Saturday, 15 September 2018 00:00

“ብአዴን” ስያሜውን ለመቀየር አራት አማራጮችን አቅርቧል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

  ላለፉት 27 ዓመታት የአማራ ክልልን ሲያስተዳድር የቆየው የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን)፤ ስያሜውንና አርማውን እንደሚቀይር አስታወቀ፡፡
የአማራ ህዝብ ትግል የደረሰበትን ደረጃ መሠረት በማድረግ፣ አርማና ስያሜውን ለመቀየር መወሰኑን የገለፀው ብአዴን፤ አዲሱን መጠሪያውንና አርማውን ከሳምንት በኋላ በሚያካሂደው ጠቅላላ ጉባኤው ይፋ ያደርጋል ተብሏል፡፡
የድርጅቱን ቀጣይ ስያሜና አርማ በተመለከተም አማራጮችን አቅርቦ እስከ ወረዳ ባለው መዋቅሩ እያወያየበት መሆኑን ድርጅቱ አስታውቋል፡፡ ለድርጅቱ መጠሪያነት አራት አማራጮችን ለውይይት ማቅረቡም ታውቋል፡፡
ለውይይት የቀረቡት አማራጮችም፤ “የአማራ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ” (አህዴፓ)፣ “የአማራ ክልል ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ አንድነት ፓርቲ” (አህዴፓ)፣ “የአማራ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት” (አህዴድ)ና “የአማራ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ” (አህዴን) የሚሉ ናቸው፡፡
የአርማ አማራጮችም ተዘጋጅተው ለንቅናቄው አባላት ውይይት ይቀርባሉ ተብሏል፡፡
በተመሳሳይ፤ የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ስያሜውን፣ አርማውንና ድርጅታዊ መዝሙሩን ለመቀየር እንዳቀደና ይህም ከመስከረም 8 እስከ 10 በጅማ ከተማ በሚካሄደው የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ውሣኔ እንደሚያገኝ ተገልጿል፡፡


Read 3513 times