Print this page
Monday, 10 September 2018 00:00

“አርበኞች ግንቦት 7 በመላ ሃገሪቱ የህቡዕ አደረጃጀት ነበረው”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

 • የአቀባበል ሥነ ሥርዓቱ በዋናነት እርቁን ለማብሰር ነው
    • ለኢትዮጵያ አንድነት የሚበጀው የዜግነት ፖለቲካ ነው

    ላለፉት 8 ዓመታት ገደማ በኢትዮጵያ መንግስት በአሸባሪነት ተፈርጆ፣ ኤርትራን መቀመጫው አድርጐና ትጥቅን ጨምሮ ሁሉን አቀፍ ትግል ሲያካሂድ የቆየው የአርበኞች ግንቦት 7 አመራሮች፤ ነገ እሁድ ጳጉሜ 4  አዲስ አበባ ይገባሉ ተብሏል፡፡ ለንቅናቄው አባላት አቀባበል ለማድረግ ከወር በፊት ተቋቁሞ በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን የጠቆሙት የአቀባበል ኮሚቴው አስተባባሪ አቶ ብርሃኑ ተ/ያሬድን፣ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ያነጋገራቸው ሲሆን ንቅናቄው ወደ ፖለቲካ ድርጅትነት የሚቀየርበትን ሂደት፣በከተማ ስለነበረው ህቡዕ አደረጃጀት፣በወደፊት የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለሙና ተያያዥ ጉዳዮችን ጠይቋቸዋል። እነሆ፡-



    እስቲ የነገውን የአቀባበል ዝግጅት በተመለከተ ይንገሩኝ?
በጣም ሰፊ ነው፡፡ የሚመጡት ሰዎች 250 ይሆናሉ። የንቅናቄው ሊቀ መንበር ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ጭምር ስለሚመጣ የደህንነት ስጋትም አለብን። በተለያዩ የሃገራችን ክፍሎች እየታዩ ያሉ ችግሮች፣ በደህንነት ዝግጅቱ ላይ በጣም እንድንጨነቅ አድርገውናል፡፡ በሌላ በኩል፤ አመራሮቹ በአደባባይ ከናፈቁት ህዝብ ጋር የሚገናኙባቸው ሰፋፊ መርሃ ግብሮች አሉ፡፡ በዚህ ረገድም ብዙ ስራ እየሰራን ነው፡፡ ነገ እሁድ ጳጉሜ 4 ማለዳ፣ አዲስ አበባ ይገባሉ፡፡ ዋነኛ የአቀባበል ፕሮግራሙ የሚካሄደው ደግሞ በአዲስ አበባ ስታዲዬም ነው፡፡
በስታዲዬም ያለውን መርሃ ግብር በተመለከተ ከመንግስት፣ ከደህንነትና ከፖሊሲ አካላት ጋር በስፋት ስንሰራ ቆይተናል፡፡ ሌላው ትኩረት ሰጥተን የሰራነው፣ አቀባበሉ ደማቅና መነቃቃትን የሚፈጥር እንዲሆን የማሸብረቅ ጉዳይ ነው። በየክፍለ ከተማው ተወካዮች አሉን። ተወካዮቻችን ወጣቶችን በማስተባበር በትግሉ የተሰዉ ጓዶችን ምስል፣ የድርጅታችንን አርማ፣ የኢትዮጵያን ባንዲራ በመስቀል ከተማዋን ሲያሸበርቁ ሰንብተዋል፡፡ ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ መሪዎቹን ይቀበላል ብለን እንጠብቃለን፡፡
የደህንነት ስጋቱን ለመቀነስ ምን የተለየ ጥንቃቄ አድርጋችኋል?
ከደህንነት ጋር በተገናኘ ለምናከናውነው ተግባር፣ የንቅናቄው የደህንነት ቡድን አዲስ አበባ መጥቶ፣ አስፈላጊውን ዝግጅት ሲያካሂድ ቆይቷል። በየዕለቱ ከመንግሥት የደህንነት አካላትና ከፖሊስ ጋር እየተገናኘ ደህንነቱን አስተማማኝ ለማድረግ እየሰራ ነው፡፡ ደህንነቱ የደረሰበትን ግኝት ለኛ ለኮሚቴዎች ያሳውቃል፡፡ እኛም በዚያ መሰረት ፕሮግራማችንን እያስተካከልን፣ ዝግጅታችንን እያጠናቀቅን ነው፡፡ በዚህ መሰረት ነው እየተሰራ ያለው፡፡
በአቀባበል ስነ ስርዓቱ ላይ ምን ያህል ህዝብ ይታደማል ተብሎ ይጠበቃል?
በተለያዩ ክ/ከተማ ካሉ አስተባባሪዎቻችን ጋር በአቀባበሉ ዙሪያ ስብሰባዎች አድርገናል። በዚህም የህዝቡ ተነሳሽነት ከፍተኛ መሆኑን መረዳት ችለናል። አንዳንድ አካባቢዎች ላይ የኛ አስተባባሪዎች ሳይኖሩም፣ ሰዎች በራሳቸው ተነሳሽነት ሰንደቅ አላማዎችን፣ ባነሮችን በመስቀል አቀባበሉን ለማድመቅ ሲንቀሳቀሱ እያየን ነው፡፡ በተለያዩ መንገዶች የተደራጁ ሰዎችም ቲ-ሸርቶችን በማሰራት፣ ባንዲራ በማዘጋጀት ላይ ተጠምደው መሰንበታቸውን አይተናል፡፡ እኛ ለማስተባበር በከፈትነው ቢሮ ከምንቆጣጠረው በላይ የሆነ ሰው ነው በየቀኑ እየመጣ ቲ-ሸርት፣ ስቲከሮች፣ ባነሮች እየወሰደ ያለው፡፡ ከእነዚህ እንቅስቃሴዎች አንፃር በአቀባበሉ ላይ በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ይወጣል የሚል እምነት አለን፡፡
የዕለቱ ዋና ዋና ፕሮግራሞች ምንድን ናቸው?
ነገ ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ እስከ 1፡30 ድረስ ልኡካኑ ከተለያዩ ሃገሮች፣ በተለያዩ በረራዎች፣ አዲስ አበባ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ገብተው ይጠናቀቃሉ፡፡ ከተለያዩ ሃገራት በተለያዩ በረራዎች ነው የሚመጡት። መሪዎቹ ከተሰባሰቡ በኋላ እዚያው አጭር ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣሉ። ከዚያ በኋላ ጉዞ ወደ ስታዲዬም ይሆናል፡፡ ከረፋዱ 5 ሰዓት እስከ ቀኑ 9 ሰዓት የአቀባበል ስነ ስርአቱ ይካሄዳል፡፡ እኛ ፕሮግራሙ እንዲሆን የምንፈልገው፣ የድርጅት የፖለቲካ ፕሮግራም አይደለም፡፡ የእርቅ ብስራት ቀን እንዲሆን ነው የምንፈልገው፡፡ የሚገዳደሉ፣ እርስ በእርስ የሚታኮሱ ወንድማማቾች እርቅ አውርደዋል፡፡ ከአሁን በኋላ የሰለጠነ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ነው የሚካሄደው። ይሄ የትግል ስልት ደግሞ ለዘመናት ስንናፍቀው የነበረ ነው፡፡ ቀኑ የአርበኞች ግንቦት 7 የአቀባበል ቀን ሳይሆን፣ የህዝብ የደስታና የእርቅ ቀን እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡ ዛሬ በዋዜማው በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች በሚገኙ ዋና ዋና አደባባዮች፣ የጧፍ ማብራት ስነ ስርአት ይካሄዳል፡፡ ይሄ የጧፍ ማብራት ስነ ስርአት አላማው፣ ባለፉት ዓመታት በተደረገው ትግል ውስጥ ለተሰዉ ሰማዕታት በሙሉ መታሰቢያ እንዲሆን ነው፡፡ በፖለቲካ መገዳደል ከእንግዲህ እንዲያበቃ መልዕክት የምናስተላልፍበትና የወደፊት ተስፋችንን የምናመላክትበት ደማቅ ስነ ስርዓት ይሆናል ብለን እናምናለን፡፡ ህዝቡ በአዲስ መንፈስ፣ አዲስ ነገር ተፈጥሯል የሚል እምነት እንዲያድርበት ማድረግ ነው አላማው፡፡ በስታዲዬም በሚኖረው መርሃ ግብር፤ የሃይማኖት አባቶች፣ የመንግሥት ተወካዮች፣ የአዲስ አበባ መላ ህዝብ ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
እስቲ ወደ እርስዎ እንምጣ ----- የአርበኞች ግንቦት 7 አባል የሆኑት መቼና እንዴት ነው?
እኔ ቀደም ሲል የሰማያዊ ፓርቲ አባል ነበርኩ። ከአባልነቱም ባለፈ የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊም ነበርኩ፡፡ በኛ ሃገር የፓርቲ ፖለቲካ ውስጥ ብዙዎች እንደሚያስተውሉት ችግሮች አሉ፡፡ የገዢው ፓርቲ ጫና እንዳለ ሆኖ፣ የእርስ በእርስ መጠላለፍ ፖለቲካ ከባድ ነው፡፡ የፓርቲ ውስጠ ዲሞክራሲ አለመኖርና ፖለቲካውን በዋና ጉዳይነት ያለመያዝ፣ ለሰላማዊ ትግል ቀና አመለካከት ያላቸውን ሰዎች በብዙ መልኩ ጎድቷል፡፡ በኔ እምነት፤ በሀገራችን ባሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ከመቆየት እስር ቤት ውስጥ መቆየቱ ቀሎኛል፡፡
ምንድን ነው እንደዚህ ያስባልዎት ጉዳይ?
አንተ በቀናነት ለሀገርህ ስትታገል፣ ሌላው ጠልፎህ ለመጣል ነው የሚታገልህ። መጠላለፉ ከባድ ነው፡፡ ፍረጃው ከባድ ነው። ተኝተህ ስትነቃ ወያኔ ተደርገህ ራስህን ልታገኝ ትችላለህ። ቡድንተኝነት አለ፡፡ ከገዥው ፓርቲ ጋር የሚተካከል ቁመና የፈጠረ፣ የሃገር ውስጥ የፖለቲካ ድርጅት ያልኖረበት ምክንያትም በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ስለቆየን ነው፡፡ እርስ በእርስ ስንተጋገል ጥርሳችን ያልቅና ስንወጣ፣ ጥርስ የሌለው አንበሳ እንሆናለን፡፡ ይሄ በጣም አድካሚ ነው፡፡ ለእኔም ይሄ ሁኔታ አድካሚ ነበር፡፡ ከዚያም  የተሻለ ታግሎ የሚያታግለኝን ድርጅት ፍለጋ አማተርኩ፡፡ አርበኞች ግንቦት 7ን ከዚያ በፊት የሚያወጣቸውን የትግል ፅሁፎችን በማንበብ ነው የማውቀው፡፡ 2005 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ግን የተወሰንን ወዳጃሞች እየተሰባሰብን ስለ ሃገራችን ሁኔታ እንወያይ ነበር፡፡ በዚያ ውስጥ ነው ቀስ በቀስ ከንቅናቄው አመራሮች ጋር የመገናኘት እድል ያገኘሁት፡፡ እነሱም የፖለቲካ አቋም፣ የመታገያ ስልት፣ ማኒፌስቶአቸው እንዲደርሰን አደረጉ። ከሚመስሉኝ ወጣቶች ጋር እነዚህን ፅሁፎች እያነበብን መወያየት ጀመርን፡፡ እንቅስቃሴያችን በህቡዕ ነበር፡፡ በኋላ የሚጠቅመውን ውጤት ያመጣል ያልኩትን መስመር መርጠን፣ የአርበኞች ግንቦት 7 አባል ሆንን፡፡ እዚህ ሆነን በውጭ ካሉ አመራሮች ጋር በድብቅ እንገናኝ ነበር፡፡ ህዝባዊ ኃይሉን ለመቀላቀል ፍላጎት እንዳለን ለመሪዎቹ አሳወቅን፡፡ እነሱም ጉዳያችንን መርምረው አዎንታዊ ምላሽ ሰጡን፡፡ በዚያው ወደ ኤርትራ ጉዞ አደረግን። ያው ኤርትራ ልንደርስ ጥቂት ሲቀረን ማይካድራ በተባለች ቦታ በመንግስት የደህንነት ኃይሎች ተያዝንና ታሰርን፡፡ አምስት አመት ተፈርዶብንም፣ ወደ ቃሊቲ እስር ቤት ገባን።
ፍ/ቤት ስትቀርቡ “የግንቦት 7 አባል ነን፣ ወደ ኤርትራ የምንሄደውም ህዝባዊ ኃይሉን ለመቀላቀል ነው” ብላችሁ ነበር ---
አዎ! እውነት ለመናገር ከዚህ ጉዞአችንን ስንጀምር መያዝና መታሰር እንዳለም አምነን ነበር። ቃላችንም አንድ ሆኖ የመጣው ለዚያ ነው። ከተያዝን ምንድን ነው የምንለው የሚለውን እየተነጋገርን ነው ጉዞ ያደረግነው፤ከመያዛችን በፊትም ምልክቶችን አይተን ነበር፡፡ ማይካድራ የምትባለው ከተማ በጣም ጠባብ ከተማ በመሆኗ፣ የመንግስት መኪናዎች ብዙም አይገኙባትም፡፡ በሆነ አጋጣሚ ሶስትና አራት የመንግስት መኪኖች በማየታችን፣ ልንታሰር እንደምንችል ተረድተነው ነበር፡፡ ስንታሰር ግን ብዙ ስሜት ነው የተሰማኝ፡፡ ትግሉን እንዳላግዝ ወደ እስር ቤት መጣሌ አናዶኝ ነበር፡፡ በወቅቱ ደግሞ የንቅናቄው አመራሮች፣ እኛን ለመቀበል ድንበር ላይ እየጠበቁን ነበር። እኛም ደግሞ ደርሰናል የሚል ስሜት ነው የነበረን፡፡ የያዙን የሁመራ፣ የጎንደርና የአዲስ አበባ ደህንነቶች በጋራ ሆነው ነው፡፡ ከ15 ሰው በላይ ነው የከበበን፡፡ ሁሉም የታጠቁ ናቸው። አያያዛቸውም አስደንጋጭ ነበር፡፡ አይናችንን በጨርቅ አስረው ለ3 ቀናት የት እንዳለን እንኳ ሳናውቅ ነው የቆየነው፡፡ ወዴት እንደሚወስዱን፣ ምን ውስጥ እንደሚያስገቡን፣ በቀጣይ ምን እርምጃ እንደሚወስዱ ስለማናውቅ ሁኔታው ደስ የማይል ነበር፡፡ እጃችን ወደ ኋላ ታስሮ፣ አይናችን በጨርቅ ተሸፍኖ ነበርና፣ ምን ሊያደርጉን እንደሆነ እንኳ ማወቅ አንችልም ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ተይዘው እስካሁን የት እንዳሉ የማይታወቁ ሰዎችም አሉ፡፡ እጣ ፈንታችን እንደዚያ ሊሆን ይችላል የሚል እምነት ነበረኝ፡፡ ነገር ግን ከ5 ቀናት በኋላ ራሴን ማዕከላዊ አገኘሁት፡፡ ማዕከላዊ መግባቴን የነገሩኝም እስረኞች ናቸው፡፡
ግን ለምን ነበር ለፍ/ቤት “የግንቦት 7 አባል ነን” ያላችሁት?
እኛ መጀመሪያውኑ ግንቦት 7 አሸባሪ አይደለም ብለን ለመከራከር ወስነን ነበር፡፡ “ግንቦት 7 ነን” ብለን ለሃገር መታገል ኩራት እንጂ ውርደት እንዳልሆነ ለማሳየት ነው፣ “አዎ አባል ነን፤ የምንታገለውም ለሃገር ነፃነት ነው” ያልነው፡፡ ሁላችንም የተከሳሽነት ቃላችንን በፍ/ቤት ስንሰጥ፣ “ሃገራችን ላይ ያለው ስርአት እንኳን የፓርቲ ፖለቲካ ቀርቶ የግል ሃይማኖትን እንኳ ለማራመድ ምቹ አይደለም፤ ይሄን ውርደት ደግሞ እንደ አንድ ወጣት ተቀብሎ መኖር አግባብ አይደለም፤ ስለዚህ ኤርትራ ሄጄ፣ ከህዝባዊ ኃይሉ ጋር ለመቀላቀል ወስኛለሁ” ነበር ያልነው፡፡ ጥፋተኛ ነህ አይደለህም? ብለው በጠየቁኝ ጊዜም፣ “ሃገራችንን ለማዳን ድልድይ አፍርሰን፣ ህፃን ገድለን፣ ባንክ ዘርፈን መጣን የሚሉ ሚኒስትሮች ባሉባት ሃገር፣ ስርአት ይከበር ነፃነት ይምጣ ብሎ በረሃ ገብቶ፣ መታገል የፅድቅ ስራ እንጂ ሃጢያት ወይም ወንጀል አይደለም” የሚል ምላሽ ነበር የሰጠሁት፡፡ ያንን ያደረግነው ከንቅናቄው ጋር ስማቸው ተያይዞ የሚታሰሩ ሰዎች ደፍረው እንዲናገሩ ምሳሌ ለመሆን ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ “አዎ የድርጅቱ አባል ነኝ፣ አዎ ተዋግቼያለሁ” የሚሉ ተከሳሾች ቁጥር ተበራክቷል። ከመንግስት ውጪ ያሉ ሰዎች፤ ”አርበኞች ግንቦት 7 ሽብርተኛ ነው” ብለው እንዳያምኑ፣ ወደ ቀልባቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ነበር፤ በዚያ መልክ የእምነት ቃላችንን የሰጠነው። ሀገር ውስጥ ያሉ ተቃዋሚዎች ጭምር ከግንቦት 7 ጋር ላለመነካካት ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጉ ነበር፤ ያንን ባህል ነበር ለመስበር የፈለግነው፡፡ አርበኞች ግንቦት 7 ለህዝብ ነፃነትን ለማምጣት እንጂ ሃገር ለመዝረፍ ለማሸበር የተደራጀ የማፍያ ቡድን አለመሆኑን ህዝብ እንዲረዳው ነበር፤ ያንን ያደረግነው፡፡
በወቅቱ በሽብርተኝነት የተፈረጀው አርበኞች ግንቦት 7፤ በሀገር ቤት ምን ያህል በህቡዕ የተደራጀ ህዋስ  ነበረው?
የህቡ አደረጃጀት በባህሪው ሰፊውን መዋቅር አይገልጥም፡፡ አንድ ሰው ሊያውቅ የሚችለው፣ እሱን የመለመለውን ወይም ያደራጀውን አካል ብቻ ነው። ነገር ግን እስር ቤት ሆኜ ባየሁት ሁኔታ፣ ንቅናቄው በርካታ የህቡዕ አደረጃጀት እንዳለው ነው የተረዳሁት። ብዙዎች በህቡዕ አደረጃጀት ውስጥ ሆነው ብዙ ስራ እንደሰሩ መረዳት ችለናል፡፡ በፖለቲካ ድርጅት ውስጥ ያሉም የሌሉም በርካቶች የህቡዕ አደረጃጀቱ አካል እንደሆኑ ነግረውኛል፡፡ የመንግስት ኃላፊነት ላይ ያሉ ሰዎች ጭምር የአደረጃጀቱ አካል እንደነበሩ ለማወቅ ችያለሁ፡፡ እኛን ለመጠየቅ ይመጡ የነበሩ ሰዎችን ስመለከት፣ አደረጃጀቱ ሰፊ እንደነበር ተገንዝቤአለሁ። ሁለተኛው አሁን በግልፅ መንቀሳቀስ በጀመርንበት ወቅት ያስተዋልኩት ነው፡፡ በድርጅቱ ጉዳይ በቅርቡ ባካሄድናቸው የተለያዩ ውይይቶች ላይ የህቡዕ አደረጃጀት አካላትን ዝርዝር በየአካባቢው ስመለከት፣ አድማሱ ከጠበቅሁት በላይም የሰፋ እንደነበር ተረድቻለሁ፡፡ ከአዲስ አበባ ውጪ በተለያዩ ክልሎች አደረጃጀቱ በመሳሪያም የታገዘ ነበር፡፡
በመሳሪያ የታገዘ ነው የሚለው በማህበራዊ ሚዲያዎች አወዛጋቢ ሆኖ ሰንብቷል … ንቅናቄው፤ የራሱ አባል ያልሆኑትን አባሎቼ ናቸው ብሏል የሚል ወቀሳም ተሰንዝሯል፡፡… በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
“በክፍለ ሀገር ታጣቂ የነበሩ ሰዎችን የኔ ናቸው ይላል፣ በገንዘብ እየገዛ ነው” የሚሉ ሃሜቶችን እኛም እንሰማለን፡፡ ይህ ህዝብን መናቅ ነው። በገንዘብ ተገዝተሃል በሚል ህዝብን ለገንዘብ ያደረ አድርጎ ማሳነስ ነው፡፡ እኔ ባለኝ መረጃ፣ በክፍለ ሃገሮች የታጠቁ ኃይሎች ቀድሞም ቢሆን ከንቅናቄው ጋር ግንኙነት የነበራቸው ናቸው። ለምሳሌ ሊቦ ከምከም አካባቢ አረጋ ወይም መይሳው የሚባለውን አርበኛ እንዲሁም አንቃሽ ያለውን መሳፍንት የተባለ አርበኛን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ህዝቡ አሁን ለእነዚህ አርበኞች ክብር ለመስጠት እየተዘጋጀ ነው፡፡ አርበኞች ግንቦት 7 በገጠሩ ክፍል ነዋሪዎች ሰፊ የህቡዕ አደረጃጀት ነበረው። ከዚያ በመለስ ደግሞ በዱር በገደሉ ከሚታገሉ እንደ መሳፍንት ያሉ አርበኞች ጋር ሰፊ ግንኙነት ነበረው፡፡ እንደሚታወቀው አሁን ኤርትራ የሚገኘው ወታደራዊ ካምፕ ተዘግቶ፣ ወታደሮቹ ወደ ሃገር ውስጥ ገብተዋል። ቀጥሎ ደግሞ በየአካባቢው ያሉ አርበኞች ከህዝባቸው ጋር ይቀላቀላሉ፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ያህል የታጠቁ ኃይሎች ነበራችሁ?
ከዚህ ቀደም በድርጅቱ ዋና ፀሐፊ እንደተገለፀው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ5 ሺህ በላይ የታጠቀ ኃይል ነበር፡፡ መታወቅ ያለበት አርበኞች ግንቦት 7 ከውጭ የሚመጣ ድርጅት አይደለም። መሪዎቹና ሃገር ውስጥ ትግል ማድረግ ያልቻሉ ብቻ ናቸው የሚመጡት እንጂ የንቅናቄው ሰፊ አደረጃጀት የነበረው ሀገር ውስጥ ነው፡፡ እኛ የለውጡ አካል ነን ብለን ስለምናምን፣ በለውጡ ውስጥ ብዙ ድርሻ አለን እያልን ነው፡፡ ከውጪ የሚመጣ ድርጅትን ለመቀበል አይደለም ሽር ጉድ እያልን ያለነው፤እርቅን ለማብሰር እንጂ፡፡ ድርጀቱ ዋና መሰረቱ ሃገር ውስጥ ነበር፡፡ ይሄን ዛሬ ሁሉም ሊያውቀው ይገባል፡፡
አደረጃጀቱ የነበረባቸውን አካባቢዎች ሊነግሩኝ ይችላሉ?
በርካታ ናቸው፡፡ ከብዙ በጥቂቱ የአማራ ክልል አብዛኞቹ አካባቢዎች፣ ደቡብ ሃዋሳ፣ አርባ ምንጭ፣ ወልቂጤ፣ ሳውላ፣ ሃድያ፣ አዳማ፣ አሰላ፣ ቴፒን መጥቀስ እችላለሁ፡፡ በነገራችን ላይ መሪዎቹ ህዝባዊ ስብሰባ ከሚያደርጉባቸው አካባቢዎች መካከልም የተጠቀሱት አካባቢዎች ይገኛሉ፡፡ እነዚህ አካባቢዎች ላይ ጠንካራ መዋቅር አለን፡፡ መታወቅ ያለበት አንድ አካባቢ ላይ በርካታ አባላት ሊኖረን ይችላል፤ አንዳንድ ቦታ ጥቂት ሊሆኑ ይችላሉ፤ ነገር ግን ዋናው የሚሰራው ሥራ ጥንካሬ ነው፡፡ ጥቂት ሆነው ጠንካራ ስራ የሚሰሩ አሉ። መላው ኢትዮጵያ ላይ መዋቅር ነበረን ማለት ይቻላል፡፡
ንቅናቄው ወደ ፖለቲካ ድርጅት እንደሚለወጥ ተነግሯል፡፡ የለውጥ ሂደቱ እንዴት ነው የሚከናወነው?
እንግዲህ አርበኞች ግንቦት 7 ፓርቲ ሳይሆን ንቅናቄ ነው፡፡ ንቅናቄ ደግሞ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲፈጠር ጥረት ያደርጋል እንጂ ወደ ስልጣን ፉክክር አይገባም፡፡ አሁን በኤርትራ ካሉ የሠራዊት አባላት፣ ሃገር ቤት ካሉ ታጋዮች እንዲሁም በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ከሚገኙ አባላትና አመራሮች ጋር በተደረጉ ውይይቶች ላይ ከንቅናቄ ወደ ፓርቲነት መቀየር እንዳለበት ሃሳብ ተነስቷል፡፡ ወደ ፖለቲካ ድርጅትነት ተቀይሮ፣ በሃገሪቱ አንድ ጠንካራ፣ ለስልጣን ተፎካካሪ የሚሆን ፓርቲ ይመሠረታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከተቻለ በሃገሪቱ ውስጥ ያሉ ፓርቲዎችን አሰባስቦ እንደ ጥላ ሆኖ፣ አንድ ትልቅ፣ ገዥውን ፓርቲ ሊገዳደርና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሊገነባ የሚችል የፖለቲካ ድርጅት መፈጠር አለበት ከሚል ውሳኔ ላይ ተደርሷል።
አዲሱ የፖለቲካ ድርጅት ምን ዓይነት ርዕዮተ ዓለም ነው የሚከተለው?
ፓርቲው ምን አይነት ርዕዮተ ዓለም ነው መከተል ያለበት፣ ፖሊሲው ምን ይሁን የሚለውን የሚያዘጋጅ ኮሚቴ ተመርጦ እየተሰራ ነው፡፡ ምናልባት ከመሪዎችም ንግግር ተነስተን፣ የሶሻል ዲሞክራሲ አስተሳሰብ ያለው ድርጅት ነው የሚፈጠረው ብለን መገመት እንችላለን። በዜግነት ማንነት ላይ የተመሠረተ ፖለቲካ ነው ለኢትዮጵያ የሚያስፈልገው የሚለው ደግሞ እስከ መጨረሻው የሚታገልለት ዓላማ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ አንድነት የሚበጀው የዜግነት ፖለቲካ ነው፡፡ ከብሄር ማንነት ምን አገኘን? ከመራራቅ፣ በመሃከላችን ግንብ ከመገንባት በቀር ምን አተረፍን? የሚለውን ገምግመው፣ የተነሱ ታጋዮች ናቸው፤ በዚህ ድርጅት ውስጥ ያሉት፡፡ አርበኞች ግንቦት 7 በብሔር መደራጀት አይጠቅምም ይበል እንጂ አምነውበት የተደራጁ አካላት ትክክል አይደሉም አላለም፡፡ ለራሱ ያመነበትን ነው እያራመደ ያለው፡፡ በብሄር ከተደራጁ ኃይሎች ጋርም አብሮ ለመሥራት ብዙ ርቀት ተጉዟል፡፡ አሁንም የሚመሰረተው ድርጅት፣ ይሄን አብሮ የመስራት ጥረት ያስቀጥላል ተብሎ ይታሰባል፡፡
የአንድነት ኃይል ወይም በዜግነት ፖለቲካ ላይ የተመሠረተው ድርጅት፣ ወካይ ላጣው ህዝብ ወኪል ነው የሚሆነው፡፡ ይሄን አስተሳሰብ ለማስፋት ነው በቀጣይም እንቅሰቃሴ የሚደረገው። በብሔር መደራጀት ትርፉ መከፋፈል ነው፤ ከዚያ ይልቅ በዜግነት ላይ ተመስርቶ መንቀሳቀሱ የተሻለ ነው ብለን እናምናለን፡፡  

Read 5599 times