Monday, 10 September 2018 00:00

“ከብረው ይቆዩ ከብረው!--”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(5 votes)


  “--ከሰልፎቻችን፣ ከኮንሰርቶቻችን እፎይ ብለን ትንፋሽ ስንሰበስብ፣ ያኔ ሁሉም እየለየ መሄዱ አይቀርም፡፡ እስከዛው ግን አንዳንዴ ግለሰቦችና ቡድኖች ላይ ሲሰነዘሩ የምንሰማቸው አስተያየቶችም ሆኑ ትችቶች የተሳሳቱ ድምዳሜዎች ላይ እንዳይወስዱን ጥንቃቄ የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ ነን፡፡--”
 
    እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እንኳን ለአዲስ ዓመት ዋዜማ አደረሳችሁማ!
እንቁጣጣሽ፣ እንኳን መጣሽ
በአበቦች መሀል እንምነሽነሽ
ተብሏል፡፡ መምነሽነሽ ደረጃ ባንደርስ እንኳን ዘና ባለ መንፈስ፣ ፈካ ባለ ገጽታ…መቀበል መቻል ቀላል አይደለም፡፡ “እንኳን አደረሰህ”፣ “እንኳን አደረሰሽ!” ለመባባል መብቃት ትልቅ ፀጋ ነው፣ እንደ እውነቱ እድለኝነትም ነው፡፡ ምክንያቱም...ለዚህ ያልታደሉ ብዙ አሉና፣ መንገድ ላይ የቀሩ አያሌ ናቸውና!
ስሙኝማ…ይቺን ሰሞን እንግዲህ ቸስ ነው። ምናልባትም ከበርካታ ዓመታት በኋላ ‘ማንም ሳይቀር ሁላችንንም’ ባይባልም…አለ አይደል…ብዙዎቻችንን ያቀፈ የበዓል ስሜት ያለ ይመስላል። ማለት…በተለመደው እኛ በዓልን ከሸመታ ጋር ብቻ ከምንመዝንበት ወጥተን፣ በዓልን ከእውነተኛ ውስጣዊ ዘና ማለት ጋር የምናይበት፡፡ እውነተኛ ውስጣዊ ዘና ማለት ደግሞ “የሰንጋው ጎድን ተዳቢት” “የዶሮዋ አጭሬና ፈረሰኛ” ጉዳይ አይደለም…ውስጣዊ ደስታ የእነ እንትና ሆቴል ኮንሰርት፣ የእነ እንትና አዝማሪ ቤት ማሲንቆ፣ የእከሊት ውስኪ ቤት ብሉ ሌብል …ብቻ አይደለም፡፡
እውነተኛ ደስታ ላለፉት ጥቂት ወራት ስንሰማቸው ከከረምናቸው መልካም መልዕክቶች፣ የመዋደድ መልዕክቶች፣ የመተቃቀፍ መልዕክቶች፣ ይቅር የመባባል ጥሪ መልዕክቶች የሚመጣ ነው፡፡ እንዲህ በአንጻራዊነቱ ከሌሎች ጊዜያት በተሻለ ‘ዘና ያለ’ ስሜት ውስጥ ሆነን…… እነኛ ውብ መልዕክቶች “እንዲህ ተብሎ ነበር…” ሆነው እንዳይቀሩ እንመኛለን፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ወደ ሀያ አምስት ሺህ ገደማ የዳያስፖራ ወገኖቻችን ወይ መጥተዋል፣ ወይ እየመጡ ነው ተብሏል፡፡ (አንድ ወዳጃችን እንዲሁ ዓይነ ውሀቸውንና በተለይ ደግሞ የተለያዩ እንቅስቃሴዎቻቸውን አይቶ “ይሄ ፓርኪንግ ነው የሚሰራው”፣  “ይሄኛው የሞል ዘቡሌ ነገር ነው” “ይቺኛዋ የአዛውንቶች ሞግዚት ነች” ምናምን የሚለው ነገር አለው፡፡) እናማ… ‘ዳያስፖራ’ ብለን የምንናገረው ጠቅለል ስለሚያደርግልን ነው እንጂ ሁሉንም በአንድ ዓይን ማየታችን እንዳልሆነ ይታወቅልንማ! (አሀ… ልክ ነዋ!  ከጨርቆስ የሚመጣ ክንዱን የተነቀሰ እንትናና ከእንትን ሰፈር የሚመጣ፣ ጸጉሩን አሁንም መሀል ለመሀል እንደ ኤልቪስ የሚከፍል እንትና፣ በአንድ ዓይን ይታያሉ!? ለጠቅላላ እውቀት ያህል ነው፡፡ ስሙኝማ…አዲስ አበባ ውስጥ ‘ጂ ፕላስ ፎር’ ምናምን የሚሏቸው ‘አራዶች’ አሉ ይባላል…አለ አይደል፣ ሰዓታችንን ከእጃችን ሳያወልቁት፣ ራሳችን አውልቅን እንድንሰጣቸው የሚያደርጉ አይነት!)  እናማ…አሁን ለምሳሌ የመን ዳያስፖራ ነች! (ቂ…ቂ…ቂ…) የምር እኮ ብዙዎቻችን ዳያስፖራ የሚባለውን ነገር ከአሜሪካና ከአውሮፓ ጋር ስለምናያይዘው፣ ከሌላ ቦታ የሚመጣውን ከአሜሪካን ግቢ እስከ አንበሳ ግቢ የመሄድ አይነት እናደርገዋለን፡፡  እንግዲህ እንደ ዓለም አቀፍ ህጉ ከሆነ፣ ከጎረቤታችን የሚመጡ የአገር ልጆችም እኮ ያው ዳያስፖራ ናቸው፡፡  
እናማ…ከአንዱ ዘመን ወደ ሌላ ዘመን ለመሸጋገር ጫፍ ላይ ባለንበት ጊዜ፣ ልንጥላቸው የሚገቡ ባህሪያት አሉ፡፡ ካልጣልናቸው ውለው አድረው እኛኑ ሊጥሉ የሚችሉ ባህሪያት፤ ካልጣልናቸው ከግለሰብ፣ ከማህበረሰብ አልፈው አገር ላይ አደጋ ሊጋርጡ የሚችሉ ባህሪያት!!
ከስሜታዊነት መውጣት አለብን …ሰሞኑን በአቀባበሎችና በመሳሰሉት ላይ የምናያቸው ግለሰቦችን የሚመለከቱ መፈክሮችና ምስሎች አይነት ስሜታዊነት እኮ ከምንልው ሁሉ ጋር የሚጋጭ ነው። “አንተ በየማታው ከእነሱ ጋር እንትን ሉካንዳ ቁርጥ ስትቆርጥ አልነበር!” “እንትን ሆቴል ጎልድ ሌብሉን ደብል ደብሉን ስትገለብጥ አልነበር!” አይነት መካሰሶች ከትልቁ ግብ የሚያርቁ ናቸው፡፡ እነሱ፤ እኛ የሚለውን ነገር ስንጠላ እንደኖርነው፣ አሁን “እነሱ” “እኛ” ከሚለው አይነት ‘ታርጋዎች’ መራቅ ግድ ይላል፡፡ ምክንያቱም የአለቃ ኪዳነወልድም ይሁን የመርሴሃዘን መዝገበ ቃላት  ባላሰፈሩት ትርጓሜ… አለ አይደል… ዘንድሮ የትኛውም ወገን ‘እነሱ’ ሲል “ከእኛ የተለየ አማራጭ ሀሳቦች ያሏቸው…” ማለት ሳይሆን “ደመኛ ጠላቶቻችን” ማለት ሆኗልና! 
ስሙኝማ…ከተጨዋወትን አይቀር… ትንሽ ተርመስመስ ያሉ ነገሮች አሉ…ትንሽ ‘ፈካ ሊል ነው’ ያልነውን አየር የሚያጠይሙብን ነገሮች አሉ፡፡ ማለትም…ከዛሬ አንዳንድ እንቅስቃሴዎች ተነስተን ነገን ስናይ… “ፍቅሬ፣ ፍቅሬ በዛ እኔ አላማረኝም” የሚያሰኙ ነገሮች! ደግሞ፣ ደጋግሞ እንደሚሰማው ህጎችን በማክበር ረገድ አሳሳቢ ነገሮች አሉ፡፡ «ህግ ይከበር፣ ህግ ተጣሰ፣ ግለሰቦች ህጉን እንደፈለጉ የሚያሽከረክሩበት አሠራር ይቁም!» ብለን ስንነሳ፣ ለህግ ትልቁን ስፍራ ሰጥተናል ማለት ነው…ማግኘት የሚገባውን ስፍራ። ዋናው የአቋማችን መለኪያ መሆን ያለበት ደግሞ እኛስ ህጉን እንዴት ነው አክብረን የምናስከብረው የሚለው ነው፡፡ አሁን አንድ ሁለቱን ህጎች ከጣስን፣ ነገና ከነገ ወዲያ ሀያና ሠላሳዎቹን ላለመጣሳችን ምን ማስተማማኛ አለ! ሊለወጡ፣ ሊስተካከሉ፣ ጭርሱንም ሊሰረዙ የሚገባቸው ህጎች መኖራቸው አያከራክረንም። ግን እነኚህ አልተመቹንም ያልናቸው ህጎች እስካልተሻሻሉ ወይም እስካልተሰረዙ ድረስ ሥራ ላይ ናቸው…ሊከበሩም ይገባል፡፡
እናላችሁ…ትንሽ ተርመስመስ ያሉ ነገሮች አሉ። ስሙኝማ …የምር ግን ብዙዎቻችን አሁን አገሩን የሞላነው ሰዎች ‘ነገር ከተረጋጋ’ በኋላ…አለ አይደል… በምንፋቅ ጊዜ ከስር ምን እንደሚወጣ ለማየት አልናፈቃችሁም! አሁን እኮ…ገና ማን ከማን እንደሚለይ ለመነጋገር፣ ማንና ማን ተመሳሳይ መስመር ላይ እንደቆሙ ለማወቅ፣ የትኛው ወገን ምን አይነት ሀሳቦች እንዳሉት ለመለየት፣ የትኞቻችን በየአደባባዩና በየመድረኩ የምንናገረው ከአንገት ሳይሆን ከአንጀት እንደሆነ ለመወቅ፣ የትኛው ሰልፍ ከእውነተኛ ስሜት የመነጨ፣ የትኛው ደግሞ ዝም ብሎ ለ‘አድቬንቸር’ ያህል የተደረገ ነገር እንደሆነ ለመለየት ትንሽ የቀረን ይመስላል፡፡ ከሰልፎቻችን፣ ከኮንሰርቶቻችን እፎይ ብለን ትንፋሽ ስንሰበስብ፣ ያኔ ሁሉም እየለየ መሄዱ አይቀርም፡፡ እስከዛው ግን አንዳንዴ ግለሰቦችና ቡድኖች ላይ ሲሰነዘሩ የምንሰማቸው አስተያየቶችም ሆኑ ትችቶች የተሳሳቱ ድምዳሜዎች ላይ እንዳይወስዱን ጥንቃቄ የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ ጉድለት የሌለበት የለም…ግን እዛው ጉድለት ያልነው ነገር ላይ የሙጥኝ ብሎ ከማማረር ይልቅ ‘ጉድለት’ የተባለውን ወደ መልካም ለመለወጥ መሞከሩ ሳይሻለን አይቀርም…ብዙ፣ እጅግ ብዙ ጉድለቶች አሉብንና!
አንድ ቻይናዊ ውሀ ከወንዝ እየቀዳ ወደ ቤቱ የሚያመጣባቸው ሁለት ማሰሮዎች ነበሩት፡፡ አንደኛው ማሰሮ ምንም ጉድለት የለበትም፣ ሌላኛው ግን ስንጥቅ ነበረበት፡፡ ሁለቱንም ማሰሮዎች ውሀ ሞልቶ ወደ ቤት ሲወስድ ባለ ስንጥቁ ውስጥ ያለው ውሀ መንገድ ላይ ትንሽ በትንሽ ይፈሳል፡፡ ቤት ሲደርስም ባለ ስንጥቁ ማሰሮ ውስጥ ያለው ውሀ ግማሽ ብቻ ነው የሚሆነው፡፡
ከጊዜ በኋላ ስንጥቁ ማሰሮ ይመረውና ባለቤቱን ይናገረዋል፡፡ “በራሴ እጅግ አፍሬያለሁ፣ ምከንያቱም እላዬ ላይ ያለው ስንጥቅ፣ ቤት እስክንደርስ ግማሹን ውሀ ያፈሰዋል” አለው፡፡
ይሄኔ ባለ ማሰሮው እንዲህ አለ… “በአንተ ወገን ያለው መንገድ ላይ መሬቱን ልብ ብለህ ከሆነ፣ ሙሉ በሙሉ አበባ ጸድቆበታል፡፡ በዛኛው ማሰሮ ወገን ግን ደረቅ መሬት ነው፡፡ አንተ ላይ የነበረውን ጉድለት ሳውቅ፣ በአንተ ወገን ባለው መንገድ ላይ የአበባ ዘሮች ዘራሁ፡፡ በየቀኑ ወደ ቤት ስንሄድ፣ አንተ ታጠጣቸው ነበር፡፡ ለሁለት ዓመትም አበቦች እየቀጠፍኩ ቤቴን ሳስጌጥ ኖሬያለሁ፡፡ አንተ ስንጥቅ ባይኖርብህ ኖሮ፣ ቤቴ እንዲህ አያምርም ነበር” አለው ይባላል፡፡  
ክረምት አልፎ በጋ መስከረም ሲጠባ
አሮጌው ዓመት አልፎ አዲሱ ሲገባ
ፈሳሽ የወንዝ ውሀ ተውሳኩን ይውሰደው
ጤና መሆንን ነው እኛ የምንወደው
እኛም እንደዛ እያልን ነው፡፡ ዘንድሮ ተውሳኩ በቤተ መኩራ በአጉሊ መነጽር ብቻ ተፈልጎ የሚገኝ ሳይሆን ፊት ለፊት የሚታይ ነው፡፡ ያፈጠጠ ተውሳክ! ዘረኝነት የሚሉት ተውሳክ! ጎጠኝነት የሚሉት ተውሳክ!…እኛ ጤና መሆንን ስለምንፈልግ፣ ጠራርጎ የሚወስዳቸው ፈሳሽ የወንዝ ውሀ ያምጣልንማ!
ከብረው ይቆዩ ከብረው
በዓመት ወንድ ልጅ ወልደው
ሠላሳ ጥጆች አስረው
ከብረው ይቆዩ ከብረው!
ይላሉ ህጻናቱ፡፡ ህዝባችን፣ አገራችን፣ ዓለማችን ‘ከብረው ይቆዩልንማ!’
መልካም የበዓል ዋዜማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 5613 times