Saturday, 22 September 2018 15:07

የፀጉር ባለሙያው ፍልስፍና!

Written by  አብይ ተስፋዬ አሳልፍ (አተአ)
Rate this item
(3 votes)

 ‹‹… ሁሉም ነገር የመለማመድና የልምድ ጉዳይ ነው! አዲስ ነገር ሲመጣ ያስገርምሃል፣ ያስበረግግሃል ወይም ያስደነግጥሃል፡፡ ውሎ ሲያድርና ሲደጋገም ግን ልቦናህ ሌላ አዲስ ነገር ካልመጣ በቀር ለቀድሞው መደንገጡን ያቆማል!…››
*   *   *
ግድግዳዬ ላይ ካንጠለጠልኳት መስተዋት ፊት ለፊት ስቆም ብዙ ጊዜ የማየው እኔን ራሴን አይመስለኝም፡፡ በርግጥ መስተዋቱ መጀመሪያ ላይ ክብና አዲስ የነበረ ቢሆንም፣ አንድ ዕለት ከእጄ አመለጠኝና ትንሽና ግማሽ ፊት የሚያሳይ ሆነ፡፡ (ብዙ ጊዜ የሆነ ክልል ካርታ ይመስላል እያልኩ በልቦናዬ አስባለሁ!) ለነገሩ እርሱንም ቢሆን ደጋግሜ አላየውም፡፡
በጣም ብዙ ጊዜ ራሴን ታዝቤዋለሁ፤ ከውስጥ በማየው ነገር ደስ ብሎኝ አያውቅም፡፡ እንዴት እንደሆነ ባይገባኝም፣ ራሳቸውን በማየት የተጠመዱ ሰዎችን ሳይ ግን እጅግ ይደንቀኛል፡፡ ይህ የእኔ ተፈጥሮ ነው፡፡ ፊቴን በወር እንኳ አይቼው አላውቅም ብል አታምኑም። አስቀያሚ ነኝ ብዬ ስለማስብ አይደለም፣ ምክንያቱ ግን ለእኔም አልተገለጸልኝም፡፡ ራሴን ማየት ደስታ አይሰጠኝም፡፡ እንዲያውም ትዝም አይለኝ፡፡ (ወይም በራስ መተማመን የለኝ ይሆንን እላለሁ!)
ትናንትና ልክ ከመስተዋቱ ፊት እንደቆምኩ ከአናቴ ላይ የፈሉትን ነጫጭ ፀጉሮች ማየት አስደነገጠኝ፡፡ እንዲህ ገብስማ እስክመስል ድረስ የት ነበርኩ! ፊቴም እንዲሁ፡፡ እነዚህ የሚሻክሩ የፊት ፀጉሮቼን እየደባበስኩ ጋሽ ፈይሳን አሰብኩ፡፡
ባለፈው አንድ የሰፈራችን ልጅ ሞቶ፣ ቀብር ደርሰን ተመልሰን፣ ቁጭ ብለን ስንጨዋወት ድንገት እንዲህ አልኳቸው፡፡ ‹‹የወጣት መሞት በጣም እኮ ነው የሚያሳዝነው፡፡ ሞት ግን ምንድን ነው ጋሼ! ፣በስራ የሰፈራችን አንጋፋ ፀጉር ከርካሚ ሲሆኑ፣ ወግ የማያልቅባቸውና ወዝ ያለው ጨዋታ የሚያውቁ ሰው ናቸው፡፡ የሚያስገርመኝ ነገር ሁሉም ወግ ከስራቸው ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ተፈጥሯዊ በሆነ ሁኔታ ጨዋታቸውና ወጋቸው አስደናቂ ነው፡፡
ጥቂት አሰቡና በፈገግታ እንዲህ አሉ፤‹‹እንግዲህ ሞት ማለት፣  ልክ ፀጉርህ ላይ እንደምትወጣ የመጀመሪያዋ ሽበት ማለት ይመስለኛል፡፡ የመጀመሪያዋን ሽበት በፀጉሩ ላይ ሲያይ የማይገረም፣ ሁለተኛዋና ሦስተኛዋን ሲያይ የማይደነግጥ ሰው የለም፡፡ ነገር ግን ጊዜው እየገፋና የነጫጮቹ ቁጥር እየበዛ ሲሄድ ትለማመዳቸውና ድንጋጤህ ይቀንሳል፡፡ ከዚያ መጨነቅህን ትተዋለህ። ትለማመዳቸውና አብረሃቸው በሰላም ትኖራለህ። እናም ሞት እንደ ሽበት ለሁሉም የማይቀር ፀጋ ቢሆንም፣ ንቃትህ እያደገና ልምምድህ እየሰፋ ሲሄድ ነው በስርዐት የምትቀበለው፡፡ በተቀበልከው ቁጥር ደግሞ ተስማምተህ መኖር ትችላለህ፡፡ የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ሞቶች በአካባቢህ መከሰት ቢያስደነግጥም፤ ፈጥኖም ሆነ ዘግይቶ ሌላ እንደሚከሰት መቀበል ስለሚኖርብህ መዘጋጀት አለብህ፡፡ ከልምምዶች በኋላ ግን ልቦናህም ይህን በዝግታ ይቀበላል፡፡ እንዲያውም ልብ ብለህ ካሰብከው በማይቀር ነገር ፊት መንጨት አያስፈልግም፡፡ ዕጣ ፈንታህ ከሆነ፣ የሆነውን ነገር ሁሉ በስርዓት መቀበልን መልመድ አለብህ፡፡››
እናም አሁን መስተዋቱ ላይ አፍጥጬ በጥልቁ አሰብኩበት፡፡ እነዚህ ነጫጭ ፀጉሮቼ እየበዙ ነው፡፡ በቀስታ ዳበስኳቸው ፡፡ የመጀመሪያዋን ያየሁበትን ግዜ አላስታውስም፣ አሁን በብዛት ሲከሰቱ ግን በመገረም ተመለከትኳቸው፡፡ ሞትም እንዲሁ ሊሆን ይችላል፣ እዚህም እዚያም ብቅ ብቅ ሲል ብቻ ነው ትዝ የሚለኝ እንጂ እኔ ከነመኖሩም አስቤው አላውቅም፡፡ አሁንም አያስደንቀኝም፡፡ እንዲያው ድንገቴ ሲሆን ብቻ ያስበረግገኛል እንጂ፡፡
እንደው ለመሆኑ አሁን ትናንትና ወዳጄ አዳም ይሞታል ብዬ መቼ አሰብኩ፡፡ እነሆ ሞተ አስደነገጠኝም (እደነግጣለሁ ማለት ነው!) እኔ ሞት ምንም አይገርመኝም፣ አያስደነግጠኝምም! ነበር የምለው። ሁሉም ነገር የመለማመድና የልምድ ጉዳይ ነው! አዲስ ነገር ሲመጣ ያስገርምሃል፣ ያስበረግግሃል ወይም ያስደነግጥሃል፡፡ ውሎ ሲያድርና ሲደጋገም ግን ልቦናህ ሌላ አዲስ ካልመጣ በቀር ለቀድሞው መደንገጡን ያቆማል!
***
ዛሬ ፀጉሬን ታጠብኩና በፎጣ አደራረቅሁ። እናም ወደ ጋሽ ፈይሳ ጋ እየተካከዝኩ አመራሁ፡፡ ፀጉሬን መስተካከል የጀመርኩት ገና ልጅ ሆኜ ነበር፡፡ አባቴ ነበር በቆርቆሮ ከተሰራችው ትንሽዬ ፀጉር ቤት እየጎተተ የሚያስገባኝ፡፡ የሰፈር ልጆች በየአጥሩ ስር በመቀስና በየጓሯቸው በምላጭ በሚላጩበት ጊዜ እኔ ጋሽ ፈይሳ ጋር በእጅ በሚሰራ ቶንዶስ ይመደምዱኝ ነበር፡፡ በመቀጠል ነፍስ ካወቅሁ በኋላ በራሴ እግር መጣሁ፡፡ ጋሼ ግን አላረጁም፣ ድሮም ሳውቃቸው እንዲሁ ነበሩ፡፡ ሳቅና ቁም ነገርም አላለቀባቸውም፣ እናም ደንበኝነቴንም አላቆምኩም፡፡ አሁን እርሳቸው ቁጭ ብለው ይውላሉ እንጂ አብዛኛውን የፀጉር ስራ የሚሰሩት ልጆቹ ናቸው፡፡ እኔም ከልጆቹ ጋር አዲስ ደንበኛ ሆኛለሁ፡፡ ነገር ግን ሁልግዜ ከቤቱ ስለማይጠፉና ጨዋታቸው ስለሚጥመኝ ተቀምጬ ወረፋ ስጠብቅ የማወራው ከእርሳቸው ጋር ነበር፡፡
(እንደው ለነገሩ ፀጉር አስተካካይ እንዲህ ጨዋታ አዋቂ የሆነው ለምንድነው ብዬ አስባለሁ! እናም መልሱም ወዲያው ይመጣልኛል፡፡ ፀጉር አስተካካይ ከብዙ ሰው ጋር ሲወያይ ፣ ሁሉን ቆብ ሲያስወልቅና አስቀምጦ ሲያናዝዝ፣ ከሁሉ ሲሰማና ለሁሉ አስተያየት ሲሰጥ ይውላልና በሃሳብ ይበልፅጋል፡፡ ይኸው ይመስለኛል!)
ዛሬም ልክ ስገባ በሰላምታ ተቀበሉኝ፤ ‹‹ ልጅ ጌታመሳይ እንደምን ነህ!››
‹‹አለሁ ጋሼ፤ እንዴት ነዎት!››
‹‹ፈጣሪን አይክፋው፤ ይኸው ከድሃውም ከሃብታሙም ላይ ፀጉርና ቆሻሻ ሳራግፍ አለሁ፡፡ እኔና የሐገሬ ህዝብ አንድ ነን፡፡ ለእኛ ሳያልፍልን ባለ ወንበሩን (ተቀምጦ የሚሽከረከረውን!) እንዳሳመርን እንኖራለን።›› አሉና መሳቅ ጀመሩ፡፡
‹‹ኸረ ሃጢያት እንዳይሆንብዎ!›› … እኔም እየፈገግሁ።
‹‹ሃጢያትማ ልክ እንደ ጢም ጠጉር ነው፡፡ ዛሬ ሙልጭ አድርጌ ባጠፋው፣ ለነገ ወይ ለከነገ ወዲያ ከእንደገና በብዛት ቡፍፍ ብሎ ይበቅላል፡፡ ለዘመናት እንዲሁ ስንጠርገውና ስናሰማምረው እንኖራለን እንጂ ሁሌም ከእኛ ጋር ይኖራል፡፡ እና ጭራሽ ይጠፋል ብዬ አልደክምም፡፡››
‹‹እና…›› አልኩ ግራ እየገባኝ፡፡
‹‹…እናማ ሐጢያት ብንሰራም ፈጣሪ በይቅርታና በንስሃ ያጠራውና ያሰማምረናል፣ ይምረናል፣ ይቅር ይለናል፣ ያጸዳናል ማለት ነው፡፡ በማግስቱ ደግሞ ተመልሰን በመዓት ሐጢያት እንወረራለን ስለዚህ የሚያስፈራ ነገር አይደለም፡፡ እሱንም ትለምደዋለህ፣ ትለማመደዋለህ፡፡ መርሳት የሌለብህ ነገር መልሰህ ንስሃ መግባቱን ብቻ ነው፡፡ ይቅር በለኝ ፈጣሪዬ፣ ቢሆንም ግን ስራችንን በትክክል ነው የገለፅኩት ፡፡ አይደለምንዴ!››
‹‹በትክክል!›› ብዬ አረጋግጣለሁ፡፡
(እናም ማሰላሰል እጀምራለሁ፡፡ እውነት ይሆን! ስል ራሴን እጠይቃለሁ፡፡) እውነት ነውንጂ፡፡ ግን ደግሞ ሃሳቡ ተሻጋሪ ሆኖ ወደ ቤቴ አብሮ የሚከተለኝ ስራ ይሆንብኛል፡፡ ያመራምረኛል፡፡ ይገርመኛል፡፡ ቆየት ብዬ እየፈገግሁ ለራሴ ‹‹ሃጢያት ልክ እንደ ፊቴ (ሪዝ!) ፀጉር ነው!›› እላለሁ፡፡ በየዕለቱ እስክሞት ድረስ ይወርረኛል፣ መልሼ አፀዳዋለሁ እንጂ፡፡ ሰው ነኝና አቧራ ሳይራገፍብኝ አልውልም፡፡ ሳልቆሽሽ አልውልም። ሳልታጠብና ሳልፀዳም አልቀርም፡፡ ተመስገን እላለሁ አሁንም በለሆሳስ፡፡ ቆሽሾ መቅረት ነው የማይገባው፡፡
***
ደግሞ ስተነኩሳቸው  ‹‹… ጋሼ፡፡ ኑሮንና ፖለቲካውን ምን ይሉታል፡፡ ካድሬውን፣ ፖለቲከኛውን፣ መንግስትንስ … ›› እላቸዋለሁ፡፡  እንዲያወሩ ስገፋፋቸው ነው፡፡ ነገሩን ሁሉ ከፀጉራችንንና ከጢማችን እንዲሁም ከንፅህናችን ጋር አዛምደው ሲያወሩ አዳዲስ ሀሳብ ይመጣልኛል፡፡
‹‹…ካድሬ ምን መሰለህ፣ ካድሬ ፀጉሩን እንደሚስተካከል ህፃን ማለት ነው፣ ከረሜላ ወይ ብስኩት እሰጥሃለሁ ብለህ ደልለኸው፣ ወይ ደግሞ ይሰጠኛል ብሎ አስቦ ከወንበሩ ላይ ይቀመጣል። (በየመሃሉ እሪሪ አውርዱኝ ሊል ይችላል!) የበለጠ ማባበያ ታቀርብለታለህ! አንዳንዱ ደግሞ ይመቸዋል። አሽከርክረኝ፣ በወንበሩ አጫውተኝ ይላል፡፡ ተቀምጦ እንቅልፍ የሚወስደውም አለ፡፡ ድንገት ደግሞ ማሽን ቆንጠጥ ሲያደርገው የሚጮህ አለ፡፡ በእጁም ማባበያና መሸንገያውን ካልያዘ የማይታዘዝም አለ፡፡ መጨረሻ ከወንበሩ ስታወርደው ግን አምሮበት ከነወዙ ቢወርድም ያው ጠጉሩን የተስተካከለ ቆንጆ ህጻን ነው። ከሳምንት በኋላ ፀጉሩ ያድግና ሌላ ሰው መምሰሉ አይቀርም፡፡
እንግዲህ ካድሬው ከወንበሩ ወርዶ ወደ ተራው ኑሮው ሲመለስ ያን ይመስላል፡፡ ወንበሩ ላይ ሲቀመጥ አዙሩኝ አሽከርክሩኝ፣ ደጉሙኝ፣ አስጨብጡኝ፣ አባብሉኝ፣ እያለ ያለቃቅሳል፡፡ ኑሮው ያው ከወንበሩ ሲመለስ የሚሆነው ሁኔታ ነው፡፡ ፖለቲካው ደግሞ የሚሆነውና የማይሆነውንና የተገባውን ቃል ይመስላል። ካድሬ ቀጣፊና አለቃቃሹ ልጅ ነው። ያው ከሆነ ግዜ በኋላ ከምቹውና ከተሸከርካሪው ወንበር አምሮበት መውረዱ የማይቀር ነው፡፡ ከዚያም ከተራው ህዝብ ጋር ለሐጩን እየጠራረገ ይቀላቀላል። ሲያለቃቅስና አምጡ ሲል እንዳልኖረ፣ ምንም ያጠፋሁት ነገር የለም ይላል፡፡››
እንዲህ እንዲህ እያሉ ሲፈላሰፉ እዝናናለሁ፡፡ ተስተካክዬ ስጨርስና ‹ደህና ዋሉ! › ብዬ ስወጣ እንዲህ አሉኝ፡፡
‹‹…እንደናዝራዊ ፀጉሬ የሃይል ምንጬ ነው ብለህ ማሳደግ ከጀመርክ አትመጣም ካልሆነ ግን በቅርቡ ደግሞ ትመለሳለህ፡፡ ፖለቲከኛም እንዲሁ ነው፡፡ ራሱንና አስተሳሰቡን ማበልፀግና ማሳደግ ከጀመረ ይነቃል፣ እውቀትና ንቃትም የሃይሉ ምንጭ ከሆኑለት ወደ ወንበር አይመለስም ተራ ሆኖ መኖር እንደሚሻል ይገባዋልና! … አይይ! … ንቃቴና እውቀቴ አይጠቅመኝም ካለና ካስወገደው ወደ ወንበሩ ይመላለሳል፡፡ እኛም እንጠብቃለን፣ እናስቀምጣለን፣ እናሽከረክራለን፣ ብዙ ግዜ የሱን መልክና ኑሮ እናሳምራለን፡፡ አንዳንዴም ይበላሽብናል…››
‹‹ምን ይበላሻል ብለው ነው ጋሽ ፈዬ፤ ሁሉን አሳምረው ነው የሚልኩት አይደል!››
‹‹አንዳንዴ ስራችንን ትተን ወሬ ስንፈተፍት አንዱን ጎን እንላጨው ይሆናል፣ መልሰህም ልትተክለው ስለማንችል ሁሉንም ለማመሳሰልና ለማስተካከል ስንል ሌላውንም እንላጫለን፡፡ ፖለቲካውም እንዲሁ ነው፣ በስህተት አንዱን ወገን ከላጨኸው ለማስተካከል ስትል ደግሞ ሌላውን ጎን ወደ መላጨትና ስህተትን በስህተት ወደ ማረም ልትገባ ትችላለህ፡፡››
‹‹ኦህ!›› … ስርቅ በምትል የመገለጥ ብርሃን መሃል የሚመጣ መደነቅ ይከበኛል፡፡ ፈገግታዬን በአልኮል ከተለበለበው ፊቴ ላይ እየረጨሁ ወደ ፊቴ እነጉዳለሁ። ‹መቼም መመለሴ አይቀርም!› ስል አስባለሁ፡፡ ከእንግዲህ ወደ መስተዋቴም ለሳምንታት  አላይምና ብዙም ወደ ፍልስፍናው አልመለስም፡፡ ተራና እርባና ቢስ ህይወቴን እቀጥላለሁ፡፡ (የማይጠይቅና የማይመራመር ህይወት እርባና ቢስ ይባላል፤ ይላልና መፅሃፈ ትርጓሜ ዘአለቃ ነጋሲ ቡልቱ፡፡ …ምናባዊ ማጣቀሻ!...) ምናልባት የሰዎች ተንጨባረሃል የሚል አስተያየት ሲከታተልብኝ ወይም ደግሞ ዳበስ ዳበስ አድርጌ ሲበዛብኝ እመጣለሁ እንጂ እንደሳምራዊውስ አላሳድግም፡፡


Read 3833 times