Saturday, 25 August 2018 13:12

የ21ኛው ዓለም ዋንጫ ልዩ ማስታወሻ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(3 votes)


 • ልዩ ምስጋና ካሜራ ላዋሰኝ ፎቶግራፈር አንተነህ አክሊሉ
 • የፎቶ ጋዜጠኝነት በዓለም ዋንጫ ውስጥና ውጭ
 • ከ5ሺ በላይ ፎቶዎች፤ በ4 የተለያዩ የራሽያ ከተሞች፤ በ5 ዘመናዊ ስታድዬሞች፤ በ15 የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎችና በ12 ብሄራዊ    ቡድኖች…
 • 1.5 ሚሊዮን ፎቶዎች በጌቲ ሜጅስ ፤ በቀን ከ1200 በላይ ፎቶዎች በኤኤፍፒ
 • የጃፓኖቹ ኒከንና ካኖን ካሜራዎችና ሌንሶች የሚያውሱባቸው ልዩ ጣቢያዎች
 • ምርጥ የዓለም ዋንጫ ፎቶዎች እስከ 500 ዶላር ይሸጣሉ፡፡


   በራሽያ አስተናጋጅነት የተካሄደው 21ኛው የዓለም ዋንጫ የምንግዜም ምርጥ ተብሎ ከተደነቀባቸው ምክንያቶች አንዱ በምስልና ቪድዮ ክምችት ከመቼው ግዜ የላቀ ስለነበር ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ዓለም ዋንጫው በኢንተርኔት ማህበራዊ ሚዲያዎች፤ በፎቶ እና የቪድዮ ምስል ማሰራጫ ማህበራዊ ሚዲያዎች አዳዲስ ክብረወሰኖች ተመዝግበውበታል።
በየሳምንቱ በሚታተመው አዲስ አድማስ ጋዜጣ የስፖርት አድማስ አምድ ላይ በአዘጋጅነትና በከፍተኛ ሪፖርተርነት በአጠቃላይ በስፖርት ጋዜጠኝነት ከ15 ዓመታት በላይ ሳገለግል ቆይቻለሁ፡፡ በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ ግን ኢትዮጵያን በመወከል የምሰራበትን እድል ያገኘሁት በፍሪላንስ የፎቶ ጋዜጠኛነት ነበር፡፡ ከዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ በፍሪላንስ ፎቶ ጋዜጠኝነት ዓለም ዋንጫ ላይ እንድሰራ  የሚገልፀው ደብዳቤ ሲደርሰኝ በመጀመርያ ግር ብሎኝ ነበር። ሁኔታውን ለማጣራት አስቀድሜ ለፊፋ የሚዲያ ክፍል በአዲስ አድማስ በጋዜጣ ላይ በስፖርት አዘጋጅነት እንደምሰራ ጠቅሼ ፅፌ ነበር፡፡ የፊፋ ሚዲያ ኦፊሰር በሰጠው ፈጣን ምላሽ ስለምሰራበት ሳምንታዊ ጋዜጣ እና ስለነበረኝ ልምድ እንደሚያውቅና በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ ኢትዮጵያን በመወከል በነፃ የፎቶ ጋዜጠኛነት  እንድሰራ መመደቤን በሌላ ደብዳቤ ሲያረጋግጥልኝ ለኢትዮጵያ በተሰጠው ኮታ ለመጠቀም አላመነታሁም፡፡ በነገራችን ላይ  ከፊፋ ለሚመጣው እድል ብቁ ለመሆን የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር እና የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ጋዜጠኞች ማህበር አባልም መሆን ያስፈልጋል፡፡ በህትመት ሚዲያው መስራትም ሌላው መስፈርት ነበር፡፡
በርግጥ በዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ውድድሮች ላይ ኢትዮጵያውያን በፎቶ ጋዜጠኝነት የነበራቸው ተሳትፎ ጠንካራ አለመሆኑ አውቃለሁ፡፡ ስለዚህም በእግር ኳስ ፌደሬሽንና በስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር የቀረበውን እድል ለመጠቀም ስነሳ የበኩሌን አስተዋፅኦ ማድረግ እንደምችል በማመን ነበር፡፡ በከፍተኛ የሙያ ፍቅርና ትጋት ለምሰራው የስፖርት ጋዜጠኝነትም ተጨማሪ እውቀቶችና ወሳኝ  ልምዶች በዓለም ዋንጫው እንደሚፈጠሩም ስለማውቅ ልዩ ጉጉት አድሮብኛል።  የዓለም ዋንጫ የዓለማችን ግዙፍ የስፖርት መድረክ እንደመሆኑ በፍሪላንስ ፎቶ ጋዜጠኛነት በመስራት የሚፈጠሩት እድሎች ቀላል ግምት የሚሰጣቸው አልነበሩም፡፡ በዚህ ታላቅ አጋጣሚ ላይ በልዩ ፍቃድ መስራት በሙያዬ አዲስ ምዕራፍ እንደሚከፍትልኝም ማሰቤም አነሳስቶኛል፡፡ ከታላላቅ የፎቶ ኤጀንሲዎች ፤ አንጋፋ እና ምርጥ የፎቶ ጋዜጠኞች፤ የቪድዮ ባለሙያዎችና ፕሮፌሽናል  ፎቶግራፈሮች በቅርብ የምገናኝበት መድረክ ነው፡፡ የፎቶ ጋዜጠኛነቱን በተግባር ለመስራትና ለማወቅ ከዓለም ዋንጫ የላቀ መድረክም ሊኖር አይችልም።  በኢትዮጵያ  በተለይም በስፖርት ሚዲያው ለሚሰሩ የፎቶ ጋዜጠኞችና ጥቂት ፎቶግራፈሮች  ፈርቀዳጅ የሚሆኑ ብዙ ታሪኮችና ገድሎችን እንደምሰራበትም ተስፋ አድርጊያለሁ፡፡
በስፖርት ጋዜጠኝነት ከ15 ዓመታት በላይ የሰራሁበት ልምድ በፎቶ ጋዜጠኝነቱ ስኬታማ ተግባር ላከናውን እንደምችል ያስተማመነኝ ነበር፡፡ ምን፤ ማን፤ እነማን፤ መቼ እና ለምን የሚሉ ምክንያቶች በጋዜጠኝነት ሙያው የተማርኳቸው ልዩ ማስተዋሎች ናቸው፡፡ በዚህ አይነት አስተሳሰብ ላይ ዘመናዊ ካሜራና ሌንስ በመጠቀም መስራት  የሚያዳግተኝ አልመሰለኝም። በኢትዮጵያ የስፖርት ሚዲያ በፎቶ ጋዜጠኝነት ዓለም አቀፍ ደረጃ  ያለውን ክፍተት ለማጥበብ በሩ እንደተከፈተልኝም አስብ ነበር፡፡ በርግጥም በአገሪቱ ምርጥ የፎቶ ጋዜጠኞች፤ ፎቶግራፈሮች እና የፎቶ ባለሙያዎች በተለያዩ መስኮች የሉም ማለት አይደለም፡፡ በተለይ ግን በስፖርት ሚዲያ የሚሰሩት ጥቂት የፎቶ ጋዜጠኞችና ፕሮፌሽናል ፎተግራፈሮች በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው ተሳትፎ እና ብቃት ያደገ አይደለም፡፡
ልዩ ምስጋና ካሜራውን ላዋሰኝ አንተነህ አክሊሉ
ዓለም ዋንጫውን በፍሪላንስ ፎቶ ጋዜጠኝነት እንድዘግብ ከፊፋ ልዩ ፍቃድ ያለውን የድጋፍ ደብዳቤ ይዣለሁ፡፡ ወደ ራሽያ ለመጓዝ በወሰንኩበት ወቅት ግን የራሴ ካሜራ አልነበረኝም።  የተማመንኩት በተለያዩ ዓለም አቀፍና  አህጉራዊ የስፖርት  ውድድሮች በነበሩኝ ልምዶች ብቻ ናቸው። በ27ኛው ኦሎምፒያድ ቻይና፤ በ19ኛው የዓለም ዋንጫ ደቡብ አፍሪካ ፤ በ29ኛው  የአፍሪካ ዋንጫ ደቡብ አፍሪካ፤ በ5ኛው የቻን ሻምፒዮና ደቡብ አፍሪካ እንዲሁም በ14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሞስኮ ላይ የሰራሁባቸው ልምዶች ነበሩ፡፡ በእነዚህ ታላላቅ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የስፖርት መድረኮች ከመላው ዓለም ከሚሰባሰቡ ሚዲያዎች ጋር ተወዳድሬ ለመስራት በቅቻለሁ፡፡ ይሁንና አስቀድሞ ከኢትዮጵያ ውጭ በመጓዝ በተሳተፍኩባቸው የስፖርት መድረኮች በምሰራበት ሳምንታዊ ጋዜጣና በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች ትኩስ ዜናዎች፤ ወቅታዊ ቃለምልልሶች እና ዘገባዎች ሳቀርብ የምጠቅምባቸውን የማጀቢያ ፎቶዎች በተለያየ መንገድ የማገኛቸው ነበሩ፡፡ ፎቶዎችን ከተለያዩ እውቅ ድረገፆች ለማሰባሰብ እሞክራለሁ ወይንም በቻልኩት አጋጣሚ በራሴው  ዲጂታል ካሜራዎች እና ስማርት ሞባይሎች በማነሳቸው ፎቶዎች  ፅሁፎቼን አቀርብ ነበር፡፡  በ21ኛው የዓለም ዋንጫ  ላይ በፎቶ ጋዜጠኝነት ለመስራት የተሰጠኝ ሃላፊነት እያጓጓኝ ቆይቼ ካሜራ ከየት አገኛለሁ በሚለው ጥያቄ ሃሳብ ገብቶኛል፡፡  ይህን ችግሬን በመረዳት ልዩና ፈጣን ድጋፉን የሰጠኝ አብሮኝ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ  የሰራው ምርጥ ፎቶግራፈር አንተነህ አክሊሉ ነበር፡፡   አሁን በካፒታል ጋዜጣ እየሰራ የሚገኘው አንተነህ ፤ በመጀመርያ ዓለም ዋንጫን ለመሳተፍ ባገኘሁት እድል በጣም መደሰቱን ገልፆልኛል፡፡ በፍሪላንስ ፎቶ ጋዜጠኝነት እንድሰራ መመደቤን ስነግረው ደግሞ በሽልማት ያገኘውን ኒኮን ዲ90 ካሜራውን እንደሚያውሰኝ ቃል ገባልኝ፡፡ የዓለም ዋንጫውን ፎቶ ጋዜጠኝነት በተገቢው ካሜራ እንድሰራ የተሰጠኝን አገራዊ ሃላፊነት በብቃት እንድወጣ  ፎቶግራፈር አንተነህ ያሳየው በጎ ፈቃደኝነት የሚያስደንቅ ነበር። በፎቶ ጋዜጠኝነት ዓለም ዋንጫው ላይ የሚኖረኝን ልምድ ተረድቶታል፡፡ ለኢትዮጵያ የፎቶ ጋዜጠኞችና ፕሮፌሽናል ፎቶግራፈሮች ወደፊት ለሚፈጠሩ እድሎችና  መነቃቃቶችም ትብብሩ እንደሚያስፈልግ አምኖበታል፡፡
የካፒታሉ ፎቶግራፈር አንተነህ  አክሊሉ የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበርና የዓለም አቀፉ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር አባል ነው፡፡ በኢትዮጵያ የግል ሚዲያ በተለይ በፎቶግራፍ መስክ  ንቁ ተሳታፊ ከሆኑ ባለሙያዎችም ተርታ ይሰለፋል።  በተለያዩ አጋጣሚዎች በፎቶግራፈርነቱ ያበረከታቸውን አስተዋፅኦዎችን የሰጠኝን ድጋፍ ለማድነቅና ለማመስገን ያህል መጠቃቀስ እፈልጋለሁ፡፡ ከ2 ዓመት በፊት ከተወሰኑ የስፖርት ጋዜጠኞች ጋር በመተባበር ‹አንድ ብዕር  ለአንድ ተማሪ› በሚል መርህ ለችግረኛ ተማሪዎች የመማርያ ቁሳቁሶች ለመሰብሰብ ልዩ እንቅስቃሴ አድርገን ነበር፡፡  በወቅቱ በአዲስ አበባ ስታድዬም በተዘጋጀው ልዩ ስነስርዓት ላይ እንደ ማህበሩ አባልነት ብቻ ሳይሆን በጎ ፈቃደኛ ሆኖ ፎቶዎችን በማንሳት ሙሉ ድጋፍ ሰጥቶን ነበር፡፡ የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር በተመሰረተበት ጉባኤና በተለያዩ ስልጠናዎች እና ሌሎች ስብሰባዎች ላይም ካሜራውን ይዞ በመገኘት አገልግሎናል፡፡ አንተነህ ከአዲስ አድማስና ከካፒታል ጋዜጣዎች ሌላ በነጋድራስ ጋዜጣ ላይ የሰራበት ልምድ አለው፡፡ በፎሪን ኮረስፖንዳንት አሶሼሽን በተዘጋጀ እና በፈረንሳይ እና በአሜሪካ ኤምባሲዎች የስፖንሰርሺፕ  ድጋፍ በተካሄደ ብሄራዊ ውድድርም አሸናፊ ሆኗል፡፡ ያሸነፈበት ፎቶ በትንሽ ዲጂታል ካሜራ ያነሳው ቢሆንም ከ20 ተወዳዳሪዎች ብልጫ አግኝቶ ለእኔ ያዋሳትን ኒኮን ዲ 90 ካሜራን በአሊያንስ ኢትዮፍራንሴስ በተዘጋጀ ስነስርዓት ተሸልሟታል፡፡ አንተነህ  የአዲስ አድማስ ፎቶ ጋዜጠኛ ሆኖ በሰራበት ወቅት ካነሳቸው ብዙ ፎቶዎች ከ30 በላይ የሚሆኑትን ደግሞ  “ላይት ኢን ሻዶው” በተባለ የፎቶግራፍ አውደርእይ ካዛንቺስ በሚገኘው ኦዳ ታወርም አሳይቶ ነበር። “ጥበብ፣ ከተማና ገጠር” በሚል መሪ ቃል የተካሄደው ኤግዚብሽኑ ፎቶግራፈሩ በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ተዘዋውሮ ያነሳቸው ምርጥ ፎቶግራፎች የተካተቱበት ነበር፡፡ አንተነህ ዋልያዎቹ በአፍሪካ ደረጃ ስኬታማ በነበሩበት ዘመን፤ በ2012 እኤአ ላይ በተካሄደው የለንደኑ 30ኛው ኦሎምፒያድ፤ በእግር ኳስ እና በአትሌቲክስ ፌደሬሽን ጉባኤዎች እንዲሁም በተለያዩ ጊዜያት በሚደረጉ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድሮች በምርጥ ባልደረባነት አብሮኝ የሰራ ነበር፡፡
የካፒታል ጋዜጣ ፎቶግራፈር አንተነህ አክሊሉ  ኒኮን ካሜራውን ሲያውሰኝ 21ኛው የዓለም ዋንጫ በራሽያ ሊጀመር 5 ቀናት ቀርተዋል፡፡ ካሜራውን በሰጠኝ ቀንም በጥንቃቄ ስራዬን አከናውኜ እንድመልስለት ሲነግረኝ፤ እኔ ደግሞ በኢትዮጵያ የስፖርት ሚዲያ ለሚንቀሳቀሱ የፎቶ ጋዜጠኞችና ፎቶግራፈሮች በዓለም አቀፍ የስፖርት መድረኮች ላይ የሚኖሯቸውን ተሳትፎዎች የሚያሳድጉ ፈርቀዳጅ ተግባራት እንደማከናውን ቃል በመግባት ከልዩ ምስጋና ጋር ተረክቤዋለሁ፡፡ በመጀመርያ በውሰት ያገኘኋትን ትንሿን የአንተነህ ኒኮን ካሜራ ወደ 21ኛው የዓለም ዋንጫ ይዤ ከመጓዜ በፊት በነበሩት 5 ቀናት  ልምምድ አድርጌባታለሁ፡፡ ስለዚህም የመጀመርያውን ልምምድ ያደረግኩት ከፒያሳ ጀምሮ በከተማው ዋና ዋና አደባባዮች እና አውራጎዳናዎች በመዘዋወር ሲሆን ሐውልቶችን፤ የከተማውን ድባቦች፤ ህንፃዎች እና ሌሎች ሁኔታዎችን በማሰስ ፎቶዎችን አነሳሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ  ካሳንቺስ አካባቢ በሚገኘው የ28 ሜዳ ጭቃማ ሜዳ ላይ ወጣቶች ያደረጓቸውን የተለያዩ የሰፈር ጨዋታዎች በመታደም የተለያዩ ፎቶዎችን እያነሳሁ ተፍታችቻለሁ፡፡ በመጨረሻም ለካፒታሉ ፎቶግራፈር አንተነህ ልባዊ ምስጋናዬን በመግለፅ ኒኮን ካሜራዋን አንግቤ ጉዞ ወደ ራሽያ ሆነ፡፡
በፊፋ ፈቃድ የተሰጣቸው የፎቶ ጋዜጠኞችና
ፕሮፌሽናል ፎቶግራፈሮች
ፊፋ በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ ከ140 በላይ አገራትን ለሚወክሉ ከ1800 በላይ የፎቶ ጋዜጠኞች፤ ፕሮፌሽናል ፎተግራፈሮች እና የፎቶግራፍ ባለሙያዎች የዘገባ ፍቃድ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ለፊፋ አባል አገራት በተለያዩ ደረጃዎች ከተሰጡ ኮታዎች  ባሻገር ልዩ ትኩረት በማግኘት የዓለም ዋንጫ ፎቶዎችን በማንሳት ስራ ላይ እንዲሳተፉ ትልልቅ ዓለም አቀፍ የፎቶ ሚዲያዎች እና ድርጅቶችም  ነበሩ፡፡ Getty, Reuters, Associated Press, Agence France-Press ከግዙፎቹ የፎቶ ኤጀንሲዎች የሚጠቀሱ ሲሆን በዓለም ዋንጫው ላይ ከ20 እስከ 50 የፎቶ ባለሙያዎች በማሰማራት የሰሩ ናቸው። በሌላ በኩል በብዛት ተሳትፎ የነበራቸው የአዘጋጇ አገር  ራሽያ ፎቶግራፈሮችም ነበሩ፡፡ ከፎቶግራፈሮቹ መካከል በአውሮፓ እግር ኳስ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው፤ በ4 እና ከዚያም በላይ የዓለም ዋንጫዎች ላይ የሰሩ፤ በኦሎምፒክ፤ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች እና በሌሎች አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የስፖርት ውድድሮች በመስራት ልምድ ያካበቱ ብዛት ነበራቸው። ብዙዎቹ ምርጥና እውቅ ፎቶግራፈሮች እንደ ስፖርት ጋዜጠኞቹ እና የሚዲያ ባለሙያዎች ሁሉ በእድሚያቸው ገፋ ያሉ ማለትም ከጉልምስና ከፍም ያሉ ናቸው፡፡ ትልልቆቹን ዓለም አቀፍ የፎቶ ኤጀንሲዎች የወከሉት ፎቶግራፈሮች በየጨዋታው ስታድዬም ገብተው ሜዳ  ውስጥ ለማንሳት በሚችሉባቸው ምርጥ ቦታዎች ቅድሚያ ይሰጣቸው ነበር፡፡ እነ ጌቲ ኢሜጅስ፤ አሶሴየትድ ፕሬስ፤ ሮይተርስ፤ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ፤ እንዲሁም በርካታ የአውሮፓ እውቅ ሚዲያዎች በዓለም ዋንጫው ላይ በስፋት ከሰሩት ግዙፍ ተቋማት ይጠቀሳሉ፡፡ በአጠቃላይ በእነ ጌቲ ኢሜጅስና ኤኤፍፒ ሰራተኝነት የሚንቀሳቀሱ ፎቶግራፈሮች በዓለም ዋንጫው ወቅት በእያንዳንዱ የጨዋታ ቀን በየሰከንዱ 12 ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን ፎቶዎች በየሚዲያ አውታሮቻቸው ያሰራጩ ነበር፡፡
ለምሳሌ ያህል ከ50 በላይ ተሸላሚና እና ታዋቂ ፎቶግራፈሮቹን ያሰማራውን ጌቲ ኢሜጅስ መጥቀስ ይቻላል። 21ኛው የዓለም ዋንጫ ካበቃ በኋላ የፎቶ ስብስቦቹ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ መሆናቸውን በይፋ ያስታወቀው ጌቲ ኢሜጅስ በመላው ዓለም የማይዳሰው የስፖርት ውድድር የለም፡፡ በዓለም ዋንጫው ሰሞን በየ59 ደቂቃው የተነሱ ፎቶዎችን በዓለም ዙርያ ያሰራጭ የነበረው ጌቲኢሜጅስ ለሁሉም ክስተቶች ሽፋን መስጠቱን ደግሞ በምሳሌ ማመልከት ይቻላል፡፡ በሉዚሂንኪ ስታድዬም በጎፈቃደኞችን ለማመስገን በተዘጋጀው የመጨረሻ ዝግጅት ላይ የጌቲኢሜጅስ ፎቶግራፈሮች ነበሩ፡፡ ዓለም ዋንጫውን ያሸነፉት የፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች በተለይም ኡምቲቲ እና ሜንዲ ከእኔ የተዋሱትን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ኮፍያ እየተፈራረቁ በማድረግ በጎ ፈቃደኞቹን ለማመስገን  ሲጨፍሩ የነበረበትን ትእይንት የጌቲ ኢሜጅስ ራሽያዊ ፎቶግራፈር አንስቶት በኦፊሴላዊ ድረገፁ ነው ለማግኘት የበቃሁት፡፡ በሌላ በኩል አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ወይም ኤኤፍፒ በዓለም ዋንጫ ላይ በነበረው ተሳትፎ በፎቶ፤ በቪድዮ ቀረፃ፤ በኢንፎግራፊክ እና በቪድዮግራፊክ፤ እና በተለያዩ ስራዎች የሚሳተፉ ከ140 በላይ ባለሙያዎቹን ማሰማራቱን ለማረጋገጥ ችያለሁ፡፡ በየቀኑ ለ24 ሰዓት በ6 ቋንቋዎች የሚሰራው ኤኤፍፒ ፎቶግራፈሮች በእያንዳንዱ የዓለም ዋንጫ ቀን ከ1200 በላይ ፎቶዎችን ለሚዲያ ደንበኞቻቸው እና ተከታታዮቻቸው ያቀርቡ ነበር፡፡
ፊፋ በየስታድዬሞቹ ለፎቶግራፈሮች የስታድዬም ሚዲያ ትሪቢውንና ስታድዬም ሜዳ ውስጥ መግቢያ ትኬቶችና ካርዶች በሚሰጥባቸው ዴስኮች ይሰራ የነበረ ሲሆን የፎቶግራፈሮችን ጉዳይ የሚከታተሉ እና የሚያስፈፅሙ  ሃላፊዎችም በመመደብ ድጋፍ ያደርግ ነበር፡፡ በዓለም ዋንጫ ላይ በፊፋ ፈቃድ የሚሰሩ ፎቶግራፈሮች በየስታድዬሞቹ የሚዲያ ትሪቡን እኩል ስፍራ የማግኘት እድል አላቸው፡፡ ሜዳ ውስጥ ገብቶ ጨዋታዎችን በቅርበት ለመከታተል በሚያስችሉ 150 ፎቶ ማንሻ ስፍራዎች በሚሰጠው እድል ግን  ፎቶግራፈሮቹንበ3 የተለያዩ ደረጃዎች በመከፋፈል ፊፋ ለስራቸው ይመድባቸዋል፡፡ የመጀመርያው ቡድን ከየጎሎቹ ጀርባ ሆነው የሚሰሩ ሲሆን ለዚህ እድል ታዋቂ የፎቶግራፍ ኤጀንሺዎች እና የሚዲያ አውታሮች ቅድሚያ ይሰጣቸዋል፡፡
ሁለተኛው ቡድን ደግሞ ከተጋጣሚ አገራት እንዲሁም ከአዘጋጅ አገር የተውጣጡ ፎቶግራፈሮች እንዲሁም የታዋቂ ስፖርት ሚዲያ ባለሙያዎች የሚመደቡበት ሲሆን ሜዳ ላይ በማዕዘን መምቻ ስፍራዎች በመቀመጥ ስራቸውን ያከናውናሉ። እኔ የነበርኩበት ሶስተኛው ምድብ ደግሞ በተለያዩ አገራት የሚሰራጩ ህትመቶች፤ ድረገፆች እና የፎቶ ድረገፆች ላይ የሚሰሩ ፎቶግራፈሮች የሚሰባሰቡበት ሲሆን በሜዳው የመሃል ክፍል በሚዘጋጁ ስፍራዎች የምንሰራ ነበርን፡፡  በየጨዋታው ሜዳ ውስጥ በመግባት እስከ 100 ፎቶግራፈሮች በሶስት ምድብ ተከፋፍለው የሚሰሩ ሲሆን ሌሎች ፎቶግራፈሮች ደግሞ ከፕሬስ ጋዜጠኞች ጋር በየስታድዬሞቹ የሚዲያ ትሪቡን ላይ በሚዘጋጅላቸው  ልዩ ስፍራ ላይ ሆነው ፎቶዎቻቸውን ማንሳት ይችላሉ፡፡ ከላይ ከተጠቀሱትና አረንጓዴ የፎቶ ካባ ከሚለብሱ ፎቶግራፈሮች ባሻገር ፊፋ የራሱን ፎቶግራፈሮች ውሃ ሰመያዊ ካባ በማልበስ በወሳኝ እና ቁልፍ ስፍራዎች እንዲሰሩ ያሰማራቸዋል፡፡
በፊፋ ፈቃድ የተሰጣቸው ፎቶግራፈሮች
ብዙውን ጊዜ ከጨዋታው ሁለትና ሶስት ሰዓታት ቀደም ብሎ ስታድዬም መገኘት፤ ሜዳ ላይ መግቢያ ባጅ እና የፎቶ ትሪቡን ትኬት መውሰድ፤ ጨዋታው አንድ ሰዓት ሲቀረው ደግሞ ሜዳ ላይ የሚመረጥ ስፍራን መያዝ…የመጀመርያ ስራቸው ነው። በዓለም ዋንጫው ለፎቶግራፈሮች የነበረው ፈተና በየስታድዬም የሚደረገው ጥብቅ ቁጥጥር እና ፍተሻ ነበር፡፡ ካሜራዎቻቸው፤ ላፕቶፖቻቸው እና ሌሎች ተያያዥ ቁሳቁሶችን በየመቆጣጠርያው ማስፈተሽ፤  በማብራት እንደሚሰሩ ማረጋገጥ በተደጋጋሚ የሚያልፉበት  አሰልቺ ሂደቶች ናቸው፡፡  
በዓለም ዋንጫው ውስጥ…
ራሽያ የገባሁት ከ21ኛው የዓለም ዋንጫ መክፈቻ እለት ሁለት ቀናት አስቀድሞ ነበር፡፡  የመጀመርያው ስራዬ በዋና ከተማዋ ሞስኮ በሚገኘው ሉዚሂኒኪ ስታድዬም የፊፋ የሚዲያ ማዕከል በመገኘት አስፈላጊውን ምዝገባ ማከናወን ነበር፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያን የወከልኩ የፍሪላንስ ፎቶ ጋዜጠኛ መሆኑን የፊፋ የሚዲያ ማዕከል በማረጋገጥ ተመዘገብኩ፡፡ በ11 ከተሞች በሚገኙት 12 ዘመናዊ ስታድዬሞች በሙሉ መስራት የምችልበት SENBETO GIRUM SEIFU / MEDIA- PHO/ Freelance (ETH) የሚሉና ሌሎች መረጃዎች የሰፈሩበትን ልዩ የዓለም ዋንጫ መታወቂያ ተረከብኩ፡፡ በተጨማሪ ከፊፋ  1165 ቁጥር አረንጓዴ ቀለም የፎቶግራፈር የስራ ልብስ ተሰጠኝ፡፡ ከካፒታሉ ፎቶግራፈር አንተነህ አክሊሉ በተዋስኳት ኒኮን ካሜራ ስራዬን የጀመርኩት ከ21ኛው የዓለም ዋንጫ መክፈቻ በፊት በዋዜማው ነበር፡፡  በሞስኮው የክሬምሊን ቤተመንግስት እና ቀዩ አደባባይ ላይ የዓለም እግር ኳስ ደጋፊዎች በተሰባሰቡበት ደማቅ ምሽት ላይ ነው፡፡ ለዓለም ዋንጫው ራሽያ ከገቡት የእግር ኳስ ደጋፊዎች ከደቡብና መካከለኛው አሜሪካ የመጡት ብዛት ነበራቸው፡፡ በታሪካዊው አደባባይ የተሰበሰቡት የተለያዩ አገራት እግር ኳስ ደጋፊዎች፤ በየብሄራዊ ቡድኖቻቸው እና የአገራቸው መለያ ቀለሞች ከላይ እስከታች ደምቀዋል፡፡ የየአገራቸውን ባህል በሚያስተዋውቁባቸው አለባበሳቸው፤ በተለያዩ ቋንቋዎች በሚያሰሟቸው ህብረዝማሬዎች፤ ከሌሎች አገራት ደጋፊዎች ጋር በጋራ ሆነው በሚደሰቱባቸው ትእይንቶች ለዓለም ዋንጫው ልዩ ፍቅርና አንድነት እያሳዩ ነበር፡፡  ካሜራዬን በመደቀን በአደባባዩ ላይ መዘዋወር ጀመርኩ፡፡ ከእግር ኳስ አፍቃሪዎቹ ማራኪ አለባበስ የነበራቸው፤ ሰንደቅ ዓላማቸውንና የተለያዩ የድጋፍ ቀለማት ፊታቸውንና የተለያዩ የሰውነት ክፍሎቻቸውን አዥጎርጉረው  የተቀቡና እና ልዩ  ባነሮች የተሸከሙ፤ በማራኪ ዝማሬዎች እና ውዝዋዜዎቻቸው የአደባባዩን ድምቀት የፈጠሩ  የተለያዩ አገራት ደጋፊዎችን እያደንኩ በብዛት ፎቶ አነሳኋቸው። በጣም ከረካሁባቸው እና ካስደሰቱኝ የደጋፊዎች ፎቶዎች መካከል የኮሎምቢያ፤ የፔሩ፤ የግብፅ፤ የአርጀንቲና እንዲሁም የአዘጋጇ ራሽያ ደጋፊዎች ይገኙበታል፡፡
በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ዋዜማ ቀን ላይ ፎቶዎችን በማንሳት ከነበረኝ መልካም አጀማመር በኋላ በፍሪላንስ ፎቶ ጋዜጠኛነት ለ33 ቀናት በራሽያ  የተሳካ ቆይታን ለማሳለፍ በቅቻለሁ።  የፎቶ ጋዜጠኝነቱ  በዓለም ዋንጫ ላይ በዋና ከተማዋ ሞስኮ በሚገኘው ሉዚሂንኪ ስታድዬም እና ዓለም ዋንጫውን ባስተናገዱ ሌሎች 4 የተለያዩ ከተሞች ላይ በሚገኙ አምስት  ዘመናዊ ስታድዬሞች ውስጥ በሚደረጉት ጨዋታዎች የተወሰነ ብቻ አልነበረም፡፡ በዋናነት በየከተሞቹ ከሚገኙት ስታድዬሞች ውጭ በተሰማራሁባቸው የተለያዩ ጉብኝቶች እና የጉዞ አጋጣሚዎችን የሚያካትት ነበር፡፡ የየከተማዎቹን ስነህንፃዎች ፤ ታሪካዊ ሃውልቶች እና ቅርሶች፤ ማራኪ ትእይንቶችና ቅፅበቶች፤ የህይወት መልኮችን በማንሳት ከዓለም ዋንጫው ውጭ የተለየ ልምድ ለማግኘት በቅቻለሁ፡፡ በርግጥ ከስታድዬም ውጭ በፎቶ ጋዜጠኝነት ስዘዋወር ባለውለታዬ የነበረችው የካፒታሉ አንተነህ አክሊሉ ያዋሰኝ ኒኮን ካሜራ ነበረች፡፡ በሚገርም ሁኔታ ደግሞ በዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች ላይ በየስታድዬሞቹ   የኒኮን እና የካኖን ኩባንያዎች በልዩ ድጋፍ በሚሰሩባቸው ጊዜያዊ ጣቢያዎች በውሰት በሚሰጣቸው ካሜራዎች ተገልግያለሁ፡፡ በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ራሽያ ላይ በፍሪላንስ የፎቶ ጋዜጠኛነት በመሰማራት በስታድዬም ውስጥ ውጭ እና በየከተሞቹ በመዘዋወር ያነሳኋቸው ፎቶዎች ብዛት ከ5ሺ በላይ ይሆናል፡፡ በ4 የተለያዩ ከተሞች በሚገኙ አምስት ዘመናዊ ስታድዬሞች 12 ብሄራዊ ቡድኖችን በማሳተፍ የተካሄዱ 15 ግጥሚያዎችን  ከምድብ ማጣርያው አንስቶ፤ በጥሎ ማለፍ፤በሩብ ፍፃሜ ፤ በግማሽ ፍፃሜ እና በፍፃሜ  ላይ በመታደም የፍሪላንስ ፎቶ ጋዜጠኝነቱን በዓለም ዋንጫው ላይ  ሰርቻለሁ፡፡ የዓለም ዋንጫው የፎቶ ጋዜጠኝነት ሜዳ ውስጥ በመግባት፤ በፎቶ እና የሚዲያ ትሪቡኖች በመገኘት ጨዋታዎቹን በምስል በማስቀረት እና በመከታተተል  ከፍተኛ ልምድም ነው ያገኘሁት፡፡  
በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ የፎቶ ጋዜጠኛ ሆኜ በፎቶ ትሪቢውን ከሰራሁባቸው ጨዋታዎች አርጀንቲና ከአይስላንድ በስፓርታክ ስታድዬም  ሞስኮ ፤ ፖርቱጋል ከሞሮኮ በሉዚንሂኪ ስታድዬም ሞስኮ፤ ጀርመን ከሜክሲኮ በስፓርታክ ስታድዬም ሞስኮ፤ ስፔን ከራሽያ በሉዚንሂኪ ስታድዬም ሞስኮ፤ እንግሊዝ ከኮሎምቢያ በስፓርታክ ስታድዬም ሞስኮ እንዲሁም ፈረንሳይ ከክሮሽያ በ21ኛው የዓለም ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ በሉዚንሂኪ ስታድዬም ሞስኮ የተገናኙባቸው ጨዋታዎች ይጠቀሳሉ። በሌላ በኩል የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች ባስተናገዱ ዘመናዊ ስታድዬሞች ሜዳ ውስጥ በመግባት የሰራሁባቸው ደግሞ አርጀንቲና ከክሮሽያ በኖቭጎሮድ ስታድዬም ኒዚሂኒ ኖቭጎሮድ፤ ናይጄርያ ከአርጀንቲና በፒተር…..ስታድዬም ሴንትፒትስበርግ   እንዲሁም ራሽያ ከክሮሽያ በፊችት ስታድዬም ሶቺ  ላይ የተገናኙባቸው ነበሩ፡፡ በስታድዬም የፎቶ ትሪቡን በመሆንና ሜዳ ውስጥ በመግባት ካነሳኋቸው ፎቶዎች የአርጀንቲና፤ የክሮሽያ፤ የእንግሊዝ፤ የራሽያ፤ የናይጀርያና የኮሎምቢያ ብሄራዊ ቡድኖች ሙሉ ስብስብ፤ የተጋጣሚ አገራት ደጋፊዎች በስታድዬም ውስጥ እና ከስታድዬም ውጭ፤ ጨዋታዎቹን ያስተናገዱ ዘመናዊ ስታድዬሞችን የሚያሳዩ ነበሩ፡፡  በቅርበት ባነሳኋቸው ፎቶዎች ምስላቸውን ለታሪክ ካስቀራኋቸው ተጨዋቾች መካከል ደግሞ  ሜሲ፤ አጉዌሮ፤ ኦቢ ሚኬል፤ ሞሰስ፤ ሞድሪች፤ፖግባ ፤ሃሪ ኬንና በርካታ የራሽያ ተጨዋቾች … ሌሎችም ይገኙበታል፡፡ በየስታድዬሞቹ የነበሩ የደጋፊዎች ድባብ እና ሁኔታ፤ ከጨዋታው በፊት የበጎ ፈቃደኞችን ባንዲራ የመዘርጋት እና የመጠቅለል እንቅስቃሴ… ሌሎች ትእይንቶችም በካሜራዬ እይታ የገቡ ነበሩ፡፡
ከዓለም ዋንጫው ውጭ…
በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ ከተሰማሩ የዓለማችን ፕሮፌሽናል ፎቶግራፈሮች እና የፎቶ ጋዜጠኞች የምለየው ደግሞ ከዓለም ዋንጫው ውጭ በነበረኝ እንቅስቃሴ ነበር፡፡ ዋና ስራዬ በነፃ የፎቶ ጋዜጠኝነት ታላቁን የስፖርት መድረክ   በፎቶ ሜዳ ላይ፤ በፎቶ ትሪቢውን በፊፋ ባገኘሁት ፈቃድ መሰረት በየስታድዬሙ ገብቶ መዘገብ ብቻ አልተወሰነም፡፡ የሞስኮ ፤ ኒዚሂኒ ኖቭጎሮድ ሴንት ፒተርስበርግና ሶቺ ከተሞችን ተዟዙሬ በመጎብኘት ልዩ የጉዞ ማስታወሻዎችን ጎን ለጎን በማዘጋጀት ከዓለም ዋንጫው ስታድዬሞች ውጭ  የነበሩ ትዕይንቶችን በፎቶዎች አስቀርቻቸዋለሁ፡፡ የቱሪስት መስህቦች፤ ታዋቂ ስፍራዎች፤ ሐውልቶች እና የከተማ ትእይንቶችን የሚያካትተቱ የሚገርሙ የፎቶ ስብስቦች ነበሩ፡፡ ዓለም ዋንጫውን ባስተናገዱ ከተሞች በሚገኙ የቱሪስት መስህቦች፤ አውራ ጎዳናዎች እና ዋና አደባባዮች እንዲሁም የዓለም ዋንጫ የፌሽታ ሲኒማዎች የተዘዋወርኩት ፎቶዎችን እያነሳሁ ብቻ አልነበረም፡፡ የጉዞ ማስታወሻዎቼን ለመፃፍ የሚያግዙ ቃለምልልሶች በመስራት፤ የተለያዩ ታሪካዊ እውነታዎችና ጠቃሚ መረጃዎችን በመሰብሰብ ጭምር ነበር፡፡ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎዬ ከእግር ኳሱ የስታድዬም ድራማ ባሻገር በአስተናጋጅ ከተሞች ያሉ አስገራሚ ሁኔታዎች፤ጠቃሚና አስደናቂ ተመክሮዎች፤ የየከተሞቹ ክላሲክ እና ዘመናዊ ህንፃዎች፤ የመታሰቢያ ሃውልቶች እና የጎበኘኋቸው የተለያዩ ከተሞች ልዩ ምልክቶች… በመተረክ እና ባነሳኋቸው ፎቶዎች በማጀብ የላቀ ልምድ የቀሰምኩበት ሆኗል፡፡ በዚህም በኢትዮጵያ ለሚገኙ የስፖርት ሚዲያ የፎቶ ጋዜጠኞች በሚያገኙት የውጭ እድል ተጠቅመው ከሚጓዙበት ዋና ዓላማ ባሻገር እንዲሰሩ የማነሳሳቸው ይመስለኛል፡፡
የጃፓኖቹ ኒከንና ካኖን  ልዩ ጣቢያዎች
 በዓለም ዋንጫው ከሰሩ ታዋቂ ዓለም አቀፍ የካሜራ ብራንዶች መካከል የጃፓኖቹ  ኒከን እና ካኖን ዋናዎቹ ተጠቃሾች ሲሆኑ ብዙዎቹ የፎቶ ጋዜጠኞችና ፎቶግራፈሮች የሚገለገሏቸው የእነሱ ምርቶች ነበሩ፡፡ የሁለቱ ኩባንያዎች ዘመናዊ ካሜራዎችና ሌንሶች ተፈላጊ የሆኑት የሜዳ ላይ ትእይንቶችን በደንብ አቅርቦ ለማንሳት እና በርካታ ምስሎችን በፍጥነት ለመያዝ የሚያግዙ ስለነበሩ ነው፡፡ ኒኮንና ካኖን በዓለም ዋንጫው እያንዳንዱ ጨዋታዎች በየስታድዬሞቹ በሚያንቀሳቅሷቸው ልዩ ጣቢያዎችን ለዓለም ሚዲያዎች ካሜራዎች እና ሌንሶች በማዋስ መስራታቸው በ21ኛ የዓለም ዋንጫ ራሽያ ላይ የተጀመረ አይደለም፡፡ ሁለቱ ትልልቅ የካሜራ አምራች ኩባንያዎች የዓለም ዋንጫ ገበያን ለመቆጣጠር ይህን መሰሉን እንቅስቃሴ ከ2010 የደቡብ አፍሪካ 19ኛው የዓለም ዋንጫ ወዲህ ሰርተውበታል። ከ2012 የአውሮፓ ዋንጫና የለንደኑ 30ኛው ኦሎምፒያድ ወዲህ ደግሞ በዚህ አይነቱ አስደናቂ ተግባር ላይ ሰፊ ትኩረት በመስጠት ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ ሁለቱ ኩባንያዎች በዓለም ዋንጫ ላይ በ2010 ደቡብ አፍሪካ ላይ 60 በመቶ፤ በ2014 ብራዚል ላይ 70 በመቶ ተፈላጊነት እና የገበያ ድርሻ የነበራቸው ሲሆን በ2018 የራሽያ ዓለም ዋንጫ ደግሞ ይህን ድርሻ ወደ 80 በመቶ ሊያሳድጉት ችለዋል፡፡
በዓለም ዋንጫው ላይ ኒከን እና ካኖን ለፎቶግራፈሮች የፈጠሩት እድል የሚያስደንቅ ነበር፡፡በሁሉም የዓለም ዋንጫ አሰተናጋጅ ከተሞች እየተዘዋወሩ  ልዩ ልዩ ዘመናዊ ካሜራዎች እና የተለያየ ደረጃ ያላቸው ሌንሶችን በየስታድዬሙ በሚያቆሟቸው ጊዜያዊ ጣቢያዎች  ለውሰት በማቅረብ አገልግለዋል፡፡ እነዚህ በየስታድዬሙ ያገኘናቸው የኒከን እና ካኖን  የካሜራ ጣቢያዎች እና እያንዳንዳቸው የነበሯቸው ከ20 በላይ ባለሙያዎች የተሟላ አገልግሎት ለዓለም ሚዲያ መስጠት በመቻላቸው መመስገን አለባቸው፡፡ የካራና ሌንስ ማከራያ ጣቢያዎቹ እያንዳንዱ ጨዋታ ከመጀመሩ ሁለት ሰዓት ቀደም ብሎ ስራቸውን ይጀምራሉ፡፡ ጣቢያቸውን በዚሁ ወቅት የሚከፍቱት በፊፋ ፍቃድ ላላቸው ፎቶ ጋዜጠኞች እና ፕሮፌሽናል ፎቶግራፈሮች በተለያዩ ደረጃዎች የጥገና ድጋፍ ለመስጠት ነው፡፡ ይህን ስራ ሲያከናውኑ ጎን ለጎን  ከሁለቱ የካሜራ አምራቾች የተለያዩ እቃዎችን መዋስ የሚፈልጉ  ሁሉ ወረፋቸውን ይዘው ይጠባበቃሉ፡፡ ከጨዋታ አንድ ሰዓት ቀደም ብሎ ደግሞ በተያዘው ወረፋ መሰረት ካሜራዎች እና ሌንሶችን በበሙሉ ፈቃደኝነት ማዋስ ይጀምራሉ። ለመዋስ በፊፋ የተሰጠ ልዩ ፈቃድና መታወቂያን ማመዝገብ በቂ ነበር።  ሁሉንም የዓለም ስፖርት የፎቶ  ጋዜጠኞች በእኩል የስራ እቃዎች እና ቁሳቁሶች እንዲሰሩና እንዲተጉ ያስቻለ  ምርጥ የፕሮሞሽን ስራ ነበር፡፡ ብዙዎቹ ፎቶግራፈሮች ጥቁርና ነጭ ቀለም ያላቸውን የካኖን ወይም የኒከን ኩባንያ ግዙፍ ሌንሶችን ይጠቀሙ ነበር፡፡ እኔ ግን እንደጀማሪ የፎቶ ጋዜጠኛነቴ  ኒኮን ዲ 580  የምዋሰው ልዩ ካሜራ ሲሆን 70 በ200 ሚሊሚትር እና 70 በ400 ሚሊሚትር ኒከን ሌንሶችን በተደጋጋሚ በመዋስ ተገልግዬባቸዋለሁ፡፡ከተመሰረተ ከ100 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የጃፓኑ ኦፕቲካል ኢንዱስትርያ ኮርፖሬሽን ኒኮን ሰራተኛ እንደገለፀልኝ ኩባንያዎቹ ካሜራዎቹንና ሌንሶቹን በማዋስ በሰሩባቸው ያለፉት 8 ዓመታት በፎቶ ጋዜጠኝነቱ ላይ አዎንታዊ ሚና አበርክተዋል፡፡ ለዚህም ማስረጃው በጥራት ደረጃቸው የተሻሉ እና ባለብዙ አማራጭ ፎቶዎችን ለዓለም ህዝብ ለማቅረብ ስለታቸለም ጭምር ነው፡፡
ልዩ ተመክሮዎችና ልምዶች
በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ የስፖርት ጋዜጠኛነቴ ወደ የተሻለ ምዕራፍ ተሸጋግሯል፡፡ በፎቶ ጋዜጠኝነት በቀሰምኩት አስገራሚ ልምድ ገና ብዙ እንደምሰራ ተስፋ አደርጋለሁ። በጋዜጠኝነቴ ተጨዋቾቹን ማወቄ፤ የምፈልገውን ፎቶ ለማንሳት በምችልበት ልምድ እና ወሳኝ ምስሎችን በመረዳት አቅም ስለነበረኝ ምርጥ ፎቶዎችን እንዳነሳ አግዞኛል፡፡ ከታዋቂ ዓለም አቀፍ የፎቶ ኤጀንሲዎች እና ምርጥ ፎቶግራፈሮች ጋር ለመተዋወቅ እና ከልምዳቸውም ብዙ ትምህርት ለመውሰድም ችያለሁ፡፡
በዓለም ዋንጫው ላይ በልዩ ብቃታቸው ትኩረቴን የሳቡት አብዛኛዎቹ ፕሮፌሽናል ፎቶግራፈሮች እጅግ ዘመናዊ ልዩ ጥራት  እና ከፍተኛ የማጉላ አቅም ያላቸውን ሌንሶች እና ካሜራዎች የሚጠቀሙ ናቸው፡፡ እነዚህ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ፕሮፌሽናል ፎቶግራፈሮች በአንድ ጨዋታ 2 እና 3 የተለያዩ ካሜራዎችን በመያዝ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ፎቶግራፈሮች ሜዳ ላይ እንዲሁም በትሪቡን  ሆነው በካሜራዎቻቸው ከመስራትም በላይ ከጎን ያስቀመጧቸውን ላፕቶፖች በመጠቀም  የሚያነሷቸውን ፎቶዎች ከስር ከስር በፎቶ ኤዲቲንግ ሶፍትዌር በማዘጋጀትና በማደራጀት ፊፋ በሚያቀርበው በፈጣን ኢንተርኔት ተጠቅመው ያሰራጩ ነበር፡፡  ፎቶዎቹም በተለያዩ የኦንላይን ሚዲያዎች፤ የኢንተርኔት ፎቶ መጋዚኖች፤ ዲጅታል ሚዲያዎች እና ሌሎች ህትመቶች ታትመው የሚወጡና የሚሰራጩ ናቸው፡፡ ምርጥና ታዋቂ ፕሮፌሽናል ፎቶግራፈሮች ትኩስ ፎቶዎቻቸውን  በራሽያ ሚዲያዎች እስከ 170 ዶላር በተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ደግሞ ከ200 እስከ 500 ዶላር ዋጋ በመጠየቅ ይቸበችባሉ፡፡
ከተዋወቅኳቸው ፕሮፌሽናል ፎቶግራፈሮች መካከል ቱኒዚያዊው ሃሰን ኤዲን ማኑዲ በልዩ አለባበሱ የማስታውሰው ነው፡፡ የስፖርት ጋዜጠኝነቱን ከአባቱ የወረሰው ሃሰን በአሁኑ ጊዜ በአፍሪካ ስፖርት አንቱ ተብለው ከሚጠቀሱ ፎቶግራፈሮች አንዱ ሲሆን በዓለም ዋንጫው ላይ በተለያዩ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የስፖርት መድረኮች በመሳተፍ ከፍተኛ ልምድ ያካበተ ነው፡፡ ሃሰን ኤዲን በየስታድዬሙ ስንገናኝ ቀያይ ሰፊ ባርኔጣ እና ቀይ አጭር ካፖርት አድርጎ በአስገራሚ አለባበሱ እንደታጀበ ሲሆን  በታላላቅ የስፖርት ውድድር መድረኮች ሎጎዎች፤ የልብስ ጌጦች የተዥጎረጎሩ ናቸው፡፡ ከ1978 እኤአ ጀምሮ በተካሄዱት 11 የዓለም ዋንጫዎች በፎቶግራፈርነት የሰራው ሀነሪ ስዋዛርክ ሌላው የተዋወቅኩት ምርጥ ፕሮፌሽናል ፎቶግራፈር ነው፡፡ ሄነሪ ታላላቅ የእግር ኳስ ተጨዋቾችን የማይረሱ ምስሎች በማንሳት ዝና ያተረፈ ሲሆን ከታሪካዊ የፎቶ ስብስቦቹ የፔሌ፤ የማራዶና፤ የክሩፍ የዚዳን …. ይገኙበታል። ከሄነሪ ጋር በፍፃሜው እለት በሚዲያ ማዕከል ስንገናኝ አንድ ታሪክ ነገሮኝ ነበር፡፡ ፈረንሳዊውን ኪሊያን ምባፔ የሚመለከት ነበር፡፡  የ15 ዓመት ታዳጊ በነበረበት ጊዜ ኪሊያንን ፎቶ አንስቶት እንደነበርና በወቅቱ ወደፊት ኮከብ ሊሆን እንደሚችል ለጓደኞቹ መናገሩን ነበር፡፡ በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ኪሊያን ምባፔ ኮከብ ወጣት ተጨዋች ሆኖ መሸለሙን ሲያይ ሄነሪ ስዋርዛ በጣም እንደሚደሰት እርግጠኛ ነኝ፡፡
ይቀጥላል…

Read 4543 times