Saturday, 15 September 2018 00:00

የአዲስ አመት አዲስ ጥያቄ!

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(2 votes)


    በዚያን ጊዜ አውቄና በቅቼ ለእኔ ስለተደረገልኝ መመስከር ባልችልም፣ አድጌና ኖሬ ያየሁት፣ ያረጋገጥኩት የሴትን ልጅ እናትነት ነው፡፡ ሴትም ትሁን ወንድ፣ አንድ ሕፃን በተወለደ ጊዜ፣ የእኔ ብላ ሰፍ ብላ ልጅን የምትፈልግ እናት ናት፡፡ ምንም አይነት ምግብ መቀበል በማይችልበት በዚህ ሰዓት ጡቷን አጥብታ ሕይወቱን የምታቆየው እሷ ናት። ጤናውን ጠብቃ የምታኖረው  እናት ናት፡፡ እናት ሲከፋውና ሲታመም ፊቷ ከሰል ይመስላል፤ሲስቅ  ሲፈነድቅ ደግም ፊቷ በብርሃን ይሞላል፡፡
በእንስሳት ዘንድ እናት መሆን የአጭር ጊዜ ችግር ነው፡፡ በሰው ዘንድ ግን ለዓመታት ያደክማል። ያንን ድካም ችላ የምትቆም፣ ኮሽ ባለ ቁጥር ልጇ ባለበት ደርሳ፣ ችግሩን ለመጋራት የምትገኝ እናት ናት፡፡ የእናትን ስሱነት፣ ተጨናቂነት፣ ለልጇ ስትል በአደጋዎች ውስጥ  መግባትና ማለፍን፣ የአስራ ስምንት አመት ልጅ ሆኜ አይቼዋለሁ፡፡ ታሟል መባልን የሰሙት እናቴ  ወይዘሮ ይከኑ አሰን፣ በሐምሌ 30 አባይን በዋናተኛ ተሻግረው፣ ከውሎ ጫቀታ ጎጃም ደብረ ማርቆስ የገቡት እናት ስለሆኑ ነው፡፡ በውሃ የመወሰድ፣ በአዞ የመበላት አደጋ እንዳለ ቢያውቁም፣ የእናትነት ባሕሪያቸውን፣ አደጋውና ስጋቱ ሊያሸንፈው አልቻለም፡፡ እናትነት ከባድ ነው፣ ሴትነትም ከባድ ነው፡፡
ሴት ትንሽ ወይም ትልቅ ሆና ስታድግ ደግም እህት ናት፡፡ እህት፤ ከእህቷ ይልቅ ለወንድሟ ታደላለች፡፡ እህቷን እታለም ብላ …. ለወንድሟ ጥላዬ፣ ወንድም ጋሼ ወዘተ-- የሚሉ ብዙ የቁልምጫ ስሞች ታወጣለች። ጥቃት ሲደርስባት የምትጠራው ወንድሟን ነው፤ እህቷ እንደሷ ግፍ የሚፈፀምባት ሌላዋ ተጎጂ ናት፡፡ ሴትነት  እዳ ነው፡፡
ወንድ ልጅ ለአካለ መጠን ሲደርስ፣ አይኑን የሚወረውረው ወደ እህቱ አይደለም፣ ወደ አክስቱ ልጅና አጎቱ ሴት  ልጅ  አይደለም፤ በስጋ ወደ ማይዛመዱት  ነው፡፡ ለእነሱ ሌላ የሚያጠምዳቸው፣ አይኑን የሚጥልባቸው ወንድ አለ፡፡ እሱ የሌሎችን እህቶች በፍቅር ለማጥመድ ሲባክን፣ በእሱ እህቶች ዙሪያ ደግሞ ሌሎች መረባቸውን ይጥላሉ፡፡ መረቡ ቀድሞ የያዘለት፣ የሚያፈቅራትን ሴት አገኘ ማለት ነው፡፡  እሷም መረቡ ውስጥ ከገባች፣ ልቧ የፈቀደውን  አገኘች ማለት ነው፡፡
ይህ ግን አንዳንድ ጊዜ ትክክል አይደለም፡፡ ባህልና ልማድ፤ ሴቶች የሚፈልጉትን ወንድ ባል እንዲያደርጉ አይፈቅድላቸውም፡፡ መፈለጋቸውን እየተሽኮረመሙ እየተቅለሰለሱ ቢያሳዩም፣ ይህን የሚረዳላቸው ወንድ ላያጋጥማቸው ይችላል፡፡ የተረዳውም  የእንጋባ ጥያቄውን ማንሳት  ያለበት እሱ ነው፡፡ ድካማቸው ተሳክቶ ጥያቄውን ወንዱ ሊያነሳ ለጋብቻ ከበቁ፣ አልፎ አልፎ፣ ሴቶችን የሚጠብቃቸው ዘለፋ ‹‹ለምነሽ  አገባሽኝ እንጂ ለምኜ ያገባሁሽ መሰለሽ›› የሚል ነው፡፡ ይህ ያስመርራል፡፡ በፈጣሪ ላይ ‹‹ምነው  ሴት አድርገህ  ፈጠርከኝ›› በማለት ለማጉረምረም ያስገድዳል፡፡
ሴት ሆኖ ተፈጥሮ፣ ሴት ሆኖ መኖር የሚያስቀሩት ትልቅ ሽግግር ነው፤ ሴት ሆኖ መኖር ማፍቀር፣ ማርገዝ፣ ማማጥ፣ ጡት ማጥባት፣ ልጅ ማሳዳግ ---በአጭሩ ተዘርዝሮ የሚያልቅ ኃላፊነት ያስከትላል፡፡ ሴት… ሴት ሆነች ማለት፣ ጣጣዋ በዛ ማለት ነው፡፡
እኔ አፍቅሬ አግብቼ፣ ልጅ የልጅ ልጅ አይቻለሁ። በልጆቼ ባለቤቶች፣ እግዚአብሔር ይመስገን፣ ክፉ አልገጠመኝም፡፡ አንዳንድ ወላጆች ግን ሴት በመውለዳቸው እጃቸውን ተቆርጠዋል፤ ተስፋቸው  ጨልሞባቸዋል፡፡
የእኔን ጨምሮ የብዙ ወንዶች ልብ፣ ዛሬም ከአያቶቻቸውና ከአባቶቻቸው የተለየ አይደለም። የሴቶች እኩልነት ሲነሳ ፊታቸውን የሚያዞሩ ብዙ ናቸው፡፡ በጉልበትና በእውቀት የሚሰሩ ሥራዎችን እየዘረዘርን፣ሴቶች በዚህ በዚህ እኩል ናቸው እያልን፣ ልናስረዳ እንችላለን፡፡ ሴቶች ያንን እኩልነት የሚሞሉት ከእነሱ ሌላ ማንም የማይሞላውን ጐዶሎ ቦታ ሞልተው ነው፡፡ ስለ ሴቶች እኩልነት የምንናገረው፣ ትልቁን ክፍል እንዳይታይብን ደብቀን ወይም እያወቅን ሸፍጠን ነው ባይ ነኝ፡፡
የዚህ ጽሑፍ መነሻ ዋና ምክንያቶች  ባለፉት  ጥቂት ወራት በመገናኛ  ብዙኃን የተላለፉ ሶስት ታሪኮች ናቸው፡፡ የመጀመሪያው የወይዘሮ ሐሊማ አብዱል አዚዝ ጉዳይ ነው፡፡ ሐሊማ እንደ ማንም እናት፣ የታመመ ልጃቸውን ሐኪም ቤት ይዘው ይሄዳሉ፡፡ ሐኪሞች የሰመመን መርፌ እንዲሰጠው አድርገው፣ የሕክምና ሥራቸውን ይሠራሉ።  የቀዶ ጥገና ሥራው ከአለቀ በኋላ ግን ልጅ ከተሰጠው ማደንዘዣ መንቃት ሳይችል ይቀራል። ወ/ሮ ሐሊማ እናት በመሆናቸው፣ በሕይወትና በሞት መካከል ከሚገኝ ልጃቸው አልጋ ሥር ተቀምጠው፣ ከአሁን አሁን ይነቃ ይሆን ብለው እየጠበቁ፣ 13 ዓመታትን አሳልፈዋል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ድጋፍ፣ ከሳኡዲ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው፣ ከወገኖቻቸው መሐል ቢሆኑም፣ የእናትነት ልፋታቸው ግን እንዳለ ቀጥሏል፡፡
ሁለተኛዋ፣ የሶስት ልጆች እናት የሆነችው፣ ወይዘሮ ብዙነሽ ታቦር ናት፡፡ አንቱ የማልለው በኑሮዋ የተመቻት መስላ እንዳትታይ እንጂ ከእሷ በላይ መከበር ያለበት ኖሮኝ አይደለም። የወይዘሮ ብዙነሽ ልጅ ናርዶስ አለማየሁ አስር ዓመት ሞልቶታል፡፡ መቆም፣ መራመድ፣ መናገር፣ መስማት አይችልም፡፡ በተቀመጠበት ቦታ እንኳ ረግቶ መቀመጥ አይችልም፤ ያለ ማቋረጥ ይወራጫል፡፡ የእናት አንጀቷ አልችልላት ብሎ የካ ሚካኤል በላይ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቷ፣ ኮከበ ጽባሕ ልዩ ፍላጐት ትምህርት ቤት ድረስ ለሁለት ዓመት ይዛው ውላ፣ ይዛው ትመለሳለች። ስትሄድም አዝላ፣ስትመለስም አዝላ ነው፡፡ የአስር ዓመት ልጅ አዝሎ፣ የየካን ዳገት መውጣትና መውረድ ምን ያህል እንደሚከብድ መገመት አያዳግትም፡፡ አሁን እየጨነቃት ያለው መጪውን 2011 እንዴት እንደምታሳልፈው ነው- የእናትነት ፈተና፡፡
እንኳን የሴትየዋን ስም፣ ዜናውን ያስተላለፈውን የቴሌቭዥን ጣቢያ ማስታወስ አቅቶኛል፡፡ የሶስተኛዋ ሴት ታሪክ ግን ከአእምሮ የሚጠፋ አይደለም፡፡ ሴትየዋ በሐኪም እርዳታ ለመውለድ ይሄዳሉ፡፡ ማደንዘዣ ይሰጣቸዋል፡፡ የማዋለዱ ሥራ ከተጠናቀቀ በኋላ ግን ሴትየዋ ሳይነቁ ቀሩ። ሶስቱም ሴቶች ለዚህ ችግር የተጋለጡት በሌላ ሳይሆን ሴት ሆነው በመፈጠራቸው ነው፡፡
አረገዝኩ ሲባሉ የራስሽ ጉዳይ ብለው አድራሻቸውን የሚያጠፉ ወፈ ሰማያት ወንዶች አሉ፡፡ በፍቺና በሞት ትዳር ሲፈርስ፣ ልጅ የማሳደግ ቀንበር የሚወድቀው በሴቶች ላይ ነው፡፡ በአጋጣሚ በጠየቅኋቸው ሰማኒያ አባላት ካሏቸው ሶስት የሴት ዕድሮች ውስጥ ሃያ ስምንት ሴቶች በሞትና በፍቺ ሳቢያ ልጆቻቸውን ለብቻቸው እያሳደጉ መሆናቸው ተነግሮኛል፡፡ ሃያ ዘጠነኛው ወንድ ነው፡፡
ሁለቱ ጾታዊ ግንኙነት በሚያደርጉበት ጊዜ በሴቷ ላይ በህይወት ኑሮን ታግሎ ማለፍ ከሚጠይቀው ችግር በተጨማሪ የአካል ጉዳት (ለምሳሌ ፌስቱላ) አልፎም ሕይወትን እስከ ማሳጣት ሊያደርስ እንደሚችል ምን ያህሉ ይገነዘባሉ? ብሎ መጠየቅ ይገባል፡፡
በእኔ እምነት፣ የሴቶች ችግር፣ እንደ ማርክስ፣ ሴቶች ድርብ የመደብ ጭቆና አለባቸው በማለት፣ እንደ ምዕራባዊያን በጾታ እኩልነት ሊሸፈንና ሊድበሰበስ የሚገባው አይደለም፡፡ ተፈጥሮ፤ ሴት ሆነው እንዲፈጠሩ በማድረጉ ያስከተለባቸው ሸክም ጐልቶ ሊወጣ ይገባል፡፡ የተፈጥሮ ሕግን ማፍረስ ባይቻልም፣ ሰው ሊሰራው በሚችለው መንገድ ሁሉ ወረታ ሊከፈላቸው የግድ ያስፈልጋል፡፡
መንግስት ይህን ሁሉ ችግር ተረድቶም ይሁን በሌላ፣ ሴቶችን ለማገዝ መፈለጉን የሚያሳዩ አንዳንድ ምልክቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ፤ ከጋራ የመኖሪያ ቤቶች 30 በመቶ የሚሆኑት ተለይተው፣ ሴቶች እርስ በርስ በእጣ ተወዳድረው እንዲያገኙ እያደረገ ነው፡፡ የጅምር ጅምር ቢሆንም፤ በአንዳንድ መ/ቤቶች ውስጥ የሕፃናት ማቆያ ቤቶች እየተሰሩ፣ እናቶች ከሥራ ላይ እየተነሱ፣ ብቅ ብለው ልጆቻቸውን አይተው ወደ ሥራ እየተመለሱ ነው። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ሴቶች፣ ከወንዶች ትንሽ በቀነሰ ነጥብ፣ ዩኒቨርሲቲ ገብተው፣ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ እየተደረገ ነው፡፡ ይህ ግን ከችግሩ ስፋት አንጻር ኢምንት ነው፡፡  
የሴት አገሯ የባሏ አገር ነው ተብሎ ስለሚታመን፣ ሴት የመሬት ውርስ እንዳታገኝ ይደረግበት በነበረው አካባቢ ባህሉን ሰብሮ፣ ሴቶች መሬት እንዲያገኙ ያደረገው መንግሥት ነው፡፡ መንግሥት በነካ እጁ፣ ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተጨማሪ እርምጃዎችን መውሰድ አለበት፡፡ ለእኩል ሥራ እኩል ክፍያን ማስከበር አልቻለም፤አሁንም እየተውተረተረ ነው። ሴት መሆን በሴቶች ላይ የሚያስከትለውን ሸክም ማቅለል የሚያስችል፣ በሚያገኙት ክፍያ ላይ 10 በመቶ ጭማሪ እንዲያገኙ፣ ሴቶችና ወንዶች የሃብት ክፍፍል ሲያደርጉ የሃብት ድልድል 60 ከመቶው የሴቷ እንዲሆን--መንግሥት በአዋጅ ቢደነግግ፣ የሚሰበሩ ልቦች በመጠኑ እንደሚጠገኑ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ሴቶች እራሳቸው፣ መንግሥትም በበኩሉ፣ ተፈጥሮ በሴቶች ላይ የጫነውን ቀንበር፣ ሕብረተሰቡ እንዲያውቀው እንዲገነዘበው አጥብቀው መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡  
የአዲሱ ዓመት አዲስ ጥያቄዬ፤ ተፈጥሮ፣ በዚያ ላይ ባሕልና ሃይማኖት ተባብረው እየደቆሷቸው ላሉ ሴቶች፣መንግስት በሚችለው ሕግ ሊያግዝ፣ ሊደግፍ ይገባል፡፡  
መልካም አዲስ ዓመት ለሴቶች ሁሉ!
ለወንዶች ልብ የመግዣ አዲስ ዓመት እመኛለሁ!

Read 1126 times