Monday, 20 August 2018 00:00

ኢትዮጵያ የመንፈስ አገር ናት!

Written by  ደረጀ ኅብስቱ
Rate this item
(4 votes)

 የጥንታዊ ዓለም ተመራማሪዎችና የታሪክ ጸሐፍት ስለ ኢትዮጵያ ገናናነትና ልዕልና በብዙ ድርሳናት ውስጥ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
የግሪክ አማልክት ሲደክማቸው ለመዝናናትና እራሳቸውን ለማናፈስ ኢትዮጵያ ነበረች መጠለያቸው፤ የጣና ዳርቻዎችንና የአባይ ፏፏቴን የመዝናኛ መዳረሻቸው አድርገው ሳይጠቀሙበት እንዳልቀረም ይነገራል፡፡ ጥቋቁር ኢትዮጵያዊያን በጦር የማይረቱ ኃያላን እንደ ነበሩ፣ በግሪክና በሮም መንግስታት ዘንድም ብርቱ ተዋጊዎችና የጦር ጀብደኞች መሆናቸው የተመሰከረላቸው ነበሩ፡፡ የቀይ ባሕርን ለንግድ ቀጠናነት እንዲመች በማድረግ እንዲሁም የሕንድ /ምናልባትም በንግስት ሕንደኬ የተሰየመ ውቅያኖስ ሊሆን ይችላል/ ውቅያኖስን ከቻይና እስከ አፍሪካ መዳረሻዎች ድረስ ከባሕር ዘራፊዎች በመጠበቅ የተረጋጋ የንግድ መስመር እንዲሆን በሕንድ ውቅያኖስ ደሴቶች ላይ የጦር ካምፕ አቋቁመው እንደ ነበር የሰነዱ የታሪክ መዛግብትም አሉ፡፡
ከጥንታዊ መጽሐፍት አንዱ “ኦሪት ዘፍጥረት” በተቀዳሚ ገጾቹ ከሚጠቅሳቸው ሃገራት ውስጥ የኢትዮጵያ ስም አንዱ ነው፤ ከህይወት ዛፍ ከግዮን ወንዝና ከጥበብ ጋር በተያያዘ ይጠቅሳታል። ጥንታዊያን ኢትዮጵያዊያን፤ እውቀት የማያልቅባቸው ተመራማሪዎች ተደርገው ስለሚቆጠሩ፣ ኤዞጵ የተባለ ጥቁር፤ በግሪክ ገበያ ላይ ድንገት ቢከሰትና ሊገዙት የሚመጡትን ባላባቶች በፍልስፍናዊ ጥያቄዎች ቢያጣድፋቸው፣ “ይሄ ከኢትዮጵያ የመጣ ቢሆን ነው” ብለው እግሩ ስር ቁጭ ብለው፣ ፍልስፍና ትምህርታቸውን ጀመሩ፡፡ እነ ጻዲቁ ሔኖክ፣ እነ ነብዩ ኤልያስ፣ ዘላለማዊው ካህን መልከ ጸዴቅ፣ እነ ደቂቀ ነብያት አቤሜሌክ ወዘተ … የኢትዮጵያ ቤተኞች እንደ ነበሩ መጻሕፍት ያስገነዝባሉ፡፡” ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ በቅርብ በጻፉት አጭር ጽሑፍ ላይ፡-‹‹ ጣልያኖች ኢትዮጵያን በመያዛቸው፥ “ንጉሣችን የአንድ ጥንታዊትና ታላቅ አገር ንጉሠ ነገሥት ሆነ” ብለው ኩራት ተሰምቷቸው ነበር፤›› ይላሉ፡፡ ፕሪስተር ጆን የሚባል መሲህ ከኢትዮጵያ ተነስቶ በጨለማ ዘመን የነበረችውን አውሮጳን ነፃ እንደሚያወጣት ይተማመኑ ለነበሩ አውሮጳዊያን፤ ኢትዮጵያን መውጋት ኩራት ቢሆናቸው አይደንቅም፡፡ በነብዩ ኢሳያስ፤ ‹‹ኀይለኛ ሰው፤ በአለባበሱም ግሩም የሆነ ይህ ማነው?›› የተባለላት ኢትዮጵያ ትመስለኛለች፡፡
ለዘመናችን ሳይንሳዊ ትንታኔ የሚያስቸግሩ፣ በምህንድስና ጥበብ ተራቅቀው፣ በጥንታዊው ሰው ዘንድ የታወቁ ከሚያደርጋቸው ስራዎቻቸው መካከል የአክሱም ሐውልትና ባሁኑ ጊዜ በሰሜን ሱዳን ኑብያ እንዲሁም ግብጽ /ምስር/ ውስጥ የሚገኙት ፒራሚዶች ማስረጃ እንደሆኑ የሚጠቅሱ መጽሐፍትም አሉ፤ በመካከለኛው የታሪክ ዘመንም ወለል ያለውን የላሊበላ አለት ሜዳ ፈልፍለው፤ ያምላክ መታሰቢያ በመስቀል ቅርጽ፤ የምድር ውስጥ ከተማ ህንጻ ማነጽ፤ አዲስ የጥበብ ብስራቶች ነበሩ ለመላው ዓለም። ጁሊያና ቦናቼ የተባለች ተመራማሪም፤ በዓለም ላይ የኢትዮጵያ መንፈስ ቀበቶ ሰርቶ ተጠምጥሞ ነበር ትላለች፡፡ የፀረ ባርነት ትግልን በዓለም ላይ በተለይም ጥቁር አፍሪካዊያን በያሉበት የዓለም ክፍል ሁሉ እንዲያቀጣጥሉት የመንፈስ ብርታት የሆነቻቸው ኢትዮጵያ ናት፤ እናም ይህ የኢትዮጵያ መንፈስ ፀረ ባርነት እንቅስቃሴው በዓለም ካርታ ላይ እንደ ቀበቶ ተነጥፎበት ነበር፡፡ ከኢትዮጵያ ተነስቶ ወደ ታች በታንዛኒያ እስከ ደቡብ አፍሪካ ይወርድና የአፍሪካ ዳርቻዎችን እየዳሰሰ፣ ወደ ማዕከላዊና ምዕራብ አፍሪካ ከወጣ በኋላ የአፍሪካ ደሴቶችን እየነካካ፣ በአትላንቲክ ውቅያኖስ ወደ ላቲን አሜሪካ ደሴቶች ተሸጋግሮ፣ ሰሜን አሜሪካ ድረስ የጥቁሮችን የነፃነት መንፈስ በመቀስቀስ ቀበቶ ሰርቷል ትላለች - ተመራማሪዋ ጁሊያና ቦናቼ፡፡
ፈጣሪ ለኢትዮጵያዊያን ቅዱሳት በሰማይ ላይ ሰሌዳ ዘርግቶ የተለያዩ የእንስሳት ምልክትን እየመሰለ፣ በጽሑፍ መነጋገርና ምልክቶችም ቋንቋ መሆናቸውን አስተምሯቸዋልና፣ የጽሑፍ ጥበብን ከጥንት ጀምሮ በመጠቀምና ጥንታዊ መጽሐፍትን ጠብቆ ለትውልድ በማውረስ፣ ኢትዮጵያዊያንን የሚተካከሉ እጅግ ጥቂት አገራት ቢሆኑ ነው ሺ ዓመታትን ያስቆጠረው የዓለም የመጀመሪያው በስዕላዊ መግለጫ የተዋበ ወንጌል፣ ኢትዮጵያ ውስጥ አለ፡፡ ከአለም ላይ ጠፍቷል ተብሎ የነበረው “መጽሐፈ ሔኖክ” የተገኘው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፤ በቀሪው ዓለም በተለያዩ ጦርነቶችና ዝርፊያ ወድሞ የነበረው “የዮሐንስ ራዕይ” ሙሉ ሆኖ የተገኘው፣ በዚችው በእኛዋ ድሃይቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡
ኢትዮጵያ እንደ ዖፈ ብርጋባ የከበረ እንቁን የምትጥል ፍጡር ትመስለኛለች፡፡ የአስተሳሰብ ችጋር፣ የማደጎ ልጆች፤ በሃገር ውስጥ ሲበዙና ገዢ ሲሆኑ ታላቋ ኢትዮጵያ ከዓለም መድረክ ላይ ትጠፋና በውስጧ ላለነውም የማትበቃ ችጋራም ትሆናለች፤ ታሪኳ ለገዛ ዜጎቿም ተረት ተረት ይሆናል፡፡ የውስጣችን ስንፍናና የአዕምሯችን መጫጨት፣ የሃገራችንን ታሪክና ክብር አጫጭቶ ያሳየናል፤ ሳንጠራጠርም ሳንመራመርም አምነን፣ የጫጨው አዕምሯችን የሚያፈልቀውን ጭባ እውቀት አግዝፈን እንቀበላለን። አቅማችንን ከማጎልበትና ድካምን ሳይፈሩ ከመታተር ይልቅ የስንፍና አቋራጭ መንገዶችን እንደ መጨረሻ መዳረሻችን እንቆጥራቸዋለን፡፡ የታሪክ ማፈሪያዎች መሆናችንን አዕምሯችን እንዳያሳብቅብን፣ ኑሯችንን በተብለጭላጭና ፊታችንን በሜክአፕ እናስውባለን፡፡ ልባችን ግን አመዳም ብቻ ሳይሆን ጨለምተኛም ነው፡፡
በዓለም የታሪክ መድረክ እዚህ ግቡ የማይባሉ የቅርብ ጊዜ አገራትን እንደ ስልጡን ህዝቦች ለልጆቻችን እያስተማርንና ፖሊሲዎቻችንን በዚያው መርህ እየቀረጽን፣ አገራችንን አዋርደን፣ እኛም ወራዳነታችንን እናጌጥበታለን፡፡ በተቃራኒው አያሌ አገራት፣ የእኛኑ ታሪክ እየመረመሩና ጥንታዊውን ጥበባችንን እየቀሰሙ በእኛው ታሪክ ሲከብሩና ሲመኩ እናያለን ሳንታክት እናነባቸዋለን እናጣቅሳቸዋለን እንጅ የኛው ታሪክና ጥበብ ነው ብለን ወደ ራሳችን ለመመለስ እንኳ ዝንባሌ አናሳይም፡፡ እኛው እራሳችንን አዋርደን፣ አዋርደው ለሚገዙን በሽያጭነት እናቀርባለን፤ እረክሰን አገራችንን እናራክስና “እርካሽ የሰው ኃይል ያለባት አገራችን የአለም የኢንቨስትመንት መስህብ ትሆናለች” እንላለን። ጥንታዊው ያባቶቻችን ትምህርት ግን ሌላ ነው፡፡ ‹‹አንተ ግን ለኢትዮጵያዊያን የዘላለም ምግባቸውን ሰጠሃቸው›› ይላል መዝሙረኛው ዳዊት፡፡
የግሪክ አባቶች የውኃ፣ የጉም፣ የጭጋግ አማልክት እያሉ ለልጆቻቸው ያስተማሩትን እንደ ትልቅ ጥበብና እውቀት በዩኒቨርሲቲ ደረጃ እያስተማርን፤ እነ ክርስቶስ ሠምራ መናፍስትን ለማስታረቅ በምልጃ፤ በሱባዔ ጦም ጸሎት ስግጃ የተጋደሉትን ተጋድሎ የእኛው ስለሆነ እንደ ተረት ተረት እንቆጥረዋለን፤ የተጋደሉትን ገድል ታሪክ የሰለጠኑት ዓለማት የራሳቸው ቢሆን ኖሮ፣ በፊልምና በመጽሐፍቶቻቸው አስውበው አስፍረው፣ ለልጆቻቸው ስለ ጽናትና የህይወት ተጋድሎ ምርጥ ማስተማሪያ ያደርጉት ነበር፡፡ የታሪክ እንቁዎችን ማምከን ተክነንበታልና የታሪክ አጋጣሚ ሆነና የእኛው መቀለጃ ሆነ፡፡ ለብራና ጽሕፈት የሚጠቀሙበት ቀለም፣ ለሺዎች አመታት መቆየት እንደሚችል አስመስክሯል፤ ግንብ ሲገነቡ የሚያቦኩት ኖራ፣ የተገነባውን ድንጋይ አጣብቆ ይዞ ለሺዎች አመታት መቆየት እንደሚችል አስመስክሯል፤ ነገር ግን እንደ መጤ ቱሪስት ከስሩ ቁጭ ብለን ፎቶግራፍ እንነሳለን እንጅ ጥበቡ ያባቶቻችን ነውና እኛም እንካንበት እንጠበበው አንልም፡፡ አባቶቻችን ግን ‹‹መንፈስ ሁሉንም ያውቃል›› ይላሉ፡፡
ኢትዮጵያ አፈር፣ ድንጋይ፣ ባህር፣ ዳርድንበር፣ ደን፣ ሳር ምድር ብቻ አይደለችም፤ ኢትዮጵያ መንፈስ ናት። ኢትዮጵያ ስለ ሰው ልጆች ሁሉ ደህንነትና ብልጽግና የሚጸለይባት፤ ለዜጎቿ ብቻ ሳይሆን ለዛፎች፣ ለወንዞች፣ ለዱር አራዊት፣ ለአእዋፍትና ለመላ ፍጥረታት በሙሉ ይጠግቡ ይሞሉ ዘንድ እለት ተእለት ምልጃ የሚቀርብባት አገር ናት፡፡ በሼህ ሁሴን ትንቢት የክፋት መንፈስ ብን ብሎ እንደሚጠፋና መልካምነት መልሶ በኢትዮጵያ አየር ላይ እንደሚናኝ ስለሚነገር ዘወትር እንጓጓ ነበር፡፡
ሰው ስጋና ደም ብቻ አይደለም፤ መንፈስም ጭምር ነው፤ አዳም ከአፈር ከተሰራ በኋላ የአምላኩ መንፈስ እፍ ተብሎበታልና ይቺ እፍታ ከአዳም ጀምሮ በዘመን ቅብብሎሽ ደመ ነፍሳዊ እውቀትን ታስተላልፋለች፤ ስለዚህም የሰው ልጅ “ከአፈር በላይ መንፈስ ነኝ” ብሎ መንፈሳዊ ብቃቱን ካጎለበተ፣ በውስጡ ያለውን ጥንታዊ እውቀት እየፈነቃቀለ እያወጣ የመጠቀም እድሉን ይቀዳጃል፡፡
ኢትዮጵያን ከስጋና ደም ባሻገር፤ ከአፈርና ውሃ፤ ከዱርና ሸንተረር እንዲሁም ከዳር ድንበር ባሻገር የመንፈስ ሃገር መሆኗን የሚገነዘብላት ህዝብና መሪ የምትሻ ይመስለኛል፡፡ በማርክሲስታዊ፣ ዲሞክራያሲያዊ፣ ልማታዊ አሊያም አብዮታዊ ቋንቋ ሳይሆን በኢትዮጵያዊ ቋንቋ የሚያነጋግራት የምትፈልግ ይመስለኛል፡፡ የኮብልስቶን ወይም የህንፃ ጋጋታ አሊያም የአስፋልት ዝርጋታ አሊያም የትራክተሮች እርሻ ቡረቃ ሳይሆን፤ በራሱ በኢትዮጵያዊነቱ የበቃ የነቃ ትውልድን የምትሻ ይመስለኛል፡፡
በዝናቧ የማይቋሸሽ፣ በአቧራዋ የማይሸማቀቅ፣ በጭቃዋ የሚንቦራጨቅ፣ ከእነወዟ የሚወዛባት የሚኮራባትን የመንፈስ አርበኛ ትውልድ የምትሻ ይመስለኛል፡፡ የጥንታዊ ገናና ጉዞዋን ለመጀመር እያኮበኮበች ያለችውን ኢትዮጵያ “እንኳን ደህና መጣሽ” ማለት ያለብኝ ይመስለኛል፡፡
ኢትዮጵያ ከቁሳቁስነቷ ይልቅ መንፈስነቷ ገዝፎ ይታየኛል፤ የምትሻውን አይነት ትውልድ ካገኘች አለት ተጠርቦ እንዴት ለሺህ አመታት መቆም እንደሚችል ወይም የመሬት ንጣፍ አለትን እየቦረቦሩ የምድር ውስጥ ከተማ እንዴት እንደሚቆረቆር ለማስተማር የሚያግዳት ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡
ሲጀመር በህገ ልቦና፣ ከዚያም ትዕዛዛተ ኦሪት፣ ከዚያም የወንጌላዊያንን ትምህርት፣ ቀጥሎም የነብዩን ትምህርት ከነ ዘመዶቻቸው ማስተናገድ የቻለች የዓለማችን ልዩ አገር ናት - ኢትዮጵያ፡፡ ሃበሾች ሲነሱ በግርማ፤ሊታይ የድንጋይ ጥበባቸው ማማ፤ ወዲያውም ፍጻሜ ሊሆን ለክፋት፤ የኢትዮጵያ መንፈስ ይነግሳል በፍካት፤ጴጥሮስ ዓለት ሆኖ የመሠረታት፤ የኢትዮጵያ መንፈስ አዋቂናት።  በመጀመሪያ የእግዚአብሔር መንፈስ በውሆች (በግዮን) ላይ ሰፍፎ ነበር ይላል መጽሐፉ፡፡

Read 5121 times