Monday, 10 September 2018 00:00

የአዲስ ዓመት እንግዳ ከሞስኮ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

ኢትዮጵያዊው የፍልስፍና ፕሮፌሰሩ ምን ይላሉ?

    • ጠ/ሚኒስትር ዐቢይን ከፕሌቶ « ፈላስፋው ንጉስ» ጋር ያመሳስሉታል
    • ግዴታውንና መብቱን የማያውቅን ዜጋ ነጻ ነው ማለት አይቻልም


     በፍልስፍና ሁለተኛና ሦስተኛ ድግሪያቸውን ከራሽያው ሞስኮ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ያገኙትና በተመረቁበት ዩኒቨርሲቲ ማስተማር የጀመሩት ኢትዮጵያዊው ፕሮፌሰር አንጌሳ ዱጋ ጫላ፤ ከፍልስፍና ሙያቸው ጎን ለጎን በዲፕሎማሲ መስክ በኤክስፐርትነት ለረዥም ዓመታት በመሥራት ልምድ ማካበታቸውን ይናገራሉ፡፡ አዲስ አድማስ ይህን ቃለምልልስ ያደረገው በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ወቅት በሞስኮ፤ ራሽያ ነው፡፡
   ግሩም ሠይፉ


     ጨዋታችንን  ከትውልድዎ-- አስተዳደግዎ--ትምህርትዎ--- ብንጀምርስ ----?
ከአዲስ አበባ 80 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ቱሉ ቦሎ ከተማ አካባቢ፤ ሶዶ ሊበን በሚባል ስፍራ ተወልጄ አደግሁ፡፡ ሰባት አመት እንደሞላኝ፣ የቄስ ትምህርት ጀምሬ ነበር። ላቀው ሰንደቄ የሚባሉ አስተማሪዬ ቄስ፣ ከጎንደር የመጡ ነበሩ፡፡ “ጎበዝ ተማሪ ነህና ትምህርትህን በደንብ እንድትቀጥል፣ ወደ ጎንደር ልውሰድህ፣ ጥሩ ቄስ ትሆናለህ” ብለውኝ፤ ይህንኑ ገብቼ ለአባቴ ብነግረው፣ በማግስቱ ከቄሱ ለይቶኝ ቱሉቦሎ ከተማ መንግስት ትምህርት ቤት አስገባኝ፡፡ እናም እድሜዬ ለትምህርት ደርሶ ቱሉ ቦሎ ፊታውራሪ ሐብተጊዮርጊስ አባ መቻል መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብቼ፣ እስከ 8ኛ ከፍል ተማርኩ፤ ከዚያም ወሊሶ ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ እስከ 11ኛ ክፍል ተምሪያለሁ፡፡ በእድገት በህብረት ዘመቻ በ1967 ዓ.ም ወልቂጤ ተመድቤ አገለገልኩ፡፡ ከወልቂጤ ከተመለስኩ በኋላ የ11ኛ ክፍል ትምህርቴን በወሊሶው ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ  ጨረስኩ፡፡ ያን ጊዜ በ11ኛ ክፍል የሚሰጥ ልዩ ፈተና ነበር፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ይገኝ የነበረው በእደማሪያም ትምህርት ቤት ለመቀላቀል ነበር፡፡ ከወሊሶ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣የተሰጠውን ፈተና አልፈን ወደ በዕደ ማርያም ትምህርት ቤት የገባነው አራት ልጆች ነበርን። በእደማርያም የመምህርነት ስልጠና የሚሰጥበትና መሰረት የሚያዝበት ትምህርት ቤት ሲሆን እዚያ ለመግባት የቻሉ ልጆች ማትሪክ ሁሉ ሳይፈተኑ በቀጥታ ለዩኒቨርስቲ ትምህርት ይበቁ ነበር፡፡ በአብዛኛው የታሪክ፣ ጂኦግራፊ፣ ሂሳብና ሌሎች ትምህርቶችን የማስተማር ዘዴ ሰልጥነህ በሰርተፍኬት ትመረቃለህ። የአስተማሪነት ሙያን ስለሚሰጥ በቀጥታ ወደ በመምህርነት መግባት ቢቻልም፤ እኔ ግን የዩኒቨርስቲ ትምህርቴን ለመቀጠል ወስኜ አካውንቲንግን ለመማር መረጥኩ፡፡ አካውንቲንግን የመረጥኩት የስራ እድል እንደማገኝበት በማሰብ ነበር፡፡ ይሁንና ምድባው ላይ እንድማር የተፈቀደልኝ በፍልስፍና ዲፓርትመንት ነበር፡፡ ፍልስፍና ከባድና ብዙም የስራ እድል ስለሌለው የሚፈለግ አልነበረም፡፡ በህብረተሰቡ ዘንድ ፍልስፍና መማርም እንደ ቅንጦት ይታይ ነበር፡፡ ፍልስፍና ትምህርቱን ብወደውም ሙያዬ ይሆናል የሚል ግምት ግን ከጅምሩ አልነበረኝም፡፡
በፍልስፍና ዲፓርትመንት ተመዝግቤ ትምህርቴን ከቀጠልኩ በኋላ ግን በደስታ ተከታተልኩት፡፡ ትምህርቱ በጣም የሚያስደስት ቢሆንም መምህራችን ዶክተር መሳይ ማርክ አሰጣጥ ላይ የመሰሰት አዝማሚያ እንደነበራቸው አስታውሳለሁ፡፡ ይህም ባህርያቸው በመስኩ ብዙ እንድንሰራ አስችሎናል፡፡ በኋላም እኛም በተራችን አስተማረቲዎች ሆነን ፈለጋቸውን ከሞላ ጎደል የተከተልን ይመስለኛል፡፡
ያኔ የሶሻሊዝም ርእዮተ ዓለም፣ በወጣቱ መሐል በመጠኑም ቢሆን ሰርፆ ስለነበር እኔም ይህንኑ ንቃተ ህሊና  እጋራ ነበር፡፡ ይህም ከፍልስፍና ጋር በተዘዋዋሪ መንገድ ዝምድና ስላለው በፊሎሶፊ ዲፓርትመንት ይሰጥ የነበረው ትምህርት እምብዛም እንግዳ አልነበረም ለማለት ይቻላል፡፡ እንደማስታውሰው በጊዜው  በ16 እና 17 ዓመት እድሜ ወጣቶች ሆነን፤  የማርክስ፣ የሌኒን፣ እንዲሁም ሌሎች የሶሻሊዝም ምሁራንና መሪዎችን መጻሃፍት በብዛት እናሳድድ ነበር፡፡ የኢህአፓ አባላትም ዲሞክራሲያ የተባለ ህትመት ያሰራጩ ነበር። ትልልቅ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ስለነበሩ ወጣቶች ጎራ ለይተው ይከራከሩ ነበር፡፡  አስታውሳለሁ በወሊሶ ሃይስኩል የነበረው እንቅስቃሴም ቀላል አልነበረም፡፡ በየጊዜው ተቃውሞዎችና ከመንግስት ጋር ግጭቶች ነበሩ፡፡ ብዙዎች የኢህአፓ ወይም  የመኢሶን አባላት ሆነው ይንቀሳቀሱ ነበር፡፡
በዚሁ የተነሳ በወሊሶ ከተማ  በሃይስኩል የማውቃቸው፣ ሰባት አብሮ አደጎቼና ጓደኞቼ፣ ኢህአፓ ናቸው ተብለው ተረሽነው፣ ሬሳቸው በወሊሶ ከተማ መንገድ ላይ ይታይ ነበር፡፡ እኔም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ወሊሶ ሄጄ የጓደኞቼን ሬሳ አንድባንድ ማየቴ ትዝ ይለኛል፡፡ በሐሰት “የህዝብ ጠላት” ተብለው የነበረበትን ሁኔታ እስከ ዛሬ ድረስ በጥልቅ ሃዘን አስታውሳለሁ፡፡  እነዚያ ወጣቶች ትግላቸው ለኢትዮጵያ ህዝብ ፍትህ፣ እኩልነትና ነፃነት ነበር፡፡ በተለይ የኢህአፓ ልጆች፤ ወታደራዊውን መንግስት ክፉኛ ይቃወሙ ነበር፡፡ ወታደር ህዝብን መጠበቅ እንጂ አገርን መምራት አይችልም የሚል አቋም ነበራቸው። ህዝባዊ መንግስት እንዲቋቋም ጥሪ ያደርጉ ነበር፡፡ አገሪቱን ወደ ትክክለኛ የእድገት አቅጣጫ የሚመራው፣ ምሁር መሆን አለበት የሚል ድምፅ ያሰሙ ነበር፡፡ ወታደራዊው መንግስት ግን እሮሮ የወለደውን የህዝብ ትግልና የለውጥ ጥያቄ፣ ከባለቤቱ ቀምቶ ወጣቱን ፈጀ። ሊገኙ የሚችሉ የትግል ፍሬዎችን የከለከለ መጥፎ እርምጃ ነበር፡፡ መኢሶን ከደርግ ወገነ፡፡ ኢህአፓ ደርግን በመሳርያ ታገለ፡፡ ወታደራዊው አገዛዝ በዚህ መንገድ ለውጥ ያመጡ ምሁራንን አጨፋጨፈ፤ራሱም ጨፈጨፈ፡፡ ይሄ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለዓለም የሚበቁ ወጣት ምሁራን ያለቁበት አሳዛኝ ክስተት ነው፡፡ በወሊሶ ከተማ ብቻ ሳይሆን በመላው አገሪቱ፣ ኢትዮጵያ  ምርጥ ልጆቿንና ንቁ ትውልድን ያጣችበት ወቅት ነበር፡፡
ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ  የፍልስፍና ዲፓርትመንት ቆይታዎ እንመለስ----?
 በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቴን ለመቀጠል ስመዘገብ፣ አንድ ላይ ፊሎሶፊ ዲፓርትመንት የገባነው 40 ልጆች ነበርን፡፡ በርግጥ የፍልስፍና ታሪክን ስናጠና ትምህርታችን ከማርክሲዝም ፈለግ አንፃር  ቢሆንም፤ ለማርክሲዝም አስተዋፅኦ ያደረጉ ታላላቅ ፈላስፎችን ለመማርና ለማወቅ ሞክረናል ፡፡ ፍልስፍና ትክክለኛ የሃሳብ ዘይቤን የምትማርበት መስክ ነው፡፡ እንደ ሳይንስ ሎጂክን የምትማርበት ጥልቅ ትምህርት በመሆኑ፣ ብዙ ማሰብንና  ማሰላሰልን ይጠይቃል፡፡ ፍልስፍና የአንዱን ወይም የሌላውን ቀኖናዊ እውቀት የሚቀበል ሳይሆን ሁሉንም መስክ የሚያስተናግድ በመሆኑ አመዛዝኖ፤ አስተያይቶና አነፃፅሮ ትክክለኛውን እውቀት የሚያስገኝ ነው፡፡ ፍልስፍና፤ከሃይማኖትና ከፖለቲካ አቋሞች የሚለየውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡
አስቀድመን ፍልስፍና ዲፓርትመንት የገባን 40 ተማሪዎች፤ ትምህርቱን ስንከታተል ቆይተን በመጨረሻ ግን በፍልስፍና ሙያ በ1973 ዓ.ም ከዲፓርትመንቱ የተመረቅነው 6 ልጆች ነበርን፡፡ ከመካከላችንም አራታችን  ተመራቂዎች ብቻ በዩኒቨርስቲው ውስጥ በአስተማሪነት ተመድበን ቀረን፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ ካምፓስ፣ ከ1973 እስከ 1978 ዓ.ም ድረስ በፍልስፍና ዲፓርትመንት፣ ለአምስት አመታት አስተምሬአለሁ፡፡ በፍልስፍና ከፈረንሳይ ተመርቆ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰው ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፍልስፍና ዲፓርትመንት በተገቢው መዋቅር እንዲጠናከር በማድረግ የሚጠቀስ ሲሆን እኛም ከተማርን በኋላ ተመርቀን በማስተማር መቀጠላችን የሱ ጅምር ውጤት ነበር፡፡ በዲፓርትመንቱ ሌሎች  የማስታውሳቸው ፈር ቀዳጅ የፍልስፍና መምህራን ውስጥ የፖለቲካል ፊሎሶፊ ምሁር የነበረው ደሳለኝ ራህማቶ፤ ፕሮፌሰር ክሎድ ሰምነር እንዲሁም በየጊዜው ከራሽያና ከምስራቅ ጀርመን የሚመጡ ምሁራኖችም በዲፓርትመንቱ በማገልገል አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፍልስፍና ዲፓርትመንት  ለአምስት ዓመታት ሲያስተምሩ ከቆዩ በኋላ ምን አዲስ ለውጥ መጣ----?
በ1978 ዓ.ም የድህረ ምረቃ የትምህርት እድል ከጀርመን ላይፕሲንግ ዩኒቨርሲቲ አግኝቼ ለመሄድ እየተዘጋጀሁ ሳለ፣ ከአንድ የፊሎሶፊ ዲፓርትመንት ባልደረባዬ ጋር ወደ ሶቭየት ህብረት ሄደን እንድንማር፣ ከዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፅህፈት ቤት በተፃፈ ደብዳቤ መሰረት ተላክን። በራሽያም በ1981 በማስተርስ ዲግሪ፣ በ1986 በዶክተሬት ዲግሪ ተመረቅያለሁ፡፡ ወደ አገሬ ለመመለስ እየተዘጋጀሁ ሳለሁ ግን በተመረቅሁበት ሞስኮ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የማስተማር እድል ተሰጥቶኝ  እስከ 1990 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲው ሳስተምር ቆይቻለሁ፡፡ በተመሳሳይ ዓመት ሰኔ ላይ በሞስኮ የኢትዮጵያ አምባሳደር ካሳ ገብረህይወት፣ የኤምባሲውን የዲፕሎማሲ ስራ እንድረዳ ጠየቁኝ። አገሬን ለመርዳት እፈልግ ስለነበር በቀረበልኝ ጥያቄ ተስማማሁና ሞስኮ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ውስጥ በኤክስፐርትነት ተመድቤም ለስድስት አመት አገሬን አገልግያለሁ፡፡ የተሰጠኝ ሃላፊነት በኤምባሲው በኩል የትምህርትና የባህል ጉዳይን  መከታተል ሲሆን ባለኝ እውቀት ሰራሁ፡፡ በተለይ ተዳክሞ የነበረውን በራሽያ የነፃ ትምህርት መጠቀሙ እንዲቀጥል በማድረግ፤ መንግስት ባይልካቸውም በግላቸው ወጭ ሸፍነውም ሆነ ስፖንሰር አግኝተው ወደ ራሽያ ለሚመጡ ኢትዮጵያውያን መንገድ በመከፍት ስለሰራን  ብዙዎች ኢትዮጵያውያን በዚሁ እድል ለመጠቀም ችለዋል፡፡
በ1996 ዓ.ም ላይ ግን በሞስኮ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት ጀነራል አሳምነው በዳኔ የሚባሉ ሰው፤ ያለ በቂ ምክንያት በጭፍን “የፖለቲካ አመለካከት ችግር አለብህ” በማለትና ዘር በመቁጠር፣ ከኤምባሲው እንድለቅ አደረጉኝ፡፡ ሰው በጎም ሆነ ክፉ ስራው ህይወቱን ሙሉ ይከተለዋል፤ በህይወት እያለም ሆነ ከህይወት በኋላ በዚሁ ተግባሩ ይመዘናል። በመሰረቱ በእኚሁ ጄኔራል የአምባሳደርነት ዘመን ሦስት የኤምባሲው ዲፕሎማቶች መንግስታቸውን ከድተው፣ ስራቸውን ለቀው፣ ወደ ሶስተኛ አገር የተሰደዱ ሲሆን ሁለት ኢትዮጵያዊ ሰራተኞች ደግሞ ያለ አግባብ ከስራቸው ተሰናብተዋል። እኔም ጉዳዩ እጅግ ያሳዘነኝ ከመሆኑም በላይ አገሬን በተቻለኝ ሁሉ የማገልገል ተስፋዬን ስላመነመነው ወደ ዩኒቨርስቲ ተመልሼ የማስተማር ስራዬን ቀጥያለሁ፡፡  በዩኒቨርሲቲ ከማስተማሬ ጎን ለጎን፣ በራሽያ የአፍሪካ ዲፕሎማቶች ህብረት አማካሪ ሆኜ እየሰራሁ በመሆኔ  በተለያዩ የአፍሪካ ኤምባሲዎች ውስጥ የመስራት እድል አግኝቻለሁ። እነሆ ላለፉት 20 ዓመታት የዲፕሎማሲንና የማስተማር ስራዎችን አጣምሬ ሳከናውን ቆይቻለሁ።
ከፍልስፍና እውቀትም ሆነ ከዲፕሎማሲ ሥራ አግኝቻለሁ የሚሉት ትልቁ ነገር ምንድን ነው?
በርግጥ ፍልስፍና እንደ ሙያ ቅንጦት ነው። ባለንበት ጊዜ  ከሌሎች የሙያ ዘርፎች አንጻር ሲታይ በህብረተሰቡ ውስጥ ያለው አስፈላጊነት በቂ ግንዛቤ ያገኘ አይመስለኝም። ስለዚህ የፍልስፍና እውቀት ጠቃሚነቱ ሊገመገም የሚችለው ከሚሰጠን ቁሳዊ ሃብት አንጻር ሳይሆን ተመርተንበት ከምንደርስበት የጥበብ (wisdom) ከፍታ ነው። ትልቁ የፍልስፍና መገለጫ፣ የተወሳሰበ ንድፈ ሃሳብነቱ ሳይሆን የእውቀቱ ተሸካሚ የሆነው ግለሰብ የእለት ተእለት ተግባርና ምግባር፣ የዚህ እውቀት ተጨባጭነትና (concrete) ህያው መከሰቻ ሲሆን ነው። ስለዚህ ፍልስፍና ባዶና ረቂቅ የሃሳብ መረብ ሳይሆን ፍልስፍናው ምርጫውና እምነቱ የሆነ ህያው ሰው የኑሮ ዘይቤና ተግባር ነው። ዲፕሎማሲ ከዓለም አቀፍ ግንኙነት ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነው። የዓለም አቀፍ ግንኙነት በህብረተሰብ እውቀት አወቃቀር ውስጥ ከፍተኛውን እርከን የያዘ ነው። ይህ መስክ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአገሮችንና የድርጅቶችን መስተጋብርና ይህም በአገራት እጣ ፋንታ ላይ የሚኖረውን ተጽእኖ የሚመለከት በመሆኑ እጅግ ወሳኝነት እንዳለው ለመገንዘብ ችያለሁ። በራሽያናበአፍሪካ በተለይም በራሽያና በኢትዮጵያ መካከል ያሉትን የዲፕሎማሲ ግንኙነቶች ታሪክ ወሳኝ እርከኖቻቸውንና የወደፊት አዝማሚያቸውን ለማጤን እየሞከርኩ ነው፡፡
ስለ ኢትዮጵያ የወቅቱ ሁኔታና አዝማሚያው ላይ ምን ይላሉ?
የአለም ታሪክ የሰው ልጅን የነጻነት እድገት ጉዞን ይሳያል። ሰዎች ከቤተሰቦችና ጉርብትናቸው እስከ አለማቀፍ ግንኙነቶች ድረስ በሚያደርጉት መስተጋብር ልምድ በመለዋወጥ፣ ስለ ራሳቸውና ስለ አካባቢያቸው የተሻለ እያወቁ ሲሄዱ፤ ከማህበራዊና ከተፈጥሮ ችግሮች፣ እራሳቸውን በግልም ሆነ በጋራ ነጻ እያወጡ ይሄዳሉ። ዳሩ ግን ለኔ ብቻ ባይነትንና ስግብግብነትን ለማሸነፍ ባለመቻላቸው፣ ሰዎች ያካበቱትን እዉቀትና የደረሱበትን የቴክኖሎጂ ጥበብ፣ ለጋራ ቁሳዊ ምቾትና ነጻነት ማረጋገጫ እንደ መጠቀም ፋንታ፣ ለግልና ለቡድን ምቾት ሲባል፣ ሌሎች መሰል ፍጡራንን ማጥቂያና ነጻነት መንሻ ሆኖ ሲያገለግል በብዛት እናያለን።
ኢትዮጵያ የዚህ የአለም የታሪክ ጉዞ አካል ናት። የአለም ህዝቦች አጠቃላይ ሂደት ተጓዳኝ ሆና፣ የጽድቁም ሆነ የኩነኔው ተካፋይ ናት። የአውሮፓዊያን ስግብግብነት ባስከተለው አፍሪካን የመቀራመት ሂደት እንደ ሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ኢትዮጵያ በውጭ ሃይል በቀጥታ ባትገዛም ድብቅ እጅ አዙር አሉታዊ ተጽእኖ እስከ ዛሬ ድረስ ለእውነተኛ የህዝቦችዋ ነጻነትና እድገት መሰናክል መሆኑ አልቀረም፡፡ አገራችንን ባጋጠሙዋት ፈታኝ ሁኔታዎች ሁሉ ላይ ከሞላ ጎደል የውጭ አሻራን መገንዘብ ይቻላል። ይህ ግን ችግሮቻችን ሁሉ መንስኤያቸው ከውጭ ነው ማለት አይደለም፣ ወይም የውጭ ግንኙነቶቻችን ሁሉ አሉታዊ ይዘት አላቸው ማለትም አይደለም። አገራችን ከአርባ አመታት በፊት ሶሻሊዝምን አውጃ 17 አመታት ስትንገላታ የቆየችበትና አንድ ብሩህ ወጣት ትውልዷን ያጣችበት ወቅት ነበር።
ቀጥሎም ከ27 አመታት በፊት አብዮታዊ ዲሞክራሲን አውጃ፣ ፌዴራል ስርአትን በመዘርጋት ለረዥም ዓመታት ታፍነው የቆዩትን የብሄር ብሄረሰብ ችግሮች ከሞላ ጎደል ለመቅረፍ ቢቻልም ስግብግብነት የወለደው የአገር ሃብት መቀራመትና ዘርን ለይቶ፣ ዜጎችን በጅምላ ማፈናቀል፣ መዝረፍና ማሳደድ ያስከተለው ህዝባዊ አመጽና ፍጥጫ፤ለብዙ ሺ ለጋ የኦሮሞና የአማራ ወጣቶች መታፈን፣ መታሰር፣ መገደልና መንገላታት ብሎም ለሚሊዮን ሰላማዊ ህዝቦች መፈናቀልና መሰቃየት ሰበብ ሆኗል።
ይህ የኢትዮጵያ ህዝብ ትግል በተለይም ቄሮ የኦሮሞ ወጣቶች ባሳዩት ቁርጠኝነትና መስዋእትነት አገሪቷን የሚያስተዳድረው ግንባር ጥፋቱን በይፋ እንዲያምን ከማስገደዱም በላይ የገዥው ግንባር አካል የሆነው የኦሮሞው ኦህዴድ አመራርና የአማራው ድርጅት አመራር፣ከህዝቡ ጎን እንዲቆሙና ሊደርስ ከሚችለው አደጋ አገሪቷን እንድያድኑ አስችሏቸዋል። በተለይ የቄሮ ትግል የወለደው ቲም ለማ የተሰኘው ቡድን በሰከነና ጥበብ በተመላው አሰራር የአገሪቷን ቁልፍ የስልጣን በትር ቢጨብጥም መፈታት ያለባቸው ችግሮች እጅግ ብዙና የተወሳሰቡ በመሆናቸው ጠንካራ የህዝብ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል።
እንደ አንድ የፍልስፍና ፕሮፌሰር፣ ለአገሪቱ የወደፊት እድገት ሊረዱ ይችላሉ የሚሉትን ፍሬ ሀሳቦች ቢነግሩን ---?
አገርን የሚያክል ግዙፍ አካል ቀርቶ በዕለት ተእለት የተግባር እንቅስቃሴያችን እንኳን አስበንና አቅደን ነው የምንራመደው፡፡ የመንግስት መሪም ያለ ራእይና ያለ ክንዋኔ እቅዶች፣ አገሪቱን ወደፊት ሊያንቀሳቀስ አይችልም። ትልቁ አላማና አገራዊ ራእይ መሆን የሚገባው፣ ፍትሃዊ ህብረተሰብን መገንባት ነው። ፍጹም የሆነ ፍትሃዊ ህብረተሰብ ባይኖርም፣ እንደ ራእይና የመንግስት እንቅስቃሴ መድረሻ፣ ግብ መቀመጥ መቻል አለበት። ለዚህ እውን መሆን መንግስት ለዜጎቹ ማረጋገጥ የሚገባው መርሆዎች፤ ነጻነት እኩልነትና ወንድማማችነት ናቸው። ነጻነት ግዴታንና መብትን በማወቅ ላይ ይመሰረታል። ግዴታውንና መብቱን የማያውቅን ዜጋ ነጻ ነው ማለት አይቻልም። ስለዚህም ነጻነትና እውቀት ተጓዳኞች ናቸው። ህዝብን በመሃይምነት ጨለማ ጋርዶ፣ ነጻ ነህ ማለት፣ በህዝብ መቀለድ ነው። ስለዚህም ነው መንግስት ለትምህርት ጥራትና ለሰፊው ህዝብ መዳረስ ቀዳሚ ትኩረት መስጠት ያለበት።
ከእውቀት ሌላ ለነጻነት መረጋገጥ ዋስትናው የህግ የበላይነት ነው። የዜጎችን ነጻነት ለማስጠበቅ፣ ህግና የህግ ተቋማት እራሳቸው ነጻ መሆን መቻል አለባቸው። የህግና የህግ ተቋማት የበላይነትና ነጻነት ራሱ፣ በመሪዎች ነጻ መሆን ላይ ይመሰረታል። በውጭ አገር መሪዎች ቅኝት የሚንቀሳቀስ ወይም ለተለየ ቡድን ልዩ ጥቅም ተገዥ የሆነ የአገር መሪ፤ ራሱ ነጻ ባለመሆኑ፣ እርሱ የሚመራት አገርም ሆነች ዜጎችዋ ነጻ ናቸው ማለት አይቻልም።
የእኩልነትን መርሆች በተመለከተ የዜጎችም ሆነ የህዝቦች እኩልነት ይሰፍን ዘንድ መንግስት የዜጎችን የፖለቲካ ተሳትፎ በተቻለ መጠን ማስፋትና ማበረታታት አለበት። ህዝብ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ   በአገሪቱ የፖለቲካ ህይወት ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ለማድረግና በነጻነት የፈለገውን ለመምረጥ ከቻለ፣ የመንግስት መሪዎች፣ የህዝብን ድምጽ ለመሰማትና ፍላጎቶቹን ለማከናወን ይችላሉ ማለት ነው። የዜጎችና የህዝቦች ፍላጎቶች አንድ ወጥ ባለመሆናቸው፣ መንግስት ልዩነቶችን አስታርቆና አማክሎ ለእኩል ተሳትፎ የፖለቲካ ምህዳርን ማስፋት አለበት። የፖለቲካ ፓርቲዎችና ድርጅቶች የቆሙለትን ህዝብ በሰፊው በማወያየት በህገሪቱ ፖለቲካ ሂደት ማሳተፍ መቻል አለባቸው። ለእኩልነት መርሆች መፋለስና ለፍትህ መጓደል አንዱና ዋነኛ ምልክት፤የሙስና መንሰራፋትና ባህል መሆን ነው። ስለዚህ ሙስናን በብቃት መዋጋት፣ ለፍትህ መስፈንና ለአገር እድገት አስፈላጊ ነው።
በህዝቦች መካከል ወንድማማችነትን ማጎልበትና በተከታታይ በዚህ ላይ እቅድ አውጥቶ መስራት፣ የሰላምና የአገር አንድነት ዋስትና ነው። ይህንኑ መርሆ በአለማቀፍ መስክም መተግበር አስፈላጊ ነው። የአለማቀፍ ግንኙነቶች መስክ እጅግ አስፈላጊና ወሳኝ በመሆኑ፣ መንግስት በዚህ ዘርፍ፣ በጥልቅ ጥናት የተደገፈ ሪፎርምና ማስተካከያዎችን ማድረግ አለበት። የአለማቀፍ ግንኙነቶች ታሪክና የዓለም አቀፍ ህግጋት ባለሙያዎችን አሰባስቦ ማሰራትና በብቃት ላይ የተመሰረተ የሀገርንና የህዝብን ጥቅምና ደህንነት የሚያስጠብቅ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መቀየስና መተግበር ወሳኝነት አለው። ሙያንና ብቃትን ብሎም ልምድን መሰረት ያደረገ የዲፕሎማቶችም ምደባ አስፈላጊ ሲሆን በተለይ ለግልም ሆነ ለዘር ጥቅም ሳይሆን ለሀገር ጥቅምና መልካም ገጽታ ራሳቸውን ያሳደሩ መሆናቸው መረጋገጥ አለበት።
ዋናው ጉዳይ በስግብግብነት ስሜት ሳይሆን በእውቀትና በአዋቂዎች መመራት ያስፈልጋል። መንግስት ለእውቀት ጥራትና ሰፊ ስርጭት ከፍተኛ ትኩረት መስጠት አለበት ሲባል፣ እውቀት እራሱን የቻለ ግብ ስለሆነ ሳይሆን ለህዝብ ህይወት መሻሻልና ለሃገር እድገት ፍቱን መሳሪያ በመሆኑ ነው። መንግስት ለህዝብ የሚያስብ ከሆነ መስተካከል ያለባቸውን ነገሮች የመስራት ሃላፊነት አለበት፡፡ ህዝብ ነፃነትና እድገት ይፈልጋል፡፡ ለዚያም ይታገላል፡፡ አንዱ የነፃነት መሰረት እውቀት ነው፤ ስለዚህ ወጣቱ ትውልድ ከልጅነቱ ጀምሮ በአግባቡ መማር አለበት፡፡ ታዳጊውን ትውልድ አለማስተማር ለመንግስት ትልቅ ወንጀል ነው፡፡ የተማረ ህብረተሰብ ወንጀል ከመስራት የሚቆጠብ፤ አገሩን በእውቀቱ የሚያሳድግና የሚያሰለጥን ነው፡፡ የእውቀት መከበርን ባህልን ማሳደግ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ስናይ የቆየነውና ያለፍንበት ታሪክ የተማረ ዜጋ የሚሳደድበት፤ የሚበደልበት፤ የሚሰቃይበትና የሚታሰርበት ነበር፡፡ አገሪቷን ሊመሩ፤ ሊያስተምሩ የሚችሉትን የአገሪቱ የትምህርት እንቅስቃሴ ውጤት የሆኑ ምሁራንን አስሮ ማንገላታትና ማዋረድ ተገቢ አልነበረም፡፡ መንግስት ምሁራንን እንደሙያቸው አሳትፎ መጠቀምና አገሪቱን ለማልማት እና ለማሳደግ መትጋት ይኖርበታል፡፡
ስለዚህም ምሁራን በየሙያ ዘርፎቻቸው ሁሉ ለህዝብ ኑሮ መሻሻልና በአገሪቱ ውስጥ ለፍትህ መረጋገጥን ንቁና ቀጥተኛ ተሳትፎ ማድረግ ሲገባቸው መንግስት በበኩሉ፤ለዚህ ሰፊ የምሁራን ተሳትፎ አመቺ ሁኔታዎችን መፍጠር አለበት ብዬ አምናለሁ። በአሁኑ ወቅት በተለይ የኦሮሞና የአማራ ምሁራን በአጠቃላይ በአገሪቱም ሆነ በህዝቦቻቸው ፊት ልዩ ሃላፊነት ያለባቸው ይመስለኛል። የምሁር ምሁርነቱ መለያ አብይ ጉዳይ ተጨባጭ ሁኔታዎችን በምክንያት አሰጣጥ ዘይቤ በመተንተንና ትክክልኛ አወቃቀራቸውን በማሳየት ብሎም የወደፊት አቅጣጫዎችን መጠቆም መቻሉ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ምሁር ሰብዓዊ ፍጡር በመሆኑና በማህበራዊ ኑሮ አወቃቀር ውስጥ ስለሆነ የሁኔታዎች ትንተናና የወደፊት አቅጣጫቸው ጥቆማ ከወገናዊነት ሙ በሙሉ ነፃ ሊሆን አይችልም፡፡ በተቻለ መጠን ግን በሳይንሳዊ የምክንያት አሰጣጥ ላይ ተመርኩዞ ነባራዊ አቋም መውሰድ ይጠበቅበታል፡፡ከሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች በላይ የኦሮሞና የአማራ ህዝብ ግንኙነቶችና መስተጋብሮችን በተገቢው በጥንቃቄ መያዝ የሁለቱ ህዝቦች ምሁራንና መንግስት ወሳኝ ሃላፊነት ነው፡፡
አዲሱ የኢትዮጵያ አመራር በተያያዘው የለውጥ እርምጃ ከቀጠለ፣ አገሪቱ ከተፈጥሮ ፀጋዋእና ከህዝቧ ብዛት አንፃር ከሚገባትና ከሚመጥናት ደረጃ ላይ ለመድረስ ተስፋ አላት ብዬ እገምታለሁ። አዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፤ በወጣትነት የእድሜ ክልል ያሉ፤ በቂና ዘርፈ ብዙ እውቀትና ልምድ ያካበቱ ሰው በመሆናቸው፣ ሚዛናዊ በሆነ አመራር አገሪቷን ከተዘፈቀችበት ችግር የሚያወጡዋት ይመስለኛል። እስካሁን ባሳዩት የአመራር ብቃትና ስልታዊ አካሄድ የአብዛኛውን የኢትዮጵያ ህዝቦች ድጋፍ ማግኘታቸው አይደንቅም። በሀገር መሪነት እስካሁን ባሳዩት ባህሪያት፣ የጥንቱ የግሪክ ተመራማሪ ፕሌቶ፣ በምናቡ ከሳለውና “ሪፑብሊክ” በተሰኘው መጽሐፉ ከቀረጸው «ፈላስፋው ንጉስ» ጋር ማመሳሰል ይቻላል። እናም ከልጅነታቸው ጀምረው ንጉስ እንደሚሆኑ የታያቸው ያለነገር አይሆንም፡፡

Read 1574 times