Monday, 10 September 2018 00:00

ይሄ ሌላ እንቁጣጣሽ ነው!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(0 votes)

 “--እጅ ለእጅ ተያይዘን አዲሱን ዓመት ሆያ ሆዬ እንላለን፡፡ ፊታችን ያለው አዲስ ዓመት አድማሳት - ፍቅርን ይተርካሉ፤ ነፃነትን ያውጃሉ፡፡ በእርግጥም ይህ ሌላ እንቁጣጣሽ ነው፡፡ የፍቅር እንቁጣጣሽ!!--”
       
    አዲስ ዓመት የሚባለው - ምድር የለበሰችውን አሮጌ ጨርቅ አውልቃ፣ አዲስ አደይ አበባ ገላዋ ላይ ስትነሰንስ ነው፡፡ ጥቀርሻ የለበሱ፣ አፈር የመሰሉ ወንዞችዋ፣ ወለል ብለው ጠጠራቸውን ሲያስቆጥሩ፣ ሰማይ የነሰነሰብንን ጢስ፣ የደሩብንን ብርድ ልብስ ይዞ ጠርግ ሲል፤ ችቦዋችንን ለኩሰን ሆያ ሆዬ እንላለን፡፡ ልጃገረዶችም የክት ልብሳቸውን ለብሰው፣ በእንቁጣጣሹ “አበባዬ ሆይ!” እያሉ በሚጥም ዜማ ተስፋችንን ያስጌጡታል፡፡
ይሁንና ሁሉም አዲስ ዓመት አንድ አይነት አይሆንም!... አንዳንዱ ፍርሃትና ስቃይ፣ እንባና ሰቀቀን ይዞ ይመጣል፡፡ ባብዛኛው ሣቅና ደስታ፣ ምኞትና እርካታ ተሞልቶ ብቅ ይላል፡፡
ገጣሚው ስንኝ የሚቋጥረው፣ ሠዓሊው ብሩሽ የሚያነሳውም ለዚያ ነው፡፡ ዜማ - ዜማ የሚያሰኘውም፣ ይህ ከተፈጥሮ ጋር የተቆራኘ ምትሀት ነው፡፡ ሰማይና ምድር ሲያጌጡ፣ የሰው ልጅ በችቦ የማጀቡ መነሻም ይህ ይመስለኛል፡፡
በ2009 ዓ.ም የታተመው “የማለዳ ድባብ” ስለ እንቁጣጣሾች ልዩነት አንዳች ነገር ሹክ የሚለን ይመስላል፡፡ አንዳንዴ ድባቴ ውስጥ ሆነንና ቀን ከፍቶብን ሳለ፣ ድንገት እንደ ሌባ ከተፍ ሊልብን እንደሚችል ይጠቁማል፡፡
አገር እንቁጣጣሽ
የ’ዳ ክንድሽ አቅፎኝ
ያሳር ክንፍሽ አቅፎኝ
እንቁሽን ስመኘው፣ ጣጣሽ ብቻ ተርፎኝ
መኖርን ስፈራ፤ መሞትን ስፈራ
ካየር ንብረት በቀር፣ ንብረት ሳላፈራ
ወሩ ተጠራቅሞ፣ አንድ ደርዘን ሞልቶ
እንደባለጌ ልጅ፣ በሩን በግሩ ገፍቶ
አዲስ ዘመን ገባ፤
አንዳንዴ አዲስ ዘመን እንዲህ ነው፡፡ ደስ የማይልበት አጋጣሚ አለ፡፡ በደም ሊነከር፣ በእንባ ሊዘፈቅ ይችላል፡፡ ያለፈው ዓመት እንቁጣጣሽ ስሜትና መልክ ደግ አልነበረም፡፡ አደይ አበባው በሣቅ፣ ሳቂታው ሰማይ በዝማሬ አልታጀበም፡፡ የችቦው ብርሃን ወደ ልባችን አልዘለቀም፡፡ ታላቅ ፍርሃት ነበር፡፡ እንደ በዕውቀቱ ግጥም፤ እንደ ስንኞቹ ሽሙጥ ነበር- ዕን-ቁጣጣሹ!
አበባ አለቀሰ - አለቀሰ ልጄ
እንደቅጠል ረግፎ ጠውልጐ ከደጄ፤
አለቀሰ አምርሮ
ውስጡን አሳርፎ
ደምስሩን ገትሮ-
አንጀቱን አንፍሮ
አለቀሰ አበባው - ያይኑ ምንጩ ደርቆ
እምባው ደም ተሾመ ደምነቱን አውቆ፤
ድፍን ክረምት በጋ
ድፍን ቆላ ደጋ
ድፍን ዐመቱን
ተረታ ልቡን
ታመመ ጭንቁን
አበባው ተጐዳ - መሶቡ ደረቀ
ከታች ዕድሜ ከዳው - ከላይ ቅስሙ አለቀ፡፡
ለአዲስ ዘመን ተስፋ፣ ለዐውዳመት ፌሽታ፣ የሰው ልጅ የነገ ስንቁን ይቋጥራል፡፡ ያዘነ ይፅናናል! ይህ ሁሉ ግን ከሀገር ሠላም ጋር ይያያዛል፡፡ ከመንግሥት መረጋጋትና ማረጋጋት ጋር አይነጣጠልም፡፡
ያምናው መስከረም፤ ቀለሙ የፈዘዘው፣ ፍርሃቱ የነገሰው ለዚያ ነበር፡፡ ሀገር በእንባ ቦክታለች። በሰቀቀን ተቀፍድዳለች፣ በያለበት ነውጥ ነበር፡፡ የለውጥ መንገዶች ጠብበዋል፡፡ መንግሥታችንም እንደለመደው ቅዥት ውስጥ ገብቶ ይዳክራል፡፡ ጠመንጃውን እየወለወለ ይዘፍንብናል፡፡ ዘፈኑ እንደ ሁሌው ስድብ ነው፡፡ ሞት አንገሽግሾን፣ ነፃነት ርቦን ሳለ፤ “በረከት” ይዘፍንልናል፡፡ ያስቸኳይ ጊዜ እዋጅ ነጋሪት ይጐስማል፣ የልማት ከበሮ ይደበድባል፡፡
ስለዚህ ችቦዋችንን ጠልተን፣ ሆያ ሆዬ ተናንቆን፣ ቄጤማችን እንደ ሾህ ኮስኩሶን አሳለፍን፡፡ ተፈጥሮ እንደ ቀድሞዋ፣ ቀሚሷን ብታጠልቅም የኛ ልብ ከስሏል፡፡ የኛ ሣቅ  ተነጥቋል፡፡ ቅኔዎች ከከንፈራችን ሸሽተዋል፡፡ መዝሙራችን “አባታችን ሆይ በሰማያት የምትኖር!” ብቻ ሆነ፡፡ መንገዱ ጠፋን፡፡ ሬዲዮው ይዘፍናል፣ ቴሌቭዥኑ ያቅራራል፡፡ የአምናው እንቁጣጣሽ እንደዚያ ነበር! እንደ ቀድባ፡፡
የመስቀል ወፍና የአደይ አበባ
ቀጠሮ እንዳላቸው መስከረም ሲጠባ
ማን ያውቃል?
--- አላልንም፡፡ የጋሽ ፀጋዬ ገብረመድህንን “በራ የመስቀል ደመራ” አላወራነውም፡፡
የአደይ አበባ ችቦ እየፋመ፣ እየጋመ
ኢዮሃ እያስገመገመ እየተመመ
የመስቀል ደመራ
በራ፡፡
በራ የአዲስ ዘመን ችቦ
በመስከረም ሰብል አብቦ
ከዋክብቱ ፈነጠቀ
ርችቱን አንፀባረቀ
ተኳለ አዲስ ደመቀ
መስኩን በቀለም አዝርእት፣ በጥበብ አጥለቀለቀ
ሸለቆው ተንቆጠቆጠ፣ ተራራው አሸበረቀ
ኢዮሃ ኢዮሃ አበባዬ! ምድር ሕይወት አፈለቀ፡፡
እያልን በቀድሞ ስንኞች ሠራዊት ምድሪቱን አላጀብናትም፡፡ ከፈለገች ምድር ለራሷ ትሳቅ፣ ቀሚሷን ነስንሳ ትዘምር ብለን በራችንን ዘጋን። አደይ አበባዎች በተራራ ላይ ነድደዋል፣ የኛም ልቦች ከደረታችን ሥር ከስለዋል፡፡ ትዝታው እንቁጣጣሻችን ያ - ነበር፡፡ መንግሥታችን ግን ነቢይ ሆኖ “መጪው ዘመን የከፍታ ነው!” ሲል አሽሟጠጥን፡፡
የዘንድሮ እንቁጣጣሽ ደግሞ ሌላ እንቁጣጣሽ ነው፡፡ ዐውደ ዓመት የበዛበት 2010 ዓ.ም ሀገር ከሀገር ጋር፣ ሕዝብ ከሕዝብ ጋር የታረቀበት፣ እሥረኞች ከወህኒ የወጡበት፣ ስደተኞች ሀገራቸው የገቡበት ዓመት ነው፡፡ የፖለቲካው ዕጣን አየሩን አውዶ፣ ለውጥ የነገሰበት! አደባባዮች በእንግዳ ቅበላ የተፍነከነኩበት ነው፡፡ ለዓመታት ሀገራቸውን ጥለው የተሰደዱ፤ ሞት የተፈረደባቸው ሳይቀር ሀገራቸው ጠርታቸው፣ ሀገራቸው ጋብዛቸው እየተመሙ ነው።
ያምናው ፍርሃት የለም፡፡ ያምናው ልቅሶ የለም። ልንጠፋ ነው ማለት ቀረ፡፡ ነፍሳችንን ሊነጥቁ ያሰፈሰፉ አፈ ሙዞች ወደ ኋላ ተመልሰዋል፡፡ ምላሳቸውን ከትተዋል፡፡
ይልቅስ አደባባዮች በ”አሸባሪዎች” ፎቶ ተሞልተዋል፡፡ በእንኳን ደህና መጣችሁ ምኞቶች - ሰክረዋል፡፡ ዓይኖች ማመን ያቃታቸውን ትዕይንቶች አስተናግደዋል፡፡ “አፈሯን አይረግጡም!” የተባሉ ኢትዮጵያውያን አንገታቸው ላይ ጉንጉን አበባ ጠልቆ፣ ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ ዘምሮ ተቀብሏቸዋል። የዘንድሮ እንቁጣጣሽ አደይ አበባ ብቻ አይደለም፤ የሕዝቡ ሣቅም ተቀይሯል፡፡ ከልቡ እየሳቀ ነው፡፡
የደበበ ሠይፉን “ያቺ ሟች ቀን” እያልን፣ አምና ላይ እንገጥምባታለን፡፡
ጊዜ ሆይ
ሕያው ጊዜ ሆይ
በማይሞተው ገፅህ ላይ
የወጣችን ያቺን ቀን
ያቺን -
የነቀርሳ እባጭ መሳይ
የመርዝ ከረጢት ሥራይ
ሥሯን በርብረህ ንቀል
ዕጯን ፈንግለህ - ግደል፡፡
ትብነን
አይኑራት አምሳያ፤
ትምከን
ወራሽ አይኑራት ዝርያ፣
የሰውን ልጅ ብሩህ ጉዞ
የሰውን ልጅ ብሩህ ዕጣ
በጥላዋ ሳታዳምን፣ በግንባሯ ሳታነጣ፡፡
የአምናዋን እንቁጣጣሽ እየረገምን፣ በዘንድሮዋ እየዘመርን፣ የተስፋ እሸት ቀንጥሰናል፤ የሣቅ እንጐቻ ቀምሰናል - ስንል መዝሙራችን ፍቅር፣ ይቅርታና አንድነት ነው፡፡ ደመራችን ኢትዮጵያዊነት፣ ችቦዎቻችን ፍትህና ርትዕ ናቸው፡፡
የዘንድሮ እንቁጣጣሽ፤ “አሸባሪው ኦነግ፣ አሸባሪው ግንቦት ሰባት” ሳይቀሩ፣ ታሪካቸው ተቀይሮ፣ ኢትዮጵያ የምትባለውን ታቦት አጅበው የሚያነግሱባት ናት፡፡ የዘንድሮ እንቁጣጣሽ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከተመልካች የታረቀበት፣ ፋናና ዋልታ ሕዝባዊ እስትንፋስ የሆኑበት ነው፡፡ ተሳዳቢዎች መራቂ፣ የሞት ማቅ የለበሱ የፌሽታ ቬሎ የለበሱበት ነው፡፡ ከተስፋው ተራራ ጫፍ ላይ ነን፡፡ ችቦዋችን ሲነድድ፣ ሆያ ሆዬው ሲጦፍ፣ አድማሳት ሲያስተጋቡ፣ ልጃገረዶች በጣፋጭ ዜማቸው፡-
አበባዬ ሆይ - ለምለም
አበባዬ ሆይ - ለምለም
ባልንጀሮቼ -
ቁሙ በተራ -
እንጨት ሰብሬ
ለምለም
ቤት እስክሠራ፡፡
እያልን----የሀገራችንን አቅመ ደካሞች ቤት በሕብረት የምንሠራበት ነው፡፡ አረጋዊያን የሚጦሩበት፣ህመምተኞች አስታማሚ የሚያገኙበት፣ ሁላችን ከድህነት ለመውጣት የምንፋለምበት ነው፡፡
የዘንድሮ እንቁጣጣሽ - ሁሉም ኢትዮጵያዊ እጅ ለእጅ ተያይዞ፣ በጋራ ልማት፣ ለጋራ ዕድገት የሚሠራበት ነው፡፡ በፍቅርና በመደመር ፍልስፍና የሚመራን መሪ አግኝተናል፤ የሚራራልን ጠቅላይ ሚኒስትር መጥቶልናል፡፡
ድሆችን መርዳት፣ መተጋገዝ፣ ሌብነትን መፋለም - የሚያስተምረን ጀግና ሀገራችንን ይዟል፡፡ ይህኛው እንቁጣጣሽ - ዐቢይ አህመድ የለኮሰውን ችቦ ይዞ መሮጥ፣ አንድ ላይ ሆያ ሆዬ ማለት፣ የፍቅር አበቦች መነስነስ የሚቻልበት ነው፡፡ አርአያ የሚሆኑ መሪዎች፤ ሀገራቸውን ብቻ ሳይሆን ዓለምን ይለውጣሉ። አሁን ከበሮዋችንን እየደለቅን - “አበባዬ ሆይ!” እንላለን፡፡ አሁን ቤተ መንግሥቱ አያስፈራም፤ አሁን ፌዴራል ፖሊሱ ጥይት አያጤስብንም፡፡ እጅ ለእጅ ተያይዘን አዲሱን ዓመት ሆያ ሆዬ እንላለን፡፡ ፊታችን ያለው አዲስ ዓመት አድማሳት - ፍቅርን ይተርካሉ፤ ነፃነትን ያውጃሉ፡፡ በእርግጥም ይህ ሌላ እንቁጣጣሽ ነው፡፡ የፍቅር እንቁጣጣሽ!! ለመላው የአገሬ የጦቢያ ህዝብ መልካም እንቁጣጣሽ ተመኘሁ! ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!    

Read 1198 times