ ነገር ግን ለአእምሮ የተወሳሰቡ ነገሮችን እንደ ሠርክ ጉዳይ ቀለል አድርጋ ዓይታ፣ እንዲህ ቢሆን ብላ የምትሰጣቸው መፍትሄዎች ሲይዙ ሳይ እገረማለሁ፡፡ በተለይ ከሙታን ጋር የተያያዙ ነገሮችን፡፡ ግን በሞትና በህይወት መሀል ያለው መስመር ውፍረቱ ምን ያህል ነው? ዕድሜ ሲጨምር የሞትን መንደር አጥር አሻግረን የምናይበት ቁመታችን ይጨምራል እንዴ? ምናልባት መልሱን በዚያ እየሾፈች ከሆነ፡፡
ትናንትና የእናቴን ተዝካር አወጣሁላት፡፡ ከተዝካሩ በኋላ እናቴ በህልሜ እንደማትመጣ እርግጠኛ ሆኜ ነው ወደ መኝታዬ የሄድኩት። እኔም የአያቴ ጥበብ ተካፋይ ሆኛለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ ነገ ከዛች ከሶስና ጋር ተጋብተንና ወልደን ስንኖር ድንገት ብትሞትና ልጄን በህልሙ እየመጣች ብታስቸግረዉ፤ ለልጄ ‹እናትህ እርቧት ይሆናል› ብዬ ማጽናናቴ አይቀርም። ድሮስ ቅጠል ስትበላ ኖራ ላይርባት ነው እንዴ? ኧረ እንደውም፣ በየወሩ እየተመላለሰች፣ እርቦኛል ልትል ሁሉ ትችላለች፡፡
መቼም ሶስናን፣ ይሄ አትክልትና ዮጋዋ አንድ ቀን ሳይደፋት አይቀርም፡፡ እሷ ግን ጭራሽ እኔኑ እረጅም እድሜ መኖር ከፈለግህ ስጋና ቅቤውን ትተህ፣ ቅጠል ብትበላ ይሻልሀል እያለች ትመክረኛለች፡፡ ሰላም ከፈለግህ እግርህን አነባብረህ፤ ዓይኖችህን ጨፍነህ ተቀመጥ ትለኛለች፡፡
ሶስናን እህ ብዬ ካደመጥኳት ብዙ የማይገቡኝን ነገሮች አውርታኝ፣ ልታሳምነኝ ጫፍ ትደርሳለች፡፡ ከዛ አያቴ ወደ ህሊናዬ ትመጣና ቅጠል ከመብላትና እግር አነባብሮ ከመቀመጥ ትታደገኛለች፡፡ አያቴ በዕድሜዋ ቀጋ እንጂ ዮጋ አታውቅም፡፡ እግሮቿን አጥፋ እንጂ አነባብራ ተቀምጣም አታውቅም። ለማሸለብ ካልሆነ በስተቀር ዓይኖቿን ከድና የምታውቅ አይመስለኝም፡፡ ግን የእድሜ ባለጠጋና ደስተኛ ሴት ናት፡፡ በህይወቷ በጣም የሚያስደስታት ሥራ ቅቤ ማንጠር ነው፡፡ ይህን ሳስብ ሶስና ያልገባት አንድ ነገር እንዳለ ይሰማኛል። እሷ እንኳን ገብቷት ቢሆን፣ ከእኔ መረዳት በላይ የሆነ ነገር እንዳለ ይሰማኛል፡፡ ምናልባትም አንድ የህይወት ጥያቄ፤ ብዙ መልሶች ይኖሩታል፡፡ ወይ አንድ መልስ ብዙ ወደ እሱ የሚወስዱ አቋራጮች ይኖሩታል፡፡ ለምሳሌ ሁለት እና ሁለትን ደምሮ፣ አራት ለማምጣት፣ በጭንቅላት ማስላት፣ በወረቀት ማስላት፣ ጠጠር ወይ ባቄላ ተጠቅሞ ማስላት፣ የሞባይል ስልክ ወይ የሂሳብ ስሌት መሥርያ ማሽን ተጠቅሞ ማስላት ይቻላል፡፡ ዉጤቱ ግን አንድ ነዉ፡፡
እናቴ እንደ አጎቴ በህልሜ መምጣቱን ታቆማለች ብዬ ባስብም ሌቱን በህልሜ፤ መኝታዬ አካባቢ፣ አየር ላይ በክንድ እርቀት ሆና ስታየኝ አየሁ፡፡ ከወገቧ በታች ያለው አካሏ ደመና ውስጥ እንደተቀበረ አይታየኝም፡፡ ግን እርግጠኛ ነኝ አካሏ በህይወት እንዳለችው ሞንዳላ አይደለም። ምናልባት እሷም አትክልትና ዮጋ ጀምራ ይሆናል!፡፡ ምናልባትም አትክልትና ዮጋ ለዛኛዉ ዓለም የተፈጠሩ ይሆናሉ፡፡ እናቴ አገጯን በእጇ ደግፋ፤ ቁልቁል ስታየኝ አደረች፡፡ ዓይኖቿ ሰሞኑን ካየኋቸዉ በላይ ንቁህና ብሩህ ናቸዉ፡፡ ተዝካሩን ማውጣቴ የፈጠረው ለውጥ አለ መሰለኝ፡፡ እረሀቧን አሸንፋለች!፡፡
ጠዋት እንደነቃሁ ቀጥታ ወደ አያቴ ቤት ሄድኩኝ፤ ቤቷ ስደርስ ቀድማ ተነስታ ቤተ ክርስቲያን ለመሄድ ፈልጋ ብርዱን ስለፈራችው ተቀምጣ፣ ነጠላ ስትቋጭ አገኘኋት፡፡ ብርዱ ላይ የዚያ እርኩስ እጅ ይኖር ይሆን እንዴ? ስል አሰብኩ። አያቴን ከቤተ ክርስቲያን ያስቀራት ብርዱ ነው ወይስ ብርድ መቋቋም እየተሳነው የመጣው አካሏ? ብርዱ ካልሆነ እኔ እንዴት ብርዱን አሸንፌ እሷ ዘንድ መጣሁ? ቤተ ክርስትያን ለመሳለም ለመሄድ ብነሳ፣ እንደሷ በርዶኝ መሄዱን እተወው ነበር ወይስ አሸንፌ እሄድ ነበር? ግራ የሚያጋባ ነገር ነዉ፡፡
ከአያቴ ጋር ጉንጭ ለጉንጭ ተሳስመን ስናበቃ አጠገቧ ቁጭ አልኩ፡፡ ከምትቋጨው ነጠላ ላይ ዓይኖቿን ነቅላ ማታ እሷ ወደ ቤቷ ከተመለሰች በኋላ ጠበል ሊቀምስና ነፍስ ይማር ሊል የመጣ ሰው እንዳለ ጠየቀቺኝ፡፡ ከመጡት ሰዎች ታውቃቸዋለች ያልኳቸዉን አንድ ሁለቱን ነገርኳት፡፡
‹‹ተባረኩ! ቆንጆ አድርጋችሁ ነው ያወጣችሁላት፡፡ እሷንም ነብሷን ይማረዉ፡፡……›› አለችና ተከዘች፡፡ ትንሽ ቆይታ፣ “እግዜሩ እኔ እናትየውን ቁጭ አድሮጎ፣ ልጄን ወሰደ” እያለች ማለቃቀስ መጀመሯ ስለማይቀር ብዬ፣ በፍጥነት የመጣሁበትን ጉዳይ አብራርቼ ነገርኳት፡፡ አጎቴ ተዝካሩ ከወጣለት በኋላ የዚያኑ ዕለት እንደጠፋና፣ እስካሁንም በህልሜ ዓይቼው እንደማላውቅ ነግርያት፣ እናቴ ለምን ደግማ እንደታየችኝ ጠየቅኋት፡፡
‹‹ከአንድ ክፉ ነገር ልትጠብቅህ ነዉ!›› አለች አያቴ፣ በእርግጠኝነት፡፡ ምላሿ ፈጣን ነበር፡፡
‹‹የምን ክፉ ነገር?›› አልኳት በመገረም፡፡
ሰዉ እኔን ለመጉዳት ምንም ምክንያት ይኖረዋል ብዬ አላስብም፡፡ እንዲያ ቢሆን እንኳን ግርማ ሞገሴ፣ ማጅራት መቺዎችን ሳይቀር አንገታቸውን ደፍተው፣ በክብር እንዲያሳልፉኝ የማድረግ አቅም እንዳለው ነው የሚሰማኝ። ምናልባት የማልፈልገውን ነገር በማድረግ ልትጎዳኝ የምትችለው ያቺ ሜንጦ ሶስና ናት። እሷ የምታቀርብልኝን ቅጠል የመብላት ሃሳብ ደግሞ በፍጹም የምቀበለው አይደልም፡፡ ታዲያ እናቴ እንደ መኝታ ቤቴ አምፖል፣ አልጋዬ አናት ላይ ተሰቅላ ከምን ይሆን የምትጠብቀኝ? ካልጋ እንዳልወድቅ?
‹‹ልታመሰግንህ ነዉ!›› አለችኝ አያቴ፣ ድንገት አንድ ነገር ትዝ እንዳላት፡፡ ከመቼው ከ‹ልትጠብቅህ ነዉ!› ወደ ‹ልታመሰግንህ ነዉ!› እንደተሸጋገረች ደነቀኝ፡፡ ደግሞ እኮ ደረቷን ነፍታ ነዉ በእርግጠኝነት የምታወራዉ፡፡ በመገረም አፌን ያዝሁኝ፡፡
‹‹ልጄ የኔም ቀን ሲደርስ እንዲሁ አስታውሰህ ተዝካሬን አውጣልኝ፡፡ በሰማይ ቤት እንዳታስረበኝ! እኔም እየመጣሁ አመሰግንሀለሁ!››
‹‹አያቴ ምን ማለትሽ ነዉ? ለምን በራስሽ ላይ ታሟርቻለሽ?››
በራሷ ላይ ከማሟረቷ በላይ ያስጨነቀኝ፣ ከሞተች በኋላ ባሉት ሰባት ዓመታት፣ ዕለተ ሞቷን አስታኮ፣ የማያቸው ህልሞች ናቸው፡፡ ቢያንስ ከሙት ዓመቷ በፊት ሰባት ቅን ቀድማ መታየት ብትጀምር፣ በሰባት ዓመት ውስጥ አርባ ዘጠኝ ጊዜ በህልሜ ልትመጣ ነው ማለት ነው፡፡ ‹ምስጋናዉ› ወይ ደግሞ ‹ጥበቃዉ› ከተጨመረ ደግሞ ከአርባ ዘጠኝ አለፈ ማለት ነው፡፡ አሳ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል አሉ፡፡
‹‹ግን አያቴ ቁልቁል አፍጥጣ እያየችኝ ነበር እኮ! ምስጋና እንደዚህ ነዉ እንዴ?››
‹‹ናፍቀኻት ነው ልጄ! አይዞህ አታስብ!›› አለቺኝ አሁንም፤ እርግጠኛ ሆና፡፡ ጥበቃ-ምስጋና-ናፍቆት!
ትንሽ ከቆየሁ ሌላ እርግጠኛ የሆነችበትን መልስ ትሰጠኛለች ብዬ ስለሰጋሁ ግንባሯን ሳምኳትና ወጣሁ። ከአያቴ ግቢ ወጥቼ የኮብልስቶኑን መንገድ ይዤ ወደ ዋናው አስፋልት መውረድ እንደጀመርኩ አንድ ነገር ትዝ አለኝ። ልጅ እያለሁ አያቴና አሁን በህይወት የሌሉት ጓደኞቿ ተሰባስበው ቡና ሲጠጡ፤ አያቴ ቡና የጠጡበትን ስኒ እየተቀበለች ውስጡ ያለዉን አተላ ሰሃን ላይ ትደፋና አተላው የስኒው ግድግዳ ላይ የሠራውን ቀጭን መስመር እያነበበች የዕለቱን ዕጣ ፈንታቸውን ትነግራቸዋለች፡፡ አልፎ አልፎ ሲሳይ እንደሚያጋጥማቸው ከመናገሯ ውጪ ለሁሉም፣ ሁልጊዜም በእርግጠኝነት ‹ዛሬ እረዥም መንገድ አለብሽ!› ነበር- የአያቴ የንባቧ ውጤት፡፡ አሮጊቶቹ ከሰፈር ወጥተው ባያውቁም የሚነገራቸዉን ነገር አምነው ነበር የሚቀበሉት፡፡ እስኪ ይምሽና…ልተኛና ዛሬ ደግሞ ምን እንደሚፈጠር ልየው፡፡ መቼም አያቴ ያለችዉ ነገር ጠብ አይል፡፡

Read 3488 times