Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 12 May 2012 10:21

ዓለም አላፊ ነው! መልክ ረጋፊ ነው! ፎቶግራፍ ቀሪ ነው!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን ጌታዋን ለረዥም ጊዜ ያገለገለች አንዲት አህያ እና ከጐረቤት ኑሮ አስመርሮት የወጣ አንድ ውሻ፤ ተያይዘው ወደ ጫካ ይሄዳሉ፡፡ አህያዋ ሳር ስትግጥ ውሻው የወዳደቀ አጥንት አግኝቶ ሲበላ የጥጋብ ጊዜ ሆኖላቸው ዋለ፡፡

ወደማታ ላይ አህያ በጣም ሆዷ ሞላና፤

“አያ ውሻ” አለችው፡፡

“አቤት” አለ ውሻ፡፡

“ሆዴን ነፋኝ ቀበተተኝ”

“ምን ታረጊ ታዲያ?”

“አንድ ጊዜ ልጩህ”

“ተይ አይሆንም፡፡ እዚህ ጫካ ውስጥ ጅብ ሳይኖር አይቀርም፡፡ ድምፅሽን ከሰማ ያለንበትን ቦታ

ይጠረጥርና ይመጣል”

“አይ በዚህ ድቅድቅ ጨለማ እንዲህ ጥቅጥቅ ባለ ደን ውስጥ ያለንበትን ሊያኘው አይችልም”

“እንግዲህ እንዳሻሽ፡፡ እኔ የለሁበትም”

“ሃ! ሃ! ሃ!” አለችና ጮኸች አህያ፡፡

ከዚያም እንደገና ወደ ግጦሿ ተመልሳ መጋጥ ቀጠለች፡፡ ሆዷ ሲሞላ፤

“አያ ውሻ” አለች፡፡

“አቤትሿ!”

“ሆዴን ነፋኝ፣ ቀበተተኝ! እባክህ አንድ ጊዜ ልጩህ?”

“ተይ አይሆንም፡፡ አያ ጅቦ ከሰማ የት ጋ እንዳለሽ ይገመታል፡፡ ቅድም በጮህሺውም ይሄኔ ጠርጥሮ

ፍለጋ ጀምሮ ይሆናል፡፡” አለ ውሻ ፍርጥም ብሎ፡፡

አጅሪት “በጭራሽ ሊያገኘን አይችልም” አለችና

“ሃ! ሃ! ሃ! ሃ!” ብላ ጮኸች፡፡

አያ ጅቦ በሁለት ጊዜ ጩኸትዋ ፍለጋ ጀምሯል፡፡ አጅሪት መጋጧን ቀጠለች፡፡ ሁን ሆድዋ ሞላ፡፡

“አያ ውሻ”

“አቤት”

“እባክህ አንዴ ለመጨረሻ ጊዜ ልጩህ! ከዚህ በኋላ ሳርም አልግጥም፤ ሆዴንም አይቀበትተኝም!”

አለችው፡፡

ውሻም፤

“እመት አህያ እንደምገምተው አደጋ እየጋበዝሽ ነው፡፡ ምክንያቱም:-

የመጀመሪያው መጥሪያ

ሁለተኛው ማቅረቢያ

ሦስተኛው መበያ፤ ነው፡፡ ስለዚህ ይቅርብሽ” አለ አያ ውሻ፡፡ አጅሪት በጄ አላለችም፡፡

“ሃ! ሃ! ሃ!” አለችና ጮኸች፡፡

አያ ጅቦ አጠገቧ ደርሶ ኖሮ በትክክል ያለችበትን አውቆ፤ መጥቶ ሆዷን ዘነጠላት፡፡ ውሻ ጢሻ ገብቶ

አመለጠ!

***

የማስጠንቀቂያና የግንዛቤ ደወል የማያዳምጥ ሁሉ የአህይት ዕጣ ፈንታ ይጠብቀዋል፡፡ ማንም ይሁን ማን መውደቂያው ሲቃረብ ጩኸት ማብዛቱ፣ ማስጠንቀቂያ አለመስማቱ፣ የተለመደ ነገር ነው፡፡ ደራሲ ከበደ ሚካኤል፤

“አሁን የት ይገኛል፣ ቢፈልጉ ዞሮ

መስማት ከማይፈልግ፣ የባሰ ደንቆሮ” ይሉናል፡፡

ማናቸውንም አገራችንን የሚመለከት ጉዳይ ሥራዬ ብለን ብናዳምጥ ከነገ አባዜ እንድናለን፡፡ እስከዛሬም ብዙ ፍሬዎቻችን መክነው፣ ያበበው ረግፎ፣ የቸገንነው ጠውልጐ የቀረው፤ በንቀት ምክንያት ነው! ንቀት ደግሞ ከቆየው ፊውዳላዊ አስተሳሰባችን የሚመነጭ ነው! ስለሚተከለው ችግኝ ንቃት አለን፡፡ ስለሚታቀደው እቅድ ንቀት አለን፡፡ ስለሚቋቋመውም ሆነ ስለተቋቋመ ፓርቲ፣ ድርጅት ወይም ማህበር ንቀት አለን፡፡ ስለዲሞክራሲ ንቀት አለን፡፡ ስለፕሬስ ንቀት አለን፡፡ ስለፍትህ ርትዕ ንቀት አለን፡፡ ስለ መልካም አስተዳደር ንቀት አለን፡፡ አፋችን የሚያወራውን ልባችን ቸል ይለዋል፡፡ ፖለቲካችንም ሆነ ኢኮኖሚያችን ከጉንጭ-አልፋ ክርክር በላይ የማይዘለው ለዚሁ ነው፡፡ ችግሮቻችንን ጠንቅቀን ካላስተዋልን መፍትሄዎቻችንም ከአንገት-በላይ ነው የሚሆኑት!

የገንዘብ ገቢ የማሰባሰቢያ መንገዶችን ስናቅድ የሰውን ስነልቦና ማሰባሰቢያም መንገድ ሊኖረን ይገባል፡፡ ጥናቶቻችን ሁሉ የህዝብን አመለካከት ያጤኑ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ እስከዛሬ የሄድንበት መንገድ የት አደረሰን? ጓዳችንን እንመርምር! ደጃችንን እንይ! ስሜታዊ አንሁን! በትንሽ በትልቁ ጠብ ያለሽ በዳቦ አንበል! ማን አለብኝን እንተው! ጊዜ እንዳነሳን ሁሉ ጊዜ ይጥለናል የሚለውን እሳቤ ለሰከንድም ቢሆን አንዘንጋ! “ዓለም አላፊ ነው! መልክ ረጋፊ ነው! ፎቶግራፍ ቀሪ ነው” የሚባለው ለዚህ ነው!!

 

 

Read 5846 times Last modified on Saturday, 12 May 2012 10:28