Saturday, 01 September 2018 15:17

እውን ኢሕአዴግ አለ?

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(7 votes)

 ብዙዎች ኢሕአዴግ አለ? ብለው ይጠይቃሉ። መልሱ አጭር ነው፡፡ ለስሙ አለ፤ ግብሩ ግን የለም። ዶክተር ዐቢይ አሕመድን ሊቀመንበሩ  አድርጎ የመረጠው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ የሾመው ኢሕአዴግ ነው፡፡ እሱ ግን በዐቢይ መምጣት በዐቢይ ተቀባይነት ማግኘት የበለጠ መጠላት ገጥሞት፣ ከሰው ልብና መንፈስ ቀድሞ ሞቷል፡፡ ተገንዞ የሚቀበር ግዙፍ የሆነ ነገር ባይኖረውም፣ በእኔና በብዙዎች ልብ ሞቶ፣ አርባው ከወጣም ቆይቷል፡፡ በእሱ ሞት በተገኘ ዕድል እሱ በመላ ኢትዮጵያ የዘራው፣ ያበቀለውና ኮትኩቶ ያሳደገው ዘረኝነት ቀስ በቀስ እየተቀነቀለ ነው፡፡ እሱ በመሞቱ ክርችም አድርጎ ዘግቶት የነበረው ሀሳብን የመግለጥ የነፃነት በር፤ ቦግ ብሎ ተከፍቶ እኔም ሞት ለኢሕአዴግ እያልኩ እየፃፍኩ ነው፡፡ ከልቤ እደግመዋለሁ ሞት ለኢሕአዴግ፡፡
ከአራቱ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች፣ ዘጠኝ ዘጠኝ ሰዎች ተውጣጥተው፣ በድምሩ 36 ሰዎች የሚገኙበት የኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ፤ ከአስር ቀን በፊት ለሁለት ቀን ስብሰባ አድርጎ ነበር። ነሐሴ 16 ቀን 2010 ዓ.ም ባወጣው መግለጫው፤ የዶክተር ዐቢይ መንግሥት ያደረገውን እንቅስቃሴ “ከሚጠበቀው በላይ” በማለት አድንቆታል። አድናቆቱን ብወድለትም በዶክተር ዐቢይ ጀርባ ታዝሎ ወደ ሕዝብ ለመውረድ፣ በሕዝብ የተወደደ ድርጅት መስሎ ለመታየት የሚያደርገው ጥረት ግን አሳስቦኛል፡፡ እንዲያውም ይበልጥ ስለ ድርጅቱ አስረግጦ የነገረኝ ዐይን ያወጣና ፀፀት የሚያሰማው፣ በአጋጣሚዎች ተጠቅሞ ሰዎችን መደለል የሚፈልግ መሆኑ ነው። እናም በሐረርጌዎች አማርኛ “አቦ አታቁስለን” እላለሁ፡፡
አቶ መለስ ዜናዊና አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ሁለቱም ኢሕአዴግን በሊቀ መንበርነትና ኢትዮጵያን በጠቅላይ ሚኒስትርነት መርተዋል። አቶ ኃይለማርያም እራሳቸውን ለመግለጥ ዕድል እንዳልነበራቸው አምናለሁ፡፡ የሕወሓቱ አቶ ጌታቸው ረዳ “በሥራቸው ላይ እንቅፋት ሆነንባቸው ነበር” ሲሉም መስክረውላቸዋል፡፡ አቶ መለስ ግን ከግራም ከቀኝም የሚጋፋቸው ኃይል ሳይኖር፣ ኢሕአዴግን እንዳሻቸው መርተውታል። የጠቅላይ ሚኒስትር ሥልጣናቸውንም ያለ ገደብ ተጠቅመውበታል፡፡ መለስ ተወደው ሳይሆን ተፈርተው አገር የገዙ መሪ ናቸው፡፡ ሰዎች ፎቶ ግራፋቸው ያለበትን ካኒቴራና ኮፍያ ቢያጠልቁ ወደዋቸው ሳይሆን ፈርተዋቸው ነበር። ይህን ደግሞ የሚያረጋግጠው በየጉባኤው በገፍ የሚታደለው ፎቶግራፋቸው ያለበት ኮፊያና ከኒቴራ ከአዳራሽ ውጭ የሚጠቀምበት አለመገኘቱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ በየቀበሌው፤ በገጠር የወረዳው የተቋቋሙት “የመለስ ፓርኮች” በመለስ ፍቅር የተነደፉ ያቆሟቸው ሳይሆኑ የመለስን ጥላ ማለትም በሕውሓት ላለመጠቆር ሲሉ የተተከሉ እንደነበሩ የሚታወቅ ነው፡፡
ሰው በገዛ ገንዘቡ የዶ/ር ዐቢይን ፎቶግራፍ ገዝቶ ስለያዘ፣ የእሳቸው ፎቶግራፍ ያለበትን ካኒቴራ ስለለበሰ ኢሕአዴግና ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው፤ ኢሕአዴግ በሕዝብ ተቀባይነት እያገኘ ነው ብሎ አስቦ ከሆነ እጅግ ተሳስቷል፡፡ ዐቢይ ሌላ ኢሕአዴግ ሌላ ናቸው፡፡ “አቦ አታቁስሉን” አሁንም ቃሌ ነው፡፡
ኢሕአዴግ ወደ አነሳውና ወደረሳው አጀንዳ ልግባ፡፡ አጀንዳው ሳር እንዲበቅልበት መደረግ የለበትም፡፡
ደርግና ኢሕአዴግ ቀዳሚና ተከታይ ናቸው፡፡ ደርግ ያስር፣ ይገርፍ፣ ይደበድብ፣ ይገድል፣ የሰዎችን አድራሻ ያጠፋ እንደነበረው ሁሉ ኢሕአዴግም ይህን ሃያ ሰባት ዓመት ሙሉ አድርጎታል፡፡ በደርግ ጊዜ ያልነበረ፤ በኢሕአዴግ በሕዝብ ላይ የተፈፀመ ብዙ ወንጀል አለ፡፡ ለከፋፍለህ ግዛ እንዲመች ሰውን በዘር መለያየት፣ አንደኛው ሌላኛውን ሕዝብ ጠላቱ አድርጎ እንዲቆጥር ማድረግ፣ ከተወለደበት አካባቢ የወጣ ሁሉ በአንድ አገር በአንድ ሕገ መንግሥት በምትመራ ሀገር መጤ ሆኖ እንዲታይም አስደርጓል፡፡ በዚህ መንገድ ደግሞ አማራው በአማራ፣ ኦሮሞ በኦሮምያ፣ አፋሩ በአፋር ወዘተ ካልሆነ በስተቀር በሌላው አካባቢ ገብቶ የፖለቲካ እንቅስቃሴም እንዳያደርግ ከልክሏል፡፡
ሌላም ችግር አለ፡፡ ጆርጅ ኦርዌል የተባለው ደራሲ ብዙ ጊዜ የሚጠቀስለት ንግግር አለው፡- “ሁሉም እንስሳት እኩል ናቸው፡፡ ከእንስሳቱ መካከል ይበልጥ እኩል የሆኑ እንስሳትም አሉ” ክልሎችን እየመሩ ያሉት ሁሉም የብሔር የፖለቲካ ድርጅቶች ናቸው፡፡ በዚህ ሁሉም እኩል ቢሆኑም፣ ከሁሉም የብሔር ድርጅቶች የበለጡት አራቱ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች፣ ከብሔር ክልላቸው ተሻግረው፣ መላ ኢትዮጵያን እየገዙ እያስተዳደሩ ናቸው፡፡
ኢሕአዴግ በተወካዮች ምክር ቤት 481 መቀመጫ አለው፡፡ ለአለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የሀገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትሮች፣ ፕሬዚዳንቶች፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን ወዘተ ሲሾምና ሲሽር የከረመው እሱ ነው፡፡
አንዳንድ ጊዜ ከሌሎች የክልል ፓርቲዎች ሰው እየወሰደ የባህል ሚኒስትር፣ የማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር እያለ ቢሾምም እሱንም የሚያደርገው ግዴታ ኖሮበት ሳይሆን ከራሱ በጎ ፈቃድ በመነሳት ነው። ኢሕአዴግ ካልጠፋና ካልፈረሰ ወይም ኢሕአዴግ አካሄዱን ካልለወጠ ምንም ያህል ብቃት ይኑረው አንድ የክልል ፓርቲ አባል ወይም አጋር ፓርቲዎች ከሚያስተዳድሩት አካባቢ የተገኘ ሰው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ፕሬዚዳንት ወይም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የመሆን ዕድሉ እንደ ሰማይ የራቀ ነው፡፡
ይህ መገፋት የመረራቸውና ያስመረራቸው አንድ የኢትዮጵያ ሶማሌ ሰው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጅጅጋ ላይ ባደረጉት ስብሰባ ላይ “እኛ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን እንፈልጋለን፤ መቼ ነው ለዚህ ዕድል የምንበቃው” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለዚህ ጥያቄ በሰጡት መልስ፣ በኢሕአዴግ “አጋር ድርጅቶች” እየተባሉ የሚጠሩት ገዥ ፓርቲዎች፣ ከኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች እኩል እንደሚታዩና ከፍፍሉም እንደሚጠፋ ገልፀው እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ በወቅቱ የኢህአዴግ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሺፈራው ሽጉጤ፤ ድርጅቱን ወደ አገር አቀፍ ፓርቲነት ለመለወጥ እንደሚጠና ተናግረውም ነበር፡፡ ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሔር (ሞንጆርኖ) የኢሕአዴግ ጽ/ቤት ኃላፊ ከሆኑ ጊዜ ጀምሮ ደግሞ ነገሩ ጨርሶ የተረሳ ሆኖአል፡፡ እሳቸው የኢሕአዴግ መታደስን ስለማይደግፉም እንዲያ ቢያደርጉ አይገርምም፡፡ ሌሎችም ዝም ማለታቸው ተገቢ አልነበረም፡፡
እሱ ቀርቶ ሌላ ዘፈን መጥቶ አለ ገጠሬ፡፡ በቅርብ ኦሕዴድና ብአዴን በየራሳቸው ክልላቸውን ሲመሩ የነበሩትን ፓርቲዎች ለመለወጥ መነሳታቸውን አሳውቀዋል፡፡ ከኦሕዴድ ወ/ሮ አዳነች አበቤ “ኦሕዴድ ፓርቲ ይሆናል፡፡ አርማ እንጂ ሰንደቅ አላማ አይኖረውም” ያሉ ሲሆን፣ የብአዴን የገጠር አደረጃጀትና የብአዴን ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ምግባሩ ከበደ፤ ብአዴን ወደ ፓርቲ በመለወጥ ብቻ ሳይወሰን ድርጅቱ ይመራበት የነበረውን ርዕዮተ ዓለም ሳይቀር ሊቀየር እንደሚችል ገልጠዋል፡፡
ሁለቱም ለመለወጥ ያላቸውን ፍላጎታቸውን ብወደውም መንገዱ ግን የቀደመውን ከመመለስ የተለየ ሆኖ አይታየኝም፡፡ ሕውሐትና ደኢሕዴግ ምን እያሰቡ እንደሆነ አለመተቃወቁ ደግሞ የበለጠ ነገሩን አሳሳቢ ማድረጉ አይቀርም፡፡ እንዲያውም ኢሕአዴግ ራሱን እያፈረሰ ነወይ ብሎ ለመጠየቅም ገፋፍቶኛል፡፡ እንዲሁ ዝም ብሎ መፍረሱ ጎጂ መሆኑም ሊሰመርበት ይገባል፡፡
አንድ አገር አቀፍ ፓርቲ፣ የወረዳ ሆነ የክልል ምክር ቤትን በምርጫ አሸንፎ፣ ወረዳውን ሆነ ክልሉን አልፎም የፌደራል መንግሥቱን እንዳይመራ የሚከለክል ሕግ የለም፡፡ ሕጉ ለክልሎች የሰጠውን መብት እራስን በራስ የማስተዳደር መብት ተግባራዊ ማድረግ ግን አለበት፡፡ እራስን በራስ በማስተዳደር ስም እንደ አቶ አብዲ አሊ መሐመድ አይነት ሰው፣ በክልሎች ላይ እንዳይሰለጥንም መላ መምታት ያስፈልጋል። ዲግሪ አለው ብቻ ሳይሆን በተግባር የተለካም መልካም ፀባይና ሥራ መመዘኛ ሆኖ መቀመጥ አለበት፡፡
በፌደራል መንግሥቱ ውስጥ ተገቢ ውክልና አላገኘንም የሚለውን ቅሬታ ለማስወገድና ለእነሱ ተሰሚነት ለማስገኘት ሁለት መንገዶች ኢሕአዴግ አሉት፡፡ አንደኛው አጋር የክልል ፓርቲዎችን ሰብስቦ አባል አድርጎ እኩል ወንበር መስጠት፤ ኢሕአዴግ በአዲስ መንገድ ማደራጀት ሲሆን ሁለተኛው እንደ ደርግ አደራጅ ኮሚሽን አቋቁሞ፣ በሁሉም ገዥ ፓርቲዎች ውስጥ ያሉ ሰዎች በአንድ አገር አቀፍ ፓርቲ ስር እንዲታቀፉ ማድረግ ነው። ከደርግ ማሰርን፣ መግረፍን፣ መግደልን ወዘተ የተማረው ኢሕአዴግ፤ ይህን መልመድ መተግበር ይከብደዋል ብዬ አላስብም።
በዚያም ተባለ በዚህ ለሕዝብ የተሰጠው ቃል ማለትም ኢሕአዴግ ፈርሶ በአዲስ ፓርቲ የመተካቱ ተግባር ፈጥኖ መጀመር፣ ከተጀመረም መቀጠል አለበት። ብአዴንና ኦህዴድ በጀመሩት መንገድ ከቀጠሉ ደግሞ የኢሕአዴግ እጣ ፈንታ ወዴት እንደሚወድቅ አስቀድሞ መወሰን አለበት፡፡ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው በኢህአዴግ የሚመራው መንግሥት፤ በ2012 በሚካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ አሸናፊ ለሚሆነው ፓርቲ ሥልጣን እንዴት እንደሚተላለፍም በሕግ መደንገግ ይኖርበታል፡፡
ኢሕአዴግ በራሱ ሲፈርድ ማየት መታደል ይሆናል  - ዕድሜ ይስጠን፡፡

Read 2615 times