Print this page
Saturday, 21 July 2018 14:08

ሰሞነኛ ወሬዎች

Written by 
Rate this item
(12 votes)

 የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ሠራተኞች አድማ

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ሠራተኞች፤ ደሞዝና ጥቅማጥቅም አነሰን በሚል በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ለሁለት ቀናት የሥራ ማቆም አድማ አደረጉ፡፡
በጥቅማጥቅም ጉዳይ ከምድር ባቡር አስተዳደር ጋር የተስማሙ ሲሆን በደሞዝ ጉዳይ ግን ለወደፊት እንስማማለን ብለው ከሁለት ቀናት አድማ በኋላ ሐሙስ እለት ስራቸውን ጀምረዋል። በሥራ ማቆም አድማው ምድር ባቡር 1 ሚሊዮን ብር ያህል ሳያጣ እንዳልቀረ ይገመታል፡፡

     አዲስ አበባ አዲስ ከንቲባ አግኝታለች

የአዲስ አበባ አስተዳደር ከንቲባ ሆነው ለ5 ዓመታት ያገለገሉት አቶ ድሪባ ኩማ ከስልጣን ተነስተው የካናዳ አምባሣደር ሆነው መሾማቸውን ተከትሎ፣ አዲስ አበባ የምክር ቤቷ አባል ባልሆኑት ኢንጂነር ታከለ ኡማ እንድትመራ ተወስኗል፡፡
ኢንጂነር ታከለ ኩማ የቀድሞ የሰበታ ከተማ ከንቲባ ሲሆኑ አዲስ አበባን በምክትል ከንቲባነት ያስተዳድራሉ፡፡ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ እና ዶ/ር ሠለሞን ም/ከንቲባዎች ሆነዋል፡፡

        እንባ ያራጨው የመጀመሪያው የአስመራ በረራ
 
ኤርትራና ኢትዮጵያ በይፋ እርቅ ማውረዳቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፈው ረቡዕ 460 ተጓዦችን ከአዲስ አበባ አሳፍሮ ወደ አሥመራ የበረረ ሲሆን በዚህ ከ20 ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በተደረገ ታሪካዊ በረራ፤ ለዓመታት የተቆራረጡና የተነፋፈቁ ቤተሰቦች በእንባ እየተራጩ ናፍቆታቸውን ተወጥተዋል፡፡
“ይህ የተፈጠረው ሰላም በጣም ያስደስታል፤ ከሰማይ የመጣ ነው የሚመስለው” ብሏል፤ ከ20 ዓመት በኋላ ከቤተሰቦቹ ጋር የተገናኘ ኤርትራዊ ወጣት፡፡
ይህን የጉዞ ቡድንም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማርያም ደሣለኝ እና ባለቤታቸው ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬ መርተውታል፡፡

    የደህንነት ሰራተኞች የፓርቲ አባል መሆን አይችሉም

የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት አዲሱ ሃላፊ ጀነራል አደም መሃመድ፤ የደህንነት ባለሙያዎች የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆን እንደማይችሉ ገለጹ፡፡
የተቋሙ ሃላፊዎች ሰሞኑን ከሰራተኞች ጋር ባደረጉት ስብሰባ፤ ”የማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባል የሆናችሁ ወይ ተቋሙን አሊያም ፓርቲውን ልቀቁ” ብለዋል፤ ጀነራል አደም፡፡ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ በመከላከያ ሚኒስቴርና በደህንነት ተቋም ላይ የሪፎርም ሥራ መጀመሩን መናገራቸው አይዘነጋም፡፡

    ቴዲ አፍሮ በአዲስ አበባ  ኮንሰርት ያቀርባል

ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) በሚሊኒየም አዳራሽና በመስቀል አደባባይ ኮንሠርት ያቀርባል፡፡ ኮንሠርቶቹ መቼ እንደሚቀርቡ ባይገለፅም ለአዲስ ዓመት ወይም ለመስቀል ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል፡፡
በሚሊኒየም አዳራሽ የሚቀርበው ኮንሰርት ከፍ ያለ የመግቢያ ክፍያ የሚኖረው ሲሆን በመስቀል አደባባይ የሚዘጋጀው የሙዚቃ ድግስ ግን በነፃ እንደሚሆን ታውቋል፡፡

      የተቃውሞ ሰልፍ በመቐሌ

ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች በግፍ ተፈናቅለናል የሚሉ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በመቐሌ የሠማዕታት ሃውልት ፊት ለፊት ከትናንት በስቲያ ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡
ያለ ምንም ጠያቂ አውላላ ሜዳ ላይ ወድቀናል ያሉት ተጎጂዎቹ፤ ለክልሉ መንግስት በተደጋጋሚ አቤት ብንልም ምላሽ ማግኘት አልቻልንም ሲሉ ምሬታቸውን ገልጸዋል።
ተቃዋሚዎቹ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል መጥተው የማያነጋግሩን ከሆነ ከሰልፋችን ንቅንቅ አንልም ብለው እንደነበርና በኋላ ግን በፀጥታ አካላት የማረጋጋት ሥራ መበተናቸውን ለማወቅ ተችሏል።  

      ኢትዮ-ቴሌኮም አዲስ ሥራ አስፈጻሚ ተሾመለት

የኢትዮ-ቴሌኮም ስራ አስፈጻሚ በመሆን ድርጅቱን ለ3 ዓመት የመሩት ዶ/ር አንዷለም አድማሴ፤ ከሃላፊነታቸው ተነስተው ምክትላቸው ወ/ሮ ፍሬህይወት ታምሩ በሥራ አስፈጻሚነት ተሾመዋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም በከፊል ወደ ግል ይዞታነት እንዲዘዋወሩ ከተወሰነባቸው የመንግስት የልማት ድርጅቶች አንዱ ነው፡፡ ዶ/ር አንዷለም አድማሴ፤ የከፍተኛ ትምህርት ጥራት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ተመድበዋል፡፡

Read 3946 times
Administrator

Latest from Administrator