Saturday, 22 September 2018 14:48

በሁለት ወራት ውስጥ በግጭትና ዘር ተኮር ጥቃት የ215 ዜጐች ህይወት ጠፍቷል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

 በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ በግጭና  ብሔር ተኮር ጥቃቶች፤ በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች የ215 ዜጐች ህይወት በአሰቃቂ ሁኔታ ማለፉን የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ከትናንት በስቲያ ያወጣው ሪፖርት አመልክቷል፡፡
በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰቱ ያሉ ብሔር ተኮር ግጭቶችና በቡድን የተደራጁ ኃይሎች እየፈፀሟቸው ያሉትን ከባድ ጥቃቶች መንግስት በአስቸኳይ ሊያስቆም እንደሚገባ ሰመጉ አሳስቧል። በተለያዩ አካባቢዎች ግድያዎች፣ ዘርን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችና ግጭቶች፣ የመንጋ ፍትህና ሥርዓት አልበኝነት እየተንሰራፋ መሆኑን የጠቆመው የሰመጉ ሪፖርት፤ በአደባባይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችም በባህሪያቸው ዘግናኝ ናቸው ብሏል፡፡
ካለፈው ሐምሌ አጋማሽ ጀምሮ በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች 215 ያህል ዜጐች በግጭትና በጥቃት መሞታቸውን ያስታወቀው ሪፖርቱ፤ እነዚህ ግጭቶችና ጥቃቶች በከፍተኛ መስዋዕትነት የተገኘውን የዴሞክራሲ ጭላንጭል ያጨልም ስር የሰደዱ ችግሮች እየተገዳደሩት ይገኛሉ ብሏል፡፡
በግጭት በቃትና በመንጋ ፍትህ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ከተገደሉባቸው አካባቢዎች መካከልም፤- በደቡብ ክልል ፔፒ ከተማ 5 ሰዎች፣ በኦሮሚያ ክልል ባሌ-ጐባ 10 ሰዎች፣ በደቡብ ክልል የም ወረዳ 6 ሰዎች፣ እንዲሁም ዳውሮ ዞንሪ ተርጫ ከተማ 5 ሰዎች፣ በሻሸመኔ 4 ሰው፣ በድሬዳዋ 15 ሰዎች፣ በሐረር ሙሉ ሙሉ 31 ሰዎች፣ በአማራ ክልል ኮረም 1 ሰው መገደላቸው ተመልክቷል፡፡
ከሐምሌ 28 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በሶማሌ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በተፈፀመ ዘርና ሃይማኖት ተኮር ጥቃት፤ ከ100 በላይ ሰዎች መገደላቸውን፤ ዘጠኝ አብያተ ክርስቲያናት መቃጠላቸውን ሰመጉ በዚሁ ሪፖርቱ አስታውቋል፡፡
ከሰሞኑም በቡታጅራ 8 ሰዎች በግጭት መገደላቸውን የጠቀሰው ይኸው ሪፖርት የመንግስትን ሪፖርት ዋቢ በማድረግም በቡራዩ በተፈፀመው ዘር ተኮር ጥቃት 25 ሰዎች ተገድለዋል፡፡ በአዲስ አበባ ሰልፍም 5 ሰዎች ተገድለዋል ብሏል፡፡
በአዲስ አበባና በቡራዩ የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ በቅርቡ የራሴን ሪፖርት አቀርባለሁ ብሏል - ሰመጉ፡፡ በአዲስ አበባ ሰሞኑን የተፈጠረው ግጭትና ግርግር ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰው የፀጥታ ኃይሎች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው ነው ብሎ እንደሚያምንም ሰመጉ አስታውቋል፡፡  

Read 5822 times