Saturday, 11 August 2018 10:28

‹‹ለኑሮ ውድነት ዋነኛው ምክንያት የሊዝ ፖሊሲ ነው››

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(3 votes)

 - የሊዝ ፖሊሲን ለኢትዮጵያ የሰጠው ሻቢያ ነው የሚለው ሀሰት ነው
   - በሀገራችን መሬትን በሊዝ መስጠት የጀመሩት አፄ ምኒልክ ናቸው
   - የኤምባሲዎች ይዞታ በሊዝ ሊመዘገብ ታስቦ ነበር

    ኢንጅነር ሣህሉ አለማየሁ በ1952 ዓ.ም ነው የተወለዱት - በአምቦ ግንደበረት፡፡ ትምህርታቸውን በወለንኮሚ አንጩና አምቦ ማዕረገ ሕይወት 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል፡፡ ከተማ ፕላን ኮሌጅ በመግባትም፣ በሲቪል ምህንድስና ከተመረቁ በኋላ ከሐምሌ 1975 እስከ ሚያዝያ 1988 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት፣ በቦታና ቤት አስተዳደር ክፍል በከፍተኛ ቴክኒሻንነትና በቴክኒክ ጉዳዮች አማካሪነት አገልግለዋል፡፡ ‹‹ከተቀጠርኩበት ኃላፊነት በተጨማሪ ሀገርና ሕዝብን ሊጎዱ የሚችሉ ናቸው የምላቸው ሕጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ሲወጡ ለማስቀየር እሟገት ነበር›› የሚሉት ኢንጅነር ሣህሉ አለማየሁ፤ ‹‹በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን ለሚታየው የኑሮ
ውድነት ዋነኛው ምክንያት የሊዝ ፖሊሲ ነው›› ብለው እንደሚያምኑ ይናገራሉ፡፡ መሬትን በኪራይ የሚያሲዘው ፖሊሲ እንዳይጸድቅ አጥብቀው እንደታገሉ የሚናገሩት ኢ/ር ሣህሉ አለማየሁ፤ ከአዲስ አድማስ ጸሃፊ ብርሃኑ ሰሙ ጋር በሊዝ ዙሪያ ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡


     መሬትን በኪራይ ማስያዝን በተመለከተ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ታሪክ ምን ይመስላል?
የመሬት ኪራይ ይዞታ ሥርዓትን የፈጠሩት ቅኝ ገዥዎች ናቸው፡፡ የቅኝ ተገዥ ሀገር ዜጎች የእርሻ መሬታቸው፣ የተፈጥሮ ማእድን ሀብታቸው፣ የከተማ ይዞታቸው …  የእኔ ነው የሚል የባለቤትነት ስሜት እንዳይሰማቸውና በሂደት ከገዛ ሀገራቸው እንዲፈናቀሉ ታስቦበት የተሰራ ነው፡፡ በቅኝ ግዛት በርካታ የዓለም ሀገራትን ተቆጣጥራ የነበረችው እንግሊዝ፣ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ በስፋት ተንቀሳቅሳለች፡፡ መሬትን በኪራይ የመስጠት አሰራር፤ የቅኝ ተገዢዎችን ቀልብ እንደሰለበ፣ ሀሳብና ምኞታቸው እንዲቀጭጭ ማድረጉን የተረዱ በርካታ ቅኝ ገዢዎች ይህንን አሰራር ተግባራዊ አድርገውታል፡፡ የመሬት ኪራይ ይዞታ ውል ሲጀመር የጊዜ ገደቡ አንድ ሺህ ዓመት ነበር። በኋላ ነው 999 ዓመት እንዲሆን የተደረገው፡፡ ሆንግ ኮንግና ታይዋንን የመሳሰሉ ትናንሽ ሀገሮችና ደሴቶች በሊዝ ኪራይ ተይዘው ለብዙ ዓመታት የቆዩት በዚህ መልኩ ነበር፡፡
በሀገራችን  መሬትን በኪራይ የማስያዝ ሀሳብን ለኢሕአዴግ የሰጠው የኤርትራ መንግስት (ሻቢያ) ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ በተቃራኒው ኢሕአዴግ በትጥቅ ትግል ጫካ በነበረበት ወቅት ለአስተዳደር እንዲመቸው ከቀመራቸው እቅዶች አንዱ ነበር የሚሉ ወገኖችም አሉ፡፡ የትኛው ነው እውነቱ?
ሁለቱም መላምት እንጂ እውነት አይደሉም። መሬትን በኪራይ ማስያዝ በሚለው ዓለም ዓቀፍ ታሪክ ውስጥ ሀገራችን ኢትዮጵያም ከአንድ መቶ ዓመት በፊት ያስመዘገበችው ታሪክ አለ፡፡ ከጅቡቲ አዲስ አበባ የባቡር መስመር ዝርጋታ ሲጀመር፣ አፄ ምኒልክ ለፈረንሳይ መንግስት የጅቡቲን ወደብ በኪራይ ሲሰጡ አንዱና ዋናው አከራካሪ ጉዳይ የኪራይ ዘመኑ ነበር፡፡ ፈረንሳይ ያቀረበውን አንድ መቶ ዓመት፤ አንድ ዓመት በማስቀነስ 99 ዓመት ያስደረጉት አፄ ምኒልክ ነበሩ፡፡ ሀገራችንን ጨምሮ በብዙ አገራት የሊዝ ኪራይ ዘመን 99 ዓመት የሆነው ይህንኑ መነሻ በማድረግ ነው፡፡
መሬትን በኪራይ የማስያዝ ሀሳብ የመነጨው ከሻቢያ ተለግሶ ወይም ኢሕአዴግ ቀደም ብሎ አስቦበት ሳይሆን በ1983 ዓ.ም የመንግስት ለውጥ እንደተደረገ የከተማ መሬት አሰጣጥና የተገልጋይ መስተንግዶን በተመለከተ ውዝግብ ተፈጥሮ ነበር። በየካቲት ወር 1985 ዓ.ም ችግሩን ለመቅረፍ ምን ይደረግ ? የሚል ሀሳብ ተነሳ፡፡ በዚህ ምክንያት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር (በወቅቱ ክልል 14 ይባል ነበር) አንድ የኤክስፐርቶች አጥኚ ቡድን ተቋቋመ፡፡ ቡድኑ “የመሬት ይዞታ ስሪት ሊዝ ብቻ መሆን አለበት›› በሚል አቋም፤ አዲስ የሚሰጥ ቦታ ብቻ ሳይሆን ነባር የመንግስትና የግል መኖሪያ ቤቶች፣ መንግስታዊና ሕዝባዊ ድርጅቶች፣ የግል ድርጅት ባለይዞታዎች በሙሉ በሊዝ በመመዝገብ አዲስ ካርታ መውሰድ አለባቸው በማለት ጥናቱን በወቅቱ ከንቲባ ለነበሩት አቶ ተፈራ ዋልዋ አቀረበ። እኔ የከንቲባው የቴክኒክ ጉዳዮች አማካሪ ስለነበርኩ በአጥኚ ቡድኑ የቀረበውን ሃሳብ ተቃወምኩ፡፡
ጥናቱን የተቃወሙበት ምክንያት ምን ነበር?
የሊዝ ይዞታ ስሪት ለውጭ ዜጎች እንጂ ለኢትዮጵያዊያን ተግባራዊ መሆን የለበትም የሚል ነበር ተቃውሞዬ፡፡ ከንቲባው ተቃውሞዬን ስላልተቀበሉት ጥናቱን ወደ ክልል 14 ምክር ቤት ወስደው በማስፀደቅ ‹‹በአዲስ ነጋሪ ጋዜጣ›› አዋጅ ሆኖ ወጣ፡፡ አዋጁ በሕዝቡ ዘንድ አነጋጋሪና አጨቃጫቂ ስሜት ስለፈጠረ የሽግግሩ መንግስት ጣልቃ በመግባት፣ ክልል 14 መስተዳድር ያወጣው አዋጅ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት እንደገና ተጠንቶ እንዲቀርብ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ታምራት ላይኔ በደብዳቤ አዘዙ፡፡ ጥናቱ ዳግም ለውይይት ሲቀርብ በመጀመሪያም ብቸኛው ተቃዋሚ ስለነበርኩ የተቃውሞዬን ምክንያቶች እንዳብራራ ተጠየቅኩ፡፡
1ኛ- ነባር የመንግስትና የግል ቤቶች በሊዝ ስርዓት አስገዳጅነት በግል ይዞታ ውስጥ ከገቡ በከፍተኛ የሊዝ ክፍያ ምክንያት የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ ስለሚጨምር ዜጎችን በረንዳ አዳሪ ያደርጋል፣
2ኛ- የመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ የግልና ሕዝባዊ ድርጅቶች በሊዝ ኪራይ ይዞታ ውስጥ ከገቡ በሚሰጡት አገልግሎት ላይ ከፍተኛ ዋጋ ስለሚጭኑ ተገልጋዩ ይጎዳል፣
3ኛ- ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች ይዞታቸው በሊዝ ይግባ ከተባለ ነፃ የትምህርትና ነፃ የሕክምና አገልግሎት የመስጠት ዕድሎች ታሪክ ይሆናል፣
4ኛ- የሊዝ ፖሊሲ የዜጎችን ብሔራዊ ስሜትና ፍቅር፣ ክብርና ነፃነት፣ መብትና ግዴታ፣ ጥቅምና ድጋፍ … ያሳጣል፡፡ በዚህም ምክንያት በሀገርና በዜጎች ላይ ከጊዜያዊነት ያለፈ ዘለቄታነት ያለው ጉዳት ያስከትላል በሚል ምክንያቶቼን አቀረብኩ፡፡
የሊዝ ስሪት በኢትዮጵያ በሚኖሩ የውጭ ሀገር ዜጎችና ድርጅቶች ላይ ተግባራዊ ይሁን ያሉበት ምክንያትስ ምን ነበር?
ለዚህም ምክንያቴ ለዜግነት መብትና ክብር ቅድሚያ እንዲሰጥ ለማሳሰብ ነበር፡፡ በሊዝ ፖሊሲ ኢትዮጵያዊያን በሀገራቸው ዘላቂ ባለመብት አይሁኑ እየተባለ፣ በተቃራኒው የውጭ ሀገር ዜጎች የተሻለ ባለመብት መሆናቸው የሚታይበት ሁኔታ አለ፡፡ ለምሳሌ የንጉሥ ኃይለሥላሴ መንግስት ከቼኮዝላቪያ ጋር በነበረው ወዳጅነት ምክንያት በአዲስ አበባ ከተማ ብሔራዊ ቴአትር ፊት ለፊት፣ ውሀ ልማት ጀርባና የካዛንችስ ግቢ (የማርሻል ቲቶ ቤት ያለበት)፤ ሦስቱ ይዞታዎች ያለ ሊዝ ውል በመሰጠታቸው፣ ፤ቼኮዝላቫኪያዊያን ‹‹ቼክ›› እና ‹‹ስሎቫኪያ›› በሚል ለሁለት ሲነጣጠሉ፤ በቼኮዝላቫኪያ ስም ተመዝግቦ የነበረውን የአዲስ አበባ ይዞታ ለሁለት ተካፍለውታል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ በመሬት አዋጁ ትልቅ ለውጥ ያመጣው የደርግ መንግስት እንኳን በእነዚህና መሰል የውጭ ሀገር ዜጎች በተያዙ ይዞታዎች ላይ ምንም ማድረግ አልቻለም፡፡
በአፄዎቹ ዘመን ለዲፕሎማቲክና ዓለም አቀፍ ተቋማት ያለ ሊዝ ውል ስምምነት በስማቸው ወይም በሽያጭ ሰፋፊ መሬት ተሰጥቷል፡፡ በዚህ ምክንያት አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ሩሲያ፣ ጣሊያንና ሌሎችም የያዙት ሰፋፊ መሬቶች የኢትዮጵያ አይደሉም፡፡ ኤምባሲዎቹና ዓለም አቀፍ ተቋማቱ መሬቱን በወሰዱበት ዘመን በሊዝ ይዞታ ስሪት በዓመታት ጊዜ ገደብ በስምምነት ቢሰጣቸው ኖሮ፣ የሀገራችን መሬት በነጠብጣብ ቅኝ ግዛት ስር ባልወደቀ ነበር በሚል ማብራሪያ ሰጠሁበት፡፡
የሊዝ ይዞታ ስሪት በኢትዮጵያዊያን ላይ ሳይሆን በውጭ ሀገራት ዜጎችና ተቋማት ላይ ነው ተግባራዊ መሆን ያለበት ብዬ ስከራከር፣ አፍሪካ አንድነት ድርጅት (አሁን አፍሪካ ህብረት) እና አፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በዚህ ውስጥ መካተት እንደሌለባቸው አመላክቻለሁ። በወቅቱ ከንቲባ የነበሩት የአቶ ተፈራ ዋልዋ ፍላጎት የተሻለ ነው የሚባል የመሬት ይዞታ ስሪት እንዲኖር እንጂ ከጀርባው ሌላ ተልዕኮ የያዘ ሀሳብ አልነበራቸውም። ‹‹በአዲስ ነጋሪ ጋዜጣ›› የወጣው አዋጅ ከተሻረ በኋላ በኤምባሲዎችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ስር ያለው መሬት በሊዝ ይመዝገብ የሚለው ሀሳብ ተቀባይነት አገኘ፡፡ አፈጻጸሙ ግን ሌላ ያልታሰበ ችግር አስከተለ።
‹‹በአዲስ ነጋሪት ጋዜጣ›› የወጣው አዋጅ ከተሻረ በኋላ በውጭ ሀገራት ዜጎችና ተቋማት ስር የሚገኝ ይዞታ በሊዝ ለመመዝገብ ኃላፊነቱን ወስዶ የተንቀሳቀሰው የሽግግር መንግስቱ ነው ወይስ የክልል 14 መስተዳድር?
በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ለሚገኙ ኤምባሲዎች ‹‹ይዞታችሁን በሊዝ አስመዝግቡ›› የሚል ደብዳቤ ተዘጋጅቶ የተላከላቸው በክልል 14 መስተዳድር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ በኩል ነበር። አሰራሩ የዲፕሎማቲክ ሥርዓትና ፕሮቶኮል ያልተከተለ ነበር። ለኤምባሲዎቹ የተላከው ደብዳቤ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ወይም በርዕሰ ብሔሩ ተዘጋጅቶ መውጣት ነበረበት። በከንቲባው የቴክኒክ አማካሪነቴ ይህንኑ ጉዳይ ላስረዳ ብሞክርም የሚሰማኝ አላገኘሁም፡፡
ከክልል 14 መስተዳድር የተላከ ጥሪ የደረሳቸው ኤምባሲዎች ተቃውሟቸውን በጽሑፍ አዘጋጅተው፣ ደብዳቤውን ለላከላቸው ክፍልና ግላባጩን በወቅቱ የሽግግሩ መንግስት ፕሬዚዳንት ለነበሩት ለአቶ መለስ ዜናዊ ላኩ፡፡ ኤምባሲዎቹ በላኩት ምላሽ ‹‹ቦታውን የገዛነው ስለሆነ የኢትዮጵያ መንግስት አያገባውም››፣ ‹‹ከኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የተበረከተልን ስለሆነ የአሁኑን መንግስት አይመለከተውም››፣ ‹‹የሁለቱ ሀገራት መንግስታት ተስማምተው የተሰጠን ስለሆነ በአዲስ መልክ ለመመዝገብ አንገደድም››፣ ‹‹እኛ ይህንን መሬት ስንወስድ በሀገራችን ምትክ ቦታ ሰጥተናችኋል››፣ ‹‹እኛ ይህንን ይዘን ስንቆይ ለናንተ በምትክነት የሰጠናችሁን … ሸጣችሁታል›› የሚሉና መሰል ምክንያቶችን በማቅረብ የተጠየቁትን ተግባራዊ እንደማያደርጉ አሳወቁ፡፡
የሽግግር መንግስት ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ግልባጭ ደብዳቤ ሲደርሳቸው ስለተበሳጩ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይኔ የሚመራና በከተማ ልማት ሚኒስቴር ስር የሚሰራ ሀገር አቀፍ የኤክስፐርቶች አጥኚ ቡድን አቋቋሙ። ይህም ቡድን የመሬት ይዞታ ስሪት ‹‹በምሪት›› መሆን አለበት የሚል ሀሳብ አቀረበ፡፡ በተቃራኒው የክልል 14 መስተዳድር የጥናት ቡድን በቀድሞ አቋሙ ጸና፡፡ ሁለቱ የጥናት ቡድን የተለያዩበትን ምክንያት እንዲያብራሩ ፕሬዚዳንት አቶ መለስ ዜናዊ የጋራ መድረክ አዘጋጅተው ጠሯቸው። የክልል 14 መስተዳድር ኤክስፐርቶች ቡድን በሰጠው ማብራሪያ፤ የመሬት ይዞታ ስሪት በሊዝ የሚሆን ከሆነ ፡-
1ኛ- መንግስት የማይነጥፍ ከፍተኛ ገቢ ያገኛል
2ኛ- ጉቦ ይጠፋል
3ኛ- የተገልጋዩ ሕዝብ መስተንግዶ የተቀላጠፈና የተፋጠነ ይሆናል… ሲል በከተማ ልማት ሚኒስቴር ስር የተቋቋመው ቡድን ‹‹በምሪት ይሁን›› ብሎ አቋም የያዘበትን ምክንያት ከላይ እኔ ቀደም ብዬ አቅርቤው የነበረውን መሰል ሀሳብ አቀረበ፡፡
የሁለቱ አጥኝ ቡድን ሀሳብ ከተደመጠ በኋላ የመሬት ስሪትን በተመለከተ የሽግግር መንግስቱ የሚያወጣው አዋጅ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደርጋል የሚል እምነት የነበረኝ ቢሆንም መንግስት ‹‹ከማይነጥፍ ከፍተኛ የቦታ ሽያጭ›› የሚገኘው ገንዘብ ስላጓጓው፣ የከተማ ቦታ በሊዝ መያዝ የሚቻልበት አዋጅ ቁጥር 80/1986 በይፋ ታወጀ። የሊዝ ፖሊሲ ለመንግስት ከፍተኛ ገንዘብ በማስገኘት ረገድ የነዳጅ ጉድጓድ ቢሆንለትም፣ ዛሬ በሀገራችን ለሚታየው የኑሮ ውድነት አንዱና ዋነኛው ምክንያት ሆኗል፡፡

Read 1837 times