Monday, 03 September 2018 00:00

“ጠ/ሚ ዐቢይ ‹‹መደመር›› ሲሉ የህይወትን መሠረታዊ ህግ እያስታወሱን ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት በተጓዝንበት ጎዳና የታዩ አንዳንድ አጥፊ የሆኑ ነገሮችን አስተውለው፤ ይህን ስህተት ለማረም ‹‹እንደመር›› አሉ፡፡ መደመር ቀላል የፍቅር ህግ ማስታወሻ ቃል ነው፡፡ የህይወትና የህብረተሰብን ቋሚና ዘላለማዊ ህግ መዘከሪያ ዘይቤ ነው፡፡ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጆች መድህን የሚሆን ፍልስፍ

Written by  ወንድወሰን ተሾመ መኩሪያ (የማህበራዊ ሳይንስና የሥነልቦና ባለሙያ)
Rate this item
(0 votes)

በአገራችን ኢትዮጵያ በብዛት ስራ ላይ ካልዋሉት ሃብቶች መካከል አንዱ ምክር ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ በምክር ሰው ይቃናል፣ ከስጋቱና ከጭንቀቱ ይወጣል፤ ተስፋን እንዲያይ ይደረጋል፤ በውስጡ ያለውን ውድ እምቅ አቅም ያወጣል፤ ለመኖር ትርጉም እንዲሰጥ ይረዳዋል፤ በትናንት ፀፀት፣ቁጭትና ሃዘን እንዲሁም በነገ ፍርሃትና ስጋት ተጠምዶ ከመኖር ይልቅ ዛሬ ማድረግ ያለበትን በሙሉ ሃይሉ እያደረገ፣ ነገን እንዲቀርፅ ያሳስበዋል ወዘተ፡፡ ይህ የምክር ጥቅም በግለሰብ ብቻ የሚወሰን አይደልም፡፡ ቡድኖችና አገራት መልካም ምክርን ጥቅም ላይ በማዋል ዘርፈ ብዙ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎቻቸውን ይጠቅማሉ፡፡
መፅሐፍ ቅዱስ “መልካም ምክር ከሌለ--ህዝብ ይወድቃል” በማለት መልካምን ምክር በማድረግ የታሰበው እንዲሳካ መካሪዎች ተግተው እንዲሰሩ ያሳስባል (ምሳሌ 11 እና 15 ይመልከቱ)፡፡ የዛሬው ፅሁፌ በአገራችን በሚኖሩ የፖለቲካና የምሁራን ውይይቶችና ክርክሮች ላይ እያንዳንዱ ተሳታፊ ልብ ሊለው የሚገቡትን መጠነኛ ጉዳዮች ለማሳየት ነው፡፡
ላለፉት አራት ወራት በዶክተር ዐቢይ እና በለወጥ አራማጅ ጓዶቻቸው እየተሰሩ ያሉት ስራዎች የወራት ጉዳይ አይመስሉም-የብዙ ዓመታት እንጂ! በርካታ ሰበብ እየተፈለገላቸው በየእስር ቤቱ የታጎሩ ብዙ ዜጎች ከእስር ተፈትተዋል፤ በውጭ አገር የሚገኙ በርካታ እስረኞች እንዲፈትቱ ተደርገዋል፤ ኢትዮጵያና ኤርትራ በብርሃን ፍጥነት በሚያሰኝ መልኩ  እርቅ ፈፅመዋል፤ የታጠቁ ቡድኖች መሳሪያ ማንገባቸውን “እርግፍ አድርገው ትተው” አብዛኞቹ ወደ አገራቸው በክብር ገብተዋል፤ሌሎችም በቅርቡ ወደ አገር ቤት በመግባት በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ቆርጠዋል፤ በአሸባሪነት የተፈረጁ ግለሰቦችና ድርጅቶች ፍረጃው ተነስቶላቸው አንዳንዶቹ በውድ አገራቸው መሬት ላይ ሆነው በነፃነት እየተናገሩ ነው፤  ሚዲያዎቻችን የተለያዩ አስተሳሰቦችንና እውቀቶችን እያሰሙን ይገኛሉ፡፡ ይህንን አጠናክሮ እንዲሄድ ከማድረግና አገራችን ሁሉም ኢትዮጵያዊ በእኩል የሚታይባት እንድትሆን፤ ዲሞክራሲንና ፍትህን አስተማማኝ ያደረገች፤ የህግ የበላይነት የሰፈነባት አገር እንድትሆን ለኛም ለልጆቻችንም  ምቹ አገር ለመፍጠር ከመትጋት የበለጠ ምን የሚያስደስት ነገር አለ? እየተጉ ያሉትን የለውጥ አራማጆችና የሚዲያ አካላት ማመስገን ተገቢ ነው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ለዓመታት በተለያዩ ርዕዮተ-ዓለሞችና በጎሳ ፖለቲካ ተከፋፍለው ሲሰሩ የኖሩ የፖለቲካ ሰዎች “እንዴት አድርገው ይግባባሉ?” የሚሉ ጥያቄዎች በዜጎች ልብ ውስጥ መፈጠሩ አይቀርም፡፡ ለዚህም ጥያቄ መነሻ የሚሆኑ ነባራዊ ስነልቦናዊና ባህላዊ ጉዳዮች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ አንዱ ሌላውን የሚመለከትበት መነፅር “ያልጠረጠረ ተመነጠረ” በሚለው እሳቤ “ጠርጥር!” የሚለውን ዘፈን የሚያቀነቅን ከሆነ፣ ስልጣን ለራስ ጥቅም ማስገኛ መሆኑን በሚገልጠው “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጫዋል” በሚል እሳቤ ከሆነ፤ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” በሚል አስተሳሰብ ከሆነ፤ ወዘተ ---- ውይይቶችና ክርክሮች መቋጫ የሌላቸው እየሆኑ የጋራ ስምምነቶች ላይ በአጭር ጊዜ ለመድረስና የተጀመረውን ለውጥ ለማፋጠን እክል ይሆናል፡፡
በኢትዮጵያውያን ስብስቦች ዙሪያ የተገነዘቡትን የራሳቸውን ምልከታ ከብዙ አመታት በፊት ጀምሮ በተለያዩ መድረኮች ሲያንፀባርቁ የነበሩት የካናዳ ነዋሪው አቶ ሰላም ክፍሌ ይትባረክ ከስድስት ወራት በፊትም እኔና የስራ ባልደረባዬ በናሁ ቴሌቪዥን በጋራ ስናቀርበው በነበረው እሴት በተሰኘው የስነልቦና እና የቤተሰብ ሳምንታዊ ፕሮግራም ላይ በአካል ተገኝተው  ቃለ መጠይቅ አድርጌላቸው ነበር፡፡ እሳቸው የኢትዮጵያ ስብስቦች የሚሏቸው  የፖለቲካ፣ የቤተሰብ፣ የዘመድ የሞያ ማህበራት፣ ሃይማኖታዊ፣ የኮሚኒቲና የበጎ አድራጎት ስብስቦችን ሲሆን በአገር ውስጥና በውጪ አገራት የሚኖሩትን ያካትታል፡፡  
በዚህ ወሳኝ ወቅት ውይይቶችና ክርክሮች መካሄዳቸው አይቀርምና በእነዚህ ውይይቶችና ክርክሮች እሳቸው ጎጂ ጠባዮች ያሏቸውን የሚከተሉትን ማስወገድ በጣም ጠቃሚ ነው እላለሁ። አቶ ሰላም ክፍሌ፤ እነዚህን ጎጂ ጠባዮች በ13 ከፍለው እንደሚከተለው አቅርበዋቸዋል፡፡
1. ነገርንና ግለሰብን ማቆራኘት
ይህ ግለሰብንና የግለሰብን ሃሳብ ለይቶ አለማየት ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ግለሰብ የተቃውሞ ሃሳብ ከሰጠ የሃሳብ ልዩነት መሆኑ ቀርቶ ግለሰቡን ለማጥቃት ይሞከራል፡፡ ተቃውሞ የተነሳበትም ግለሰብ በአንፃሩ አፀፋዊ ጥቃት ለማድረግ ይፈልጋል፡፡ በመጨረሻም የሃሳብ አለመግባባት ወደ ግለሰብ ጥል ይሸጋገራል። ይህም ግለሰቦች ክብርና ህልውናቸው የተጠቃ ስለሚመሰላቸው ነው፡፡ ላለመስማማት መስማማት የማይችሉ ሰዎች፤ በግለ ሰባዊ ፀብና ሽኩቻ ይሽመደመዱና ቡድኖች ይፈርሳሉ፡፡
2. ወገናዊነት
የፈለገው ቢሆን ለምናውቀው ወገን፣ ቤተሰብ፣ መንደር፣ ቡድንና ዘር መወገን እንፈልጋለን፡፡ ለምሳሌ ወገናችን የሆነ ሰው ከሌላ ወገን ግለሰብ ጋር ቢጋጭ፣ የነገሩን ሁኔታ እንኳን ሳናውቅ ወገንተኛነታችንን እናሳያለን፡፡ በዚህም ቅራኔ ምክንያት ጥላቻውን አስፍተን የተቃዋሚውን ወገን፣ ቤተሰብ፣ ጓደኞች፣ የሥራ ቦታ፣ ጎሳ እናወግዛለን፡፡ ይህ ለደም መፋሰስ ምንጭ ሊሆን ይችላል፡፡ ወገናዊነት ቡድን ያፈርሳል፤ ምክንያቱም ውሳኔዎች በወገናዊነት እንጂ በትክክለኛነታቸው ተፈፃሚነት ስለማይኖራቸው ወገናዊነት ድርጅቶችን ከፋፍሎ ድርጅቶቹን ያፈርሳቸዋል። ለምሳሌ አንድ ድርጅት ሁለት ቦታ ይከፈልና ሁለቱ ደግሞ ብዙ ቦታ እየተከፈሉ በመጨረሻም ባጠቃላይ ድርጅቱ ይፈርሳል፡፡
3. ጥርጣሬ
በመጀመሪያ ደረጃ እርስ በእርሳችን የምንተያየው በጥርጣሬ መንፈስ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ጉዳት የሌላቸው ሃሳቦች እንኳን ከጀርባቸው ሌላ ነገር አላቸው ተብለው ይፈራሉ። ፍፁም የዋህ የሆነ የጓደኛ አመለካከት እንኳን በጥርጣሬ እንደ እርኩስ ሃሳብ ተተርጉሞ የዳበረ ግንኙነት ይፈርሳል፡፡ ይህ አይነት ጠባይ የድርጅቶች ውስጠ ቅራኔ መሠረታዊ ምክንያት ነው፡፡ መተማመን ከሌለ ምንም ዓይነት ድርጅት ውጤታማ ሊሆን አይችልም፡፡
4. ፍርሀት
ሁሉንም ሰው እንደ አደገኛ ስለምናይ በአስተሳሰባችንና በአመለካከታችን ውስጥ ፍርሀት ይዳብራል፡፡ እንዲህ አይነት ፍርሀት ድርጅቶችን ሽባ ያደርጋቸዋል፡፡ ይህም የሚሆነው ሁሉም በፍርሀት እያመነታ ጉዳይን ከግብ ለማድረስ ወደፊት መሄድ ስለማይቻል ነው፡፡
5. ተቆርቋሪ አለመሆን
የሌሎችን ስሜት፣ ተግባርና ሁኔታ ራሳችንን በሌላው ቦታና ሁኔታ አድርገን አለማየት ለሌላው አለመቆርቆርን ያመጣል፡፡ ተቆርቋሪ መሆን ለጤናማ ግንኙነት አስፈላጊ ነው፡፡ አንድ ሰው አንድ ነገር እንዴት ሊሰራ እንደቻለ ወይንም ደግሞ እኛ በሱ ቦታ ብንሆን ኖሮ ምን ማድረግ እንደምንችል እራሳችንን አንጠይቅም፡፡ ይህ ወደተዛባ ፍርድና ጎዶሎ ግንዛቤ ያመራና በቡድኖች ውስጥ አለመግባባትና ቅራኔን ይወልዳል፡፡
6. ለመዳኘት ወይም ለመፍረድ መቸኮል
ለመዳኘት አለመቸኮል ለጤናማ ግንኙነት መሠረት ነው፡፡ ጥርጣሬና ለሌላው አለመቆርቆር ተደማምረው ውዝግብ ከማቅለል ይልቅ ፍርደ ገምድልነትን ያመጣሉ፡፡ አንድ ሰው እኛ የማይገባንን ነገር ካደረገ፣ ቆይ እስቲ እኛ የማናውቀውና እሱ የሚያውቀው ነገር ሊኖር ይችላል ብለን እራሳችንን አንጠይቅም ወይንም ከፍርድ በፊት ትእግሥት አናደርግም፡፡ የነገሮችን የመሆንና ያለመሆን ሁኔታ ሳንዳስስ ለመዳኘት እንቸኩላላን፡፡ ይህ ወደተዛባ ፍርድና ግለሰባዊ ቅራኔ ውስጥ ይከተናል፡፡
7. ስም ማጥፋትና አሉባልታ
ቅራኔዎችን ከመፍታት ይልቅ የማይግባቡን ሰዎች ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ እናደርጋለን። እንዲህ አይነቱ ዘመቻ በማኅበረሰባችን ውስጥ እንደሚሰራ እናውቃለን፡፡ አምታችና አሻሚ የሆኑ ነገሮችን በስነሥርዓት ሳንዳስስ ስለ ግለሰቦች የሚባለውን መጥፎ ነገር ማመን እንመርጣለን። የግለሰቦችን ክብር የሚነካ ነገር በማድረግ ግለሰቦችን ከጨዋታው ውጭ እንዲሆኑ እናደርጋለን፡፡ ቀደም ብሎ እንዲህ አይነት ግንዛቤ ያለው ጭንቅላት፣ ጥርጣሬውን የስም ማጥፋቱ ተግባር ግልፅ ያደርግለታል፡፡ እንዲህ አይነቱ አሉባልታ ብዙዎቻችን እንደምናውቀው ወደ ግለሰቦች ሽኩቻ፣ የቡድኖች ሽባነትና የድርጅት ውድቀት ያመራል፡፡
8. ግልፅ አለመሆን
ግልፅነት ጤናማ ግንኙነት  እንዲካሄድ  ይረዳል። እኛ አስተሳሰባችንን ግልፅ ካለማድረጋችን ባሻገር የሌላውም አስተሳሰብ ግልፅ ይሆናል ብለን አንጠብቅም፡፡ ይህም በግልፅ ከተናገርኩ ምንነቴ ይታወቃል፣ እዳኛለሁ የሚለውን ፍራቻ ያመጣል። በዚህ ምክንያት ነገሮችን አድበስብሰንና በግድየለሽነት የግንኙነት ክፍተት ፈጥረን የድርጅት ውድቀትን እናመጣለን፤ ምክንያቱም ሌሎች የተደበቀ ነገር አለ ብለው ስለሚገምቱ፡፡
9. ቂም መያዝና መቀየም
ቂመኛነት ከባህላችን የመነጨ ስለሆነ ቂም እንይዝና ይቅር ማለትን እንደ ድክመት እናየዋለን፤ ምክንያቱም ሁሉም እንደ አደገኛ ሰው ስለሚታይ ነው፡፡ በቡድን ስራዎች ውስጥ ሁሌም አለመግባባት ሊኖር ስለሚችል ቂም የምንይዝ ከሆነ ምንም አይነት ውጤታማ ሥራ መሥራት አይቻልም፡፡
10 ምቀኝነት
በብዙ መንገድ ሰዎች ከኛ ተሽለው ሲገኙ እንደነሱ ተሽሎ ለመገኘት ከመጣር ይልቅ እነሱ እንደኛ እንዲሆኑ ወደ ታች እንጎትታቸዋለን። ይህ የሚሆነው፣ ሲደመር ዜሮ እንደሚሆን የሂሳብ ስሌት እንዱ ሀብታም የሚሆነው ሌላው ደሀ ስለሆነ፣ አንዱ ደስተኛ የሆነው ሌለውን ስላሳዘነ ነው ከሚል ግንዛቤ ሊሆን ይችላል። ይህ ዓለም የተወሰነ ሀብት፣ ደስታና የመሳሰሉት ነገር እንዳለው አድርገን እናይና ሁላችንም ድርሻችንን እንጠይቃለን፡፡ በመሆኑም ሰዎች የከበሩት የሆነ ወንጀል ሠርተው ሲሆን ያጡት ደግሞ ተረግመው ነው ብለን እናስባለን፡፡
11. ግትርነት
መቻቻልን የምናየው እንደ ድክመት ነው። የመቻቻልና የመደራደር ፅንሰ ሃሳብ ለወደፊቱ ውጤታማ ጥረቶች የመሠረት ድንጋይ መሆኑን አንረዳም፡፡ እንዲያውም መቻቻልን የምናየው እንደ ተሸናፊነት ነው፡፡
12. አጉል ይሉኝታ
ይህ ሌላውን ሰው ላለማስቀየም የሚወሰድ ባህላዊ እርምጃ ነው፡፡ የግለሰቦችን ወይንም የቡድኖችን ሕልውና ላለመንካት ሲባል ከእውነት የራቀ ሃሳብ ወይንም ድርጊትን ሳናስተካክል ወይንም ሳናርም ስለምናልፍ ሁሉም እርስ በርሱ እንዳይተማመን ይሆናል፡፡ ለእውነት መቆም የተፈጠሩትን ብቻ ሳይሆን ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን ሁሉ ሊያቃልል ይችላል፡፡
13. አስመሳይነት
ራስን አለመሆንና እንደ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ይዞ መጓዝ፣ በቡድን አባሎችና ደርጅቶች ውስጥ ከፍተኛ አደጋ ያመጣል፡፡ የማናውቀውን እናውቃለን፣ የሌለንን አለን ካልን ሥራችን ልብ ወለድ እንጂ ተጨባጭ ነገሮችን ሊያንፀባርቅ የሚችል አይሆንም፡፡ በመሆኑም እንዲህ አይነቱ ጠባይ መጋለጥና መቆም ይኖርበታል፡፡
አቶ ሰላም ክፍሌ በአመዛኙ ከላይ የተዘረዘሩትን ጎጂ ጠባዮች በስብስብ ውስጥ ባለ የእርስ በእርስ ግንኙነት የታዘቧቸው ቢሆንም እነዚህ ጠባዮቸ ከሌሎች ስብስብ አባላት ጋር ባለ ግንኙነትም ሆነ በማህበረሰባችን ውስጥ የሚንፀባረቁ መሆናቸውን መታዘብ ይቻላል። በመሆኑም በፖለቲካ ድርጅቶችም ውስጥ ይሁን በሌሎች ስብስቦች በውይይቶችና ክርክሮች ወቅት ተሳታፊዎች ከላይ የተጠቀሱትን ጎጂ ጠባዮች ቢቻል ማስወገድ አለያም ለመቀነስ መሞከር ያስፈልጋቸዋል። የመልካም አስተሳስብ ጠባይ ባለቤት ለመሆን አብረውን ተጣብቀው የኖሩ አሉታዊ አስተሳሰቦችንና ጠባዮችን ቀስ በቀስ ማስወገድ ያስፈልጋል፡፡ በዚህም የአስተሳሰብ ለውጥ ምክንያት ውጤቱን ብቻ ሳይሆን ሂደቱንም መቆጣጠር ያስፈልጋል፡፡ በመጨረሻም የተገነዘቡትንና የተረዱትን ያካፈሉንን አቶ ሰላም ክፍሌን ላመሰግን እወዳለሁ፡፡  
ቸር እንሰንብት!    
የአዘጋጁ ማስታሻ፡-(ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻቸው፡ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡)

Read 1167 times