Print this page
Saturday, 01 September 2018 15:49

የ21ኛው ዓለም ዋንጫ ልዩ ማስታወሻ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)


    የእኛ ሰዎች በሞስኮ
ካፌ አቬኑ የኢትዮጵያውያንና የአፍሪካውያን  መሰብሰቢያ
ባለፉት ሳምንታት ባቀረብኳቸው የ21ኛው የዓለም ዋንጫ ማስታወሻዎች ላይ እንደገለፅኩት ወደ ራሽያ የተጓዝነው ሦስት ኢትዮጵያዊያን የስፖርት ጋዜጠኞች፤ እኔ ከአዲስ አድማስ፤ ዳዊት ቶሎሳ ከሪፖርተርና አለምሰገድ ሰይፉ ከሊግ ስፖርት ጋዜጣዎች ነበርን፡፡ በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽኖች ማህበር (ፊፋ) ኦፊሴላዊ ግብዣ ታላቁን የስፖርት መድረክ በየሚዲያ አውታሮቻችን ለመዘገብ ነው፡፡  ሞስኮ ስንገባ 21ኛው የዓለም ዋንጫ በሉዚሂኒኪ ስታድዬም በአስተናጋጇ ራሽያና ሳውድአረቢያ መካከል በሚደረግ የመክፈቻ ጨዋታ ሊጀመር ከ48 ሰዓታት ያነሰ ጊዜ ቀርቶታል፡፡ በኳታር ኤርላይንስ የሞስኮው ዴሜዴዶቭ ዓለም አቀፍ ማረፊያ ስንደርስ   አቀባበል ያደረጉልን በራሽያ ከፍተኛ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ሁለት ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች ነበሩ፡፡  በራሽያ የሚማሩ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ማህበር የሚያገለግሉት ወጣቶቹ፤ በሞስኮ ከተማ ማረፊያ እንደሚያገኙልን በመግለፅ እንድናገኛቸው ቀጠሮውን ያመቻቸልን ደግሞ በራሽያ የተማረና እዚህ በአዲስ  አበባ የሚሰራ ድርጅት ነበር፡፡ ከኢትዮጵያ ወደ  ራሽያ  ደርሶ መልስ  የአየር ትኬቶችን በወኪልነት የቆረጠው ድርጅቱ የማረፊያችሁን ጉዳይ ለእኛው ተውት ብሎንም ነበር፡፡ ከዚህ ቀደም በሞስኮ በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ያደረገውን ድጋፍ አስታውስ ስለነበር በቃሉ መሰረት ድጋፍ እንደሚያደርግልን እምነት ነበረን፡፡ ለዚህ አገልግሎቱም በተለይ በሊግ ስፖርት እና በአዲስ አድማስ ጋዜጦች የድርጅቱን ማስታወቂያዎች አውጥተንለታል፡፡ በራሽያ ከኢትዮጵያ ተማሪዎች ጋር በአየር ማረፊያው ተገናኝተን ሻንጣዎቻችንና ሌሎች ጓዞቻችን እነሱ ባዘጋጁት መኪና  ጭነን ተሳፈርን፡፡  ከዴሞዴዶቭ አየር ማረፊያ ተነስተን 50 ኪሎሜትሮችን የተጓዝነው ሚክሉማካያ ወደተባለው ሰፈር ነበር፡፡ በጉዞው ላይ በራሽያ የሚገኙት ተማሪዎች  ማረፊያችንን እንዳመቻቸን ጠየቁን፡፡ እኛም ሲጠይቁን በድርጅቱ በኩል ይመቻቻል ስለተባለው ሁኔታ ነገርናቸው፡፡ የተወሰነ አለመግባባት ነበር፡፡ ማረፊያችሁን አዘጋጅላችኃለው ቢልም ምንም አይነት ግልፅ ግንኙነት ከተማሪዎቹ ጋር አልነበረውም፡፡
ሞስኮ የገባን ቀን  መድረሻችን በሩሲያ ከሚገኙት ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ በሆነው ሉምምባ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ የሚገኘው የኢትዮጵያውያንና የአፍሪካውያን  መሰብሰቢያ   ነበር፡፡ ካፌ አቬኑ የሚባል ሲሆን በሉምምባ ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች መኖርያ አፓርትመንቶች ባሉበት ቅጥር ግቢ ውስጥ ይገኛል፡፡  የካፌ አቬኑ ባለቤትና መስራች ኢትዮጵያዊው  አቶ ተፈራ የኋላዋሴን  በሞስኮ ከተማ ሳገኛቸው ለሁለተኛ ጊዜ ነበር፡፡ ከአምስት አመታት በፊት በ2013 እኤአ ሞስኮ ባስተናገደችው 14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ተዋውቀናል፡፡ ስለህይወት ታሪካቸው፤ ስለራሽያ ቆይታቸው እና ሌሎች ጉዳዮች ሰፋ ያለ ቃለምምልስ አድርጊያቸውም በአዲስ አድማስ ጋዜጣ አቅርቤዋለሁ። አቶ ተፈራ ትውልዳቸው በባህርዳር አካባቢ በሚገኝና “መሸንቲ” የተባለ የገጠር መንደር ነበር፡፡ በቴክስታይል እና በማይኒንግ ኢንጅነሪንግ ሁለት ዲግሪዎችን የሰሩ ቢሆንም አሁን ዋንኛ ስራቸው በሞስኮ ከተማ የሚገኘውን ‹‹ካፌ አቬኑ›› በማናጀርነት ማስተዳደር ነው፡፡  በራሽያዋ ሞስኮ ከተማ እየተማሩ እና እየኖሩ ከ32 ዓመታት በላይ የሆናቸው ከራሽያዊት ጋር ትዳር መስርተው ሦስት ልጆችን አፍርተዋል፡፡
ካፌ አቬኑ በሞስኮ ከተማ ከሚገኙ የኢትዮጵያውያን መናሐርያዎች ዋንኛው ነው፡፡ ካፌው ከተለያዩ የአፍሪካ አገራትና ሌሎች የዓለም ክፍሎች ለከፍተኛ ትምህርት ሉምምባ ዩኒቨርስቲን የተቀላቀሉ ተማሪዎች መኖርያ አፓትመንቶች ቅጥር ግቢ ውስጥ መገኘቱ ልዩ ያደርገዋል። ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን እንዲሁም ሞስኮ በትምህርትም ይሁን በስራ የመጡ አፍሪካውያን ይገናኙበታል፡፡ የኢትዮጵያውያንን ምግብ ጨምሮ የበርካታ አፍሪካ ሃገራትን ምግብ በማዘጋጀትም ይታወቃል፡፡ ባለፉት 30 ዓመታት በራሽያ የተማሩ እና ነዋሪ የሆኑ  ኢትዮጵያዊያን  የአገራቸውን ምግብ ለመመገብ፤ ስለአገራቸው ናፍቆት እና ወቅታዊ ሁኔታ ለመጨዋወት፤ ስለራሽያ ኑራቸው ለመመካከር  በካፌ አቬኑ ይገናኛሉ፡፡ ሌሎች አፍሪካውያንም በተለያዩ ምክንያቶች የሚሰባሰቡበትና አንዳንዴም ልዩ ፓርቲዎች እና ድግሶችም ያዘጋጁበታል፡፡ ለ21ኛው የዓለም ዋንጫ ራሽያ ከገባንብት ቀን አንስቶ ታላቁ የስፖርት መድረክ በፈረንሳይ ሻምፒዮናነት እስኪጠናቀቅ ድረስ  ካፌ አቬኑን አዘውትረነዋል። በካፌ አቬኑ ውስጥ ከተዋወቅኳቸው ምርጥ ኢትዮጵያውያን መካከል ጌዲዮን ብርሃኑ፣ ኃይለእየሱስ አሰፋ፣ አሌክስና መቅዲ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡  በሞስኮ እና በተለያዩ ከተሞች የተደረጉ የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎችን ከመመልከታችን በፊት እና ከተመለከትን በኋላ በካፌ አቬኑ እንገኝ ነበር፡፡ በካፌው ከተዋወቅናቸው በራሽያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር  በተለያዩ ጉዳዮች እንጫወትም  ነበር፡፡ አንዳንዶቹ እንደውም  አማርኛ ቋንቋ ማውራት የናፈቃቸው ሁሉ ነበሩ፡፡ስለኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ በብዛት እየጠየቁን ብዙ ተጫውተናል፡፡ በአንዳንድ አጋጣሚዎች በካፌው በመገኘት የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎችን ከኢትዮጵያውያንና ከሌሎች አፍሪካውያን በጋራ እንመለከትም ነበር፡፡  
የካፌ አቬኑው አቶ ተፈራ የኋላዋሴ በሞስኮ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የመጀመርያውን ልዩ ድጋፍ በመስጠታቸው ከልብ አመሰግናቸዋለሁ፡፡ ዓለም ዋንጫን ለመዘገብ ራሽያ የገባን ሶስት የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች በሞስኮ ከተማ ማረፊያ እስክናገኝ፤ ሙሉ ዓለም ዋንጫን በመጨረስ ወደ አገር ቤት እስክንመለስ ድረስ ከጎናችን ነበሩ፡፡ በተለይ ሞስኮ ከገባን በኋላ የመጀመርያዎቹን ሁለት ቀናት በመኖርያ ቤታቸው እንድናርፍ ፈቅደው ያደረጉትን ልባዊ መስተንግዶ በአድናቆት ለመጥቀስ እፈልጋለሁ፡፡ የአቶ ተፈራ ድጋፍ ይህ ብቻ አልነበረም፡፡ ከዓለም ዋንጫ ጋር በተያያዘ  ወደ ራሽያ በተለያዩ ጊዜያትና ሁኔታዎች የገቡ የሚዲያ ባለሙያዎችና የደጋፊዎች ቡድንን እየተቀበሉ፤ በማስተናገድ፤ የሚያርፉባቸውን ቦታዎች በማፈላለግ እና በማመቻቸት እገዛ አድርገዋል፡፡ በእኔ በኩል ይህን ድጋፋቸውን በማድነቅና ካፌ አቬኑ የኢትዮጵያውያንና የአፍሪካውያን መሰብሰቢያ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ልዩ ስጦታ አበርክቼያላቸዋለሁ፡፡ በሰዓሊና ዲዛይነር ዳዊት ሙሉነሕ የተሳለውን የሻምበል ምሩፅ ይፍጠርን ስዕል ነበር፡፡ በስጦታ መልክ የሰጠኋቸው በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ዋዜማ  እለት ሲሆን፤ አቶ ተፈራ የኋላዋሴም በክብር ተቀብለው በሚያስተዳድሩት ካፌ አቬኑ ግድግዳ ላይ እንደሚሰቅሉት ነግረውኛል፡፡
በአቶ ተፈራ የኃላዋሴ መኖርያ ቤት ለሁለት ቀናት ካረፍን በኋላ 21ኛው የዓለም ዋንጫ በተጀመረበት እለት ወሩን ሙሉ ታላቁን የስፖርት መድረክ ለመዘገብ ስንቆይ የምናርፍበትን ስፍራ ማፈላለግ ነበረብን፡፡ በመጀመርያ ሶስታችን በጋራ አዋጥተን ሆስቴል ለመከራየት ወይንም በዩኒቨርስቲ ውስጥ በሚገኙ የተማሪዎች መኖርያዎች ተመጣጣይ የክራይ ሂሳብ ከፍለን ለመግባት ብዙ ጥረት በማድረግ ቆየን፡፡ ምናልባትም አገርን በመወከል በዓለም ዋንጫው የምንሰራ ባለሙያዎች ስለሆንን ተገቢውን ድጋፍ እናገኝ ይሆናል በሚል ተስፋ በሞስኮ ከተማ ወደ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለማቅናት ወሰንን፡፡ በራሽያ ስለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፤ ስለሁለቱ አገራት የዲፕሎማሲ ግንኙነት … እና ሌሎች ጉዳዮች በሃላፊነት ላይ ከነበሩት አምባሳደር ጋር ቃለምልልስ ለማድረግ ቀጠሮ ያዝን፡፡ ኤምባሲው ለዓለም ዋንጫ ዘገባ በምናደርገው ቆይታ የሚሰጠን ድጋፍ ካለ ለመጠየቅም አስበናል፡፡
ልዩ ቃለምልልስ ከተሰናባቹ አምባሳደር ግሩም አባይ ጋር…
በራሽያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሞስኮ ውስጥ   ፕሮስፔክት ሚራ ወይንም የሰላም ጎዳና ተብሎ በተሰየመ  አካባቢ ይገኛል፡፡  በራሽያ መንግስት ፖሊሶች እና የፀጥታ ሰራተኞች ልዩ ጥበቃ የሚደረግለት ኤምባሲው በአፓርትመንቱና በግቢው  ግዝፈት ከአፍሪካ አገራት የሚጠቀስ ነበር፡፡ ዓለም ዋንጫው በተጀመረበት ምሽት ላይ  ኤምባሲው  ቅጥር ግቢ ከገባን በኋላ በመጀመርያ በተለያዩ የስራ ድርሻዎች ላይ ከሚገኙ ኢትዮጵያዊ  ሰራተኞች ጋር ትውውቅ አድርገናል፡፡ ከተሰናባቹ አምባሳደር ግሩም አባይ ጋር ደግሞ ለቃለምልልስ  በኤምባሲው ልዩ አደራሽ ተገናኘን፡፡ አምባሳደር ግሩም አባይ በሲቪዬት ኅብረት ዘመን ራሽያ የገቡ እና  የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ተከትለው ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱ ሲሆን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተለያዩ የሃላፊነት ደረጃዎች ለ30 ዓመታት አገልግለዋል፡፡ በራሽያ የኢትዮጵያ አምባሳደር በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩት አምባሳደሩ ለ21ኛው የዓለም ዋንጫ ሞስኮ በገባንበት ወቅት ከዚሁ ሃላፊነታቸው ተነስተው  በቤልጂየም ብራስልስ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው መሾማቸውን ሰምተንም ነበር፡፡
ከአምባሳደር ግሩም አባይ በራሽያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተገኝተን ባደረግነው ልዩ ቃለምልልስ በርካታ ጉዳዮችን አንስተን ነበር፡፡ በመጀመርያ የኢትዮጵያና የራሽያን ግንኙነት  በማስመልከት ያነሷቸውን ዋና ዋና ጉዳዮችና አስተያየቶች ልጠቃቅሳቸው፡፡  ሁለቱ አገራት  በባህልና በታሪክ ከ1 ክፍለ ዘመን የዘለቀ ጠንካራ ግንኙነት እንደነበራቸው ይታወቃል። በፖለቲካና ዲፕሎማሲ ግንኙነት ያሉበትን ወቅታዊ ሁኔታ አምባሳደር ግሩም ሲገልፁ ከሶቪየት ኅብረት መፍረስ በኋላ ሁለቱ አገራት በተለያዩ መስኮች ግንኙነታቸው መቀዛቀዙን አንስተው፤ ዋንኛው ምክንያት  ራሽያ በፌደሬሽን ከተዋቀረች በኋላ ድጋፍ ስሰጣቸው በነበሩ አገራት ላይ የነበራት ትኩረት በመቀነሱ ብዙ ነገሮች ስለተቀያየሩ ነው ብለዋል። በስራ ዘመናቸው የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ግንኙነትን ለማነቃቃት የማስተካከያ ስራዎች መከናወናቸውን ግን ጎን ለጎን አንስተዋል። ለዚህም ባለፉት 5 ዓመታት ሁለቱ አገራት በሚያገናኛቸው ክልላዊም ሆነ አኅጉራዊ ብሎም ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ በተወሰኑ ደረጃዎች በጋራ መስራታቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በተለይ ኢትዮጵያ በፀጥታው ምክር ቤት አባል ከሆነች በኋላ ራሽያ ውስጥ ከኒውዮርክና ከአዲስ አበባ የልዑካን ቡድኖች መጥተው ምክክርመደረጉን አስታውሰው ፤ከዚህ መልካም ግንኙነት በኋላ በፀጥታው ምክር ቤት መድረክ ላይ በሚነሱ የጋራ ጉዳዮች ላይ የአገራቱን ግንኙነት በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ለመስራት ተችሏል ብለዋል። ኤምባሲው በየወሩ ከሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከአፍሪካ መምርያም ሆነ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች መምርያ ጋር ተገናኝቶ በቋሚነት እየተመካከረ ሲሰራ መቆየቱን ያመለከቱት አምባሳደሩ፤ ከራሽያ ፓርላማ እና ሌሎች የመንግስት ተቋማት ጋር የተለያዩ ስምምነቶችን ለመፈራረም በሚያስችል ደረጃ የነበሩትን እንቅስቀሴዎች ጠቅሰው የረቂቅ ስምምነቶች ልውውጥ መደረጉን አበረታች ተመክሮ መሆኑን አውስተዋል፡፡ በሰው ኃይል ሥልጠና በተለይ በመከላከያ ዘርፍም ያተኮረው የሁለቱ አገራት ግንኙነት የተሻለ መሆኑን ሲጠቁሙም፤ በሲቪል ሰርቪስ ተማሪዎችም የሚካሄዱ ስራዎችንም የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ትስስሩን እንዳጎለበቱ በማስገንዘብ ነው፡፡
ኤምባሲው በገፅታ ግንባታ ሲሰራ መቆየቱን ሲያብራሩ ደግሞ የራሽያ ህዝብ ስለኢትዮጵያ ምን ያውቃል በሚለው ጥያቄ መነሻነት የተከናወኑትን ተግባራት ይጠቅሳሉ፡፡ በሶቪዬት ኅብረት ዘመን የነበረው ትውልድ ስለኢትዮጵያና አፍሪካ በተወሰነ ደረጃ እውቀት ነበረው ያሉት አምባሳደር ግሩም፤ ይህን  መሰረት በማድረግ የነበሩ እንቅስቃሴዎችን ዘርዝረዋል፡፡ በራሽያ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች  በመገኘት የተለያዩ ህትመቶችና መረጃዎችን ማሰራጨት፤ ከተለያዩ የሚዲያ አካላት በመቀራረብ ሁለቱን አገራት የሚያስተዋውቁ  ጽሑፎች ማሳተም፤ በኤምባሲው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ ላይ ስለኢትዮጵያ የተለያዩ መረጃዎች ማሰራጨት ስንሰራ የቆየንባቸው አቅጣጫዎች ነበሩ ብለዋል፡፡ የራሽያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዲፕሎማቶች ማሠልጠኛ ተቋም ለኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ወጣት ዲፕሎማቶች ሥልጠና ለመስጠት መወሰኑን ጠቅሰውም፤ በመስከረም ወር 20 ወጣት ዲፕሎማቶች ወደራሽያ የሚጓዙበትን ሁኔታ የተሻለ ስራ የሚከናወንበትን አቅም የምንፈጥርበት ነው ብለዋል።  የሞስኮ ዓለም አቀፍ የግንኙነት ዩኒቨርሲቲ በሚሰጣቸው   ልዩ  ሥልጠናዎች ኢትዮጵያውያን በነፃ የመሳተፍ ዕድሉን እንዲያገኙ አድርገናል የሚሉት አምባሳደሩ፤ በየሶስት ወሩ ከራሽያ የተለያዩ ሚዲያዎች ጋር በመቀራረብ ወደ ኢትዮጵያ ጉብኝት አድርገው የተለያዩ መረጃዎችን አግኝተው እንዲያሰራጩ እና የቱሪስት መስህቦችን በማስተዋወቅ እንዲሰሩ መሞከሩንም አመልክተዋል፡፡
በራሽያ እና ኢትዮጵያ መካከል  በቢዝነስና ኢኮኖሚ ዘርፍ ሊኖር የሚችለውን ግንኙነት ለማጠናከር ግን ለኤምባሲው ፈታኝ ሆኖበት መቆየቱን አምባሳደር ግሩም አባይ አልሸሸጉም። አብዛኛዎቹ የራሽያ ኩባንያዎች በመንግሥት ባለቤትነት የተያዙ፤ ከፍተኛ ትኩረታቸውም በጋዝ፣ በዘይት፣ በማዕድንና እንዲሁም በተወሰነ ደረጃ የመሣሪያ ሽያጭ ላይ በመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ በኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚሰሩባቸውን እድሎች ማጥበቡን ነው የሚያስረዱት። የራሽያ ኢንቨስተሮችን ወደ ኢትዮጵያ ለመጋበዝ እንደ ቱርክና ህንድ ኢንቨስተሮች የሚቀል እንዳልሆነ የሚጠቅሱት አምባሳደሩ፤ የራሽያ ኢንቨስተሮች ትኩረት ትልልቅ ኢንዱስትሪዎች ላይ መሆኑን ኤምባሲያቸው ተገንዝቦ፤ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ ኢንቨስትመንት እንዲያስቡ በተለይ በምግብ ዘርፍ እንዲሳተፉ ጥረት አድርገናል ብለዋል፡፡ ኤምባሲው የንግድ ዘርፍ ግንኙነቱን በተቻለው መንገድ ለማጠናከር ያከናወናቸው ሌሎች ተግበራትም አንስተዋል፡፡ በተለይ ባህላዊ የሆኑ ምርቶችን ኤክስፖርት ለማድረግና ነባር ገበያውን ለማስጠበቅ በኢትዮጵያ በኩል የነበረውን ተሞክሮ በማዳበር ተስፋ የሚሰጡ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል፡፡ እንደ አምባሳደር ግሩም ገለፃ ለረጅም ጊዜ ወደ ሞስኮ ቀጥታ የአየር በረራ አለመኖሩ ለዚሁ የኤክስፖርት እንቅስቃሴ የፈጠረውእክል ነበር፡፡ ወደ ራሽያ  የኢትዮጵያን ምርቶች በሦስተኛ ወገን በኩል በማስገባት ሲሰራበት መቆየቱን በምሳሌ ሲያስረዱም፤  በራሽያ የኢትዮጵያ የአበባ ምርት በጣም ተፈላጊ በመሆኑ ከሆላንድ በመኪና ሲገባ እንደነበር አንስተዋል፡፡ ስለዚህም የንግድ ግንኙነቱን ለማንቀሳቀስና ለማቀላጠፍ ሲባል በሁለቱ አገሮች መካከል ቀጥታ በረራ እንዲኖር በስራ ዘመናቸው ጥረት ማድረጋቸውንና በረራው ተጀምሮ  የኢትዮጵያን ምርቶች በቀላሉ ማጓጓዝና ለገበያ ማቅረብ እየቻልን ነው ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ  የዕውቀት ሽግግር እንዲኖር በትኩረት እንሰራ ነበር ያሉት አምባሳደር ግሩም፤  የኑክሌር ኃይልን ለሰላማዊ አገልግሎት ለመጠቀምና አስፈላጊውን የዕውቀት ሽግግር ለማድረግ ስምምነት መደረጉንና ለኢነርጂ አማራጮችን መፈለግ ወሳኝ መሆኑን አምነንበት ወደ ስራ ከመገባቱ በፊት ኑክሌር መገንባት ሳይሆን የሰው ኃይልን ማሠልጠን ስለሚቀድ በዚያ አቅጣጫ ሰርተናል ብለዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም በባቡር ሐዲድ ኢንጂነሪነግ መስክ ከ4 ዓመታት በፊት  ከካሊንግራድ ከተማ 40 ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ተመርቀው በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በሥራ ላይ ይገኛሉ፡፡ ተጨማሪ ተማሪዎችም በቀጣይ ሥልጠና እንደሚወስዱ ተነጋግረናል፡፡
በቃለምልልሳችን መካከል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ በራሽያ ስለነበራቸው ጉብኝትም ተነስቶ  መንፈሳዊና ፖለቲካዊ አንድምታ እንደነበርው  አምባሳደር ግሩም  አባይ ገልፀዋል፡፡ ፓትሪያኩ በራሽያ ጉብኝታቸው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሰርጌ ላቨሮቭ ጋር መወያየታቸውን፤ ይህም የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለማጠናከር የሃይማኖት ተቋማት መወጣት ያለባቸው ኃላፊነት ማመልከቱን፤  ከራሽያ ፓርላማ የላይኛው ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔው ጋር ሲገናኙ ደግሞ፤ ከሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ጋር በተያያዘና በፓርላማ ደረጃ ሊሠሩ የሚችሉ እንቅስቃሴዎችን ማነቃቃቱን እንስተዋል፡፡ ፓትርያርኩ ወደ ራሽያ የመጡት በአገሪቱ ፓትርያርክ ኪሪ ግብዣ ነው ያሉት አምባሳደሩ፤ ከ17 ዓመታት በኋላ ሊሳካ የቻለ ጉብኝት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡  ከራሽያ ፓትርያርክ ጋርም የተለያዩ ገዳሞችን በመጎብኘት፣ ከዚህ ቀደም ተቋርጦ የነበረው የሃይማኖት ትምህርት እንዲቀጥል ስምምነት ላይ መደረሱ  የፓትርያርኩን ጉብኘት መንፈሳዊ ተልዕኮ እንደነበረው ያረጋግጣል ብለዋል በራሽያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው የሰሩት አምባሳደር ግሩም አባይ፡፡
የራሽያ መንግሥት በየዓመቱ ለኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ሰፊ የትምህርት ዕድል ቢሰጥም በኢትዮጵያ በኩል በተለይ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እና ዩኒቨርስቲዎች በኩል ያለው ፍላጎት መዳከሙ በርካታ እድሎችን አሳጥቷል፡፡ በተለይ ደግሞ ከሶቪየት ኅብረት መፈራረስ በኋላ በራሽያ የሚማሩ እና የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቁጥር እየቀነሰም ሲሆን ሌላው ምክንያት ደግሞ የራሽያ መንግሥት ስደተኞችን ካለመቀበሉ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ተሰናባቹ አምባሳደር ግሩም አባይ በኤምባሲያቸው በሰጡን ቃለምልልስ ላይ እንደተናገሩት፤  በየዓመቱ ወደ ራሽያ የሚመጡትን ኢትዮጵያውያን ማንነት የሚገልጽ መረጃ የሚይዙበት አሰራር እንዳላቸው ሲሆን በራሽያ ፌዴሬሽን፣ ዩክሬንና ቤላሩስ የሚኖሩት በአጠቃላይ 313 ኢትዮጵያውያን እንደሆኑና በራሽያ የሚገኙት 210 መሆናቸውን ነው፡፡ በየዓመቱ የነፃ የትምህርት ዕድል አግኝተው የሚመጡት የግልና የመንግሥት ተማሪዎች ከ12 እንደማይበልጡም ገልፀዋል፡፡   በራሽያ በአሁኑ ወቅት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለትምህርት ከመጡ በኋላ የቀሩ ሲሆኑ ብዙዎቹ ከ30 ዓመታትና ከዚያም በላይ የቆዩ ናቸው።  በሞስኮ እና በተለያዩ የራሽያ ከተሞች የሚኖሩት እነዚህ ኢትዮጵያውያን በከፍተኛ ደረጃ የተማሩ ሲሆኑ ከመካከላቸው የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን፤ የዓለም አቀፍ ግንኙነት እና የሚዲያ ኤክስፐርቶች፤ ዲፕሎማቶች፤ የፖለቲካና የፍልስፍና የዩኒቨርስቲ መምህሮች፤ በኢንጅነሪንግ፤ በህግ፤ በምህንድስና፤ በህክምና ሳይንስ የተመረቁም ይገኙበታል። አንዳንዶቹ በተለያዩ የውጭ አገራት ኤምባሲዎች በራሽያ ግዙፍ ኩባንያዎች የሚሰሩ ናቸው፡፡ ከኢትዮጵያውያኑ መካከል በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች በመማር ላይ የሚገኙት ከ30 የማይበልጡ ሲሆን   በሞስኮ ከተማ በሚገኙት ካፌ አቬኑ እና አዲስ አበባ ሬስቶራንት የሚሰሩም ይጠቀሳሉ፡፡ ጥቂቶቹ ከራሽያውያን ጋር ትዳር  መሰርትው የሚኖሩ ሲሆን፣ ሌሎቹ ደግሞ በየተማሩባቸው የትምህርት ዘርፎች የአገሪቷን ቋንቋና ባህል በማወቃቸው በተለያዩ ኩባንያዎች ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩም ናቸው፡፡ በራሽያ ዩኒቨርስቲዎች ያስተማሩ እና የሚያስተምሩ እንዲሁም ሞስኮ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ኢምባሲዎች ተቀጥረው የሚያገለግሉም ነበሩ፡፡ ራሽያ ገብተው ትምህርታቸውን ሳይጨርሱ አገሪቱን እንደመሸጋገርያ በመጠቀም ወደ ምእራብ አገራት በተለይ ወደ አሜሪካ የተሰደዱ አሉ፡፡ ከሶቪዬት ህብረት መፈራረስ በኋላ በርካታ ኢትዮጵያያ ምሁራን ወደ አሜሪካ በመዛወር ኑራቸውንም ቀጥለዋል፡፡  በራሽያ ከሚሰሩ እና ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ኤምባሲው እንደሚሰራ በተለያዩ ዝግጅቶችም እንደሚገናኙ አምባሳደር ግሩም የገለፁልን ቢሆንም ፤ አስቀድሞ ከነበረው የደከመ እንቅስቃሴ በኤምባሲው መኖሩን ተገንዝቢያለሁ። አምባሳደሩ ለኢትዮጵያውያኑ በኤምባሲው በኩል ቡድን ተቋቁሞ የተለያዩ ችግሮች ሲኖሩ በውይይት ለመፍታት ጥረት እንደሚያደርግና ለአገር የሚሰጥ ድጋፍ ሲያስፈልግ እንደሚያስተባብር ገልፀው፤ በራሽያ ከሚገኘው የተማሪዎች ኅብረት ጋር በየጊዜው ተገናኝተን እንሰራለን ብለዋል፡፡ ይሁንና በሞስኮ ከተማ ያነጋገርናቸው ኢትዮጵያውያን እንደነገሩን አምባሳደር ግሩም አባይ  በራሽያ እንደመማራቸው በዚያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በተሻለ ያቀራርባሉ የሚል ተስፋ ቢኖርም በሃላፊነት ዘመናቸው ያን ለመተግበር አልተቻለም ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ኤምባሲውን እንደቤታቸው  በመቁጠር ሊገለገሉበትበየጊዜው ሊሰበሰቡበት፤ የመዝናኛ እና ፌስቲቫል ዝግጅቶች ሊያካሂዱበት ቢፈልጉም ባለፉት አምስት ዓመታት ይህን ማድረግ አልቻሉም፡፡ አምባሳደር ግሩም በኤምባሲው  መስራት ከጀመሩ በኋላ በየዓመት በዓሉ እና በሌሎች ምክንያቶች በኤምባሲው የነበሩ እንቅስቃሴዎችን አስቁመዋል፡፡ ይህም በራሽያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በየጊዜው እየተገናኙ የሚደሰቱባቸውን ሁኔታዎች አስቀርቷል፡፡ ከሁሉም ግን በኤምባሲው ቅጥር ግቢ እና በህንፃው ውስጥ በሚገኘው የአፍሪካ አደራሽ ይስተናገዱ የነበሩ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት በዓላት መቅረታቸው ያሳዝናል፡፡ ኤምባሲው አስቀድሞ በነበሩት ጊዜያት በራሽያ ከሚንቀሳቀሱ የአፍሪካ ዲፕሎማቶች ጋር በነበረው ቅርርብ የአፍሪካን ገፅታ በሚያሳድጉ ዝግጅቶች ይሰራ ነበር፡፡
በራሽያዋ ሞስኮ ከተማ መኖር ከጀመረ ከ25 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው ጥላሁን በተማሪነት ዘመኑ በከፍተኛ ውጤቱ እና ማዕረግ በመመረቁ በወገኖቹ የሚደነቅ ነው። ጥላሁን እንደሚያስረዳው በራሽያ የዩኒቨርስቲ ትምህርት ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ወደ ራሽያ በነፃ የትምህርት እድል ሊማር የገባ ኢትዮጵያዊ ብርቱና ትጉህ ተማሪ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ሳይማር፤ የዩኒቨርስቲ ትምህርቱን ቢያቋርጥ አገሪቱ በምንም መልኩ አትመቸውም፡፡ በራሽያ ለመስራ እና ለመኖር የሚቻለው በትልቅ ደረጃ ተምሮ በመጨረስ ብቻ ነው፡፡ ራሽያውያንና ኢትዮጵያውያን በብዙ ሁኔታዎች ተመሳሳዮች መሆናቸውን ጥላሁን ለአዲስ አድማስ በሰጠው አጭር አስተያየት ሲያስረዳ ለምሳሌነት የጠቀሰው የራሽያ እና የኢትዮጵያን ህዝቦች የሚጠቀሟቸውን አባባሎች ነው፡፡ እንደኢትዮጵያ ሁሉ ራሽያውያንም ‹‹ከአልጋ ስትወርድ በቀኝህ ይሁን ›› ይላሉ እንዲሁም ማታ ማታ ቤትና ቆሻሻ አይጠርጉም ይላል፡፡ በራሽያ ኢትዮጵያውያን የከፍተኛ ትምህርታቸውን ለመጨረስ ሲሉ ጂንስ ሱሪዎችን ለአስተማሪዎቻቸው በጉቦ መልክ እንደሚሰጡ ስለሰማሁት የቆየ ወሬም አንስቼ ነበር፡፡ ይህን አስመልክቶ ጥላሁን ሲናገር በራሽያ የሚሰጥ ትምህርት በጉብዝና እና በትጋት የሚፈትንና የሚያመርቅ ነው ብሎ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ለመመረቅ ጂንሶች በጉቦ አይሰጡም ነበር ምናልባም ከትምህርታቸው ጎን ለጎን የሚነግዱ ስለነበሩ ነው ይላል፡፡ የድሮዎቹ ኢትዮጵያዊ ተማሪዎች ከሶቬየት ህብረት ወጥተው ወደ የተለያዩ የሶሻሊስት እና የካፒታሊስት አገራት ለእረፍት እና ለተለያዩ ሽርሽሮች መጓዝ  ይችሉ ነበር። ድሮ ዩጎስላቪያ ፤ቼኮስሎቫኪያ ተብለው በሚጠሩ አገራ እና እንዲሁም ወደ ምስራ ጀርመን ማለት ነው።  የተለያዩ አገራት ይዘዋወሩ የነበሩ ተማሪዎቹ  ጂንስ ሱሪዎች እና ሌሎች አልባሳትን ወደ ሞስኮ በማምጣት እየነገዱ ሃብታም የሆኑትን ነው የማስታውሰው በማለት ምላሹን ሰጥቶበታል፡፡
በሰላም ጎዳና ዓለም ዋንጫን በሙሉ ልብ ለመዘገብ…
በራሽያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በሃላፊነት ከመሩት ተሰናባች አምባሳደር ግሩም አባይ ጋር የምናደርገውን ቃለምልልስ ከጨረስን በኋላ ነው፡፡ 21ኛውን የዓለም ዋንጫ ለመዘገብ ራሽያ መግባታችንን፤ በፊፋ ሁሉንም የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች በራሽያ የተለያዩ ግዛቶች በመዘዋወር የምንሰራበት ፈቃድ እንዳለን ከገለፅልንላቸው በኋላ በኤምባሲው የሚደረግልን ልዩ ድጋፍ ካለ ጠየቀናቸዋል፡፡ በተለይ ዋና ያሳሰበን የማረፊያ ጉዳይ መሆኑን በመጥቀስም ነበር፡፡ አምባሳደር ግሩም አባይ የጠበቅነውን ምላሽ አልሰጡንም ነበር፡፡  እኛ ሶስታችን የስፖርት ጋዜጠኞች ዓለም ዋንጫን ለመዘገብ ኢትዮጵያን ወክለን እንደመጣን የሚያረጋግጥ ደብዳቤ ከእግር ኳስ ፌደሬሽን፤ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወይም ከሌላ የሚመለከተው ተቋም እንዳልደረሳቸው፤ ቢደርሳቸውም ኤምባሲው ምንም አይነት ድጋፍ ሊሰጥ እንደማይችል ነው በደፈናው የነገሩን፡፡ ከአምባሳደሩ ያልጠበቅነውን ምላሽ ሰጥተው ካሰናበቱን በኋላ  የኤምባሲው ሰራተኞች ምሳ ጋብዘውን ነበር፡፡ ምሳውን እየበላን ሁለት ኢትዮጵያውያን ወዳለንበት ምግብ ቤት መጡ፡፡ 21ኛውን የዓለም ዋንጫ ለመዘገብ በፊፋ ፍቃድ አግኝተን የመጣን የስፖርት ጋዜጠኞች መሆናችንን ነግረን  ተዋወቅናቸው፡፡ የፍልስፍና መምህርና ዲፕሎማት ፕሮፌሰር አንጌሳ ጫላ እና ሲቪል ኢንጅነር እና ዲፕሎማት ኢብራሂም ሞጋ ናቸው፡፡  ከአምባሳደሩ ጋር ከነበረው ቆይታችን በኋላ የጠየቅነውን  ድጋፍ ማጣታችንን የኤምባሲው ሰራተኞች ከነገሯቸው በኋላ ‹‹የዓለም ዋንጫውን በልበሙሉነት ስሩ፤ ማረፊያችሁ አያሳስባችሁ›› ብለው ወዲያውኑ ነበር የወሰኑት፡፡ በሞስኮ ከተማ ፕሮስክፔት ሚራ ‘’ የሠላም ጎዳና’’ በተባለ ሰፈር የሚገኘው የኢብራሂም ቤት ማረፊያችን እንዲሆን ፈቀዱልን፡፡  እስከ ዓለም ዋንጫ ፍፃሜም በዚሁ አፓርትመንት  ከጅማው ሰው ኢብራሂም ሞጋ  እና በአቅራቢያው ይኖሩ ከነበሩት ፕሮፌሰር አንጌሳ ጋር እጅግ መልካም ጊዜ አሳልፈናል፡፡…. ይቀጥላል

Read 8940 times