Print this page
Monday, 10 September 2018 00:00

ተቃዋሚዎች በአዲሱ ዓመት ላይ ተስፋቸውን ጥለዋል!

Written by 
Rate this item
(4 votes)

(2010 እና 2011)



            “ግማሹን ዓመት በጭንቀት፣ ግማሹን ዓመት በተስፋ”
               አቶ ተሻለ ሠብሮ (የኢራፓ ሊቀ መንበር)


     ኢትዮጵያውያን ዓመቱን ያሳለፉት በመስቀለኛ መንገድ ላይ ሆነው ነው፡፡ በአንድ በኩል ስጋት ያየለበት፣ በሌላ በኩል ደግሞ የተስፋ ጭላንጭል የታየበት ዓመት ነበር፡፡ በርካቶች ግማሹን ዓመት በጭንቀት፣ ግማሹን ዓመት በተስፋ ነው ያሳለፉት። ብጥብጦች የተስፋፉበት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀበት ዓመት ነው፡፡ የተፈጠሩ አሳሳቢ ሁኔታዎች መንግስትን ያስጨነቁት ሲሆን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝም በፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን ለመልቀቅ ተገደዋል፡፡
አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ደግሞ ማንም ባልገመተውና ባልጠበቀው መልኩ በርካታ ተስፋ ሰጪ ምላሾች መስጠታቸው ይታወቃል። የፖለቲካ እስረኞች መፈታት፣ የተሰደዱ ዜጎች ወደ ሃገር ቤት መመለስ፣ ህጐችን ለማሻሻል ጥረት መጀመሩ----ትልቅ የለውጥ ተስፋ ነው፡፡ እኛ ለብሔራዊ መግባባትና ለእርቀ ሠላም ብዙ ጮኸናል፡፡ አሁንም ይህ በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲፈፀም እንጮሃለን፡፡
በ2010 ዓ.ም ትልቅ ታሪክ ተሠርቶ አልፏል። ሁሉም በየራሱ የወረወራቸውን ጠጠሮች መደልደልና ማስተካከል ደግሞ ቀጣዩ የቤት ሥራ ነው፡፡ በ2011 ዓ.ም ቢያንስ ሦስት ጉዳዮች እንዲሆኑ እንመኛለን፡፡ አንደኛው፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በመጀመሪያው ሩብ ዓመት፣ ራሳችንን ፈትሸን መሰባሰብ አለብን፤ ከ60 እና 70 ፓርቲዎች ወደ 10 እና 15 ዝቅ እንድንል መስራት ይኖርብናል። ሁለተኛው፤ በዶ/ር ዐቢይ የተጀመረው ለውጥ ወደ ስር ነቀል ለውጥ እንዲሸጋገር እንጠብቃለን። የምንታገለው ለትራንስፎርሜሸን ሳይሆን ለሪፎርሜሽን ነው፡፡ ይህ ለውጥ ደግሞ ከአየር ላይ ወርዶ ተቋማዊ ሆኖ፣ መሬት መርገጥ አለበት። ሦስተኛ፤ ለውጡ አዲስ ሥርዓት ማምጣት አለበት፡፡ ይሄ የሚመጣው ደግሞ በምርጫ ነው። ስለዚህ በምርጫው ጉዳይ በ2011  ስር ነቀል ለውጦች እንዲመጡ መሥራት ያስፈልጋል። ሁሉም አካላት ለለውጡ ግንባር ቀደም መሆን አለባቸው፡፡ በአዲሱ ዓመት ህዝባችን ከስጋትና ከመስቀለኛ መንገድ ወጥቶ ወደ አስተማማኝ ሁኔታ እንዲሸጋገር ምኞቴ ነው፡፡


------------



               “አመራሮቻችን ከእስር የተለቀቁበት ዓመት ነበር”
                 አቶ ሙላቱ ገመቹ (የኦፌኮ ም/ሊቀመንበር


    የታሰሩ አመራሮቻችንና አባሎቻችን ከእስር የተለቀቁበት ዓመት ነበር - 2010 ዓ.ም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በ2009 ሃገሪቱ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ነበረች፡፡
ከ2010 አጋማሽ በኋላ ግን በሃገሪቱ ውስጥ ጥሩ ለውጥ እየተካሄደ ነው፡፡ አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ለዴሞክራሲ ቀና መሆናቸውን እያሳዩን ነው፡፡ ይህም ሃገሪቱ ተረጋግታ ህዝብ የሚያማክል መንግስት ማቋቋም እንደምንችል ተስፋ ሰጪ ነው። የተሻለውን ለውጥም በተስፋ እንድንጠባበቅ ያስቻሉ የለውጦች ጅማሮን ያየንበት ዓመት ነበር።
ቀጣዩ ዓመት ደግሞ ለለውጡ ተቋማዊነትና መሬት መያዝ የሚያስፈልጉ የህግ ማዕቀፎች የሚፈተሹበት፣ የሚዘጋጁበት፣ የምርጫ ቦርድ የሚቀየርበት፣ የፍትህ ተቋማት ሕገ መንግስቱን የሚያስከብሩ ብቻ የሚሆኑበት፣ ነፃ የፍትህ ሥርዓት የሚሰፍንበት ይሆናል ብለን እናስባለን፡፡ እኛም ጽ/ቤቶቻችንን በየቦታው ከፍተን፣ ህዝብን የምናደራጅበት ሁኔታ ይፈጠራል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡


-----------  


             “አዲሱ ዓመት በይቅር ባይነት ወደ ፍቅር የምንሸጋገርበት ነው”
               የሸዋስ አሰፋ (የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር)


     ያለፉት ሦስት ዓመታት ሁላችንም እንደምናውቀው፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ከአገዛዝ ወደ ዲሞክራሲ ለመሻገር እልህ አስጨራሽ ትግል ያደረገበት ነበር፡፡ 2010 ደግሞ በትግሉ የአገዛዙን ጉልበት የሰበረበት ነው ማለት ይቻላል፡፡ እስከ ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝብ መሪውን መርጦ አያውቅም፡፡ የትግሉ መጨረሻም በመረጥኩት መሪ ልተዳደር፤ እውነተኛ የስልጣን ባለቤት ልሁን የሚል ነው፡፡ በገዥው ፓርቲ በኩል የለውጥ ሃይሎች የወጡበት ዓመት ነበር፡፡ እነዚህ የለውጥ ኃይሎች ከህዝቡ፣ ከተቃዋሚዎች፣ ከአክቲቪስቶች ጋር እጅና ጓንት ሆነው፣ ለለውጥ የሰሩበት ታሪካዊ ሁነትን ያየንበት ዓመት ነበር ብሎ መናገር ይቻላል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ኃይለማርያም ደሣለኝ፤ በፈቃዳቸው፣ በህዝብ ጫና ስልጣን የለቀቁበት፣ አዲስ የለውጥ አመራር ወደ መንበሩ የመጣበት ዓመት ነበር፡፡ ምናልባትም ከ1966 በኋላ ጠ/ሚኒስትሩም የመንግስት ባለስልጣናትም ቶሎ ቶሎ የተለዋወጡበት፣ ዘርፈ ብዙ ለውጦች የታዩበት ዓመት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ፍቅርንና ይቅርታን የሚሰብክ፣ ለዜጐች የሚጨነቅ መሪ፤ ከዚያው ከኢህአዴግ ውስጥ የፈለቀበት ዓመት ነበር፡፡ በፊት መንግስት ክብር የነሳቸውን በተለያዩ አለማት የሚኖሩ ዜጐችን ክብር በመስጠት፣ ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ የተደረገበት፣ በርካቶች ከእስር የተፈቱበት ዓመት ነው፡፡
ይሄ ለውጥ የሁሉም ነው፡፡ የእከሌ ብቻ ነው ብሎ መናገር አይቻልም፡፡ በቀጣዩ አዲስ ዓመት ይሄን ለውጥ ተቋማዊ ቅርፅ ለማስያዝ መሠራት አለበት። አሁን ያለነው የለውጥና የሽግግር ሂደት ላይ ነው። ይሄ አስተማማኝ የሚሆነው በቦታው ትክክለኛ ሰው ሲቀመጥ፣ መዋቅራዊ ለውጥ ሲደረግና ለውጡ ተቋማዊ ሆኖ፣ በህግ ሲታሰር ነው፡፡ አዋጆችን፣ ህጐችን ማሻሻልና ሁሉም የተስማማባቸው፣ ለዲሞክራሲው አጋዥ የሆኑ ሕጐች ሲወጡ ነው ለውጡ አስተማማኝ የሚሆነው፡፡
ከዚህ አንፃር ቀጣዩ ዓመት ይሄን ተቋማዊ የምናደርግበት፣ ትክክለኛ ምርጫ ቦርድ፣ ትክክለኛ የፍትህ ሥርዓት፣ ነፃና ገለልተኛ የሚዲያ ሥርዓት የምንገነባበት ነው፡፡ የለውጡንና የሽግግሩን ሁለተኛ እርከን የምንፈፅምበት ዓመት ይሆናል ብለን ነው ተስፋ የምናደርገው። ህዝቡ ለውጥ ተደርጓል ብሎ ፊቱን ወደ ልማት የሚያዞረው፣ በድምፁ የመረጠውን መሪ ስልጣን ላይ ሲያስቀምጥ ብቻ ነው፡፡ እስከዚያው ለውጡን አሁን እንደምናየው፣ በዓይነቁራኛ እየተመለከተ ነው የሚቀጥለው፡፡ በአዲሱ ዓመት ደግሞ በይቅር ባይነት ወደ ፍቅር የምንሸጋገርበት፣ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የምናሰፍንበት ዓመት ይሁንልን የሚለው መልካም ምኞቴ ነው፡፡


-------------


                “ለኢትዮጵያ ህዝብ ትልቅ የተስፋ ዓመት ነው”
                  ዶ/ር በዛብህ ደምሌ (የመኢአድ ፕሬዚደንት)


     2010 ዓ.ም ብዙ የተስፋ ጭላንጭል የታየበት ዓመት ነበር፡፡ ድርጅታችን ላለፉት 26 ዓመታት ኢትዮጵያዊነትን፣ አንድነትን አቀንቅኗል፡፡ በዘርና በቋንቋ ላይ የተመሠረተ ፖለቲካ ለኢትዮጵያ ህዝብ አይበጅም በሚል ብዙ ትግል አካሂዷል፡፡ የትግላችን ፍሬ አሁን እየታየ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ስልጣን ከያዙ ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያዊነትንና አንድነትን ደጋግመው እያቀነቀኑ ነው፡፡ ማንም ኢትዮጵያዊ መብቱ እየተጠበቀ፣ በፈለገው አካባቢ መኖር እንደሚችል በየጊዜው እየተናገሩ ነው፡፡ እኚህ ጠ/ሚኒስትር ስልጣን እንደያዙ ያለ አግባብ የታሠሩ ፖለቲከኞችን እንዳሉ አምነው፣ የፖለቲካና የህሊና እስረኞችን እንዲፈቱ አድርገዋል፡፡ ይሄ በዚህች ሃገር ፖለቲካ ውስጥ ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው ጅማሮ ነው፡፡ እኛ በግለሰብና በህብረተሰብ መብት የምናምን ነን፡፡ ይሄን እምነታችንን የሚያጠናክር እንቅስቃሴ ነው። እርግጥ ነው አሁንም የሚቀሩ በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ ለምሳሌ፡- የሁሉም የለውጥ ግብ ማጠንጠኛ ለሆነው የምርጫ ጉዳይ ትኩረት እየተሰጠው አይደለም፡፡ በቀጣይ ኢህአዴግ ከሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በመሆን የምርጫ ቦርዱ በሚቀየርበትና እንደገና በሚደራጅበት ሁኔታ ላይ መስራት አለበት፡፡ የሰብአዊ መብት አከባበር በነፃና ገለልተኛ ተቋም መፈተሽ አለበት። አሁን ተቋቁመው ያሉ መሰል ተቋማት ባለፉት 25 ዓመታት፣ለህዝቡ የሰሩት ምንም ነገር የለም። የመንግስት ውግንና የነበራቸው ናቸው፡፡ ያለፈው ዓመት ግን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በታሪካዊነት የሚጠቀስ ነው - ልክ እንደ 1997፡፡
በቀጣይ ዓመት የኢትዮጵያ ህዝብ ለራሱ የተሻለውን ነገር ያመጣል የሚል እምነት አለኝ።  እኛም ባለን አቅም ሁሉ ለኢትዮጵያ ህዝብ ተግተን እንሰራለን፡፡ በሠላም ጉዳይ በከፍተኛ ደረጃ መሰራት አለበት፡፡ 2011 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ህዝብ ትልቅ የተስፋ ዓመት ነው፡፡ ወደተሻለ ለውጥ የምንሸጋገርበት ይሆናል ብዬ እገምታለሁ፡፡ አዲሱ ዓመት መንግስት የበለጠ ለዲሞክራሲ የሚሰራበት እንዲሆን እመኛለሁ፡፡


------------------


                 “የበለጠ የመግባባት ዓመት እንዲሆንልን እመኛለሁ”
                   ዶ/ር ጫኔ ከበደ (የኢዴፓ ፕሬዚደንት)

     ያለፈው 2010 ዓ.ም ሃገሪቱ ካለመረጋጋት ወደ አንፃራዊ መረጋጋት የተሸጋገረችበት ዓመት ነው። በተለይ አዲስ ጠ/ሚኒስትር ያገኘንበት ዓመት ነበር። አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ደግሞ በይቅርታ፣ በፍቅርና በመደመር መርህ ብዙ ገንቢ ሥራዎች አከናውነዋል።
ከምንም በላይ ኢትዮጵያዊነትን አግዝፈው የተናገሩበት፣ በህዝቡ ላይ ለተሠሩ በደሎችም ይቅርታ የጠየቁበት ዓመት ነበር። ኢህአዴግ ከመነሻው የነበረበትን ስህተት አርሞ፣ በአዲስ አሰራር ለህዝቡ ጥያቄ ምላሽ እየሠጠ፣ ለለውጥ የተዘጋጀበት ዓመት ሆኖ ነው ያለፈው። ይህ ሁኔታም ለኢትዮጵያ ህዝብ እርካታ የሰጠና አብዛኛው አካባቢ የተረጋጋበት ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር በ2010 የሄድንበት ርቀት፣ ለህዝቡ ትንሽም ቢሆን እፎይታ የሰጠ ነው፡፡  
ኢዴፓ እንደ ድርጅት ባለፉት አመታት፣ ለሃገሪቱ ብሔራዊ መግባባት ያስፈልጋል ሲል ነበር የኖረው። ይህ ብሔራዊ መግባባት በ2010 በከፊልም ቢሆን ተጀምሯል፡፡ ከዚህ አንፃር አኛም በዓመቱ የተወሰኑ ፕሮግራሞቻችን በተለይ የብሔራዊ መግባባት አጀንዳችን ወደ ተግባር የወረደበት ዓመት ነበር። የፖለቲካ ድርጅቶችም ተቀራርበው እንዲነጋገሩ ለውጡ እድል በመፍጠሩ፣ ዳርና ዳር ቆመን የነበርን የፖለቲካ ኃይሎች፣ ለጋራ ምክክር መቀመጥ የቻልንበት ዓመት ነበር፡፡
በቀጣይ 2011 ዓ.ም ደግሞ የሠላም፣ የአንድነት፣ የፍቅር ሂደቱ ወደ መሬት ወርዶ፣ የሃገሪቱ አጠቃላይ የአሠራር ሂደት የሚለወጥበት መሆን ይገባዋል፡፡ ለዴሞክራሲ እንቅፋት የሆኑ ሕጐች፣ አዋጆች እንዲሁም ፖሊሲዎች የሚሻሻሉበት ሁኔታም ይፈጠራል የሚል ተስፋ ነው ያለን፡፡
ከምንም በላይ የምርጫ ህጉና የምርጫ ሥርዓቱ ከተስተካከለና የፖለቲካ ምህዳሩ ሁሉን አሳታፊ ሆኖ ከተዋቀረ፣ በ2012 የሚካሄደው ብሔራዊ ምርጫ ያለ ምንም እንከን የሚፈፀምበት ሂደት ይኖራል፡፡ ይሄ ስራ በሰፊው የሚሰራበት ዓመት ሊሆን ይገባል። ሌሎች የዴሞክራሲ ተቋማት፣ የፍትህ አካላት ነፃና ገለልተኛ ሆነው መደራጀት አለባቸው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ይሄ የተጀመረው ለውጥ ግቡን እንዲመታ፣ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ፣ ሂደቱን በቅርበት መከታተል ይገባዋል፡፡ እርቅና ብሔራዊ መግባባትም መፈፀም አለበት፡፡ 2011 ዓ.ም የበለጠ የመግባባት ዓመት እንዲሆንልንም እመኛለሁ፡፡

Read 3272 times
Administrator

Latest from Administrator