Saturday, 11 August 2018 10:58

“የአበሻ መኪና አነዳድ፤ በሌላው መንገድ መገድገድ የአበሻ ንግድ፤ የሌላውን ትርፍ ማሽመድመድ”

Written by 
Rate this item
(19 votes)

 ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ጫካ ውስጥ አንድ ነብርና አንድ አጋዘን ብቻ ይቀራሉ፡፡ ነብሩ፤
“ይሄን አጋዘን ብበላው ሌላ ምንም የዱር አውሬ አይኖርምና ብቻዬን እቀራለሁ” ብሎ ያስባል፡፡ “ስለዚህ እንደ ምንም ላግባባውና በእኩልነት ተስማምተን የምንኖርበትን ዘዴ ልፍጠር” ይላል፡፡ አጋዘኑ ግን ነብሩ ይበላኛል ብሎ በመፍራት ፈፅሞ እንዳያገኘው ለማድረግ ሁሌ ይደበቀዋል፡፡
አንድ ቀን አጋዘኑ ሸሽቶ የሚያመልጥበት አጣብቂኝ ቦታ ተገኘ!
አያ ነብሮም፤
“ወዳጄ አጋዘን ሆይ! አንተን አገኝ ዘንድ ብዙ ጊዜ ደከምኩ፡፡ ነገር ግን አውቀህም ሆነ ሳታውቅ አልገኝ አልከኝ፡፡ የፈለግሁህ ለሁላችንም ለሚበጅ ብርቱ ጉዳይ ነው፡፡”
አጋዘኑም፤
“ምን ይሆን ይሄ ብርቱ ጉዳይ?” ሲል በመጠራጠር ጠየቀ፡፡
አያ ነብሮም፤
“ውድ አጋዘን፤ እንደምታውቀው በዚህ ጫካ የተረፍነው እኔና አንተ ብቻ ነን፡፡ ጠላት እንኳ ቢመጣብን በየፊናችን ብንታገል ለጥቃት የተጋለጥን ነን፡፡ አንድ አይነድ አንድ አይፈርድ ሆነናል፡፡”
አጋዘን፤
“እና ምን እናድርግ ነው የምትለው? ምን ይበጀናል?”
“የሚበጀንማ ላንነካካ ተስማምተን፣ የየግላችንን ምግብ ከሌላ ጫካ አድነን መብላት ነው፡፡ ስለዚህ ማንም ማንንም ላይነካ ተዋውለን በሰላም እንኑር፡፡”
አጋዘን ጥቂት ካቅማማ በኋላ፤
“በሀሳቡ እስማማለሁ፡፡ ለማንኛውም ግን መማማል ጥሩ ነው፡፡ በመሃላ እንተሳሰር፡፡ እሺ ካልክ እንማማል፡፡ ጉዳዩን ለፈጣሪ እንስጠው፡፡”
“እኮ በምን እንማማል?” አለ ነብሮ፡፡
አያ አጋዘንም፤
“እዚህ ጫካ ውስጥ እስከኖርን ድረስ ላትነካኝ ላልነካህ በፈጣሪ ፊት እንማል፡፡ ማንም ማንንም ቢነካ፣ በልጅ ልጁ ይድረስ!”
ነብሮም ደግሞ፤
“ማንም ማንንም ቢነካ በልጅ ልጁ ይድረስ! እኔም በልጄ፣ አንተም በልጅህ ይድረስ!”
“ይድረስ!” አለ አጋዘን፡፡
“ይድረስ” አለ አያ ነብሮ፡፡
በስምምነታቸው መሰረት፤ ነብሮም ባሻገር ካለው ጫካ የሚበላ ፈልጎ ይበላል፡፡ አጋዘንም ወደ ሌላ ጫካ እየሄደ፣ የዕለት ምግቡን ያሰናዳና ይበላል፡፡ በዚህ ዓይነት ብዙ ጊዜ በመከባበር አብረው ኖሩ፡፡
በአካባቢው ያሉትን ጫካዎች ነብሮ እያሰሰ ሲያድንና ሲመገብ ቆይቶ፣ ቀስ በቀስ ደኑም፣ ጫካውም እየተራቆተ መጣና የሚያድነው እንስሳ አጣ፡፡ ተራበ!
አንድ ቀን አንድ የሸለቆ ዋሻ ውስጥ በወዲያኛው ወገን መውጪያ በሌለው ሁኔታ አጋዘን አንድ ዛፍ ቅርንጫፍ ላይ ሲንጠለጠል ከኋላ ላቱና ታፋው አለትልቶ አስጎምዢ ሆኖ ሳለ፤ አያ ነብሮ ምራቁ ተዝረከረከ። ሆዱን ሞረሞረው! አመንትቶ ሲያስብ ከረሀቡ የሚብስ ነገር አልመጣልህም አለው፡፡ “መሀላ ማፍረስ ምን ይጎዳኛል?” አለ፡፡ ወሰነና ወደ አስጎምዢው የአጋዘን ገላ ተምዘገዘገ!
ሆኖም! ነብሮ ከመጎምዠቱ የተነሳ አጋዘኑን አልፎ ሄደና በሆዱ አጋዘኑ ቀንድ ላይ አረፈ፡፡ የአጋዘኑ ቀንድ የነብሮን ሆድ ዘንጥፎ ጣለው! ነብሮ ሊሞት ማጣጣር ጀመረ!! እንደምንም እያቃሰተ፤
“አያ አጋዘን፤ እንዳንነካካ አልተማማልንም ነበር?” አለው፡፡
አጋዘንም፤
“አያ ነብሮ! ያንተ አያትና ቅድመ አያት ከእኔ አያቶች ጋር ምን እንደተማማሉ ምን አውቄ?!” አለው፡፡
*   *   *
የኢትዮጵያ ጣጣ ብዙ መዘዝ አለው! የአያት ቅድመ አያቶቻችንን ቂምና ማላ ስናስተናግድ፤ የዘር ማንዘራችንን በደልና ግፍ ስንቆጥር ዘመናት አሳልፈናል! ተረኛ ነብሰ - ገዳይ የማንገስ ያህል፤ ከጦር ካምፕም (Barrack)፣ ከጫካም (field) ገዢና መሪ እየቀያየርን፣ ሎሬት ፀጋዬ እንዳለው፤
“እንተዋወቃለን - ሱማሌ ተራ ሞተር ቅርጫ ገበያ! ስርዝ ያንተ፣
ድልዝ የኔ፣
እመጫት የእሷ፤ ሆያ ሆዬ
የሰፊው ህዝብ ስንባባል፤ እንተዋወቃለን”… እያልን ከረምን፡፡ ዕውነትም የፖለቲካው ተዋንያን ሰፊው ህዝብ የማያውቃቸው ፀጉረ - ልውጥ ሲሆኑ፤ ህዝብ ፍዝ - ተመልካች ይሆናል (Passive audience እንዲሉ)፡፡
ዳር ቆሞ ማስተዋል ብቻ! ሆ ማለት ብቻ! ህዝብ እንደ ደላላ አካሄድ “ባየ-በሰማ” የሚባል አይደለም፡፡ ካላሳተፍነው ዛሬም “የምታቀኝ የማላውቅህ” ይባላል፡፡ “ውሸትክን ፈጥጠህ ሳቅሁ ባይ” የሚባለውን ዓይነት ይሆናል - ክፉኛ ይታዘበናል፡፡ ውሎ አድሮም ያስከፍለናል! እንደ “ማነው ምንትስ” (እሳት ወይ አበባ)
“ሥራችንን ወስደውብን
ስሙን ብቻ በተዉልን”
ብሎ ህዝብ አይተወንም፡፡ በገዛ ኃብቱ፣ በገዛ ስልጣኑ እየተሞናደልን፣ ‹ላንተ ስንል ፎቅ ሰራን፣ ላንተ ስንል ቪ-ኤይት መኪና ነዳን፣ ላንተ ስንል ልጆቻችንን ውጪ አገር ውድ ትምህርት ቤት አስገባን› ቢሉት፤ ትዝብቱ ከስላቅና ምፀት ጋር ይሆናልና በታሪክ እጠይቅሃለሁ ማለቱ አይቀሬ ነው! ዛሬ ቢያንስ የፊት ለፊት ሸፍጥ ቀርቷል፤ እንላለን፡፡ መረጃ መደበቅም፣ ዕውነት አስመስሎ የተንሸዋረረ መረጃ መስጠትም፤ ያስጠይቃል። ያሳጣል!! ያስፈርዳል!! በዘልማድ ገዢን እያወደሱ ማስጨብጨብም ሆነ ማጨብጨብ፤ መልሶ አሳፋሪ የሚሆነው ለእኛው ነው!! በኢትዮጵያ የፖለቲካ ዐውድ ላይ ለእኔ ሰፋ ያለና የተለየ ማዕረግ ካልተሰጠኝ ብሎ መመኘት፣ ዛሬ ከስግብግብነት ያለፈ ፖለቲካዊ ሙስና ነው! ቢያንስ የፈረንሳይን አብዮት ተልዕኮ ማለትም፡- “ነፃነት፣ እኩልነትና ወንድማማችነትን” እናፅና! እንፅናና!! የኢትዮጵያ በር ተከፍቶ፣ “ኑ ልጆቼ!” አለች የተባለው ቢያንስ ለመሞሻለቅና ውሻ በቀደደው ጅብ እንዲገባ ለማድረግ እንዳልሆነ ከህሊናችን ጋር ያለን ሁሉ፤ አንስተውም!! ችግራችንን በጋራ እንፍታ ለመባባል እንጂ አሁንም ዘራፍ ለማለት፣ አሁንም ጠባብ ስሜት ለመቧቸርና “እኔ በትልቁ ስታዲየም ልጫወት፤ አንተ በትንሿ ስታዲየም ተጨዋት” ለመባባል አይደለም!! እኔ እንደ ልቤ የምሄደው የሌላውን መንገድ አጥሬ ነው ማለት የወረደ አካሄድ ነው፡፡ እኔ የማድገው ሌላውን ቀብሬ ነው የሚል አስተሳሰብ አደገኛ ነው፡፡ አለበለዚያ ፀጋዬ ገ/መድህን እንዳለው፡- አሁንም “የአበሻ መኪና አነዳድ፤ በሌላው መንገድ መገድገድ!
የአበሻ ንግድ፣ የሌላውን ትርፍ ማሽመድመድ!” ይሆንብናል፡፡ ከዚህ ይሰውረን!!

Read 9504 times