Saturday, 21 July 2018 13:08

ዛሬ በጉራጌ ዞን ከ8 ሚ. በላይ ችግኞች ይተከላሉ

Written by 
Rate this item
(0 votes)


              ከአዲስ አበባ ከ800 በላይ ሰው ይጓዛል
            በጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር አስተባባሪነት ዛሬ ለስድስተኛ ጊዜ በሚካሄደው የችግኝ ተከላ ዘመቻ፣ በጉራጌ ዞን በ13ቱም ወረዳዎች ከ8 ሚ. በላይ ችግኞች እንደሚተከሉ የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር አስታወቀ፡፡ በችግኝ ተከላው ከ1 ሺህ ሰዎች በላይ የሚሳተፉ ሲሆን ከአዲስ አበባ ብቻ ከ800 በላይ ሰው ወደ ስፍራው እንደሚያቀና የማህበሩ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ መንግስቱ ኃይለማሪያም ተናግረዋል፡፡
ማኅበሩ ላለፉት አምስት ዓመታት ያለማቋረጥ በጉራጌ ዞን ወረዳዎች በርካታ ችግኞችን ከመትከሉም በላይ መፅደቃቸውን በማረጋገጥና በመንከባከብ በኩልም ውጤታማ ስራ መሥራቱን ኃላፊው ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ በማህበሩ ጽ/ቤት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀው፣ ለችግኝ ተከላው የሚያስፈልገውን ከአንድ ሚ. ብር በላይ ከአካባቢው ተወላጅ ባለሀብቶችና ከተለያዩ ድርጅቶች መሰብሰብ መቻሉን ገልፀዋል፡፡
ከአዲስ አበባ ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የተለያዩ ቢሮ ኃላፊዎች፣ የፓርላማ አባላት፣ ባለሀብቶች፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኃላፊዎች ከክፍለ ከተሞችና ከወረዳዎች፣ እንዲሁም የተለያዩ የህብረተሰብ ተወካዮችና ታዋቂ ግለሰቦች በዛሬው የችግኝ ተከላ ላይ ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅና ለጉዞውም ከ14 በላይ አውቶብሶች መዘጋጀታቸውን አቶ መንግስቱ ኃ/ማርያም ጨምረው ገልፀዋል፡፡
የጉራጌ ልማትና ባህል ማዕከል፤ በጤና፣ በትምህርት በባህል ማበልፀግና በተለያዩ ዘርፎች የልማት ስራዎችን በመስራት የሚታወቅ ሲሆን በተጨማሪም ከደን ምንጣሮና ከአካባቢ መራቆት፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋምና አካባቢውን ጤናማ ለማድረግ ወደ ችግኝ ተከላ ፊቱን በማዞር፣ ውጤታማ ስራ መስራት መቻሉንና ይሄው ተግባር በየዓመቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡

Read 2290 times