Saturday, 15 September 2018 00:00

እኛም ‹‹የኮልፌ ልጆች›› ነን!!

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(3 votes)

  በወዲያኛው ሣምንት የተወሰኑ ልባም ወጣቶች ወደ ታሪካዊው የአንዋር መስጊድ በመሄድ፣ የጽዳት ሥራ ማከናወናቸውን አይተናል፡፡ እነዚህ ወጣቶች በአዲስ አበባ ከተማ የኮልፌ ወጣቶች ክርስቲያን ማህበር አባላት ናቸው፡፡ የክርስትና እምነት ተከታዮች የሆኑት እነዚህ ልባም ወጣቶች፤ ከኮልፌ ወደ መርካቶ ሄደው፣ በአንዋር መስጊድ የጽዳት ሥራ ለማከናወን የተነሳሱት፤ የሐገራቸው አኩሪ ቅርስ የሆነን ማህበራዊ እሴት ጠብቆ ለማቆየትና የፖለቲካ ነጋዴዎችን ሴራ ለማክሸፍ ነበር፡፡
በቅርቡ በሶማሌ ክልል የታየው፤ ሐይማኖትን ዒላማ ያደረገ ጥቃት ከሁሉ በላይ የክልሉን ህዝብ አስደንግጧል፡፡ አሳፍሯል፡፡ አንዳንድ ሽማግሌዎች፣ የሐይማኖት መሪዎችና ኡጋሶች፤ በሚዲያ ቀርበው የሰጡት አስተያየት፤ በተከሰተው ነገር ምን ያህል ስሜታቸው እንደተጎዳ የሚያመለክት ነበር። በረጅም ዘመን የአብሮ መኖር ታሪክ እንዲህ ዓይነት ነገር አይቶ የማያውቀው የክልሉ ህዝብ ቀርቶ የኢትዮጵያን ታሪክ ለሚያውቅ የውጭ ሐገር ሰውም አስደንጋጭ መሆኑ አይቀርም፡፡ የተፈጠረው ነገር ለማንም ሰብአዊ ፍጡር አሳዛኝ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ክስተቱን ይበልጥ አስደንጋጭ የሚያደርገው፤ ጥቃቱን ያቀነባበሩት የፖለቲካ ነጋዴዎች የያዙት ዓላማ ነው፡፡ ጥቃቱን ያቀነባበሩት ወገኖች ይዘውት የነበረው ግብ፤ በቀላሉ ሊበርድ የማይችልና በፍጥነት የሚቀጣጠል የግጭት እሣት መለኮስ ነበር፡፡ ጥቃቱ በተፈጸመበት ወቅትም ሆነ ከዚያ በኋላ ሁሉም ተረባርቦ እሣቱን ለማጥፋት እንቅስቃሴ በማድረጉ ተገታ እንጂ የታቀደው ነገር በጣም ዘግናኝ ነበር፡፡
የኮልፌ ክርስቲያን ማህበር ወጣቶች የወሰዱት እርምጃ፤ ክፉዎች ያሰቡት ተቀጣጣይ ነገር አለመኖሩንና ኢትዮጵያውያን በሐይማኖት ልዩነት ሳቢያ ከሚመጣ አደጋ ራሳቸውን ለመጠበቅ የሚችሉ ብልህ ህዝቦች መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ጎብኝዎች ሁሉ በልዩ የአድናቆት ስሜት የሚጠቅሱትንና የሐገራችን ህዝብ ልዩ መገለጫ የሆነውን እሴት ከጥቃት ለመጠበቅ የተንቀሳቀሱት የእነዚህ ወጣቶች ተግባር፤ በትውልዱ ተስፋ እንድናሳድር የሚያደርግ ነው፡፡ ዘመናትን ያስቆጠረ የሁለቱ ሐይማኖቶች ተከታዮች ሰላማዊ ግንኙነትን፤ ከፖለቲካ ነጋዴዎች መሰሪ ጥቃት ተጠብቆና ዛሬም እንደ ትናንቱ በክብር ተይዞ ለመጪው ትውልድ ሊተላለፍ የሚችል ቅርስ መሆኑን በጉልህ የሚያመለክት ነው፡፡
የሁለቱ ሐይማኖቶች ተከታይ የሆኑ ምዕመናን ለዘመናት ይዘውት የዘለቁትና ለዓለም ህዝብ በአስተማሪነት ሊቀርብ የሚችለው ልዩ መስተጋብር፣ በአሁኑ ጊዜ ተገዳዳሪ ዓለም አቀፋዊ ክስተት እንደ ገጠመው በማሰብ የሚጨነቁ ሁሉ፤ በእነዚህ ወጣቶች ተግባር እፎይታ ይሰማቸዋል፡፡ የሁለቱ ሐይማኖቶች ተከታዮች ልዩ መስተጋብርን የሚፈታተን ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ መፈጠሩን በመጥቀስ፤ ‹‹እናንት ኢትዮጵያውያን እነሆ፤ ይህን አኩሪ እሴት መጠበቅ መቻል አለመቻላችሁ የሚፈተንበት ጊዜ መጣ›› የሚል አስተያየት የሚያቀርቡ የውጭ ወገኖች አሉ፡፡ ከግሎባላዊው ስርዓት መጠናከር፤ ማለትም ከኢንተርኔት አገልግሎት መስፋፋትና ከፖለቲካ ነጋዴዎች ሴራ ጋር አያይዘው በማሰብ የሚጨነቁ ወገኖች ሁሉ፤ በእነዚህ ወጣቶች ተግባር መጽናናት ይችላሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ከግሎባላዊው ስርዓት መጠናከር ጋር ተያይዞ የሚደቅንባቸውን አደጋ ተሻግሮ ለመሄድ የሚያበቃ የአስተሳሰብና የሞራል ከፍታ እንዳላቸው ይረዳሉ፡፡ በወጣቶቹ የተከናወነው አብነታዊ የበጎ ፈቃደኝነት ሥራ፤ እጅግ የምንሳሳለት ድንቅ ባህላዊና ታሪካዊ እሴታችን በዘመኑ ወጣቶች ተጠብቆ፣ ለመጪዎቹ ተከታታይ ትውልዶች እንደሚሻገር የሚያረጋግጥ ተግባር ነው፡፡
ኢትዮጵያ ሁለቱ ሐይማኖቶች ለመጀመሪያ ጊዜ ፊት ለፊት የተገናኙባት ምድር ናት፡፡ ኢትዮጵያ ከነቢዩ መሐመድ ዘመን ጀምሮ የተፈጠረን ሰላማዊ ግንኙነት ጠብቃ መዝለቅ የቻለች ሐገር ናት፡፡ ከመካ ቀጥሎ የእስልምና ሐይማኖት የተተገበረባት የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት ሐገር ናት። ከነቢዩ መሐመድ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያላት ናት፡፡ በእርሳቸው ዓይን ሞገስ ያገኘች ሐገር ናት፡፡
ነቢዩ መሐመድ በ610 ዓ.ም በተነሱ ጊዜ፤ የገዛ ዘመዶቻቸው በተከታዮቻቸው ላይ ጥቃት ሲሰነዝሩ፤ ‹‹ሐበሻ (ኢትዮጵያ) የእውነት አገር ናት፤ በውስጧም ሰውን የማይበድል፤ በእርሱም ዘንድ አንድም የማይበደል ንጉሥ አለና፤ ወደዚያ ብትሄዱ መልካም ነው›› በማለት ተከታዮቻቸውን ሁለት ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ልከዋቸዋል፡፡ በመጀመሪያ፤ የነቢዩ ሴት ልጅ፣ ኸሊፋው ዑስማን እና የአጎታቸው ልጅ ጃዕፈር የሚገኙባቸው 16 ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል። ከዚያም ከመቶ በላይ የሚሆኑ የሐይማኖት ጥገኞች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው 15 ዓመት በመልካም ግንኙነት ተቀምጠዋል፡፡
ሙስሊሞች ሐይማኖታቸውን እንዳይተገብሩ የማይከለክላቸው ከሆነ፤ እስላማዊ ባልሆነ ሐገር ወይም መንግስት ውስጥ ከሌሎች ጋር በሰላም መኖር እንደሚችሉ አስረጅ ሆኖ የሚጠቀስ ታሪክ ያላት ሐገር ናት፡፡ በዛው በነቢዩ ዘመን በነበረው ክርስቲያናዊ ንጉስ ትተዳደር የነበረችው ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን፤ ከዛ ወዲህ ያለችውም ኢትዮጵያ ባልተቋረጠ ሁኔታ የአብሮ መኖር መርህን ለዓለም እያሳየች ብዙ ዘመናትን ዘልቃለች፡፡ አሁንም ታሪክ በአድናቆት የሚዘክረውን ይህን ልዩ የአብሮ መኖር ባህል ጠብቀው መቆየት የሚችሉ ወጣቶች እንዳሏት አረጋግጣለች፡፡
ታሪክ እንደሚመሰክረው፤ ከምድረ - አረቢያ የተወለደውን እስልምና ከተቀበሉ፤ በነቢዩ መሐመድ ዙሪያ ከነበሩ ጥቂት የቅርብ ሰዎች ውጪ፤ ከኢትዮጵያውያን ቀድሞ እስልምናን የተቀበለ ህዝብ አይገኝም፡፡ በመካ የነበሩ የቁረይሽ ገዢዎች ስደተኞቹ ተላልፈው እንዲሰጡአቸው ሲጠይቁ ‹‹አልሰረቁም - አልገደሉም፤ አሳልፌ አልሰጥም›› በማለት፤ ስደተኞቹን በቀና መንፈስ ተቀብሎ፤ ያለ ሥጋት እምነታቸውን በነፃነት እንዲተገብሩ ከመፍቀድ የሚልቅ ኢስላማዊ ተግባርም አይኖርም፡፡ የኢትዮጵያውያንን ምግባር አልቆና አተልቆ የሚያወድስ አዲስ አረባዊ የሥነ- ጽሑፍ ዘውግ እንዲፈጠር ያደረገውም ይህ ድንቅ ተግባር ነው፡፡
በዚህ የተነሳ፤ ኢትዮጵያ፤ ክርስቲያኖች እና ሙስሊሞች ለመጀመሪያ ጊዜ፤ በአንድ መንግስት ሥር በሰላም የኖሩባትና እምነታቸውን በነፃነት የተገበሩባት ድንቅ ሐገር ሆናለች፡፡ በነቢዩ የትውልድ ሐገር እምነታቸውን በነፃነት መተግበር ያልቻሉ ሰዎች፤ በነቢዩ ትዕዛዝ በስደት የመጡባት ኢትዮጵያ፤ እንደ እሙ ሐይመን የእስልምና እምነት ሞግዚት ወይም ምትክ እናት ሆና እምነቱን የጠበቀች ሐገር ናት፡፡ በዚህም የተነሳ እንግሊዛዊው የታሪክ ፀሐፊ ኤድዋርድ ጊቦን፤ ‹‹ኢትዮጵያ ለአንድ ታላቅ ማህራዊ አብዮት መስፋፋት ምክንያት ሆናለች›› በማለት ይወቅሳታል። ጊቦን ያለ አንዳች ማለባበስ፤ ‹‹ኢትዮጵያ ወደ እርሷ የሸሹ ሙስሊሞችን ባታስጠጋና ባትጠብቃቸው ኖሮ፣ እስልምና በዓለም አይስፋፋም ነበር›› ይላል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ከነቢዩ መሐመድ ዘመን ከሦስት መቶ ዓመታት ገደማ ቀደም ብሎ የክርስትና እምነትን የተቀበለ በመሆኑ፤ እንዲሁም በአንዳንድ የአረቢያ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ ያደርግ ስለ ነበር፤ ኢትዮጵያ የ‹‹አንድ አምላክ›› እምነት የሚተገበርባት ክርስቲያናዊ ሐገር እንደ ሆነች፤ ነቢዩ መሐመድ እና የዘመናቸው ሰዎች ያውቁ ነበር፡፡ በአረብኛው ቃል፤ አል-ሐበሻ  ወይም አል- አሕባሽ በሚል የሚጠሩት የኢትዮጵያ ህዝቦች፤ ከቀይ ባህር ማዶ የሚኖሩ አፍሪካዊ ጎረቤት ህዝቦች መሆናቸውን ጥንታዊያኑ የአረቢያ ህዝቦች ያውቁ ነበር፡፡  
ገና ከእስልምና ፅንስ ጀምሮ፤ ለመላው ዓለም ሙስሊም ልዩ ትርጉም ያላት ሐገር ሆና እስከ ዛሬ የዘለቀችው ኢትዮጵያ፤ ሙስሊሞችን ከጥቃት የጠበቀው የፍትሐዊውና የክርስቲያኑ ንጉስ አልነጃሽ ሐገር ኢትዮጵያ፤ ‹‹የመጀመሪያው ሂጅራ›› (እኤአ 615-616 ዓ.ም) ምድር የሆነችው ኢትዮጵያ፤ በወቅቱ ጠቅላላውን የሙስሊም ማህበረሰብ አቅፋ - ደግፋ መጠጊያ በመስጠቷ፤ በዓለም ሙስሊም ህዝብ ዘንድ የፍትሕ ምድር ተደርጋ የመታየት የማይደበዝዝ ልዩ የታሪክ ግርማን አግኝታለች፡፡ ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ እምነቱ ያለ ጦርነት የተስፋፋባቸው ሐገሮች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች፤ ኢትዮጵያዊነታቸውንና ብሔረሰባዊ  ማንነታቸውን ከሐይማኖቱ እኩል የማንነታቸው መገለጫ አድርጎ የማየት ልዩ ዝንባሌ ያላቸው ናቸው፡፡ እስልምና ብቻ ሳይሆን ክርስትናም በኢትዮጵያ የተለየ ባህርይ ይዞ ማደጉን ምሁራን ይናገራሉ፡፡ በኢትዮጵያ ክርስትና የታየው ልዩ ባህርይ፤ በኢትዮጵያ እስልምናም ታይቷል። ሁለቱም እምነቶች ከሌላው ዓለም የመነጠል፣ ራስን ችሎ የመቆም ባህርይ ይታይባቸዋል። የኢትዮጵያ እስልምና ይበልጡን ወደ ውስጥ ተመልካች ሆኖ ተነጥሎ ብቻውን የኖረ ነው - እንደ ክርስትናው ሁሉ፡፡ ለእንዲህ አይነት ሁኔታዎች መፈጠር፤ ከመልክአ ምድራዊ ሁኔታዎች በተጨማሪ ሥነ ልቦናዊና ባህላዊ ምክንያቶች የየራሳቸው ሚና ሳይኖራቸው አይቀርም፡፡
የ‹‹ኢትዮጵያ እስልምና›› የምንለው፤ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ለእምነታቸው መሠረት የሚሆን ከሌሎች መስሊሞች የተለየ ነገር አላቸው ለማለት አይደለም። ሆኖም እስልምና በምድረ አረቢያ ተወልዶ በዓለም ሲስፋፋ፤ በየሐገሩ የገጠመው የተለያየ ታሪክና ባህል መኖሩን ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ እስልምና በዚህ ሐገር በምን ሁኔታ ተስፋፋ? የመስፋፋቱ ሂደት ምን ዓይነት ሂደት ነበረው? በሚል የሚቀርብ ጥያቄን ከማየት የሚነሳ ስያሜ ነው፡፡ ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ ከእስልምና በፊት ከነበረው ባህላዊና ማህበራዊ ሁኔታ ጋር እንዴት ተዛመደ፤ ብለን ስንመረምር የምንደርስበት መደምደሚያ ጭምር ነው፡፡
ከብዙዎች ሐገራት ታሪክ እንደምናየው፤ የእስልምና ኃይማኖት መለያ መልክ ተደርጎ የሚታየው የአረብኛ ቋንቋ ከእምነቱ ጋር አብሮ ይወሰዳል፤ ነገር ግን በኢትዮጵያ (በአጠቃላይ በምሥራቅ አፍሪካ) እንዲህ ያለ ሁኔታ አልተከሰተም፡፡ አረብኛ በኢትዮጵያ የሚነገር ቋንቋ ሆኖ አያውቅም -(አሁን በኤርትራ ከሚገኙ በቁጥር እጅግ ጥቂት ከሆኑ ጎሳዎች በስተቀር)። እንዲሁም በሌሎች ሐገሮች እንደታየው፤ በኢትዮጵያ የአረብኛ ቋንቋ ከእስልምና ጋር ተዳብሎ አልገባም። አረብኛ፤ በኢትዮጵያ የሚነገር ቋንቋ ሆኖ አያውቅም። ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የቁርዐን ጥቅሶችንና ፀሎቶችን በአረብኛ ያውቋቸዋል እንጂ አረብኛ ተናጋሪዎች አይደሉም። ይህ ከሌሎች እስልምናን ከተቀበሉ ህዝቦች ለየት ያደርገናል፡፡
በአጭሩ ኢትዮጵያ፤ እምነቱ በሰላማዊ መንገድ የተስፋፋባት፤ የመጀመሪያዎቹ ሙስሊሞች የኖሩባት እና የተቀበሩባት፤ በእስልምና ታሪክ ውስጥ ልዩ ሥፍራ ያላት፤ እምነቱ በሰላማዊ መንገድ የተስፋፋባት፤ የመጀመሪያዎቹ ሙስሊሞች የኖሩባትና የተቀበሩባት፤ በእስልምና ታሪክ ውስጥ ልዩ ሥፍራ ያላት ሐገር ነች። በሌላ በኩል፤ አንዳንድ የሐይማኖት ሊቃውንት ከኢትዮጵያ የተወሰዱ ቃላት በቅዱስ ቁርዓን ውስጥ እንደሚገኙ ይናገራሉ፡፡
እስልምና ይበልጡን በቆላማና በጠረፍ አካባቢዎች በሚኖሩ አርብቶ አደር ማህበረሰቦች ዘንድ በርካታ ተከታዮችን መሳብ የቻለ ሲሆን፤ ዝግ ባለ ሂደት ወደ መሐል ሐገር የዘለቀ ነው። የስርጭቱ ቅርጽ በመልከአ ምድር፣ በቋንቋ፣ በብሄረሰባዊ ማንነት ያልተወሰነ ነበር። የታወቁ ኢስላማዊ ማዕከላትም በሐረር፣ በምፅዋ፣ በዘይላ፤ በኋላ ደግሞ በጅማ ተፈጥረዋል፡፡
በሰላማዊ መንገድ የመስፋፋት ዕድሉና አስፋፊዎቹ ነጋዴዎች የመሆናቸው ነገር ነባሩን ባህል በመናድ የመሄድ ዝንባሌን አስቀርቷል። በተጨማሪም፤ እስልምናን ከአረብኛ ቋንቋ ጋር እንዲቀበሉ የማስገደድ ፍላጎት ቢኖር እንኳን ነገሩ የኃይል እርምጃን የሚጠይቅ መሆኑ የማይቀር ነው። የማስተዳደር ሥልጣኑን የያዘው ክርስቲያናዊ ንጉስ ባለበት ሁኔታ ይህን ማድረግ የማይታሰብ ነው፡፡ የኃይል እርምጃው ሌላ ግጭትን የሚያስከትል መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ እናም የመስፋፋት ሂደቱ ነባሩን ነቅሎ፤ አዲሱን እንደመትከል ያለ ሂደት አልተከተለም። መስፋፋቱ ይህን የማይፈቅድ ሁኔታ ባለበት የተከናወነ ነው፡፡ ስለሆነም እስልምና በዝግተኛ ሂደት ሲስፋፋ፤ ከነባሩ ባህል ጋር እየተመቻመቸ መሆኑ ግድ ነው፡፡ ከነባሩ ባህል ጋር እየተዋሀደ፣ የራሱን ልዩ መልክ ማበጀቱ የማይቀር ነው፡፡
ከዚህ ሌላ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ከአረብ የዘር ግንዳቸውን የሚስቡ አይደሉም። የአረብ ተወላጅ የሆኑ ነጋዴዎችና መምህራን በኢትዮጵያ ውስጥ ኖረው፣ ከኢትዮጵያውያን ጋር የተጋቡ ቢሆንም፣ ቁጥራቸው በጣም ውስን ነው፡፡ ስለሆነም እስላምም ሆነ ክርስትና የብዙ ብሄሮች ቅንብር ከሆነ፣ ኢትዮጵያዊ የባህል መደብ ላይ ሥር ሰደው የቆሙ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያዊ ርዕዮታዊና ሃይማኖታዊ ማዕቀፍ ላይ የተመሰረቱ ናቸው። በመሆኑም በሁለቱ ሃይማኖቶች መካከል ጠንካራ ቁርኝት አለ። የኢትዮጵያን ክርስትና ወይም እስልምና ለመረዳት አንዱን ካንዱ በመነጠል ከተሄደ፣ እውነቱን በወጉ መረዳት አይቻልም፡፡ እንደውም አንድ ነገር ልንገራችሁ። የኢትዮጵያን መልከአ ምድራዊ፣ ባህላዊና ቋንቋዊ መበጣጠሶችን በአንድነት አያይዞ በህብር ማንነት ያጌጠ ኢትዮጵያዊ ባህል በጥብጦና ለውሶ፣ ለንቁጦና ጠፍጥፎ መልክ እንዲይዝ ያደረገው ኢትዮጵያዊው ሙስሊም ነጋዴ ነው፡፡ አንዱን ካንዱ ነጥሎ መረዳት አይሞከርም ያልኩት ለዚህ ነው፡፡
እርግጥ ነው፤ በተለያየ ጊዜ ኃይል የቀላቀለ መቀናቀንና መፋጠጥ በእስላምና በክርስቲያኑ ኢትዮጵያውያን መካከል መከሰቱ አይታበልም። ይሁንና በተለይ ባለፉት 300 ዓመታት በዕለታዊ ኑሮ በተግባር በተገለጠ የአብሮ መኖርና የትብብር ህይወት (modus vivendi) እየጎለበተ ስር ሰዶ ጸንቶ ቆሟል፡፡ ኢትዮጵያውያን ነገስታት ቸል ያሉትን፤ ከፈለግንም የተሸነፉበትን ወይም ያልተጨነቁበትንና ያልደከሙበትን ወይም ያልቻሉበትን ይህን (modus vivendi) ህብር የፈጠረው የኢትዮጵያዊው ሙስሊም ነጋዴ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የተሰራችው ከሰኞ ገበያ፣ ከማክሰኞ ገበያ፣ ከረቡዕ ገበያ፣ ከሐሙስ ገበያ ወዘተ ገበያዎች ነው። በአፋር፣ በኦሮሞ በትግራይ በአማራ፣ በቤኒሻንጉል፣ በጋምቤላ በሚገኙ ገበያዎች ትስስር የተፈጠረች ሀገር ነች። ይህን ትስስር የፈጠረው ደግሞ ኢትዮጵያዊው ሙስሊም ነጋዴ ነው፡፡ ይህ (modus vivendi) የተተከለውና ስር ሰዶ የበቀለው ከኢትዮጵያዊ ሙስሊም ኢኮኖሚያዊ ክንዋኔዎች ነው፡፡
ሙስሊሙ ነጋዴ ገበያ በሌለባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች ንግድን እያስተዋወቀ ገበያ እየቆረቆረ፤ ለቆሙ ገበያዎች ደግሞ አዳዲስ ምርቶችንና ሸቀጦችን እያስተዋወቀ፣ ህዝቡ በአንድ አይነት ሸቀጥ የሚጠቀምና በንግድ የተሳሰረ እንዲሆን አድርጎ የኢትዮጵያን ህዝቦች ያቆራኘ ነው። ከኢትዮጵያ ድንበር ተሻግሮ ደግሞ ሐገሪቱን ከውጪው ዓለም ጋር ያስተሳሰረ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ እርስ በእርሱ እንዲተዋወቅ፣ በዚህም ሂደት ህብረ ብሄራዊ የጋራ እሴቶች እንዲያቆጠቁጡና እንዲለመልሙ ያደረገ ነው፡፡ እይታው በወንዘኝነት ያልታጠረ ሆኖ ተመሳሳይ ዕይታ እንዲፈጠር ምክንያት የሆነው ኢትዮጵያዊው ሙስሊም ነጋዴ ነው፡፡
እስልምና ኢትዮጵያዊነትን በመፍጠር ረገድ ትልቅ ሚና እንደ ተጫወተ ከዚህ መረዳት ይቻላል። ኢትዮጵያዊ ሙስሊም ደግሞ የኢትዮጵያ ማህበረሰቦችን የጋራ እሴቶች ሸማኔ ሆኖ በህብረ ቀለም አንቆጥቁጦ የሰራው እርሱ ነው፡፡ የሐገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና አምባሳደርም ነበር። ልብ አድርጉ፤ ነገስታቱ በኃይል የግዛት አንድነት መፍጠር ሲያቅታቸው ወይም ድንበራቸው አንዴ ሲሰፋ ሌላ ጊዜ ሲጠብ፤ እንዲሁም በፖለቲካ ረገድ የህዝቡን ግንኙነት ማጽናት ሲሳናቸው፤ በደጉም ሆነ በክፉ ዘመን፤ በመዛልም ሆነ በብርታት ዘመን ኢትዮጵያዊነት ሳይቋረጥ ትስስሩ ጸንቶ እንዲቆም ያደረገው ኢትዮጵያዊው ሙስሊም ነጋዴ ነው፡፡ ከባህል አንጻር፤ ኢትዮጵያዊነት በየቦታው በየዕለቱ ከሚቆሙ ገበያዎች ተሰርቶ የወጣ ሸማ ከሆነ፤ ሸማኔው ኢትዮጵያዊው ሙስሊም ነጋዴ ነው፡፡ በሌላ አገላለፅ ዘመን ሲቀየርና ነገስታት ሲለዋወጡ የማይቀየርና የማይለወጥ የአንድነት መንፈስ የፈጠረ እርሱ ነው፡፡
ይህ እውነታ እንደ ተጠበቀ ሆኖ፤ ዛሬ ኢትዮጵያውያን ከውጭ ዓለም ጋር እንደ ልብ እየተገናኙ ነው፡፡ ይህ ግንኙነት ግሎባላይዜሽን በሚሉት ክስተትና በመገናኛ ዘዴ ቴክኖሎጂ ዕድገትና መስፋፋት የሚታገዝ ነው፡፡ ስለዚህ፤ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ከውጪው ዓለም ጋር በሰፊው መገናኘት በመቻላቸው፤ ከዓለም አቀፍ የእስልምና እንቅስቃሴዎች ጋር የሚተሳሰሩበት ሁኔታ መፈጠሩ የማይቀር ነው፡፡  ይህ እውነት ነው፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያውያን የአብሮ መኖር ባህል እንዳይሸረሸር የሚሰጉ ወገኖች አሉ፡፡ የኮልፌ ወጣቶችና የአንዋር መስጊድ ሙስሊሞች ለዚህ ስጋት ምላሽ የሚሰጥ ሥራ ነው የሰሩት፡፡
እርግጥ የግሎባላይዜሽን ክስተት መፈጠሩና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መስፋፋቱ አዲስ የማህበራዊ ህይወት ዘዬ እንዲጠናከር እያደረገ ነው። ይህ ሁኔታም የአስተሳሰብና የአኗኗር ዘዬ ለውጥ እያስከተለ ነው፡፡ በመሆኑም አዲስ አመለካከትና አስተሳሰብ የሚያቀነቅኑና ነባሩን ነገር ለመገዳደር የሚሞክሩ ማህበራዊ ቡድኖች መነሳታቸውና  ፍልሚያ ውስጥ መግባታቸው የማይቀር ነው፡፡ አንዳንድ ማህበራዊ ቡድኖችና የሲቪል ማህበራት ድንበር ተሻጋሪ ህብረት ለመፍጠር መፈለጋቸው የማይቀር ይሆናል። ይህን ፍላጎታቸውን ለማሳካት የሚያግዝ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ስርዓት መፈጠሩ፤ እንቅስቃሴዎቻቸውም ዓለም አቀፍ ይዘት እያገኘ መምጣቱ፤ ኢትዮጵያውያንም በዚህ የትስስር መረብ ውስጥ መግባታቸውና መሳባቸው ወዘተ እስከ ዛሬ ፈጽሞ ወደ ውጭ የማማተር ዝንባሌ ባለማሳየት የሚታወቁት የኢትዮጵያ የክርስትና እና እስልምና ሐይማኖቶች ምዕመናን ዓለም ዓቀፍ ትስስር ውስጥ የገቡበት ሁኔታ እንዲፈጠር አድርጓል፡፡
ከዚህ በመነሳት፤ የኢትዮጵያ እስልምና ወይም ክርስትና ሌሎችን ያገለለ ማህበራዊ ማንነትን ለሚፈጥር ፖለቲካዊ ወይም ማህበራዊ እንቅስቃሴ ማዳወሪያ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል-አይችልም? የሚል ጥያቄ ቢነሳ የሚገርም አይደለም፡፡ በበርካታ የአፍሪካ ሐገራት የታየው ሁኔታ፤ በኢትዮጵያ ሊፈጠር ይችላል- አይችልም? ብሎ መወያየትም ተገቢ ነው፡፡  በማላዊ፣ በሱዳን እና በናይጄሪያ፤ በእስልምና እና በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚታየው አብሮ የመኖር ባህል፤ በአሁኑ ጊዜ እያቆጠቆጡ ባሉ የአክራሪነት አስተሳሰቦች ሳቢያ አዲስ መልክ ሲይዝ እያየን ነው፡፡
ስለዚህ፤ ‹‹በተጠቀሱት የአፍሪካ ሀገራት እንደታየው ያለ ሁኔታ በኢትዮጵያም ይፈጠር ይሆን?›› የሚል ጥያቄ ለሚያነሱ ምሁራን፤ በአንዋር መስጊድ እና በኮልፌ ወጣቶች ክርስቲያን ማህበር አባላት መካከል የታየው ትብብር፤ ‹‹በቃ ችግር ተወገደ›› ለማለት የሚያበቃ ባይሆንም፤ የሐገራችን ህዝቦች አሁንም በቀላሉ የማይሸነፉ መሆናቸውን የሚጠቁምና የወደፊቱን ሁኔታም ሊያመለክት የሚችል አንድ ክስተት መሆኑን መጠራጠር አይቻልም፡፡ ሁላችንም የኮልፌ ልጆች መሆን አለብን!!


Read 2094 times