Monday, 10 September 2018 00:00

ከዘንድሮ “የበጎ ሰው ተሸላሚዎች” አንደበት--

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

  “ምንም ተስፋ በሌለበት እንኳን ተስፋ ማድረግ ያስፈልጋል”
             መምህር ስመኘው መብራቱ

    መምህር ስመኘው መብራቱ ካሣ፣ የ6ኛው ዙር “የበጐ ሰው ሽልማት” የመምህራን ዘርፍ አሸናፊ ሲሆኑ ደቡብ ጐንደር ታች ጋይንት ወረዳ፣ ታጠቅ ለስራ ት/ቤት ርዕሰ መምህር ናቸው፡፡ እኚህ ታላቅ መምህር፤ ከማስተማር ሥራቸው ጎን ለጎን፣ በርካታ በጎ ተግባራትን  በወረዳው በማከናወን ይታወቃሉ፡፡
“ጮራ ቤተ መፅሐፍት የስነ ጥበብና የበጐ አድራጐት ክበብ”ን በግላቸው በማቋቋም፣ በአንድ ጊዜ 120 ሰዎች እንዲጠቀሙ  የሚያስችል አቅም ፈጥረውለታል፡፡ በክረምት ከዩኒቨርሲቲ የሚመለሱ ተማሪዎችን በማስተባበርም፣ የኪነ-ጥበብ ስራዎችን እንዲሰሩ ከማበረታታቸውም በላይ  ታናናሾችን እንዲያስተምሩም ያደርጋሉ፡፡ ት/ቤቱን ይመራሉ፣ ማኅበረሰቡን ያነቃሉ፡፡
በጥሩ ውጤት ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ተማሪዎችም እንዲሸለሙ  ያደርጋሉ፡፡ መምህሩ፤ የአካባቢውን ማኅበረሰብ አስተባብረው፣ ባህር ዛፍና ጥድ እንዲያመጣ በማድረግ፣ 6 የመማሪያ ክፍሎችን ማሰራታቸው ይነገርላቸዋል፡፡ ማየት ለተሳናቸው ወገኖች፣ በጮራ ቤተ-መፅሐፍት በኩል፣ የትምህርት እድል እንዲያገኙ በማድረግም ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡  የተለያዩ አገር በቀል ዛፎችን በመትከልና በመንከባከብ ተፈጥሮን ለመጠበቅ ያከናወኑት ተግባር፣ መምህሩ ከሚጠቀስላቸው በርካታ ሥራዎች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ መምህር ስመኘው “የበጎ ሰው ሽልማት” የመምህራን ዘርፍ ተሸላሚ በመሆናቸው፣ የተሰማቸውን ስሜት ለአዲስ አድማስ እንዲህ ገልፀዋል፡-
“-- ከልዑል ራስ መንገሻ ስዩም ጐን ቁጭ ብሎ እኩል መሸለም እንደ ሰው ልዩ ስሜት ይፈጥራል። እኔ ልዑል ራስ ስዩም መንገሻን በታሪክ ነው የማውቃቸው፤ በአካል አያቸዋለሁ ብዬ በእውኔም በህልሜም አስቤ አላውቅም፡፡
ሽልማቱን ካገኘሁ በኋላ ከአገር ውስጥም ከውጭም እየተደወለ፣ ሁሉም እንኳን ደስ ያለህ ሲለኝ፣ ሸላሚ ድርጅቱን ነው ይበልጥ ያመሰገንኩት። ምክንያቱም ታች ጋይንት በረሃ ድረስ ወርደው ፈልገው ነው ለዚህ ያበቁኝ፡፡ በጣም ነው የማመሰግነው፡፡--
“በአዲሱ ዓመት እንደ ማንኛውም ሰው ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በህይወቴ ተስፋ ቆርጬ አላውቅም፡፡ ከተማሪዎቼም በጣም የሚያናድደኝ ተስፋ የሚቆርጥ ሲሆን ነው፡፡ ተስፋ የሚቆርጥ ሰው ለምንም አይበቃም፡፡ ምንም አያገኝምም፤ስለዚህ ምንም ተስፋ በሌለበት እንኳን ተስፋ ማድረግ ያስፈልጋል። አገሪቱ ትልቅ የእምነት አገር ናት፤የሚያምን ሰው ተስፋ አይቆርጥም፡፡ በአዲሱም ዓመት ብዙ መልካም ነገሮች እንደሚመጡ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በነገራችን ላይ የቀድሞ ተማሪዎቼና ጓደኞቼ ከሽልማቱ በኋላ ቡና እንጋብዝህ ብለው ጠሩኝ፤ እኔ የመሰለኝ ሁለትና ሶስት ሆነው የሚጠብቁኝ ነበር፡፡ ስሄድ አዳራሽ ሙሉ ሰው ነው፡፡ ላደረጉልኝ ነገርና ለሰጡኝ ክብር ከልብ አመሰግናለሁ፡፡ ሸላሚ ድርጅቱንም ሆነ ለአገር ውለታ ውለው የተሸለሙትን እንደ ልዑል ራስ መንገሻ ያሉና ሌሎችንም ትልልቅ ሰዎች አመሰግናለሁ፡፡ ለሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ መልካም አዲስ ዓመት እመኛለሁ፡፡”


------------


              “ለውጡ መላው ኢትዮጵያውያን መስዋዕትነት የከፈሉበት ነው”
                 የተከበሩ አቶ ለማ መገርሳ
                 (የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚደንት)


    “--ይህ ሽልማት ለእኔ ይገባኛል ብዬ አላምንም፤ እድሜ ዘመናቸውን በምርምር፣ በጋዜጠኝነትና በሌላው ዘርፍ አገራቸውን ያገለገሉ ትልልቆች በተሸለሙበት መድረክ መሸለም በጣም ትልቅ ነገር ነው፡፡ እኔ የሰራሁት ትንሽ ነው፡፡ እሱም የግሌን ግዴታ ለመወጣት እንጂ ለዚህ ሽልማት ያበቃኛል ብዬ አይደለም----አባቴ ያወረሰኝ አንድ ትልቅ ቀርስ አለ፤ ይህ ቅርስ እስክሞት ከውስጤ አይወጣም፤ እሱም ራስን መሆን ነው!
የእኛ አገር ፖለቲካ በሸርና በክፋት የተሞላ አስቸጋሪ ነው፡፡ ይህ ክፉ ፖለቲካ ብዙዎች ንፁሃንን መስዋዕት አድርጓል፡፡ ብዙዎችንም አምክኗል። በመጠፋፋት መኖር እርግማን ነው፤ ቢያንስ በእኛ ዘመን ይህ እርግማን ይቀየር በሚል ጥቂቶች ከፊት ሆነን ተንቀሳቀስን እንጂ ለውጡ መላው ኢትዮጵያዊያን መስዋዕትነት የከፈሉበት ነው፡፡ ነገር ግን አሁንም መስቀለኛ መንገድ ላይ ነን፡፡ አንዱ ይዘነው የመጣነው እርግማን አለ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ተስፋ አለ፡፡ ስሜታችንንና ፍላጐታችንን ከገደብን፣ ኢትዮጵያ ቆሻሻ ፖለቲካዋን አራግፋ፣ ዲሞክራሲያዊት አገር ትሆናለች፡፡ ይህ ካልሆነ ወደ ቀደመው የመጠፋፋት ሥርዓት እንመለሳለን፤ ይህ ማንንም አይጠቅምም---ተፎካካሪ ፓርቲዎችና የአገር ሽማግሌዎች ቆሻሻውን ፖለቲካ ትተን፣ መልካም አገር ለመገንባት አብረን እንስራ--”
(የዘንድሮው የበጎ ሰው ልዩ ተሸላሚ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ፤ ስድስተኛው ዙር “የበጐ ሰው ሽልማት” ባለፈው እሁድ በኢንተርኮንትኔታል ሆቴል በተካሄደበት ወቅት ካደረጉት ንግግር የተወሰደ ነው።)


-------------


           “ባሸንፍም ብሸነፍም ስታጭ ነው ያሸነፍኩት”
              አርቲስት አበበ ብርሃኔ (የዜማ ደራሲ)


    ለአብዛኞቹ አንጋፋና ወጣት ድምጻውያን ብዙ ዜማዎችን ደርሷል፡፡ በትክክል ቁጥሩን መናገር ቢቸግረውም፡፡ የአንጋፋው ድምፃዊ ጌታቸው “ሀገሬ ትዝታሽ ነገሰ”፣ የማዲንጐ አፈወርቅ “ነይ ዜማ ነይ ዜማ”--- የአንጋፋው ዜማ ደራሲ የአበበ ብርሃኔ የፈጠራ ውጤቶች ናቸው፡፡ አስቴር አወቀ፣ ብርቱካን ዱባለ፣ የሺመቤት ዱባለ፣ አሰፉ ደባልቄ እንዲሁም ባለቤቱ ፍቅርአዲስ ነቃጥበብ የአበበን ዜማዎች ደጋግመው አቀንቀነዋል፡፡ አንጋፋው ድምጻ ማህሙድ አህመድ፣ ሙሉቀን መለሰ፣ ኤፍሬም ታምሩና ፀጋዬ እሸቱም --- ለአበበ ብርሃኔ የዜማ ድርሰቶች እንግዳ አይደሉም፡፡
በ1959 ዓ.ም በጐንደር የተወለደውና ከብት ሲጠብቅ ያደገው አበበ ብርሃኔ፤በቀለመወርቅ ደበበ ትምህርት ታንጾ ያደገና የቀድሞው የፋሲለደስ ኪነት ቡድን አባልም ነበር፡፡ የመጀመሪያ የዜማ ስራውን ለአሰፉ ደባልቄ መስጠቱን ያስታውሳል፡፡ ከ800 በላይ ከሰው አዕምሮ የማይጠፉ ዜማዎችን መስራቱ በበጎ ሰው ሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይ ተገልጿል፡፡ በዘንድሮው “የበጐ ሰው ሽልማት” በኪነ-ጥበብ (ዜማ) ዘርፍ፣ ከእውቁ የዜማ ደራሲ አየለ ማሞ (አየለ ማንዶሊን) እና ቴዲ አፍሮ ጋር ነበር ለመጨረሻው ዙር ውድድር በእጩነት ያለፈው፡፡ የ6ኛው ዙር የበጎ ሰው ሽልማት የኪነጥበብ ዘርፍ አሸናፊ ሆነ - አበበ ብርሃኔ፡፡ ስለ ሽልማቱና ስለ አዲስ ዓመት ተስፋው ለአዲስ አድማስ እንዲህ ተናግሯል፡-
“ለሽልማቱ ታጭተሀል ስባል ብዙ አልደነቀኝም፡፡ ምክንያቱም ሽልማት ብዙ የተለመደ ነገር አይደለም፡፡ እኔም ብዙ ጊዜዬን ስራ ላይ ማሳለፍ እንጂ ስለ ሽልማት አስቤ አላውቅም።  በእኔ እምነት፣ዝም ብሎ መስራትና ትኩረትን ሥራ ላይ ብቻ ማድረግ ጥሩ ነው፡፡ እንደዚያም ሆኖ ይህን ያህልም ሥራ ሰርቻለሁ ብዬ አላስብም ነበር፡፡ ሰርፀ “ምን ያህል ዜማ ሰርተሃል?” ሲለኝ፣ አላውቅም ነበር ያልኩት፡፡ ለመመዝገብ ጀምሬ፣ እዚህ ላይ ጊዜዬን ከማባከን፣ አንድ ዜማ ብሰራ ይሻላል ብዬ ወደ ስራዬ ነው የገባሁት፡፡ -- እንግዲህ የመጀመሪያውን ሥራ ለአሰፉ ደባልቄ ከሰጠኋት በኋላ ነው፣ አሪፍ ዜማ ሰራ እየተባለ በቡድን ሲወራ፣ ሰላማዊት ለእኔም ስጠኝ ያለችኝ፡፡ ያን ጊዜ ሌላ ለመስራት ተጨንቄ፣ ለአሰፉ የሰጠኋትን ለሰላማዊትም ልሰጣት ነበር፡፡ ግን እንዴት እንዲህ አደርጋለሁ፣ ሌላ ልስራ እንጂ ብዬ ሌላ ሰራሁ፤ በዚያው ቀጠልኩበት፡፡
“የሽልማት ሥነ ሥርዓቱ በጣም ነው የገረመኝ። በዚህ ደረጃ ከፍታ ያለው አልመሰለኝም ነበር፤ ከእነዚያ አንጋፋና ታላላቅ ሰዎች ጐን እሆናለሁ ብዬም አላሰብኩም ነበር፡፡ ፕሮፋይል ጥንቅራቸው፣ ሰው ስለ ተሸላሚው ያለው ግንዛቤ እንዲሰፋ ያደረጉት ጥረት-- በአጠቃላይ ሥነ-ሥርዓቱ አስደማሚ ነበር፡፡ የሰራኋቸው ዜማዎች በዘፋኞቹ ድምፅ ቀንጨብ ቀንጨብ እየተደረጉ ሲቀርቡ መድረክ ላይ ሆኜ ሳለቅስ ነበር፡፡ እና በጣም -- በጣም --- ደስ ብሎኛል፡፡ ለበለጠ ስራ የሚያነሳሳ ነው፡፡ አመሰግናለሁ፡፡
“ከቴዲ አፍሮና ከአየለ ማሞ እኔ አሸንፋለሁ ብለህ አስበህ ነበር ወይ ላልሺኝ፣ እኔ ብሸነፍም ባሸንፍም ስታጭ ነው ያሸነፍኩት፡፡ ለምሳሌ አንድ ቤት ውስጥ ሻማም ጧፍም ኩራዝም ቢለኮስና ቢበራ፣ብርሃኑን ይበልጥ ያደምቀዋል እንጂ ኩራዙ ሻማውን፣ ሻማው ጧፉን አያጠፋውም፡፡ በእለቱ ቴዲም፣ ጋሽ አየለም፣ እኔም ነበርን የበራነው። አንደኛውም ሶስተኛ ነው፣ ሶስተኛውም አንደኛ ነው፤በእኔ እምነት በጣም ደስ ይል ነበር፡፡
“አንዳችንም ከቁጥር ሳንጐድል ወደ አዲሱ ዓመት እንድንሸጋገርና የአዲሱን አመት ፍሬ እንድንቀምስ እመኛለሁ፡፡ አሁን ያለነው እጅግ መረጋጋትና ማስተዋልን የሚጠይቅ ወቅት ላይ ነው፡፡ ተስፋችን እንዳይበላሽ፣ ሁላችንም በያለንበት ማስተዋልና መረጋጋት ይጠበቅብናል። በተረፈ ለተሰጠኝ ክብርና እውቅና፤ ሸላሚ ድርጅቱንና አባላቱን፣ ክብር የሰጠኝን ህዝብም ጭምር አመሰግናለሁ፡፡ 2011 ዓ.ም የሰላም፣ የፍቅርና የጤና እንዲሆንልን እመኛለሁ!!”

Read 943 times