Print this page
Saturday, 29 September 2018 14:39

ኢንዱስትሪዎች ጠፍንጎ ካሰራቸው ችግር ይላቀቁ ይሆን?

Written by  መንግስቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

 አንዲት ሀገር የምትበለፅገው በኢንዱስትሪ ነው። ለዚህ ነው ምዕራባውያን ከ300 ዓመታት በፊት የኢንዱስትሪ አብዮት አካሂደው በየአገሮቻቸው ኢንዱስትሪዎችን ያቋቋሙት፡፡ የእኛ ኢኮኖሚ ግን ከብዙ ሺህ ዓመታት ጀምሮ የተመሠረተው በግብርና ላይ ነው፡፡ ያውም ዝናብ ጠብቀን፡፡ አንድ ዓመት ዝናብ ቢጠፋ የሚፈጠረውን እናውቃለን፡፡ የከተማው ሕዝብ፣ አርሶ አደሩና ከብቱ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ አገሪቷ ትራባለች፡፡
አሜሪካ ከ280 ሚሊዮን በላይ የሆነውን ሕዝቧን መግባና ተርፏት ኤክስፖርት አድርጋና እኛን ለመሳሰሉ ድሃ አገሮች የምትረዳው ከሕዝቧ፣ 5 በመቶዎቹ ብቻ በሚያመርቱት ሰብል ነው፡፡ እርሻው ታድያ እንደ እኛ አገር በበሬ ጫንቃ የሚታረስ አይደለም። ዘመናዊና ሜካናይዝድ ነው፡፡ የሚታረሰው በትራክተር ነው፡፡ የሚዘራው፣ ፀረ-አረምና ፀረ ተባይ መድኃኒቶች የሚረጩት በዘመናዊ መሳሪያዎች ነው፡፡ የሚታጨደውም በኮምባይነር ነው፡፡ የካናዳና የሌሎች የበለፀጉ አገሮችም ተሞክሮ ተመሳሳይ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በምግብ ሰብል ራሷን ለመቻል ዘዴው ሜካናይድ እርሻና ኢንዱስትሪ ነው፡፡ በተለያዩ ምክንቶች ሂደታቸውን አልጠበቁም እንጂ ጥቂት ኢንዱስትሪዎች ብቅ ብቅ ማለት የጀመሩት በንጉሡ ዘመን ነበር፡፡ ውጤታቸው የተጠበቀው ያህል ባይሆንም አሁን ግን ተበራክተዋል፡፡ ምን ያደርጋል ታዲያ፤ በርካታ ችግሮች ሰላሉባቸው፣ በሙሉ አቅማችው እያመረቱ አይደለም። ሌላው አስፈላጊ ነገር ጥሬ ዕቃ ነው፡፡ ከፍተኛ የጥሬ ዕቃ ችግር አለባቸው፡፡ ጥሬ ዕቃውን ከውጭ አገራት ለማግኘት ቢጥሩም የውጭ ምንዛሪ እጥረት የማያላውስ ችግር ሆኖባቸዋል፡፡ የኃይል መቆራረጥም ሌላው አስከፊ ችግር ነው፡፡
ኢንዱስትሪዎች የጥሬ ዕቃ አቅርቦት እንዳይገጥማቸው ለማገዝ የተቋቋመ “የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ግብአቶች ልማት ድርጅት (ኢግልድ)” አለ፡፡ ድርጅቱ፣ በሳምንቱ መጀመሪያ ከሕዝብ ክንፍና ከባለድርሻ አካላት ጋር በ2010 የዕቅድ ክንውንና በ2011 ዕቅድ ላይ ለመመካከር የአንድ ቀን ውይይት በጊዮን ሆቴል አዘጋጅቶ ነበር፡፡ በክብር እንግድነት የተገኙት የንግድ ሚኒስትርና የኢግልድ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ መላኩ አለበል፣ በመግቢያ ንግግራቸው፤ ቀደሞ ሲል ድርጅቱ የተቋቋመበትን ዓላማ በብቃት እየተወጣ አይደለም በማለት መገምገማቸውን ገልጸዋል፡፡
አቶ መላኩ፣ የአብዛኛዎቹ ኢንዱስትሪዎቻችን የማምረት አቅም ከ50 በመቶ ትንሽ ፈቀቅ ያለ (57 በመቶ) ቢሆንም አነስተኛ መሆኑን፤ ለዚህ ምክንያቱ የግብአት አቅርቦት ችግር እንደሆነ፣ ግብአቶች በመጠን፣ በጥራት፣ በአይነት፣ …አነስተኛ ስለሆኑ ብዙዎቹ ኢንዱስትሪዎች የተሻለ ዋጋ ማግኘት አልቻሉም፡፡ በ2010 ወደ ውጭ የተላከ ምርት 18.3 በመቶ ነው፡፡ በዚህ ዓይነት ሊቀጥል አይችልም፡፡ የፋብሪካዎቻችን የአቅርቦት እጥረት ተሻሽሎ የተሻለ ምርት እንዲያመርቱ በማድረግ የወጪና የገቢ ንግዳችንን ማመጣጠን አለብን፡፡ ለዚህ የኢግልድ የ2011 ዕቅድ መሳካት ደግሞ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርቦሽ የግድ ያስፈልጋል, በማለት አሳስበዋል - የንግድ ሚኒስትሩ ፡፡
የግብርናው ዘርፍ ሳያድግ ኢንዱስትሪውን ማሳደግ ማለት ዕንቁላል ሳይኖር ጫጩት እንደመጠበቅ ይቆጠራል ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ግብአቶች ልማት ድርጅት ዋና ሥራ አስፋጸሚ አቶ ወንዳለ ሀብታሙ፤ መንግስት ማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን ለማሳደግና ያሉበትን ማነቆዎች ለመፍታት በርካታ ተግባራት እያከናውነ  ቢሆንም አሁንም ቀላል የማይባሉ ችግሮች ይስተዋላሉ። ችግሮቹ በዋናነት ዘርፉን ከማሳደግ አኳያ የአመለካከት ቢሆንም፣ የግብአት፣ የአሰራር ብሎም የአደረጃጀት ችግሮች ጉልህ ድርሻ አላቸው በማለት አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያ፤ ለጥጥ ምርት፣ በአፈር፣ በውሃና በአየር ንብረት በጣም አመቺ ሁኔታ ቢኖራትም፣ ወደ ኋላ እየተመለሰን ነው ያሉት የኢትዮጵያ ጥጥ ማኀበር ኘሬዚዳንት፤ ከአራት ዓመታ በፊት 104 ሺህ ሄክታር የጥጥ እርሻ ነበረን፤ አሁን ግን 60 ሺህ ሄክታር ነው ያለን፣ አምና እንዲያውም 50ሺህ ሄክታር ገደማ ነበር። ዘንድሮ በጎንደር አካባቢ የተሻለ ነገር እየታየ ነው ብለዋል፡፡
የምርት ማሽቆልቆሉ ምክንያት ምን እንደሆነ ተጠይቀው ሲመልሱ፤ አምራቾቹ  የግብይቱ ስርዓት፣ የአመራረት ዘዴው፣ የመንግስት አካሄድ አላምር ሲላቸው የጥጥ እርሻውን እየጣሉ እንዲሄዱ ያደርጋቸዋል፡፡ የጥጥ አመራረት በጣም አድካሚ ስለሆነ ብዙ ሰው ወደዚህ ዘርፍ መግባት አይፈልግም። ስለዚህ፣ መንግስት ወደ ዘርፉ እንዲገቡ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ቢኖርበትም፣ በተግባር ግን ሲያደርግ አይታይም፡፡ ስለዚህ ሰው ወደ ጥጥ እርሻ መሰማራቱን ይተወዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ጥጥ በአገራችን እያለ ከውጭ እያስገባን ሲሆን፣ የእኛም ኤክስፖርት እየተደረገ ነው፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ የፋብሪካዎች ፍላጐት አስቸጋሪ መሆን ነው፡፡ የአገር ውስጥ ጥጥ ጥራት የለውም ይላሉ፡፡ ነገር ግን ኤክስፖርት እየተደረገ ይሸጣል። በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው አገራችን ለጥጥ ምርት አመቺ ናት፡፡ ኤክስፖርት ማድረግም ይቻላል ብለዋል፡፡
ጥናት አድርገው ለዘርፉ የሚያስፈልገውን ነገር ለይተው ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት ለጠቅላይ ሚንስትሩ ቢያቀርቡም እስካሁን ድረስ ምንም ምላሽ እንዳላገኙ የሚናገሩት ፕሬዝዳንቱ፤ ለዘርፉ የሚያስፈልገውን ነገር ሲገልፁ የአመራረት ስልት፣ የመሬት አቅርቦት፣ የባንክ ብድር፣ ከቀረጥ ነፃ ድጋፍ ያስፈልጋል፡፡ ትራክተር፤ የሚያስፈልገውን መለዋወጫ ሲያጣ ይቆማል፡፡ ትከስራለህ፡፡ ማነው 1000 ዶላር ከፍሎ መለዋወጫ ማስገባት የሚችለው? ስለዚህ ትራክተሩ ይቆማል፡፡ በአገራችን ህግ በዛ፡፡ ሁሉም ነገር በህግ ስለሚተበተብ ትከስራለህ፡፡ ዘና፣ ፈታ ብለህ የምትሰራበት ነገር የለም፡፡ ተግባሩን ብንለካው ጥሩ ነበር፡፡ ቅድሚያ የሚሰጠው በወረቀት ላይ ላለውና ለቲዎሪ ነው፡፡ በእኛ በኩል ከሚያጋጥሙን ችግሮች ተነስተን ይኼ ይኼ ይስተካከልልን እንላለን፡፡ ነገር ግን ሰሚ አናገኝም፡፡ እነዚህ ችግሮች ቢቀረፉ አገራችን በዘርፉ ጥሩ ተስፋ አላት ብለዋል፡፡
የዘርፉ ዋና ዋና ችግሮች ከጉምሩክ ጋር  የተያያዙ መሆናቸው ተገልጿል፡፡  በምሳሌ ሲያስረዱም፤ ከሚያዝያ 20 እስከ ግንቦት 30 የሚዘራው በሄክታር  30 እና 35 ኩንታል የሚሰጥ ሲሆን፤ ከሰኔ 1 ጀምሮ እስከ 30 የሚዘራው ያለማጋነን 18 ኩንታል ይሆናል። አስፈላጊውን ጊዜ ጠብቀህ ለመዝራት መለዋወጫ ያስፈልጋል፡፡ መለዋወጫ ሲጠፋ፣ ትራክተሩ 10 ወይም 15 ቀን ሊቆም ይችላል፡፡ በተፈለገው ጊዜ የምትፈልገውን ነገር  ካላገኘህ በቃ ከውድድር ወጣህ ማለት ነው፡፡ ሌላው ችግር ደግሞ ተባይ አለ፡፡ በወቅቱ ፀረ ተባይ መድሀኒት ካላስረጨህ፣ በሚፈለገው ጊዜ በሁለት ርጭት የሚቆመው ተባይ  ወቅቱ ካለፈ በኋላ የምትረጭ ከሆነ አስር ርጭት ሊፈልግ ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ፤ የዋጋ ውድነት ያስከትላል፡፡ ስለዚህ በሄክታር 40 ኩንታል ማግኝት ስንችል  በአማካይ 18 ኩንታል እናገኛለን፡፡ በሌሎች አገሮች ከ40-50 ኩንታል ነው፡፡ እንዴት አድርገን ነው ከእነዚህ ሰዎች ጋር መወዳደር የምንችለው? ከዚህ በተጨማሪም የሌላው ሀገር ገበሬ በቀላል ዋጋ ነው የሚያመርተው፡፡ ምናልባት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ጥሩ ምላሽ ይሰጡናል በሚል ተስፋ እየተጠባበቅን ነው፡፡
ማነቆው በዚህ ዘርፍ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ስለሆነ ተባብሮ መስራት ይጠበቅብናል፡፡ ለምሳሌ ከውጭ ሀገር የምናስመጣውን ስንዴ በአገር ውስጥ ማምረት ይቻላል፡፡ በረሃማ በሆነው የአፋር ክልል ስንዴ ዘርተን ከ 35-45 ኩንታል በሄክታር አግኝተናል፡፡ ስንዴ ግን እዚሁ ማምረት ትተን ከውጭ እንገዛለን፡፡ በግብርናው ላይ አተኩረን ብንሰራ ብዙ ነገሮችን መቀየር ይቻላል የሚል እምነት አለኝ በማለት አስረድተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የቆዳውን ዘርፍ እያጋጠመ ያለው ዋነኛ ችግር የቆዳው ዋጋ መርከስ ነው፡፡ አንድ በግ ወይም ፍየል እስከ 4ሺህ ብር ይሸጣል፡፡ የቆዳ ዋጋ ከ25-30 ብር አይበልጥም፡፡ የዋጋ መውረድ ብርቱ ችግር መሆኑን የጠቀሱት የኢትዮጵያ ጥሬ ቆዳና ሌጦ አቅራቢዎች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ብርሃኑ አባተ፤ ቀደም ባሉ ዓመታት ቆዳና ሌጦ ለዚህች ሀገር ከቡና ቀጥሎ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኝ እንደነበር ገልፀዋል፡፡
አገራችን ቀደም ባሉት ዓመታት ጥሬ ቆዳን ከመላክ፣ በከፊል የተለፋ ቆዳ ወደ መላክ እንደተሸጋገረች የገለፁት አቶ ብርሃኑ፤ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ያላለቀለት ቆዳ በማምረት እየላከች መሆኗን ገልፀዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገሪቷ ከ30 በላይ የቆዳ ፋብሪካዎች እንዳሉ የገለፁት ፕሬዝዳንቱ፤ ለእነዚህ ሁሉ ፋብሪካዎች የሚያስፈልገው የቆዳ ግብአት የሚገኘው ከቆዳና ሌጦ ነው፡፡ ቀደም ሲል ከኢትዮጵያ ከብቶች በዓመት ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀው አጠቃላይ ቆዳና ሌጦ ወደ 20 ሚሊዮን ነበር፡፡ አሁን የሚገኘው ግን ከተገመተው  በላይ ነው ብለዋል፡፡
አንዳንድ ፋብሪካዎች፣ ከከብቶች እድገት ጋር ተያይዞ  በሽታ ስለሚይዛቸው የቆዳና ሌጦ ጥራት ቀንሷል ይላሉ፡፡ የግብርና ሚኒስቴር ደግሞ የከብቶችን በሽታ ለመከላከል እየሰራ ስለሆነ የበሽታው መጠን ስለቀነሰ፣ በቆዳና ሌጦ ላይ ይታይ የነበረው የጥራት ጉድለትም ቀንሷል እያለ መሆኑንና ተናብቦ ያለመስራት እንዳለ አቶ ብርሃኑ  ተናግረዋል፡፡

Read 2103 times