Saturday, 18 August 2018 10:11

በፈተና መሃል ስኬት ያዝመሰገበው የኢትዮጵያ አየር መንገድ

Written by  መንግስቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

 · በዓመቱ 6.8 ቢሊዮን ብር አትርፏል
   · ባለ 4 ኮከብ ደረጃ ተሰጥቶታል
   · 1000 ክፍሎች የሚኖሩት ሆቴል እያስገነባ ነው
      


    በአምስት C-47 አውሮፕላኖች ለመጀመሪያ ጊዜ አገልግሎት መስጠት የጀመረው እ.ኤ.አ ኤፕሪል 8 ቀን 1946 ወደ ግብፅ ዋና ከተማ ካይሮ በመብረር ነበር - የኢትዮጵያ አየር መንገድ። ከዚያን ጊዜ አንስቶ በአገልግሎት ጥራትም ሆነ በመጠን ከፍተኛ ዕድገት እያሳየ በገቢ፣ በንግድ፣ በክንውንና በደንበኞች አገልግሎት ታሪካዊ የሆነ ውጤት እያመጣ፣ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካ ጭምር ኩራት ለመሆን በቅቷል፡፡
የተጠናቀቀው በጀት ዓመት (201/7/18) ደግሞ በአየር መንገዱ ታሪክ እጅግ የላቀ ስኬት ያስመዘገበበት ዓመት ነበር ማለት ይቻላል። በአየር መንገዶች ኢንዱስትሪ፣ የደንበኞችን አገልግሎት እርካታ ደረጃ በማውጣት ቀዳሚ የሆነው ስካይትራክስ (SKYTRAY) የኢትዮጵያን አየር መንገድ፣ ከዓለም አቀፍ አየር መንገዶች ጋር አወዳድሮ፣ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ባለ 4 ኮከብ ደረጃ ሰጥቶታል፡፡ ይኸው ስካይትራክስ፣ አየር መንገዱን በአፍሪካ ምርጥ አየር መንገድ፣ በአፍሪካ ምርጥ ቢዝነስ ክላስና በአፍሪካ ምርጥ ኢኮኖሚ ክላስ ብሎታል፡፡
አየር መንገዱ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በአቪዬሽን አካዳሚ አዳራሽ የበጀት ዓመቱን ክንውን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ፤ የነዳጅ ዋጋ መወደድ 36 በመቶ ደርሶ  የእንቅስቃሴውን ወጪ በመጨመር በጣም ፈታኝ ችግር ቢጋርጥበትም፣ ዓመቱን በላቀና ሪከርድ በሆነ ውጤት ማጠናቀቁን አስታውቋል፡፡
የበጀት ዓመቱን ዕቅድ ሲያወጡ፣ የአንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ 56 ዶላር እንደነበር የጠቀሱት የአየር መንገዱ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም፤ ካሰቡትና ካቀዱት ውጭ 40 እና 50 በመቶ ጭማሪ በማሳየት፣ በርካታ ዓለም አቀፍ አየር መንገዶች ላይ ኪሳራ ማስከተሉን፣ በአፍሪካም እሳቸው የሚመሩትን አየር መንገድ ጨምሮ በደቡብ አፍሪካ፣ በኬንያና በግብፅ አየር መንገዶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል፡፡
የተጠቀሰው ችግር ቢኖርም አየር መንገዱ፣ በበጀት ዓመቱ፣ 14 አዳዲስ አውሮፕላኖች  (በወር ከአንድ በላይ መሆኑ ነው) መግዛቱን፣ 8 አዳዲስ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን ማለትም ጀኔቫ (ስዊዘርላንድ)፣ ቺካጎ (አሜሪካ)፣ ባህሬን፣ ካዱና (ናይጄሪያ)፣ ቦነስአይረስ (አርጀንቲና) ኪሳንጋኒና መቡጂ-ማዲ (ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎና ኖሰይ-ቢ (ማዳጋስካር) መክፈታቸውን ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገልፀዋል። በአምስት ክፍለ አህጉራት 110 ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች፣ በአፍሪካ 58 እና በአገር ውስጥ 20 መዳረሻዎች እንዳሉት ተገልጿል።
አየር መንገዱ ያጓጓዘውም የመንገደኞች ብዛት ከምንጊዜውም ጊዜ በላይ ጨምሮ፣ 21 በመቶ የደረሰ ሲሆን በአየር መንገዱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 10.6 ሚሊዮን መንገደኞች ማጓጓዙ ተጠቅሷል። የሰጠው የጭነት አገልግሎትም ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር፣ 18 በመቶ ብልጫ በማሳየት 400,339 ቶንስ መድረሱን፣ በወጪ ረገድም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር 43 በመቶ በመጨመር፣ 89.1 ቢሊዮን ብር መውጣቱንና የአየር መንገዱ የተጣራ ትርፍም 6.8 ቢሊዮን ብር መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበጀት ዓመቱ፣ ያሉትን የአውሮፕላኖች ቁጥር ከመቶ በላይ በማድረስ፣ በታሪክ የመጀመሪያው አፍሪካዊ አየር መንገድ ለመሆን በቅቷል ተብሏል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከጊኒ አየር መንገድ 49 በመቶ፣ ከዛምቢያ አየር መንገድ 45 በመቶ፣ ከቻድ 49 በመቶ፣ ከሞዛምቢክ፣ ከኢኳቶሪያል ጊኒና ከማላዊ አየር መንገዶች መቶ ፐርሰንት ድርሻ እንዳለው ተገልጿል፡፡
አየር መንገዱ አሁን በዓመት የሚያሰለጥነውን 300 ገደማ የአብራሪዎች ቁጥር፣ ማሰልጠኛውን በማስፋፋት በዓመት 900 አብራሪዎችን ለማሰልጠን መታቀዱን፤ ተርሚናሉን ለማስፋፋትም 350 ሺህ ዶላር በጀት መያዙን፣ በአንደኛው  ምዕራፍ 1,192 ቤቶች ሰርቶ ለሰራተኞች ማስረከቡንና በሁለተኛው ምዕራፍ ፕሮጀክት 1,104 የጋራ መኖሪያ ቤቶች (አፓርትመንቶች) ለመሥራት መታቀዱን ገልፀዋል፡፡
አየር መንገዱ እያስገነባ ያለው ባለ 5 ኮከብ ሆቴል ሆቴል ላይ 80 በመቶ ተጠናቋል፡፡ በአገሪቷ ካሉት ሆቴሎች ከሸራተን አዲስና ከሂልተን ሆቴሎች ይበልጣል ተብሏል፡፡ የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታም 337 ክፍሎች ሲኖሩት፣ በሁለተኛው ምዕራፍ 663 በአጠቃላይ 1000 ክፍሎች እንደሚኖሩት ተገልጿል፡፡
ለአየር መንገዱ ስኬት ቁልፍ ሚና የሚጫወቱት ሰራተኞች በሚከፈላቸው ደሞዝ ደስተኞች አለመሆናቸውን፣ የሚያገኙት ጥቅማጥቅምም የሚያረካ እንዳልሆነ በመጠቆም፣ የተጠየቁት አቶ ተወልደ ፈገግ እያለ፤ “ደሞዝ ቢጨመርልን እኛም አንጠላም፤ የደሞዝ ጣሪያ የሚሰራበት ስኬል ስላለ በዚያ መንገድ ተሰልቶ ነው የሚከፈለው፡፡ ጥቅማ ጥቅማችን አነስተኛ ነው ያሉትን ግን እኔም ሆንኩ አብረውኝ ያሉት የማኔጅመንት አባላት አይስማሙበትም፡፡ ምክንያቱም፣ ካፍቴሪያ ብትገቡ፣ ሽሮ ወጥ በ6 ብር፣ ቀይ ወጥ በ17 ብር ይቀርብላቸዋል፡፡ ለመጓጓዣ 33 አውቶብሶች አቅርናል፡፡ (በአውቶብሶች ቁጥር ብዛት ምናልባት ከአንበሳ አውቶብሶች ቀጥሎ እኛ ሳንሆን አንቀርም) ሆስቴሶችንና በርሰሮችን ከቤታቸው ወደ አየር መንገዱ፣ እንደገናም ወደየቤታቸው የሚያደርሱ በርካታ ተሽከርካሪዎች አሰማርተናል፡፡ መኖሪያ ቤት ሠርተን ለሰራተኞች አስረክበናል፤ ሌሎች ቤቶችንም ለመስራት በዝግጅት ላይ ነን፡፡ … ይኼ ሁሉ ትቅማ ጥቅም አይደለም ወይ? በአፍሪካ፣ ለሰራተኞቹ ቤት ሰርቶ የሰጠ አየር መንገድ የለም፡፡ ትልልቅ ስም ያላቸው የኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ግብፅ … አየር መንገዶች ሰራተኞች፤ እኛ የምንሰጠውን ዓይነት ጥቅማ ጥቅም አያገኙም” በማለት መልሰዋል፡፡
አየር መንገዱ በአፍሪካ ቀዳሚና ትርፋማ ሆኖ ሳለ ለምንድነው ለፕራይቬታይዜሽን የቀረበው በሚል ተጠይቀውም በሰጡት ምላሽ፤ አየር መንገዱ እንዳለ አይደለም ለፕራይቬታይዜሽን የቀረበው፡፡ እንደ አቪዬሽን፣ ካተሪንግ፣ ሆቴል፣ … የመሳሰሉት ክፍሎች ፕራይቬታይዝ ሊደረጉ ይችላሉ፡፡ እኛ የሌሎች አገሮች አየር መንገዶች ድርሻ እንዳለን ሁሉ፣ ሌሎችም ከዚህ ስመ ጥርና ገናና አየር መንገድ ድርሻ እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ” ብለዋል - ዋና ሥራ አስፈፃሚው አቶ ተወልደ ገብረማርያም፡፡

Read 2037 times