Saturday, 21 July 2018 13:10

ዳሽን ባንክ “አሞሌ” የተሰኘ የዲጂታል መገበያያ ዘዴ አስመረቀ

Written by  መንግስቱ አበበ
Rate this item
(4 votes)

 ግንባር ቀደም ከሆኑ የግል ባንኮች አንዱ የሆነው ዳሽን ባንክ ሞኔታ ቴክኖሊጂስ አ.ማ ከተሰኘ አጋሩ ጋር በመተባበር “አሞሌ” የተሰኘ ከጥሬ ገንዘብ (የብር ኖት) ንክኪ ሳይኖር የመገባያያ መንገድ በይፋ አስመረቀ፡፡
ከጥንታዊት ኢትዮጵያ የመገበያያ ቁስ ከሆነው አሞሌ ጨው ስያሜውን ያገኘው ይህ ዘመናዊ የግብይትና የክፍያ መፈጸሚያ ዘዴ፣ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎችን ኤሌክትሮኒክስ በሆነ መንገድ፣ የአገልግሎት የዕቃ ግዢና ሽያጭ መፈጸም ያስችላል ተብሏል፡፡
ደንበኞች፣ በኢንተርኔት፣ ከሎሚ መጻሕፍት መደብር መጻሕፍትን፣ ከሸዋ ሾፒንግ ሴንተር የተለያዩ ቁሶችን፣ በሞባይላቸው፣ የስልክ የመብራትና የውሃ ክፍያዎች ሞባይል ካርድ መሙላትን፣ እንዲሁም ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው ገንዝ መላክን የመሳሰሉና ሌሎች የግብይትና ክፍያ ዓይነቶችን በ“አሞሌ” መፈጸም እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡
“አሞሌ” በሸራተን አዲስ ሆቴል ባለፈው ረቡዕ ምሽት በይፋ በተመረቀበት ወቅት፣ የዳሽን ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አሰፋ ዓለሜ አሁን ደንበኞቻችን በተመቻቸ ሁኔታ በቀላሉ ያለምንም ስጋትና ወጪን በሚቀንስ መንገድ “አሞሌ”ን በመጠቀም፣ በቤታቸው ወይም በቢሮአቸው ሆነው በማንኛውም ሰዓት ግብይት መፈጸም ይችላሉ ብለዋል፡፡
ሞኒታ ቴክኖሎጂስ አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ የምሩ ጫንያለው “አሜሌ”ን በመጠቀም አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ ካደረግናቸው ድርጅቶች ውስጥ በኢትዮጵያ አየር መንገድና በኤምሬትስ የበረራ ቲኬት መቁረጥ ከህዳሴ ቴሌኮም የሞባይል ካርድ መግዛትና በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚደረጉና የመሳሰሉ ክፍያዎች ይገኙበታል” ብለዋል፡፡
“አሞሌ” በተመረቀበት ወቅት፣ በኬንያ የሳፋሪኮም የቀድሞ ዋና ሥራ አስፈጻሚና የሞፔሳ አባት በመባል የሚታወቁት ማክል ጆሴፍ፣ “የአሞሌ ስኬት የሚለካው የፋይናንስ አቃፊነትን (ፋይናንሻል ኢንክሉሽን) በማስፋፋት የኢትዮጵያውያንን ሕይወት በዘላቂነት መቀየር መቻል አለመቻሉ ላይ ነው” ብለዋል፡፡   

Read 6546 times