Saturday, 18 August 2018 10:10

የአክሰስ ሪል እስቴት ቤት ገዢዎች፤ መንግሥት አፋጣኝ ውሳኔ እንዲሰጣቸው ተማጸኑ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የዛሬ ሳምንት ቦሌ በሚገኘው የአክሰስ ሪል እስቴት ጽ/ቤት፣ ቤት ገዢዎች ያሰሙት የነበረው ጩኸት፣ በደል ደርሶባቸው ሳይሆን የቅርብ ዘመድ የሞተባቸው ያህል አዝነው ነበር፡፡
ጩኸታቸውን ማሰማት የፈለጉት በሰላማዊ ሰልፍ እንጂ በጋዜጣዊ መግለጫ አልነበረም፡፡ የሰላማዊ ሰልፍ ፈቃድ ሰጪው ክፍል “እስከ ዛሬ ታግላችኋል፤ አሁንም በትዕግስት መልዕክታችሁን ለሚመለከታቸው የመንግሥት መዋቅሮች አሰሙ፡፡…” በማለት በለገሳቸው ምክር ተስማምተው፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማካሄድ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን ትተው፣ ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት መገደዳቸውን፣ የአክሰስ ሪል እስቴት ቤት ገዢዎች ኮሚቴ ሰብሳቢ፣ አቶ አክሎግ ስዩም ተናግረዋል፡፡  
“በሪል እስቴት የዜጎች መዘረፍ በእኛ ይብቃ! ሀገር ከሌቦች ፀድታ ትልማ! መንግሥትና ሕግ ባለበት አገር፣ ቤት ገዢዎች ተዘርፈናል፤ ሌቦች በዘረፉት ገንዘብ ፍትህ አዛብተዋል፣…” በሚሉ መፈክሮች ታጅቦ በተጀመረው ስብሰባ፣ ጠቅላይ ሚ/ር ዐቢይ አህመድ ለሚመሩት መንግሥት ባቀረቡት ጥያቄ፤ “በ50ሺ ብር ካፒታል መኖርያ ቤት ሰርቼ አቀርባለሁ” በማለት በአገር ውስጥና በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከ1.4 ቢሊዮን ብር በላይ ሰብስቦ፣ በ6 ዓመት ውስጥ አንድም ቤት ሰርቶ አለማስረከብ፣ ግልጽ ሌብነት ነው ብለዋል፡፡
አክሰስ ሪል እስቴት በተመሰረተ በአምስተኛው ዓመት፣ የድርጅቱ መስራች፣ የቦርድ ሊቀመንበርና ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ ኤርሚያስ ታጠቅ አመልጋ፤ በድርጅቱ ሳጥን ውስጥ 129 ብር ብቻ ሲቀር አገር ጥለው በመኮብለላቸው፣ ቤት ገዢዎች፣ የደረሰባቸውን ግፍና በደል ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትና ለቀድሞ ጠቅላይ ሚ/ር ኃይለማርያም ደሳለኝ ማቅረባቸውን አስታውሰዋል፡፡   አቤቱታቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጽ/ቤት አቅርበው፣ ጽ/ቤቱም የተፈጠረውን ችግር እንዲፈታና ችግሩን ከስር መሰረቱ አጥንቶ፣ የመፍትሄ ሀሳብ እንዲያቀርብ፣ በቀድሞው የከተማ ልማትና ቤቶች ልማት ሚ/ር አቶ ሙኩሪያ ኃይሌ የሚመራ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች ያሉበት ዓቢይ ኮሚቴና ከየሚኒስትሩ መ/ቤቶች ኤክስፐርቶች ያሉበት የቴክኒክ ኮሚቴ ተቋቁሞ፣ ባለ 7 ነጥብ የጥናት ውጤት ለጠቅላይ ሚ/ሩ ቢያቀርብም፣ እስካሁን ድረስ አንዳችም መፍትሔ አልተሰጠንም ብሏል፤ የቤት ገዢዎች ኮሚቴ፡፡
ከቀረቡት 7 ነጥቦች መካከል፣ የአክሲዮን ማኅበሩን ህልውና በተመለከተ፣ ማኅበሩ በሕግ አግባብ የሚፈርስበት አግባብ እንዲፈለግና መብቶቹ ለቤት ገዢዎች እንዲተላለፍ፣ የኩባንያውን የመሬት ይዞታ በተመለከተ፣ ግንባታ ያልተካሄደባቸው ይዞታዎች፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኩል በፍጥነት በአደራ ወደ መሬት ባንክ እንዲገቡ፣ ግንባታ የተጀመረባቸው ይዞታዎች፣ ለግንባታ የወጣው ወጪ በመሃንዲሶች ተገምቶና የኮንትራክተሮች ወጪ ተቀንሶ ወደፊት ለቤት ገዢዎች እንዲዛወር፣ የኦዲት ሥራ ለቀጣይ እርምጃዎች ወሳኝ በመሆኑ በተቻለ መጠን በፍጥነት እንዲጠናቀቅ የሚል ይገኝበታል ያለው ኮሚቴው፤ ኩባንያው፣ ከቤት ገዢዎች በሰበሰበው ገንዘብ የተገዙ ከ30 በላይ የመሬት ይዞታዎች በአደራ ወደ መሬት ባንክ መግባታቸውን፣ ነገር ግን ባዶ መሬቶቹ ከሊዝ አዋጅና ሕግ ውጪ፣ በሕገ ወጥ መንገድ በግለሰቦች ኢ-ፍትሐዊ አካሄድ፣ ከ160 በላይ ቤቶች ገዢዎች ይሰሩበታል የተባለ ቦታ፣ በማያውቁት መንገድ ተሸጦ ማስመለሱንና እንደገናም መሸጡን አመልክተዋል፡፡
በፋይናንስ ኦዲት ሪፖት መሰረት፣ ከተሰበሰበው 1.4 ቢሊዮን ብር ውስጥ ለመሬት ንብረት ግዢ ከ271 ሚ. ብር በላይ፣ ለሥራ ተቋራጮ ከ178 ሚ. ብር በላይ፣ የተለያየ የጥቅም ግንኙነት ላላቸው የተከፈለ ከ245 ሚ. ብር በላይ፣ አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ከኩባንያው የወሰዱት ከ59 ሚ. ብር በላይ፣ በተለያዩ ጊዜያት ለግለሰቦች የተከፈለ ከ66 ሚ. ብር በላይ፣ ለግንባታ ሥራ የዋለ ከ211 ሚ. ብር በላይ፣ ለኮሚሽን የተከፈለ ከ39 ሚ. ብር በላይ፣ ለልዩ ልዩ ወጪዎች ከ125 ሚ. ብር በላይ… ወጪ መደረጉን፣ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ደግሞ ምንም አርዕስት የሌለው ሲሆን የተጠቀሱት ወጪዎች ከተሰበሰበው ገንዘብ በላይ ሲቀነሱ፣ በአጠቃላይ ከ900 ሚ. በላይ መባከኑ ተጠቁሟል። ኩባንያው ለሁለት ዓመት ከ2002-2004 የቦርድ አባላት እንዳልነበሩት፣ አቶ ኤርሚያስ ብቻቸውን እንደሚወስኑ፣ ብቻቸውን ትዕዛዝ እንደሚሰጡ፣ ፋይናንሱንም ብቻቸውን እንደሚያንቀሳቅሱ፣ በውሸት በፈጠሯቸውና አሁን በሌሉ ድርጅቶች ስም ከ59 ሚ. በላይ ወደ ኪሳቸው ከትተው የሚጠይቃቸው አካል ስለሌለ፣ በነፃነት በከተማዋ ይንቀሳቀሳሉ ብሏል፤ ኮሚቴው፡፡
ኮሚቴው ለጠቅላይ ሚ/ር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ባቀረበው ጥያቄ፤ ዜጎች በሀገራቸው የፍትህ ስርአት የሚተማመኑ፣ በነፃነት ሀብት የሚያፈሩባት የጋራ አገር እንድትሆን፣ በአክሰስ ሪል እስቴት ቤት ገዢዎች ላይ የደረሰው በደል፤ በሌሎች ሪል እስቴቶች እንዳይደርስ፣ እንዲያደርጉ፣ ይህ ዓይን ያወጣ ዝርፊያ በእኛ እንዲበቃ፣ አገርም ከሌቦች ፀድታ እንድትለማ ፅኑ እምነት አለንና፣ መንግሥት በገባልን ቃል መሰረት፣ የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጠን፣ በጀመሩት የለውጥ እንቅስቃሴም ለጉዳያችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ቁርጠኛ ውሳኔና አመራር እንዲሰጡልን እንጠይቃለን በማለት ተማፅኗል፡፡   

Read 2820 times