Print this page
Saturday, 22 September 2018 14:41

የ21ኛው የዓለም ዋንጫ ልዩ ማስታወሻ የመጨረሻ ክፍል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(3 votes)

  ከአባ ሞጋ ልጅ ኢብራሂም ጋር

    የቃለምልልሱ መግቢያ
በፊፋ ሙሉ ፍቃድ አግኝተን 21ኛውን የዓለም ዋንጫ ለመዘገብ ራሽያ ለገባን ሶስት ጋዜጠኞች በሞስኮ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የሰጡት ድጋፍ ከልብ የሚመሰገን ነው። ይህ የ21ኛው የዓለም ዋንጫ የመጨረሻው የማስተወሻ ፅሁፍ የቀረበው ለምስጋና ብቻም ሳይሆን በሞስኮ ከሚኖሩ የእኛ ሰዎች አንዱን ለማስተዋወቅም ነው፡፡ ከኢንጅነር እና ዲፕሎማት ኢብራሂም ሞጋ ጋር የተዋወቅነው 21ኛው የዓለም ዋንጫ በተጀመረ በሁለተኛው ቀን ነው፡፡ ይህ የጅማ ሰው በሞስኮ መኖር ከጀመረ ከ27 ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል። 21ኛውን የዓለም ዋንጫ ለመዘገብ ራሽያ መዲና የገባን የስፖርት ጋዜጠኞች በማረፊያ ጉዳይ እንደምንቸገር ኢብራሂም እና የቅርብ ጓደኛው ፕሮፌሰር አንጌሳ ዱጋ ጫላ ገምተዋል። ለስራችን የሚመች ማረፊያ በማጣት ብዙም ሳንከራተት ባገኙንና በተዋወቁን ቀን ተመካክረው ሊደግፉን ወሰኑ፡፡ ሁላችንም የተማመንነው በሞስኮ ከእነሱ ጋር መገናኘታችን የእግዚአብሄር ፈቃድ ሆኖ ነው፡፡ ኢብራሂም እና ፕሮፌሰር አንጌሳ ለዓለም ዋንጫው የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች በሞስኮ መገኘታችን ከልብ አስደስቷቸዋል፡፡ ስለዚህም ‹‹የዓለም ዋንጫውን በልበሙሉነት በመላው ራሽያ እየተዘዋወራችሁ ስሩ፤ ማረፊያችሁ አያሳስባችሁ›› በማለት ነበር ድጋፍ ሊሰጡን የወሰኑት፡፡ እኛን በሚችሉት ሁሉ መደገፍ መቻላቸውንም ልዩ ክብር አድርገው ቆጥረውታል። የእነሱ ድጋፍ ባይኖር ኖሮ ዓለም ዋንጫውን ከሞስኮ ውጭ መታደም አንችልም ነበር፡፡ በሞስኮ ከተማ ፕሮስክፔት ሚራ ወይንም ‹‹የሠላም ጎዳና›› በተባለ ሰፈር የሚገኘው የኢብራሂም የመኖርያ አፓርትመንት ማረፊያችን እንዲሆን አደረጉ፡፡ አፓርትመንቱ የሚገኝበት ፕሮስፔክት ሚራ ሞስኮ ላይ ለሚካሄዱ የ21ኛው የዓለም ዋንጫ ሁሉም ትእይንቶች የቀረበ ነበር፡፡ ከዚያ ሰፈር በመነሳት ወደ 4 የራሽያ ግዛቶች የተጓዝኩባቸውን የባቡር ጉዞዎችም አሳክቻለሁ።
ፕሮስፔክት ሚራ የዓለም ዋንጫ መክፈቻ እና መዝጊያ ካስተናገደው የሉዥኒኪ ስታድዬም በመሬት ስር  ባቡር (ሜትሮ) የ8 ጣቢያዎች  ርቀት ላይ ነው፡፡ ከፕሮስፔክት ሚራ የሚነሳው የመሬት ስር ባቡር ወደ ስፖርቲቪና ወይንም ሉዥኒኪ ስታድዬም የሚገኝበት የሞስኮ ከተማ የሚደርሰው በ20 ደቂቃዎች ልዩነት ነው። የኢብራሂም እና የፕሮፌሰር አንጌሳ ድጋፍ በማረፊያ ብቻ የተወሰነ አልነበረም፡፡ በሞስኮ ከተማ ብቻ ሳይሆን በሌሎቹ የራሽያ ከተሞች ኒዥኒ ኖቭጎሮድ፤ ሴንት ፒተርስበርግና ሶቺ ከተሞች ባደረግናቸው የባቡር ጉዞዎች በልዩ ምክርና የሞራል ድጋፍ የሚያበረታቱ ነበሩ፡፡ የባቡር ጉዞ ሰዓቶችና የመሳፈርያ ቅድመ ዝግጅቶችን ያማክሩናል፡፡ ወደ ባቡር ጣቢያዎች በመሸኘትና በመቀበል አስተናግደውናል፡፡ እስከ ዓለም ዋንጫ ፍፃሜም ከጅማው ሰው ኢብራሂም ሞጋ ጋር በአፓርትመንቱ ኖረናል፡፡ ኢብራሂም በመኖርያ ቤቱ በሚገርም መስተንግዶ የምግብ አበሳሰል ችሎታውን አሳይቶ እያበላን፤ በሙዚቃ ፍቅሩ እያዝናናን፤ በራሽያ ተመክሮው እያወጋን ነበር አብረን የሰነበትነው፡፡ በአቅራቢያው ይኖሩ የነበሩት ፕሮፌሰር አንጌሳና እንዲሁም ሌሎች ጓደኞቹ ጥላሁንና ጌድዮን ነበሩ፡፡ ከሁሉም ጋር በየጊዜው እየተገናኘን ያሳለፍናቸው ሁኔታዎች ከ21ኛው የዓለም ዋንጫ ጎን ለጎን በጣም የሚያስደስት እና የማይረሳ ትዝታ የጣሉብን ነበሩ፡፡ ከዚህ በታች የቀረበው ከጅማው ልጅ ኢብራሂም አባ ሞጋ አባ ቡልጉ ጋር የተደረገ ልዩ ቃለምልልስ ነው፡፡  ስለ አባቱ አባ ሞጋ አባቡልጉ እና ቤተሰባቸው፤ ስለ ጅማ ከተማ፤ ስለ ጥይት ፋብሪካና የደርግ ዘመን ውትድርናና የስኮላርሺፕ፤ ስለ ዓለም ዋንጫ የራሽያ መስተንግዶ፤ ስለፖርቱጋል ፤ ስለ ዲፕሎማቲክ ተመክሮውና እና ስለሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ከኢብራሂም ጋር እንዲህ ተጨዋውተን ነበር፡፡
በመጀመርያ 21ኛው የዓለም ዋንጫን በልበሙሉነት እንድዘግብ በኢትዮጵያዊ ወገንተኝነት ለሰጠሐኝ ያልተቆጠበ ድጋፍ አመሰግናለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ያንተ አይነት ወገኑን መተዋወቅ ስላለበት ነው ቃለምልልስ ማድረግ ያስፈለገው። ስለዚህም ከጅማ ከተማ እውቅ ኢትዮጵያውያን አንዱ የሆኑትን አባትህን አባ ሞጋ አባ ቡልጉን በምታስተዋውቅበት ታሪክ እንጀምር…
ከትውልድ ስፍራዬ ብንነሳ ጥሩ ነው፡፡ የተወለድኩት በጅማ ከተማ መንቲና በሚባል አካባቢ ነው፡፡ የቅድመ አያቶቼና ዘመዶቼ መኖሪያ አካባቢ ነበር፡፡ መንቲናን ከጅማ ሰፈሮች ልዩ የሚያረጋት የገበያ፣ የተለያዩ ዎፍጮ በቶች፣ ሱቆች፣ የተለያዩ ንግዶችና የማመላለሻ ማእከል መሆኑዋ ነው። በዚሁ አካባቢ አባቴ አባ ሞጋ አባቡልጉ በወጣትነቱ በንግድ ሙያ ተሰማርቶ በግሉ ጥረት ትልቅ ደረጃ ለመድረስ የበቃ ነበር። አባ ሞጋ እድገቱ ከእንጀራ አባቱ ጋር ነበር፡፡ እኝህ እንጀራ አባቱ መሬት እና የንግድ ስራ ያላቸው በመሆኑ በአስተዳደጉ ያገኘው እውቀት ይህንኑ ነበር፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ በንግዱ ዘርፍ እንዲሳካለት በግሉ ይጥር ነበር፡፡ እህል በመሸጥ ንግዱን ጀመረ። በቡናና በእህል ንግድ ሲንቀሳቀስ ቆይቶ ቀጥሎም ወፍጮ ቤት ከፈተ። በዚሁ መስክና በሌሎችም የንግድ ዘርፎች ጠንክሮ በመስራት በተለይ የዎፍጮ ቤቱን በማስፋፋት በከተማዋ ካሉት ዎፍጮ ቤቶች ሰፊና ጥራት ያለው አገልግሎት በመስጠት ቀዳሚዉን ቦታ ይዞ ነበር። በተጨማሪም የጭነት ተሽከርካሪ መኪናዎች በመግዛትና በማሰማራት የንግድ እንቅስቃሴውን አስፋፍቶ ነበር። በማስከተልም በ1963 ዓ.ም ፈረንጅ አራዳ በሚባል ሰፈር በጊዜው ዘመናዊ ቪላ ቤት አሰርቶ እስከ 1968 ዓ.ም ከሰፊው ቤተሰቡና ዘመዶቹ ጋር በደስታ ሲኖር ነበር። እንደሚታወቀው ፈረንጅ አራዳ የውጭ ዜጎችና ሃብታም የከተማይቱ ሰዎች የሚኖሩበት ሰፈር ነበረች፡፡
በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን በየክፍለ አገሩ ትልቅ አስተዋፅኦ እና ስራ ያላቸው ሰዎች ልዩ የክብር ስም ይሰጣቸው እንደነበር ይታወቃል፡፡ ስለዚህም አባቴ በግሉ ባደረገው ጥረትና ለአካባቢው ዘመናዊ እድገትና ለውጥ ባሳየው ውጤት የክብር ማእረግ ተስጥቶት ግራዝማች አባ ሞጋ አባ ቡልጉ በመባል ይጠራ ነበር። አረብኛን ጨምሮ ሌሎች የውጭ ቋንቋዎችን ያውቅ ነበር። ስለዚህም በተለያዩ ቋንቋዎች የዓለም ዜናዎችንና ዓለም አቀፍ ሁኔታዎችን በንቃትና በቅርበት ይከታተል ነበር። ይህም የአውሮፓዊያንን የአኗኗር ስልትና የስልጣኔ ደረጃ እንዲከታተልና እንዲተዋወቅ አድርጎታል። በግል ጥረት ያፈራውን ሃብት ሳይሰስት በዘመናዊ አኗኗር ህይወቱን አስተካክሎ የኖረበትን ሁኔታ በተለያዩ ምሳሌዎች ማመልከትም ይቻላል፡፡ በወቅቱ በፈረንጅ አራዳ ከምንኖርበት ዘመናዊ ቪላ ቤትና የስራ ማካሄጅያ መኪናዎች ባሻገር ምርጥ ዘመናዊ ማዝዳ የቤት መኪና ነበረው፡፡
አባቴ አባ ሞጋ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የህግ ኮርስ ወስዶ በህግ ሙያ ሰርተፍኬት አግኝቷል። በህግ የነበረውን ከፍተኛ ብቃት እና እውቀት ለመመረቂያ ያቀረባቸው የክስ መከላከያዎችን ከ30 ዓመታት በኋላ አይቼ በህግ ሙያ የነበረውን እውቀት ስገነዘብ በጣም ነበር የተደነቅኩት።
ከሁሉም በላይ የሚያስገርመው ባህሪዎቹ አንዱ እጅግ ጠንካራ ዲሲፒሊን ያለው ከመሆኑም በላይ በጥራትና  በእቅድ የሚመራ ጊዜውን በትክክልና በቁምነገር ላይ የማዋል ተስጥኦ ነበረው ። ለምሳሌ የመዝገብ አያያዙን መጥቀስ ይቻላል። ይገርምሃል እያንዳንዱ ንብረት፣ የስራ ክንዉኖች፣ ወጪና ገቢዎች ሰነዶች ቁጥርና ስም ነበራቸው፣ የሚቀመጡትም ዘመናዊ በሆነ ድሮወርና ካዝና ውስጥ ነበር። እኛም የቤተሰብ አባላት እያንዳንዳችን  የየራሳችን መዝገብ ነበረን። የተወለድንበት ቀንና ሰአት ሳይቀር፣ የልደት ሰርተፊኬት፣ የህክምና ዝርዝር ውጤቶች፣ የትምህርት ሰርተፊከቶች እንዲሁም ሌሎች የግል ሰነዶቻችን በየስማችን በቅደምተከተል ተይዞልን ነበረ።   
አባቴ በጅማ እንዲሁም በአገር አቀፍ ደረጃ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ክብርና እውቅናም እንደነበረውም ማስታወስ ይቻላል።  የምስራቅ አፍሪካ ላየንስ ክለብ አባልም ነበር፡፡ ይህ አባልነቱም በአገር አቀፍ ደረጃ ለዘመናዊነትና ለእድገት ያበረከተው አስተዋፅኦ ከግምት ውስጥ ገብቶ የተሰጠው ሃላፊነት ነበር፡፡ በክለቡም አባልነት ከተለያዩ የምስራቅ አፍሪካ አገሮች ማለትም ከኬኒያ ከዩጋንዳ ከታንዛኒያ እና ከሌሎችም አገራት በደረሱት የግብዣ ጥሪዎች መሰረት የምስራቅ አፍሪካን አገሮችን ተዘዋውሮ ለመጎብኘት በቅቶ ነበር።
በጅማ ከተማ ውስጥ ሰዎችን በተለያዩ መንገዶች በመርዳት እና በመደገፍም ይታወቃል፡፡ በጅማ አባ ቡና የስፖርት ክለብ ታሪክ የነበረውን አስተዋፅኦ መጥቀስም እፈልጋለሁ፡፡ ክለቡ ሲመሰረት በፋይናንስ ከደገፉት ሰዎች ግንባር ቀደሙ ሲሆን በከፍተኛ አስተዋፅኦውም የክለቡ ፕሬዝዳንት በመሆን አገልግሏል፡፡ አባቴ እና የአዲስ አበባ ቴክኒካል ስኩል ምሩቅ የሆነው አጎቴ ካሚል ሽፋ በአንድ ወቅት ለጅማ ከተማ እድገት ያፈለቁት ትልቅ ፕሮጀክት ነበር። ይህም ለከተማዋ ልማት መሰረት ሊሆን ይችል የነበረውን ትልቅ የነዳጅ ማደያ ጣቢያ እንዲሁም የመኪና ጥገና እና እድሳት መስጫ እንዲሁም የመኪና ስፔር ፓርት መለዋወጭያ ማዕከል ለመመስረት የጠነሰሱት ፕሮጀክት ነበር፡፡
ሌላው ቤተሰብህስ.. እናትህ ፤ እህቶችና ወንድሞችህ …
እናታችን ሙንታሃ ሙዘየን ከአባታችን ከተጋቡ በኋላ ሀደ ኩማ አባ ሞጋ ተብለው ይታወቃሉ፡፡ ከአባቴ ከአባ ሞጋ ጋር ባሳለፉት የትዳር ህይወታቸው 9 ልጆችን አፍርተዋል። የመጀመሪያ ልጃቸው ታላቅ ወንድሜ አህመድ ሞጋ ሲሆን ከጅማ መምህራን ኮሌጅ ተመርቆ በአስተማሪነት ሙያ ተሰማርቶ እስካዛሬ እየሰራ ነው። ከእሱ በኋላ ነፍሷን አላህ ይማራትና  እህቴ ነኢማ ሞጋ ነበረች፡፡ በጣም በትምህርቷ ጎበዝ የሆነችና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አራት ኪሎ ገብታ ስትማር ቆይታ በአይን ህመም ብታቋርጥም በአስተማሪነት በጅማና በአዲስ አበባ አገልግላለች። ከሷ በኋላም ሁለት እህቶች ሚስኪያ ሞጋ እና ሮዛ ሞጋ ሲሆኑ ሮዛም ከጅማ መምህራን ኮሌጅ ተመርቃ በአስተማሪነት እየሰራች ነው። ሌላው ወንድሜ ፉአድ ሞጋ ይባላል፡፡ ከጂማ የእርሻ ኮሌጅ ተመርቆ በጎጃም ተመድቦ እስከ ደርግ ዉድቀት ድረስ ሲሰራ ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ ከጅማ ዞን አስተዳደር ተመርጦ በፓርላማ አባልነት ለአስር አመታት አገልግሏል። ቀጥሎም በኦሮሚያ ብሄራዊ  ክልላዊ መንግስት ውስጥ በአመራር ደረጃ በተለያዩ መስሪያ ቤቶች  እስከዛሬ በማገልገል ላይ ይገኛል። እኔ ስድስተኛ ልጅ ነኝ፡፡ ከእኔ በኋላ እህቴ አዚዛ ሞጋ፤ ወንድሞቼ እስማኤል ሞጋ እና ኤልያስ ሞጋ ነን፡፡
ወደ አባ ሞጋ ታሪክ እንመለስና በደርግ ባለስልጣናት ምን በደል ደርሶባችኋል? ከዚያ በኋላስ መላው ቤተሰብ ምን ገጥሞታል?
አባቴ የደርግ ስርዓት አገሪቱን መምራት ባይጀምር በጅማ ከተማ ብዙ እየሰራ ሊቀጥልና ከፍተኛ ደረጃ ሊደርስ ይችል ነበር፡፡ የደርግ ባለስልጣናት ግን በንጉሱ ዘመን ከመንግስት ጋር በነበረው ግንኙነት ተጠራጠሩት፡፡ በግል ጥረቱ፣ በልምዱና በእውቀቱ ያፈራቸው ሃብትና ንብረት እንዲሁም የደረሰበት የኑሮ ደረጃ በወቅቱ የአድሃሪነት ስም ተሰጥቶት ያለምንም ጥፋት በ1967 ዓ.ም መገባደጃ ላይ  ለአንድ ወር ታሰሮ ነበር።  በድጋሚ በ1968 ዓም፣ ወሩን ባላስታውስም፣ አባታችንን ሊያስሩት መኖርያ ቤታችን ድረስ የመጡበት ቀን ትዝ ይለኛል፣ ለሊት ላይ በሰላም ተኝተን ባለንበት ነበር ወታደሮች ወደ ጊቢያችንን ዘለው ገብተው በሩን ሲሰበሩ አባቴም ወደ በሩ ተጠግቶ ሊያናጋግራቸው ሲሞክር ክፉኛ መቱት በጠመንጃ እያስፈራሩ ሲጮሁበት ሲሰድቡት እኛም ልጆቹ በጣም ደንግጠን ስናለቅስ ነበር እናታችንም በተቻላት መጠን ስታባብለን ነበር።
የአባቴንም ካዝና አስከፍተው ያለዉን ገንዘብ የእናታችን ወርቆች ጌጣጌጦችና ሌሎችንም ጠቃሚ ንብረቶች ዘረፉብን። ከዝያም እንደ ወንጀለኛ እጁን ወደኋላ አስረዉት ለሚጠይቀው ጥያቄ መልስ ሳይሰጡት በጉልበት ይዘዉት ሄዱ። ይህ ለሊት ምንም ጊዘም ከአምሮዬ አይጠፋም፡፡ ያኔ የ9 ዓመት ልጅ ነበርኩ። ለጥቂት ቀናት በጂማ ከተማ ወህኒ ቤት አሰሩት፡፡
እናታችን የታሰረበት ቦታ ሄዳ ስትጠይቅ በደም የተነካካ ቆሻሻ ልብሱን ሲመልሱ በጣም ደንግጣ ስታለቅስ ነበር። በኋላም ወደ አዲስ አበባ አራተኛ ክፍለ ጦር እስር ቤት መወሰዱ ነገሯት። እናታችንም እሱን ለማየት ወደ አዲስ አበባ ሄዳም ልማግኘት ብዙ ስትጥር ነበር። በአዲስ አበባ አራተኛ ክፍለ ጦር እስር ቤት ለሁለት አመታት አሰሩት፡፡ ከዚያም በ1970 ዓ.ም በታህሳስ ወር ማለቂያ ላይ ወደ ጂማ ወህኒ ቤት መለሱት፡፡ እኛም ይሄን ስንሰማ በጣም ተደሰትን፡፡ እናታችንም እኛን ልጆቿዋን ይዛ ወደ ወህኒ ቤት ስንሄድ በቀጠሮ መለሱን፡፡ በተባለው ቀን ሄደን አባታችንን ከእርቀት ለተወሰኑ ደቂቃዎች አየነው። ፊቱም ላይ ትልቅ ሃዘን ይታይበት ነበር፡፡ ከምንም በላይ የሚወዳትን ባለቤቱን ልጆቹን አቅፎ መሳም ፤የሁለት ዓመት ናፍቆቱን መወጣት ባለመቻሉ አይኑ እምባ አዝሎ ነበር።
ሌላዋ አሳዛኝና አሰቃቂ በህይወቴ የማልረሳው ቀን የካቲት 1 ቀን 1970 ዓም ነው። ያኔ የ6ኛ ክፍል ተማሪ ነበርኩ። በዚያ ቀን የጠዋት ፈረቃ ትምህርታችንን ለመማር እየሄድኩ ወደ ኪቶ አንደኛ ት/ቤት ስቃረብ ብዙ የጠመንጃ ተኩስ ሰምቼ ነበር፡፡ ምን ይሆን ብዬ ሳስብ ምናልባት ከት/ቤታችን በላይ የወታደሮች ማሰልጠኛ ስላለ የወታደሮች የስልጠና ተኩስ ልምምድ ይሆናል ብዬ እርምጃዬን ወደ ት/ቤት ቀጠልኩ። የቀኑን ትምህርተን ጨርሼ ወዴ ቤት ስመለስ እቤት ውስጥ ሰው ሁሉ ሲያለቅስ አይቼ በድንጋጤ አክስቴን ስጠይቃት አባታችን አባ ሞጋ አባ ቡልጉ ዛሬ ጠዋት እንደ ተገደለ እያለቀሰች ነገረችኝ፡፡ እናታችንም በሃዘኑ ራሷን ስታ ነበር። በማግስቱ ከታላቋ እህቴ ጋር ሆኜ ግድያውን አስመልክቶ በጅማ መዘጋጃ ቤት ፊት ለፊት የወጣውን ማስታወቂያ አየተን ነበር። በማስታወቂያውም ላይ ከአባቴ ከአባሞጋ አባቡልጉ በተጨማሪ ወደ አርባ የሚሆኑ ሰዎች እንደተረሸኑ በዝርዝር ያሳይ ነበር። እጅግ የሚያሳዝነው  ለእነዚህ ንፁሃን ሰዎች በግፍና በጅምላ መገደል የተሰጠው ምክንያት አድሃሪና የህዝብ ጠላት የሚል ሀሰተኛ ውንጀላ ነበር። አባቴ በዚህ ሁኔታ በግፍ ሲገደል ገና የ42 አመት ጎልማሳ ነበር። እንግዲህ ይህ አሰቃቂ የሆነ መራር ገጠመኝ  የኔ ቤተሰብ ብቻ ሳይሆን የብዙዎች  ኢትዮጵያዊያን እንደነበር በዚያን ወቅት የነበረውን ሁኔታ የሚያስታውሱት ሁሉ የሚገነዘቡት ነው።  በጊዜው አገራችን እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ለእድገቷ በር ከፋች የሆኑ ብሩህና ውድ ልጆችዋን አጥታለች።
ቤተሰባችን ችግር ውስጥ የወደቀው ገና አባታችን ሲታሰር ነበር፡፡ ንብረታችን ተበታተነ ፤ አስተዳዳሪውን በማጣቱ መላ ቤተሰባችን ችግር ውስጥ ወደቀ፡፡ በደርግ ባለስልጣናት ብዙ ንብረት ተዘርፎብናል፡፡ ቪላ ቤታችን ባልታወቀ የባንክ እዳ ተወረሰብን፤ የቤት መኪና እና ሌላ የጭነት መኪናም የት እንዳገቧቸው ማወቅ አልቻልንም፡፡ በአጠቃላይ መንገድ ላይ ተበትነን ነበር የቀረነው፡፡ ቀሪውን ጊዜ በአያታችን ቤት አሳለፍን።
እስቲ ከቤተሰብ ታሪክ እንውጣና ወደ የትምህርት ቤት ህይወትህ እንሻገር፣
እስከ 6ኛ ክፍል የመጀመርያ ደረጃ ትምህርቴን የተማርኩት በትውልድ አካባቢዬ ኪቶ ሲሆን ከዚያ በኋላ 7ኛ እና 8ኛ ክፍልን የተማርኩት በሚያዚያ 27 ነው፡፡ በስምንተኛ ክፍል ሚኒስትሪ ፈተና 96 ነጥብ አገኘሁ፡፡ የሁለተኛ ከፍተኛ ደረጃ ትምህርቴን የቀጠልኩት ምርጫዬን የቴክኖሎጂ መስክ አድርጌ ነበር፡፡ በወቅቱ ቴክኖሎጂ የመረጥን አውቶ መካኒክ፤ ኤሌክትሪስቲ፣ የሜታል ዎርክ እና የዉድ ዎርክ እንዲሁም የድሮዊንግ ትምህርቶችን በቴክኒክና ሙያ ተቋም የምንማርበት እድል ነበር፡፡ 10ኛ ክፍል ላይ ከ1 እስከ 10ኛ ደረጃ ለሚያገኙ ጎበዝ ተማሪዎች አዲስ አበባ በሚገኘው የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋም ተግባረድ የመግባት እድል ተጠቃሚ ይሆኑ ነበር፡፡  በ10ኛ ክፍል የነበረኝ ውጤት 3ኛ ደረጃ ስለሆነ ወደ ተግባረድ ለመግባት ከተመረጡት አንዱ ሆኜ ወደ አዲስ አበባ ተዛወርኩ፡፡
ከተግባረድ ተመርቄ እንደወጣሁ ከሁለት ሳምንታት በኋላ በጥይት ፋብሪካ ስራ ጀመርኩ፡፡ ገና በ18 አመቴ ስራ መያዜ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢንጂነሪንግ ትምህርቴን ለመቀጠል ሃሳብ ነበረኝ፡፡ በጥይት ፋብሪካ ተቀጥረን መስራት ከጀመርን በኋላ ከተወሰኑ ጓደኞቼ ጋር በዩኒቨርስቲ ትምህርታችንን ለመቀጠል በየአቅጣጫው ማመልከቻ አስገብተናል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አምስት ኪሎ የመካኒካል ኢንጅነሪንግ ትምህርቴን ለመቀጠል የነበረኝ ፍላጎት ግን በቀላሉ የሚሳካ አልነበረም፡፡
በተግባረእድ የነበራችሁ ውጤት የጥይት ፋብሪካው ቅጥር አስገኝቶላችኋል፡፡ ታድያ ለምንድነው ከፍተኛ ትምህርት ከስራችሁ ጎን ለጎን ለመከታተል ያዳገታችሁ?
በጥይት ፋብሪካ ተቀጥረን መስራት ከቀጠልን በኋላ በመጀመርያ ወር ሁለት መቶ ሃያ አምስት ብር ሲከፈለኝ ለ18 ዓመት ወጣት ትልቅ ገቢ ነበር፡፡ ለእናቴ በየወሩ 50 ብር የምልክበት አቅም ስለፈጠረልኝ ደስተኛ ነበርኩ፡፡ ከደሞዙ ሌላ በጥይት ፋብሪካው መስራት ብዙ አጓጊ ሁኔታዎች ፈጥረውብናል፡፡ በፋብሪካው የሚሰሩት የቼክ ዜጎች ነበሩ፤ ግዙፎቹን ማሽነሪዎች እያስተዋወቁ ያስተምሩን ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ አምራች ኢንዱስትሪዎች በወቅቱ ከፍተኛ ደረጃ ያላቸው ማሽነሪዎች ነበሩ፡፡ በእነሱ ላይ መስራት እና እውቀት ማግኘት ትልቅ ጥቅም ነበረው፡፡
በኢንጀነሪንግ ትምህርት ለመቀጠል ለአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ያስገባነውን ማመልከቻ ውጤት ጎን ለጎን እየተጠባበቅን ቆየን፡፡ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ማመልከቻቸው ተቀባይነት ላገኘ ተማሪዎች ስም ዝርዝር ሲወጣ እኛ አልነበርንም፡፡ ሁኔታው ግራ ስላጋባን በአግባቡ ምዝገባችንን አከናውነን ስም ዝርዝራችን አለመውጣቱ እንዲብራራልን ዩኒቨርስቲውን ጠየቅን፡፡ ከተግባረድ ትምህርት ቤት በጥሩ ውጤት ለተመረቅነው በዩኒቨርስቲ ለመቀጠል ቅድሚያ ሊሰጡን ይገባ ነበር፡፡ ዩኒቨርስቲው በሰጠን ምላሽ አስቀድሞ ባወጣው ማስታወቂያ ስራ ለሌላቸው ተመራቂዎች ቅድሚያ እንደሚሰጥ ገለፀልን። ከተግባረእድ ትምህርት ቤት ከወጡት 75 በመቶው ስራ ማግኘታቸውን በማረጋገጣችን የትምህርት እድሉን ስራ ላላገኙት ሰጥተነዋል ነበር የተባልነው፡፡ በርግጥ ጥይት ፋብሪካ ስንገባ ብዙ ነገሮች ቃል ተገብተውልናል። በፋብሪካው ከውጭ ዜጎች ጋር እንደምንሰራ፤ ከተወሰኑ የስራ ልምዶች በኋላ በነፃ የትምህርት እድል ወደ ውጭ አገር የምንላክበት ሁኔታ እንደሚኖርም ነግረውናል፡፡ ወጣቶች ስለነበርን በጥይት ፋብሪካ የነበረው አጀማመራችን አጓጉቶን ነበር፡፡ በዚያን ወቅት ጥይት ፋብሪካው ከፍተኛ ምርት ነበረው፡፡ ከተግባረድ ተመርቀን ስራ የጀመርነው ሃላፊነታችን በጥገና የማሽነሪዎች ክትትል ላይ ያተኮረ ስራ ነው፡፡ በጥይት ፋብሪካው ከነበሩ የማምረቻ ማሽነሪዎች ጥገና ባሻገር በፋብሪካው የግራይንዲንግ፤ የቼዝና በትልልቅ ማሽነሪዎች በተለያየ መንገድ እንሰራ ነበር፡፡ ስለሆነም በፋብሪካው በምንሰራበት ወቅት በዩኒቨርስቲ ትምህርታችን ለመቀጠል የምንቀሳቀስበት አመቺ ሁኔታ አልነበረንም፡፡ ጠዋት ሁለት ሰዓት ወደ ፋብሪካው የገባን ለምሳም ሳንወጣ በዚያው ስንሰራ ቆይተን ነው ማታ የምንወጣው፡፡ በወቅቱ ወደ አዲስ አበባ ኡኒቨርሲቲ ማመልከቻ አስገብተን ጉዳያችንን ለማስፈፀም በቂ ጊዜ አልነበረንም ማለት ነው፡፡ ከእኛ ጋር ከተግባረእድ ተመርቀው የነበሩና ስራ የሌላቸው ተመራቂዎች ግን በዩኒቨርስቲ ጉዳያቸውን ተከታትለው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ብቻ ሳይሆን ወደ አስመራ ዩኒቨርስቲ ተመድበው ትምህርታቸውን የሚቀጥሉበት እድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡
በጥይት ፋብሪካው ያጊዜ የነበሩት የቼክ ዜጎች ጋር ትቀራረብ ነበር?
በወቅቱ ቼኮስሎቫኪያ ተብላ ከምትጠራው አገር የመጡ ባለሙያዎች የጥይት ፋብሪካውን በዘመናዊ መሰረት እና አቅም ላይ የገነቡ ናቸው፡፡ ከፋብሪካው ሰራተኞች እነሱን በቅርበት የተግባባ እና አብሮ የሰራ ኢትዮጵያዊ እኔ እንደነበርኩ አስታውሳለሁ፡፡ ከቼክ ተወላጆቹ ጋር የነበረኝ ጓደኝነትም ቋንቋቸውን የምረዳበት ደረጃ አደረሰኝ፡፡ ከቼኮቹ ጋር ስለትምህርት ስናዋራ ውጭ አገር መሄድ እንደምፈልግ ደጋግሜ እነግራቸው ነበር፡፡ የጥይት ፋብሪካ ከፍተኛ ባለሙያዎች የነበሩት ቼኮች በየስድስት ወሩ እና በየዓመቱ እየተቀያየሩ ወደ አገራቸው ይመላለሳሉ፡፡ አንዴ በጣም ለምግባባው አንድ የቼክ ቤተሰብ የመልካም ምኞት እና የአዲስ አመት ስጦታ ላኩኝ፡፡ ለልጆቹ ፤ለልጅ ልጆቹ ሁሉ የላኩለትን ፖስት ካርድ ቤተሰቡ አይተው እነሱም ለእኔም ይልኩልኝ ነበር፡፡ ስለዚህም ወደ ቼክ ሪፖብሊክ የመሄድ ጉጉት ነበረኝ፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ትምህርትህን ለመቀጠል በያዝከው እቅድ ቀጠልክ ወይስ ወደ ቼክ ወይንም ወደ ሌላ ውጭ አገር ለትምህርት ለመጓዝ ሙከራ ገባህ?
ወደ ቼክ ለመጓዝ በነበረኝ ፍላጎት ውስጥ ሆኜ በጥይት ፋብሪካው እየሰራሁ ከፋብሪካው ባልድረባ ከሆኑት የኢሰፓ ፓርቲ አባላት የአባልነት ጥሪ አቅርበውልኝ ነበር። ከቼኮቹ ጋር በነበረኝ መግባባት እና በስራ ትጋቴ ምስጉን መሆኔን ገልፀው ፓርቲውን በአባልነት እንዳገለግል ጠየቁኝ። በፍፁም አልሆንም የሚል ምላሽ ነበር የሰጠኋቸው፡፡ በወቅቱ ረመዳን ነበርና እንደምፆም ነግርያቸው፤ ፖለቲካም መሳተፍ አልፈልግም አልኳቸው፡፡ ያኔ ከፖለቲካ መፅሃፍት ይልቅ አዘውትሬ አነብ የነበረው የቼክ ቋንቋን መፅሃፍትመ ነበር፡፡ በኢሰፓ በአባልነት እንዳገለግል የቀረበልኝን ጥያቄ ያለመቀበሌ የኋላ ኋላ መዘዝ ነበረው፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ለፋብሪካ ሰራተኞች ነፃ የትምህርት እድል በውጭ አገር መጣ፡፡ ወደ ቼኮስሎቫኪያ ነው፡፡ በቅርበት የሚያውቁኝ ቼኮቹ በዚህ እድል አንተና ጓደኞችህ መጠቀም አለባችሁ እያሉኝ ቆይተው፤ የመጣው እድል ለኔ ሳይ ሆን የፓርቲው አባላት ለሆኑት ተስታቸው። በስራቸው ሳይሆን የፓርቲ አባል ስለነበሩ ነው የተመርጡት፡፡ ከዚያም በኋላ ተመሳሳይ እድሎች ቢመጡም የኔ እድል ተዘግቶ ቀረ። ይገርምሃል ለእኔ እድሉ ተነፍጎ በምትክነት የሄደ አንድ የፋብሪካው ሰራተኛ አንድ ልዩ ገጠመኝ ነበረው፡፡ ቼክ ሲገባ በፋብሪካ ከነበሩ የአገሬው ሰዎች ቤተሰባቸው ጋር ተገናኝቶ በስሙ ሳይሆን ኢብራሂም እያሉ ይጠሩት እንደነበር ከውጭ አገር ተመልሶ ሲመጣ ነግሮኛል፡፡ ይህን ስሰማም በጣም ቅር አለኝ ወደ ውጭ አገር ለትምህርት መጓዝ  እቅዴን በእልህ ተያያዝኩት፡፡ ማትሪክ ስፈተን ያመጣሁት 3 ነጥብ ዩኒቨርስቲ ያስገባኝ ነበር። እንግሊዘኛ ኤ ካመጣሁ በኋላ በሌሎቹ ቢ እና በፊዚኪስ ሲ ነበረኝ፡፡ ስለዚህም በግሌ በመፈተን በፊዚክስ የነበረኝን ሲ ወደ ኤ አሳደግኳት፡፡ ከዚያ በኋላ 3.4 ነጥብ ስለሆነልኝ ወደ ቼክ ለመጓዝ በግሌ አመለከትኩ፡፡ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ሃየር ኮሚሽን በግሌ ባስገባውት የትምህርት ማስረጃ መሰረት ከአንዴም ሦስቴ የስኮላር ሺፕ እድል አኝይቼ ነበር፡፡ ይሁንና የትምህርት እድሉን ለማሳካት ከተለያዩ የመንግስት ተቋማት የድጋፍ ደብዳቤዎች ያስፈልጉ ነበር፡፡ ከአኢወማ፤ ከኮሚሳሪያት፤ እና የህክምና መረጃ ከባልቻ ሆስፒታል ማፃፍም ያስፈልግ ነበር፡፡ የቀበሌዎች ከፍተኛ ኮሚሳሪያት ከአንዴም ሁለቴ ወደ ቼኮዝላቪያ የመሄድ እድሌን ዘጉብኝ። ለሦስተኛ ጊዜ ወደ ራሺያ ለመሄድ እድል ደርሶኝ ከብዙ ዉጣ ዉረድ በኋላ እድሉ ተሳክቶልኝ በመስከረም 1983 ዓ.ም ወደ ራሺያ መጣሁኝ።
ወደራሽያ እንደመጣሁ ለአንድ አመት በሞስኮው የሃይ ዌይ ኢንስቲቲዩት  የራሽያ ቋንቋ ተምሬ ከዚያም በሞስኮው ቴክኒካል ዩኒቨርሲቲ ለአምስት አመታት ተምሬ በመካኒካል ኢንጂነሪንግ የማስተር ዲግሪየን ተቀበልኩ። በነዚህ 6 አመታት በሞስኮ ከተማ ውስጥ ባለፍኩበት ኑሮ ብዙ ገጠመኞችና የህይወት ዉጣ ዉረዶች አጋጥመውኛል። ከሁሉም አብልጨ አላህን የማመሰግነው ከፖርቱጋል ዜጎች ጋር መተዋወቄ ነው። በዚሁ አጋጣሚ ላደረጉልኝ እርዳታና ለሰጡኝ ትልቅ ፍቅር ከልቤ ላመሰግናቸው እወዳለሁ፡፡
በአሁኑ ወቅት በተማርክበት የኢንጀነሪንግ ሙያ እየሰራህ አይደለም፡፡ የፖርቱጋል ኤምባሲ ሰራተኛ እንደሆንክ ነው ያወቅኩት
አዎ፡፡ በሞስኮው የፖርቱጋል ኤምባሲ በቪዛ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች አማካሪ ሆኜ ነው የማገለግለው። የኤምባሲው ፅህፈት ቤት የሚገኘው እኔ ከምኖርበት ፕሮስፔክት ሚራ የተባለው ጎዳና በ10 ደቂቃ የእግር ጉዞ ነው። በደቡብ አውሮፓ የምትገኘው ፖርቱጋል በቋንቋዋ ውበት፤ በቆየ ታሪኳ፤ በሚያምሩ የባህል ትውፊቶቿ የተከበረች ናት፡፡ እውነቱን ለመናገር ፖርቱጋሎች በጣም ጥሩ ዜጎች ናቸው፡፡ እንደ ወንድማቸው ነው የሚያዩኝ፣የሚያከብሩኝ። ያደረጉልኝን ውለታ ይሄ ነው ብዬ መግለፅ ይቸግረኛል፡፡ በዚህች ታላቅ አገር የዲፕሎማት ስራ ሳከናውን ብዙ እውቀት አግኝቻለሁ፡፡ በተለይ በፖርቹጊዝ ቋንቋ የደረስኩበት ደረጃ በጣም የምኮራበት ነው፡፡
በዓለም ዋንጫው የትኞቹን ጨዋታዎች ተከታተልክ፤ የማንስ ደጋፊ ነበርክ?
ያው እንደምታውቀው ሞስኮ ውስጥ በፖርቱጋል ኤምባሲ የምሰራ በመሆኔ በዓለም ዋንጫው ድጋፌ በክርስትያኖ ሮናልዶ የሚመራው ቡድን ነበር፡፡ ፖርቱጋል በምድቧ የመጀመርያ ጨዋታ በሞስኮው ሉዥኒኪ ስታድዬም ከስፔይን ጋር ስትገጥም ስታድዬም ለመግባት አልቻልኩም ነበር፡፡ይሁን ኢንጂ ከፖርቱጋል ጓደኞቼና ባልድረባዎቼ እንዲሁም ከራሻዊያን ጓደኞቻችን ጋር እስፔይንና ፖርቱጋል 3=3 የወጡበትን የእግር ኳስ ግጥሚያ ድራማ፣ የክርስቲያኖ ሮናልዶን የሚያስደንቅ ችሎታና ጨዋታ በትልቅ ደስታ አይተነዋል። ከዚያ በኋላ በድጋሚ ሞስኮ ላይ ፖርቱጋል ከሞሮኮ ተጋጠሙ ፡፡ጨዋታውን ለመመልከት የፖርቱጋል ፕሬዝዳንት የፑቲን የክብር እንግዳ ሆነው ሞስኮ ተጋብዘው ነበር፡፡ የፖርቱጋሉ ፕሬዝዳንት ማርሴሎ ሬቤሎ ድ ሶውሳ ይባላሉ፡፡ በሞስኮው የፖርቱጋል ኤምባሲ ከጨዋታው በፊት ጉብኝት ነበራቸው፡፡ ባደረግንላቸው አቀባበል ላይ ከእኔ ጋር ሳይቀር ሰልፊ ፎቶ ተነስተዋል፡፡ በዚያን ቀን ክርስትያኖ ሮናልዶና የፖርቱጋል ብሄራዊ ቡድንን በልምምድ ካምፓቸው መጎብኘት የምንችልበት አጋጣሚን አለመጠቀሜ በጣም ይቆጨኛል፡፡ ከዚያ በኋላ ግን የፖርቱጋልን ጨዋታ በስታድዬም የምታደምበት እድል ተፈጥሯል፡፡ ከኤምባሲ ባልደረቦቼ ጋር በመሆን የተመለከትነው ጨዋታ በሳራንስክ  ፖርቱጋል ከኢራን የተገናኙበትን ነበር፡፡ ከዚያ ውጭ የዓለም ዋንጫውን አብዛኛዎቹን ጨዋታዎች በቤቴ የተከታተልኩ ሲሆን አንዳንዶቹን ሞስኮ ውስጥ በሚገኙት ፋን ፌስቶች ተመልክቻቸዋለሁ፡፡
ራሽያ ያዘጋጀችውን 21ኛው የዓለም ዋንጫን አስመልከቶ የምትለው ምንድነው?
እንደተመለከትከው ራሽያ ግዙፍ አገር ናት፡፡ ከሞስኮ ከተማ ውጭ በተለያዩ ግዛቶች ዓለም ዋንጫን በማስተናገድ የነበሩት ተመክሮዎች የላቁ ናቸው፡፡ ወደፊትም አገሪቱ የዓለማችንን ታላላቅ የስፖርት መድረኮች በብቃት የምታስተናግድበት አቅም እንዳላት ነው የማምነው። ኦሎምፒክን ጨምሮ በተለያዩ ስፖርቶች የሚካሄዱ ዓለም አቀፍ ሻምፒዮናዎችን ራሽያ ትፈልጋለች፡፡ በዓለም ዋንጫው ወቅት በተለይ በሞስኮ ከተማ የተፈጠረው ድባብ እጅግ የሚያስደንቅ ነበር፡፡ ራሽያውያን ቡድናቸው በዓለም ዋንጫው አዲስ ታሪክ ሊሰራ ይችላል በሚል ስሜት ውስጥ መግባታቸው ደስ የሚል ነበር፡፡ በሞስኮው ቀይ አደባባይ እና በክሬምሊን አካባቢ፡ በታዋቂው የታሪክ እና የጥበብ መናሐርያ አርባት ጎዳና፤ በሞስኮው ሉዥኒኪ ስታድዬም እና በዙርያው በሚገኘው የሞስኮ ስቴት ዩኒቨርስቲ የፊፋ የደጋፊዎች አደባባይን በዓለም ዋንጫው ሰሞን ተዝዙሬ በመጎበኘቴ ተደስቻለሁ፡፡ በርግጥ የአውሮፓ ደጋፊዎች በሞስኮ በብዛት አለመኖራቸው የሚኖረውን ድምቀት ቀንሶት ሊሆን ይችላል። ዋናው ምክንያት አውሮፓውያን በስራ የሚወጠሩበት ጊዜ መሆኑ ነው፡፡ በየስታድዬሙ የተመለከትኳቸው ጥቂት የአውሮፓ አገራት ደጋፊዎች በዓለም ዋንጫው በብዛት ሆነው ዝማሬ እና ልዩ የድጋፍ ትእይንቶችን በማቅረብ ግጥሚያዎችን ከመከታተል ይልቅ ቱሪስት ሆነው የሞስኮን የምሽት ክበቦች መዝናኛዎች እና አደባባዮች ማጣበባቸውን አብረን የታዘብነው ነው፡፡
ኢንጅነርነቱን ከዚያም የዲፕሎማት ሙያህንን አንስተናል። ለመሆኑ ልዩ ዝንባሌዎች አሉህ…
በተለይ ዝንባሌዬ ብዬ የምጠቅሰው ሙዚቃ መጫወትን ነው፡፡ አባታችን ያሳደጉን በዘመናዊ አኗኗር ነው፡፡ ሲኒማ ቤት እንገባለን፡ በቤት መኪና ሽርሽሮች እንጓዛለን…. በቤታችን የሸክላ ሙዚቃ ማጫወቻ ስለነበር የጥላሁን፤ የማህሙድ፤ የአለማየሁ፤ የአሊ ቢራ ኦርጅናል ዜማዎችን ከልጅነታችን ጀምሮ እየሰማን ነው ያደግነው፡፡ የአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን የውጭ ዘፈኖችም እናዳምጥ ነበር፡፡ ከጎረቤት አገራት በተለይ የሱዳንን ሙዚቃዎች እንሰማ ነበር፡፡ ስለዚህም ዋና ዝንባሌዬ ከሙዚቃ ፍቅር ጋር ይያያዛል፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ የታዋቂ ሙዚቀኞችን ዘፈኖች ማንጎራጎር ለምጀዋለሁ፡፡ በተለይ ከኢትዮጵያ ሙዚቀኞች አሊ ቢራን በጣም አደንቀዋለሁ። እነ ማህሙድ አህመድ፤ ጥላሁን ገሰሰ፤ አለማየሁ እሸቴም ዘወትር የምሰማቸው እና ዘፈኖቻቸውን የማንጎራጉርላቸው ናቸው፡፡ ከሙዚቃ መሳርያዎች በተለይ ጊታር ለመጫወት እሞክራለሁ፡፡ አንድ ገጠመኝ አለኝ፡፡ እዚህ ራሽያ ውስጥ በሚተላለፍ ራድዮ ፕሮግራም በአንድ ወቅት በእንግድነት ተጋብዤ ነበር፡፡ እናም ጋዜጠኛዋ ከውይይታችን ባሻገር እንድዘፍንላት ጋብዛኝ ነበር፡፡እኔም በእለቱ ከአገሬ ዘፈኖች የሙሃሙድን ትዝታና የቆዩ ተወዳጅ የእንግሊዘኛ ሙዚቃዎችን እየዘፈንኩ ነበር አድማጮቼን ያስደሰትኳቸው።

Read 5244 times