Print this page
Monday, 10 September 2018 00:00

“የማስጠንቀቂያ ደወል“ን ደግሞ ማንበብ አዳጋች ነው!

Written by  ከሰገሌ
Rate this item
(0 votes)

 በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ነሐሴ 26 ቀን 2010 ዓ.ም “መተቸት ደግ ነው፤ ግን መጽሐፉን አንብበው ይጨርሱ” በሚል በእሳቱ ሰ. ለአቶ ደረጀ በላይነህ የተሰጠውን ሒስ ምላሽ አንብበናል፡፡ እሳቱ ሰ የማስጠንቀቂያ ደወል ደራሲ በጊንጥ  ተገርፈውብኛል፣  ተነቅፈውብኛል፣ የሚገባቸውን ክብር አላገኙም፣ መሳቂያ መሳለቂያ ተደርገውብኛል እና የመሳሰለውን አቤቱታ፣ በስሜት ተነድቼ ጽፌዋለሁ ስላሉን፣ በዚያ ደረጃ ዝቅ ብለን የመልስ መልስ አንሰጣቸውም፡፡ ይህን በተመለከተ ቢፈልጉ ባለ ጉዳዩ አቶ ደረጀ እራሳቸው መልስ ይስጡበት፡፡
ባይሆን የነገራችን ዋና ስለሆነውና ፀሐፊው “የማስጠንቀቂያ ደወል” የተባለውን መጽሐፍ ተቺው አቶ ደረጀ በላይነህ “በተገቢው መንገድ አልተረዱትም፤ጨርሰውም አላነበቡትም” በሚል መላምት በድጋሚ እንዲነበብ ባነሱት ጭብጥ ላይ እናተኩር፡፡
እሳቱ ሰ. ለደራሲው ባላቸው ቅርበት አልያም ባልታወቀ የሆነ ምክንያት ትችቱን ባጠቃላይ የወደዱት አይመስልም። ስለዚህ ነው አቶ ደረጀ በላይነህ መጽሐፉን ጨርሰው አላነበቡትም፤ ዓላማውም አልተገለጠላቸውምና ደግመው ቢያነቡት እመክራለሁ የሚለውን ሃሳባቸውን ቢያንስ ስምንት ያህል ጊዜ በጽሁፋቸው ውስጥ ያስገቡት፡፡ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ እንደ አቶ ደረጀ ሳንሳሳ የመጽሐፉን ጭብጥ፣ አወቃቀሩንና ሥነ-ጽሁፋዊ ውበቱን በተመለከተ ዝርዝር ዳሰሳ ማቅረብ እንችላለን፡፡ ነገር ግን የደግማችሁ አንብቡልኝ ጥሪው፣ በራሱ አንድ በቂ ርዕስ ሆኖ ስለተገኘ በዚሁ ዙሪያ ማጠንጠንን መርጠናል፡፡
አቶ ደረጀ በላይነህ “የማስጠንቀቂያ ደወል”ን ደግመው ሊያነቡት የሚችሉት ቢያንስ በሚከተሉት አምስት ያህል ነጥቦች ነው፡፡
1ኛ/     የተጀመረው ለውጥ የታሰበውን ያህል በተፈለገው ፍጥነት ባይራመድ፣
2ኛ/    ለውጡ ከዳር ደርሶ አገራችን ተጠቃሚ መሆን ስትጀምርና የሃሰት ነቢያት ትንቢት መክሸፍን ለማብሰር፣
3ኛ/    ያመለጣቸው ፍሬ ነገር ወይንም ብርቱ የተባሉ ጉዳዮች በመጽሐፍ ውስጥ ይገኙ እንደሁ ብለው ቢጠረጥሩ፣
4ኛ/    ለተዛማጅ ጽሁፍ ወይንም ጥናት ማጣቀሻ ቢፈልጉ እና
5ኛ/    እሳቱ ሰ እንደሚሉት፤ የደራሲው ዓላማ ያልተገለጠላቸው ሆኖ ቢሆን ኖሮ ይመስለኛል፡፡
አንደኛውን ምክንያት በተመለከተ አያያዙን አይተን መፍረድ እንችላለንና ለውጡ ቢንገራገጭም አይቀለበስም! አራት ነጥብ። የለውጡን ሒደት ለማዘግየት የሚሹ ጥቂት ሃይሎች ቢነሱም በተደጋጋሚ የታየው ህዝባዊው ማዕበል ጠራርጐ ይወስዳቸዋልና ስጋት አይግባዎ።
ለውጥን የሚገዳደሩ ሰዎች/ሃይሎች መጪው ጊዜ ብሩህ ሆኖ ስለማይታያቸው ደግመውም ቢነግሯቸው አይሰሙም፡፡ ለምሳሌ ደራሲው አቶ ሚካኤል ሽፈራው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢያንስ ሶስት ጊዜ ያህል ምላሽ የሰጡበትን ጥያቄ “የኢትዮ-ኤርትራ ጉዳይ“ በሚል ርዕስ ሥር /ገጽ 16/፣ ጥያቄውን ደግመው የሞኝ ለቅሶ አስመልሰውታል፡፡ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ጠ/ሚሩ በአንደበታቸው “ይህ የመንደር ፖለቲካ ነው፡፡ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት በፌደራል ደረጃ የሚፈጸም ስለሆነ ሌላ አተካሮ አያሻም” ቢሉም ደራሲው ከወደቀበት አንስተው፣ ጠጋግነውና አሰማምረው ብቅ አድርገውታል፡፡ እንደው በሞቴ ከገባንበት አዘቅት ውስጥ መውጣትን በጉጉት የሚጠብቅን ህዝብ፣ ስለ ዕርቅ አንስተን ማድከሙ የሞኝ ሥራ አይመስልዎትም? ደራሲው ይህን አገር ያወቀውን ፀሃይ የሞቀውን ጉዳይ ደግመው ለማንሳት መውተርተራቸው በራሱ፣ በለውጡ ፍጥነት ደንግጠው ከገቡበት ድባቴ እንዳልወጡ በቂ ማስረጃ ነው፡፡ ከዚህ ገብተውበታል ብለን ከምንለው የህልም ዓለም ለማንቃት፣ እሳቱ ሰ የአካባቢውን  “ጂኦ ፖለቲካል“ የጊዜ ሁኔታ እየተነተኑ፣ በሩቅ ያሉ የአገር መሪዎችና ሃያላን መንግስታት የሰጡትን ድጋፍ እያስታወሱና አገሪቱ በአለም አቀፍ ድርጅቶች እያገኘች ያለችውን ድጋፍ እያመላከቱ ቢመክሩዋቸው መልካም ነው፡፡ ይህን የማይረዱ ከሆነ ደግሞ የለውጡ ሞተርና ጠባቂ የሆኑትን የአገሪቱን ወጣቶች ሁኔታ በማሳየት ዝም አይነቅዝም ይበሏቸው። በጣም አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ በቅርቡ በኢቢሲ ቴሌቪዥን “የልቦና ውቅር” መሰናዶ ላይ ተገኝተው እያዝናኑ፣ ሃሳባቸውን ያካፈሉትን የዶ/ር ዳኛቸውን ቃለ ምልልስ ይጋብዟቸው፡፡ ባቡሩ ፈጣን ነው!
በሁለተኛ ምክንያትነት የተጠቀሰውን የሃሰት ነብይነትን ለመገምገም ደግሞ ጥቂት ጊዜ ያስፈልጋል፡፡
ከሶስተኛ እስከ አምስተኛ የተሰጡትን ምክንያቶችም አቶ ደረጀ በዝርዝር ከነገሩን፣ እኛም እያንገሸገሸን አንዴ ካነበብነው መጽሐፍ ፣ አቶ እሳቱ ሰም  ከተከላከሉበት ጭብጥ የማይወጣ ስለሆነ “የማስጠንቀቂያ ደወል”ን ደግሞ ማንበብ ጊዜ ማባከን ነው፡፡
ደግሞ ማንበብ ከተፈለገም የደራሲውን የአቶ ሚካኤል ሽፈራውን ቀደምት ሥራዎች ማንበብ ይመረጣል፡፡ ለምሳሌ የወፍ ማስፈራሪያን አንድም ሲወርድ ሲዋረድ የመጣን እና ለለውጥ እንቅፋት የሆነን ባህል ጠያቂ ትውልድ ለማነቃቃት፣ ሁለትም በወፍ አገር በወፍ ቋንቋ የተነገረውን ተረት በሰው ቋንቋ ለህፃናት ለመንገርና ለማስተማር /ደራሲው እንዳሉት/ ደግመን ብናነበው ችግር የለውም። ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው፤ ከደራሲው ሌሎች ሥራዎች ጋር ሲነፃፀር “የማስጠንቀቂያ ደወል” የሥነ-ፅሁፍ ውበትን ባፍጢሙ የደፋ፣ ህግጋትን የማይከተልና ያገኘውን ይምታልኝ ተብሎ ያለ ኢላማ የተረጨ እንቶፈንቶ ነው፡፡
“የማስጠንቀቂያ ደወል”ን ደግሞ ማንበብ ሳይሆን ጀምሮ ለመጨረስ የሚያዳግተንና እጅ እጅ የሚለን ለምን እንደሆነ ለደራሲው ለአቶ ሚካኤል፣ ለተቺው ለአቶ ደረጀ እና ለተከላካዩ ጠበቃ ለእሳቱ ሰ ከላይ የተጠቀሰውን በማስረጃ ማስደገፍ ያስፈልጋል። በመጀመሪያ መጽሐፉ በቂ ዝግጅት ያልተደረገበት የለብ-ለብ ሥራ መሆኑን ደራሲው  እራሳቸው በ ገጽ 7 ላይ “ጽሁፉን ለማዘጋጀት እጅግ ሰፊ ጥናት፤ ንባብና ውይይቶችን በማድረግ ብዙ መማር ነበረብኝ። ያገራችንን ፖለቲካዊ ታሪክ አስመልክቶ የሶቭየት ህብረትን ታሪክና ከኛ ጋር ያለውን መስተጋብር ለመረዳት ለረጅም ጊዜያት ያነበብኳቸው ንባቦች በእጅጉ ረድተውኛል፡፡ ይሁንና ዋቢ መጽሐፍትን ባግባቡና በተጠቀሱበት ሥፍራ በጥናታዊ ጽሑፍ ዲሲኘሊን ለማጣቀስ ጊዜ ብወስድ መጽሐፉ ጊዜ የሚያልፍበት ሆኖ ስለተሰማኝ ዋና ዋናዎቹን ዋቢ ጽሑፎች ብቻ በመጽሐፉ መጨረሻ ለማካተት ተገድጃለሁ፡፡” ካሉ በኋላ መጽሐፉ ደግሞ ለመታተም እድል ካገኘ በቀጣይ እትሞች ከዚህ በተሻለ የተደራጀ እንዲሆን ከወዲሁ ሥራውን እጀምራለሁ ብለዋል። ደራሲው በቀደምት ሥራዎቻቸው እንዳደረጉት ጊዜ ወስደው ባልሰሩበት ሁኔታ ተቻኩዬ ለገበያ አቅርቤዋለሁ ብለው ማመናቸውን እያወቁ /መጽሐፉን ካነበቡት/ እሳቱ ሰ. በሌሎች ደራሲያን ሥራዎች /አቶ ደረጀን ጨምሮ/ ትኩስ ፓስቲ ብለው ለመሳለቅ መሞከራቸው ከድጡ ወደ ማጡ ይወስዳቸዋል፡፡
መጽሐፉ ለህትመት ከመግባቱ በፊት የችኮላ ሥራ ስለመሠራቱ ተጨማሪ ማስረጃ የሚሆነን አቶ ደረጀ በክፍል ሁለት ጽሁፋቸው የጠቆሙትን  የቃላት ግድፈቶችን ብቻ እንኳ ለማንሳት እንሞክር። ሌላው ቢቀር በሽፋኑ ገጽ ላይ ገበያ ሳቢ ተደርገው የተቀመጡት የጠ/ሚኒስትሩ ስም የተጻፈበት መንገድና ከማውጫው ጀምሮ እስከ መጨረሻው ገጽ ድረስ የተጠቀሙበትን ተለዋጭ ፊደላት ማየት በቂ ነው፡፡ የፊደላት ግድፈቱን ዘርዝረን ስለማንጨርሰው፣ ተቺው አቶ ደረጀ የጠቀሱትንና ምስጋና በሚል ርዕስ ሥር አንድ ገጽ ውስጥ  129 ያህል ቃላትን ተጠቅመው፣ አምስት ረጃጅም ዓረፍተ ነገሮችን ሲመሠርቱ፣ አራት ያህል ግድፈቶችን ማየታችንን እሳቱ ሰ መለስ ብለው እንዲያገናዝቡ ጋብዘንዎታል፡፡ በቃ!
እሳቱ ሰ ከበረቱ ደግሞ ደራሲው በገጽ 265 ላይ ማጠቃለያ ከሚለው ርዕሳቸው ሥር የሰጡትን የግል አስተያየት ልንጠቅስ እንችላለን። በረጅሙ ሥራቸው ውስጥ ስሜት ወለድ አሳብና ምክራቸውን እንደፈለጉ ከሰገሰጉ በኋላ በፍራቻ ስሜት ይመስላል “በመጨረሻ ይህ ጽሑፍ በጥናታዊ መረጃዎች ላይ ተመርኩዞ፣ በጥቅሶችና በግርጌ ማስታወሻዎች ተደራጅቶ የቀረበ አካዳሚያዊ ጥናት ሳይሆን የግል እይታዬን በማካፈል ለውይይት የቀረበ፣ ሊጠቅም ወይም ሊወድቅ የሚችል የግል ሃሳብ መሆኑን በድጋሚ ማስገንዘብ እወዳለሁ።” ይሉናል፡፡ ይህን ሃሳባቸውን ይዘን ወለል አድርገው በከፈቱልን በር ጊዜ ሲገኝና አስፈላጊነቱ ሲታመንበት ልንመለስ እንችላለን፡፡
ሌላውና መጽሐፉን ደግመን ለማንበብ የማያስችለን ብርቱ ጉዳይ ለግማሽ ምዕተ-ዓመታት ያገሪቱ ልሒቃን የሔዱበትን፣ ተፈትነውም የወደቁበትን መንገድ ደራሲው ለመከተል መታገላቸው ነው፡፡ አቶ ሚካኤል የዚያ ትውልድ ግርፍ እስኪመስሉን ድረስ ለማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮቻችን ሁሉ የሌላን ባዕድ አገር ተሞክሮ ቀድተው በሞቴ ብሉልኝ ጠጡልኝ ያሉበት መንገድ ሲታይ የቀደምት መሪዎችና ተፅዕኖ ፈጣሪ ባለሟሎችን መንገድና ፈለግ ለመመርመር የሚሹ አልመሠለንም፡፡ የቀድሞ የሶቭየት ህብረት፣ የቻይና፣ የቬትናም፣ የፈረንሳይ አብዮት፣ ጣሊያን፣ አልባንያና ሌሎች አገሮችን ድሪቶ እንዳለ መውሰድ፣ መጣፍና መልበስ ማክተም አለበት፣ ያሠለቻል! ይመራል!  የአገር በቀል ዕውቀቶች፣ ልማዶች፣ ሃይማኖትና አስተዳደራዊ ሥርአቶች በቂ ውክልና ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ አቶ ሚካኤል ከዚህ አዙሪት ያልወጡ፣ ነገር የሚደጋግሙና በሌሎች ላይ ለመጫን የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንደሌለ ማየት ቢያስፈልግ፣ ከ 272 ገጽ መጽሐፋቸው ውስጥ ቢያንስ 37% ያህሉን ለዚሁ ከላይ ለተጠቀሰው አላማ አውለውታል፡፡ መጽሐፉን ደግሞ ማንበብ ይሠለቻል የምንለው ለዚህም ነው፡፡
አቶ ደረጀ በላይነህ በርዕስነት የተጠቀሙበት የክህደት ጉዳይ ደግሞ ሌላ መነጋገሪያ ነጥብ ነው፡፡
ተቺው ይህን ጉዳይ ርዕስ በማድረጋቸው እሳቱ ሰ ተቃጥለዋል! ተንገብግበዋል፡፡ አቶ ሚካኤል “የዶክተር ዐቢይ ህዝባዊ መሠረት” ብለው ርዕስ ሠጥተው /ገጽ 24/ ምን ዓይነት “የስታትስቲክስ” ቀመር እንደተጠቀሙ ሳይገልጹ፣ በሃሳብ ተነድተው፣ ከልቦናቸው አፍልቀው፣ ከአዕምሮዋቸው አንቅተው በሚከተሉት ሶስት ያህል ክፍሎች መድበዋቸዋል፡-
1ኛ/     ራሱን ከዚህ ወይም ከዚያ ብሔር ለመመደብ የሚቸገር ባብዛኛው በከተሞች የሚኖር …. /ገጽ 24/
2ኛ/     በተለይም በአማራ ክልል የሚኖሩ ባለፉት 27 ዓመታት በአማራነታቸው ብቻ የተጠሉና የተወገዙ /ገጽ 24/
3ኛ/    በውጭ አገር የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን /ዲያስፖራ/ /ገጽ 26/
ይህን ጉዳይ የትችቱ ርዕስ ከማድረግ ባሻገር የደቡብ /ከምባታ፣ ሃዲያ፣ አርባ ምንጭ፣ ሃዋሳ፣ ሶዶ ወዘተ/፣ ከምዕራብ የአገሪቱ ክፍሎች ለጠ/ሚኒስትሩ ድጋፍ የወጣውን ህዝብ ምነው ጆሮ ዳባ ልበስ አሉት ተብለው መጠየቅና  የለውጥ ሞተር የተባሉት ወጣቶችን ጉዳይም በተለያዩ የመጽሐፉ ገጾች አንስተው በዚህ ዋነኛ ሊባል በሚችል ርዕስ ሥር፣ ለምን  ቦታ እንደነፈጓቸውም ደራሲው ማብራሪያ እንዲሠጡ አቶ እሳቱ ሰ ቢሞክሩ መልካም ነበር፡፡ መቼም አላየሁም አልሠማሁም፣ አይኔን ግንባር ያድርገው ሊሉን አይችሉም፡፡
የጠ/ሚኒስትሩን ህዝባዊ መሠረት ለመካድ አይናቸውን በጨው አጥበው፣ ብቅ ብቅ የሚሉ፣ ሲመቻቸውም እንቅፋት በማኖር ሂደቱን ያንገራገጩ የሚመስላቸው አንዳንድ ወገኖች፣በማህበራዊ ድረገጽ የሚያናፋሱትን አሉባልታ ሲጨርሱ ጊዜው የፈቀደውን ነፃነት ተጠቅመው፣ በህትመት ሥራ መምጣታቸው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡
የክህደቱ ነገር ከተነሳ ገና ለገና ወዳጄ ለምን ተነካብኝ በማለት ያገረገሩት እሳቱ ሰ፤ ደራሲው ጊዜው ሳያመልጠኝ አግለብልቤ ያደረስኩት “ትኩስ ጥብስ” ነው ያሉትን የማስጠንቀቂያ ደወላቸውን ከጥቃት ለመከላከል በማሰብ ብቻ ሳይወሰኑ፣ ሁኔታዎች ሲመቻቹሉኝ፣ እነ አቶ ደረጀ በላይነህ ያሳተሟቸውን መጽሐፎች በተመለከተ የማደርገውን እኔ አውቃለሁ ብለው የቂም ዘገር ነቅንቀዋል፡፡ ለምን ተነካን! ጊዜ ያለፈበት ፉከራ ነው፡፡ ሁላችንም የግልም የቡድንም ሐሳብ ቢኖረንም፣ ለጊዜውም ቢሆን የኛን ትተን፣ አገራችን ከገባችበት ማጥ እንድትወጣ የተቻለንን እናበርክት በተባለ ጊዜ ሌላ ጽንፍና የነጋሪት ጉሸማ ከቶም “ተማርን” ከምንል ሰዎች አይጠበቅም፤ ቀን ሲያልፍም የሚያስተዛዝብ ይሆናል፡፡
በአጠቃላይ አቶ ሚካኤልን ደግማችሁ አንብቡልኝ ያሉትንም እሳቱ ሰን በማስጠንቀቂያ ደወል ውስጥ ስንመለከታቸው፣ “ቅኔው ሲያልቅበት ቀረርቶ የሞላበትን“ የየጁን ቄስ ይመስሉናል። የየጁው ቄስ በደህናው ዘመን እየተማረ፣ እያነበበ፣ እየደገመና እራሱን እያሻሻለ አገልግሎት ሲያበረክት የኖረ፣ በአንድ ወቅት ግን በተገቢው መጠን ባለመዘጋጀቱ ወይም በልቡ የቋጠራትን እየቆነጠረ አውጥቶ በመጨረሱ አልያም በሌላ ያልታወቀ ምክንያት ከአፈርኩ አይመልሰኝ ብሎ ቀረርቶውን በተወዳጁ የቅኔ ሥራው ላይ በመደረቱ መሳለቂያ ሆኗል፡፡ በቃ ! መታደስ ነበረበት… አልፈለገም! ዝም ማለት ያዋጣው ነበር… በል-በል ብሎታልና አላደረገውም፡፡
እሳቱ ሰ. የደራሲው አላማ አልገባችሁምና መጽሐፉን ደግማችሁ አንብቡት ለማለትም ብዙ ርቀት ሄደዋል፡፡ እኛ ገንዘብ አውጥተን መጽሐፉን ለገዛን ሰዎች፣ ዓላማው እንዲህና እንዲያ ነው ፈጽሞ አልገባችሁምና ደግማችሁ አንብቡት እየተባለ በየጋዜጣው ማስታወቂያ የሚሠራልን ከመቼ ወዲህ ነው? ደራሲው ከመግቢያቸው ጀምሮ በየምዕራፉ /ምዕራፍ እንኳ የለውም/ ወይም በየርዕሱ መጨረሻ ዓላማቸውን በግልጽ ባስቀመጡበት ሁኔታ የደግማችሁ አንብቡት የድለላ ሥራው ማደናገሪያ ነው፡፡ ለለውጡ መሪዎችና ተከታዮች የተፈለገው መልዕክት በግልጽ ተላልፏል፡፡ ምክራቸውም ያላዋቂ ሳሚ ነገር ሆኖ እንጂ ግልጽ ነው፡፡ መሪዎቹ ጊዜ አግኝተው ካነበቡላቸው፣ በራስዎ ልክ ያሰፉትን ጥብቆ አይመጥነንምና ለሰፊዎቹ በክብር ይመልሱላቸው በማለት አንጀታችንን ቅቤ የሚያጠጡት ይመስለናል፡፡ አዲዮስ!

Read 1027 times