Saturday, 21 July 2018 12:38

የ”ቅንጅቱ” አቶ በድሩ አደም የት ጠፍተው ከረሙ?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

  “በየቦታው ክትትል ይደረግብኛል፤ ትልቅ ስጋት ላይ ነኝ”

    አቶ በድሩ አደም፤ ከ1987 እስከ 1997 በግላቸው ተወዳድረው የፓርላማ አባል ነበሩ፡፡ በ1997 ደግሞ ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲን ተቀላቅለው፣ በአዲስ አበባ ወረዳ 7 (አውቶብስ ተራ አካባቢ)ተወዳድረው በማሸነፍ የፓርላማ ወንበር አግኝተዋል። ነገር ግን በወቅቱ በተፈጠረው የፖለቲካ ቀውስ የተነሳ ፓርላማውን አልተቀላቀሉም፡፡ ከዚያ ይልቅ የቅንጅት አመራሮች ሲታሠሩ እሣቸውም ታስረዋል፡፡ በፍ/ቤት ተከራክረውም በነፃ ተሠናብተዋል፡፡ በ2000 ዓ.ም መጨረሻ ከእስር ከተፈቱ በኋላ ግን ከፖለቲካው መድረክ ጠፍተው ከርመዋል፡፡  
በመስቀል አደባባይ የቅንጅት ሠልፍ ወቅት “ወያኔን ወደመጣበት ጫካ እንመልሰዋለን” በሚል ተናግረዋል በሚል የሚተቹት አንጋፋው ፖለቲከኛ አቶ በድሩ አደም፤ በዚህም ሰበብ አሁን ላሉበት እንግልትና የስጋት ኑሮ እንደተዳረጉ ያስረዳሉ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ ከአቶ በድሩ አደም ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጓል፡፡


    በመጀመሪያ እስቲ ስለ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ጅማሮዎ ይንገሩን?
በልጅነቴም የተማሪዎች የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳትፌአለሁ፡፡ የኢህአፓም አባል ነበርኩ። በደርግ ጊዜ የመንግስት ሠራተኛ ነበርኩ፡፡ በህቡዕ ግን የኢህአፓ አባል ነበርኩ፡፡ ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ሲመጣ ግን አንዳንድ ሁኔታዎች በግልፅ ወደ ፖለቲካው እንድገባ አደረጉኝ፡፡ በተለይ ከምስራ ቀጠና ጉምሩክ ስራ አስኪያጅነት ወደ ሠሜን ቀጠና ጉምሩክ ስራ አስኪያጅነት ተቀይሬ፣ ወደ ትግራይ ስሄድ ነው፣ ብዙ ነገር ወደ ፖለቲካው ጠልቄ እንድገባ የገፋፋኝ፡፡
የተወለድኩት ቀድሞ ኢሊባቡር ስር አሁን በጅማ ስር ባለው ጎማ ወረዳ ነው፡፡ በ1987 ዓ.ም በተደረገው ሃገር አቀፍ ምርጫ በግል ተወዳድሬ ነው የፓርላማ አባል የሆንኩት፡፡ ትግራይ እያለሁ ህዝቡ በጣም ጠንካራ ነበር፡፡ ድንጋይ እየለቀመ መሬቱን አፅድቶ ያርስ ነበር፡፡ በተቃራኒው ደግሞ እኔ በተወለድኩበት አካባቢ ኦነግ፣ ኦህዴድ እየተባለ የጦርነት ቀጠና ሆኖ ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ በጣም ያሣዝነኝ ነበር፡፡ ከዚህ በመነሣት ነው የህዝቡን ኑሮ ባሻሽል ብዬ፣ ወደ ፖለቲካ ገብቼ በግሌ የተወዳደርኩት፡፡
በወቅቱ በግል ተወዳድሮ ለማሸነፍ አስቸጋሪ አልነበረም?
ከባድ ነበር፡፡ ነገር ግን አባቴም በበጎ ስራዎች በአካባቢው ይታወቅ ነበር፡፡ እኔም ብሆን በተለይ በ1977 በውጭ ሃገር ከፍተኛ ትምህርቴን ተከታትዬ ስመለስ፣ የአካባቢው ልጆች በትምህርታቸው እንዲበረታቱ ብዬ የተለያዩ የትምህርት መርጃ መሣሪያዎችን ነበር ይዤ የመጣሁት፡፡ ቀደም ብሎም በግሌ ቢያንስ የአካባቢው ነዋሪ ስሙን እንኳ መፃፍ እንዲችል በግሌ አስተምር ነበር፡፡ ክረምት ክረምት ጎልማሶችን በራሴ ፍላጎት እየሰበሰብኩ እንዳስተምር የገፋፋኝ አንድ አጋጣሚ ነው፡፡ አንድ የወረዳ አስተዳዳሪ፣ አንዱን ገበሬ እጅ መንሻ በግ ስጠኝ ብሎ ይጠይቀዋል፡፡ አልሠጥም ይላል ገበሬው፡፡ ከዚያም የወረዳ አስተዳዳሪው ደብዳቤ ፅፈው “ሂድና ለወረዳው ፖሊስ ጣቢያ ደብዳቤውን ስጥ” ይሉታል፡፡ እሡም ማንበብ ስለማይችል ዝም ብሎ ሄዶ፣ ለፖሊስ ይሰጣል። ደብዳቤው “የወንጀል ተጠርጣሪ ነው ይታሠር” የሚል ነበር፡፡ በዚህም ገበሬው ራሱ ይዞ በሄደው ደብደቤ ይታሠራል፡፡ ይህ አጋጣሚ ነው ቢያንስ ማንበብ እንኳ እንዲችሉ ለምን አላስተምርም ብዬ የጀመርኩት፡፡ ይህ የሆነው በአፄ ኃይለ ስላሴ ዘመን ነው፡፡ በኋላ የፊደል ሠራዊት ሽልማት ከንጉሡ አግኝቻለሁ፡፡
የውጭ ሃገር ትምህርትዎን  የት ነው የተከታተሉት?
ዩክሬን ውስጥ ነበር፡፡ በዓለማቀፍ ኢኮኖሚ ግንኙነት በሁለተኛ ድግሪ (ማስትሬት) ነው የተማርኩት፡፡ በተጨማሪም ከአዲስ አበባ ንግድ ስራ ኮሌጅ በአካውንቲንግ በዲፕሎማ ተመርቄአለሁ፡፡ በህግ ሰርተፍኬት አግኝቼአለሁ፡፡ በስታትስቲክስም በሠርተፊኬት ደረጃ በደርግና በንጉሡ ዘመን ተምሬያለሁ፡፡ ተፈሪ መኮንን ነው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን የተማርኩት፡፡
ለሁለት የምርጫ ዘመን  በፓርላማ ቆይተዋል፤ ቆይታዎ እንዴት ነበር?
በ1987 ተወዳድሬ ከገባሁ በኋላ በተለይ የተወዳደርኩበትን አካባቢ እንደመወከሌ ለማህበረሠቡ ይጠቅማል ያልኩትን ሁሉ ለፌደራል መንግስት ለማቅረብ ሞክሬያለሁ፡፡ የተሣኩልኝ አሉ፡፡ በተለይ የመሠረተ ልማት ጉዳይ ላይ ጠንካራ ስራ ተሠርቷል። በግሌ ወደ 7 ሺህ ደብዳቤዎች ከህዝብ ደርሶኛል፡፡ እነዚያን ደብዳቤዎች እየጨመቅሁ ለሚመለከተው ሁሉ አሠማ ነበር፡፡ ቀጥታ ጠቅላይ ሚኒስትሩንም እያገኘሁ የህዝቡን ጥያቄ አቀርብ ነበር፡፡ ከሌሎች ሚኒስትሮች ጋርም በቀጥታ ቀጠሮ እየተገናኘሁ፣የህዝቡን ጥያቄ አቀርብላቸው ነበር፡፡ በወቅቱ ፓርላማ ከማቀርባቸው ጥያቄዎች በላይ በዚህ መንገድ የማቀርባቸው ይበልጡ ነበር፡፡ ጥያቄዬን በማስረጃ አስደግፌ ነበር የማቀርበው። ማስረጃ ከግል ኪሴ አውጥቼ እስከ መግዛት እደርስ ነበር፡፡ ብዙ ማስረጃዎች በዚህ መንገድ ገዝቻለሁ፡፡
ማስረጃ የሚገዙት ለምንድን ነው?
እንዳልኩህ ያለ ማስረጃ በፓርላማ መናገር አልፈልግም፡፡ ለጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ ለሚመለከታቸው አካላት ያለ ማስረጃ ጥያቄ ማቅረብ አልፈልግም ነበር፡፡ መረጃ ካገኘሁ በኋላ ማስረጃ ለማፈላለግ ነበር እንቅልፌን የማጣው፡፡ እዚህ ቦታ ማስረጃ አለ ከተባልኩ እጠይቃለሁ፡፡ እምቢ ካሉኝ እውነቱ እንዲወጣ ካለኝ ፍላጎትን የተነሳ ማስረጃውን ገንዘቤን ከፍዬ ተደራድሬ አወጣለሁ፡፡ ይህ ለኔ የመንፈስ እርካታ ነው የሚሠጠኝ፡፡ የምገዛው ከግለሠቦች፣ ከተቋማት ሊሆን ይችላል፡፡ ዋናው ማስረጃውን መያዜን ነበር የምፈልገው፡፡ ለጠቅላይ ሚኒስትሩም ማስረጃ ሳቀርብ፣ ማስረጃውን ገዥቼው ነው እላቸው ነበር፡፡ በወቅቱ የምፈልጋቸው ሚኒስትሮች በቀላሉ ቀጠሮ ይሰጡኝ ነበር፡፡ እኔም የጀመርኩትን ከዳር ሣላደርስ አልተውም፡፡
በፓርላማ ቆይታዎ ወቅት ምን ፈታኝ ሁኔታ አጋጠምዎት? ምንስ ታዘቡ?
አንድ ከባድ ነገር ነበር፡፡ በተለይ በመጀመርያው አምስት አመት ቆይታዬ፣ ሁሉም ነገር በቡድን ነበር የሚታየው፡፡ እኔ ጥያቄ ሣቀርብ፣ ጥያቄው በቡድን መቅረብ አለበት ይባል ነበር፡፡ በየቦታው ጥያቄዬን ይዤ ስሄድ፣ ይህ የግለሠብ ጉዳይ ነው እባል ነበር፡፡ የግለሰብን ጥያቄ ያለ ማስተናገድ፣ የቡድን ጥያቄን ብቻ የመፈለግ ሁኔታ ነበር፡፡ እኔ ደግሞ ለግለሰብ መቆም ካልቻልን፣ ለማህበረሠብ መቆሞ አንችልም በሚል እሟገት ነበር፡፡ ሁኔታው ለኔ ፈታኝ ነበር፡፡
እርስዎ በወቅቱ ምን አይነት ጥያቄዎችን ነበር የሚያቀርቡት?
አጠቃላይ የማህበረሠቡን የልማት ጥያቄ ነበር የማቀርበው፡፡ በዚያው ልክ ያለ አግባብ የተበደሉ ዜጎችን ጥያቄም በየመስሪያ ቤቱ እየዞርኩ አቀርብ ነበር፡፡ ያለ አግባብ ቤት የፈረሠባቸው፣ መሬታቸው በጉልበት የተወሰደባቸው ግለሠቦችን ጥያቄ ማስረጃ ይዤ አቀርብ ነበር፡፡ ይህን ሳቀርብ ግን የግለሠብ ጉዳይ ነው እባል ነበር፡፡ አንድ ህንፃ አለ፡፡ ይሄ ህንፃ በዝርፊያ የተሠራ ነው፡፡ የአንድን የቤተሠቦቹን ንብረት ወራሽ ወጣት መሬት በሃይል ወስደው ነው፣ ግለሰቦቹ ፎቁን የሠሩት፡፡ ዛሬም ይህን ፎቅ ሳይ አዝናለሁ። እነዚህን ሁሉ በማስረጃ ነው ሣቀርብ የነበረው፡፡ የኔ መሣሪያ ማስረጃዎቼ ነበሩ፡፡ ለዚህ ነው ገንዘቤን አውጥቼ ማስረጃ የምገዛው፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ሣይቀር ማስረጃ ገዥቻለሁ፡፡ ይሄንንም በወቅቱ ለነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ነግሬያቸው ነበር፡፡ ህገ ወጥ ረቂቅ አዋጆች ሳይቀር ከሚኒስትሮች ም/ቤት በገንዘብ አውጥቼ፣ ህገ ወጥ መሆኑን ለፓርላማው ያጋለጥኩበት ጊዜ ነበር፡፡ በአጠቃላይ ለኔ የ10 ዓመት የፓርላማ ቆይታዬ፣ በትግል የተሞላ፣ በዚያው ልክ በማቀርባቸው በማስረጃ የተደገፉ ሙግቶች ቢያንስ ህሊናዬ የሚረካበት ነበር፡፡
በፓርላማ ቆይታዎ በተለያዩ ዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮዎች በርካታ ሃገራትን እንደጎበኙ ይነገራል---
እውነት ነው፡፡ በአለም ላይ በርካታ ሃገራት ሄጃለሁ፡፡ አሜሪካ በመጀመሪያ በራሴ ነው የአሜሪካ መንግስት ጋብዞኝ የሄድኩት፡፡ እጩዎች እንዴት ለምርጫ እንደሚቀርቡ ለመታዘብ ነበር በ1989 የሄድኩት፡፡ የአፍሪካ ሃገራት አብዛኞቹ ጋር ሄጃለሁ። አውሮፓም እንዲሁ በተደጋጋሚ የተለያዩ ሀገራት ተጉዣለሁ፡፡ የአለም ባንክ በትራንስፓረንስ ኢንተርናሽናል አማካይነት በሃገር ውስጥ የሚደረገውን የማጋለጥ እንቅስቃሴ እንዳስረዳ ጋብዞኝ፣ ፈረንሣይ የሄድኩበት አጋጣሚ አለ፡፡ ፓሪስ ላይ ከ3ሺ በላይ ተሰብሳቢ በተገኘበት በፓርላማው የሙስና እና መልካም አስተዳደር በደሎችን እንዴት እያጋለጥኩ እንደሆነ አስረድቻለሁ፡፡ በእስያም ፊሊፒንስ ታይላንድ የመሣሠሉት ሃገራት በተባበሩ መንግስታት አማካይነት ሄጃለሁ፡፡
በ1997 ዓ.ም እንዴት ቅንጅትን ተቀላቀሉ?
ሁለቱን የምርጫ ዘመናት በግሌ ተወዳድሬ ነበር ፓርላማ የገባሁት፡፡ የፓርቲ አባል አልነበርኩም። በ1997 የወጣው የምርጫ መመሪያ፤ አንድ ግለሰብ እጩ ለመሆን 1500 ድምፅ ያስፈልገዋል የሚል ነበር፡፡ በእርግጥ እኔ ይህን ድምፅ ማግኘት ከብዶኝ አልነበረም። ነገር ግን እንደዚህ ከሆነ በመደራጀት የተሻለ ስራ መስራት እችላለሁ ብዬ ፕ/ር መስፍንን አነጋገርኳቸው፡፡ በዚያው እነ ዶ/ር ብርሃኑ የሚመሩትን ቀስተደመና ተቀላቀልኩት፤በቀስተደመና አማካኝነት ቅንጅትን ተቀላቀልኩ ማለት ነው፡፡
በቅንጅት ውስጥ የእርስዎ ድርሻ ምን ነበር?
የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ነበርኩ፡፡ የተወዳደርኩት በአዲስ አበባ አውቶብስ ተራ ወይም ወረዳ 7 ነው፡፡ በወቅቱ ከ36 ሺህ በላይ ድምፅ አግኝቼ ነበር ያሸነፍኩት፡፡
ቅንጅት በመስቀል አደባባይ ጠርቶት በነበረው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ “ወያኔን ወደ መጣበት ጫካ እንመልሰዋለን” ብለዋል በሚል በእርስዎ ላይ ትችት ይሰነዘራል ---
ሚያዚያ 30 ቀን 1997 በመስቀል አደባባይ ሠልፍ የማድረግ ሃሳቡን ያመነጨው ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ነበር። በወቅቱ ህዝቡ አደባባዩን ሞላው፡፡ ዶ/ር ብርሃኑ ደግሞ ጉራጌ ሃገር ሄጃለሁ ብሎን አልተገኘም ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት በመድረክ እንዲናገሩ ከተመረጡ አንዱ ሆንኩ፡፡ እኔ በእለቱ እንድናገር የተሠጠኝ ርዕሠ ጉዳይ በውጭ ግንኙነት፣ በሥርአተ ፆታና በሃይማኖት ጉዳይ ነው፡፡ በወቅቱ ህዝቡ በጣም ከጠበቅነው በላይ ነበር፡፡ በዚያው ልክ ደህንነቶች መሽገው ነበር፡፡ አንድ ደህንነት ጥይት ወደ ሰማይ እንኳ ከተኮሰ፣ ህዝቡ በመረጋገጥ ሊያልቅ ይችላል፤ ስለዚህ ብዙ መቆየት አያስፈልግም፣ ዝም ብለን መፈክር አሠምተን እንሂድ አልኳቸው፤ እነ ዶ/ር ሃይሉ አርአያን፡፡ በአጋጣሚ ደግሞ ዝናብ መጣ። በዚህ ተስማማንና እኔ አንደበቴ ላይ የመጣልኝ መፈክር ነው ማሠማት የጀመርኩት፡፡ በወቅቱ እኔ ያልኩት ቃል በቃል “የዛሬ አመት አንድ በፈጣሪ፣ ሁለት በእናንተ ሃይል ኢህአዴግ ወደ ነበረበት ይመለሣል” ነበር ያልኩት፡፡ ወያኔ፣ ህወኃት፣ ትግሬ አላልኩም። ፍ/ቤቱም በነፃ ያሠናበተኝ በወቅቱ የተቀዳውን ድምጼን መርምሮ ነው፡፡ ነገር ግን ይህን ንግግሬን ለራሳቸው በሚመቻቸው መንገድ ነው ተርጉመው ለፕሮፓጋንዳ ያሰራጯቸው፡፡ ለእኔ ኢህአዴግ ማለት ህወኃት ብቻ አይደለም፡፡ ኦህዴድ፣ብአዴን እና ደኢህዴን ይጨምራል፡፡ የእኔ እርግማን ቢሰራ ትልቁ ተጎጂ ኦህዴድ ነው፤ቀጥሎ ብአዴን ከዚያም ደኢህዴን ነበር። ምክንያቱም እነዚህ ናቸው የፓርላማውን አብላጫ ወንበር የያዙት፡፡ ህወኃት 38 አባላት ብቻ ነው ያሉት። ይሄ በመንግስት ምስረታ ምንም ለውጥ አያመጣም ነበር፡፡ በታደሰ ጥንቅሹና በአቶ ሴኩቱሬ ጌታቸው ተመንዝሮ ነው “ወደ ጫካ ምናምን” ተብሎ የተነገረው።
እርስዎ ምርጫውን ካሸነፉ በኋላ ወደ ፓርላማ ለመግባት ፍላጎት ነበርዎት?
አዎ! በወቅቱ ለእኔ የፈጣሪ ተዓምር ነበር የተፈጠረው፡፡ ቅንጅት አዲስ አበባን ሙሉ ለሙሉ አሸንፏል፡፡ ይህ ማለት የፌደራል መንግስቱን መቀመጫ ተቆጣጠርን ማለት ነው፡፡ የፌደራል መንግስቱን ኢህአዴግን አሸንፌያለሁ ቢልም መቀመጫ አልነበረውም ነበር፤ አየር ላይ ነበር የተንጠለጠለው፡፡ በወቅቱ “ዲፋክቶ” መንግስት አይደለም የሚሆነው፤ “ዲጁሬ” ነበር የሚሆነው። አዲስ አበባን ያለ መረከባችን፣ ያሸነፍነውን የፓርማ ወንበር ተረክበን ፓርላማ ያለመግባታችን ትልቅ እድል ነው ያስመለጠን፡፡ በወቅቱ እኔ መግባት ፈልጌ ነበር፤ ነገር ግን ብገባ በቅንጅት ስራ አስፈፃሚ ያለሁት የኦሮሞ ተወላጅ እኔ ብቻ ስለነበርኩ፣ ወደ ዘረኝነት እንዳይመነዘርብኝ ብዬ ነው የተወኩት፡፡ እኛ ፓርላማ ብንገባ ኖሮ፣ ያ ሁሉ ህዝብ አይታሠርም አይንገላታም ነበር፡፡ ኢህአዴግም መቀመጫ ያጣ ነበር፡፡ ፌደራል መንግስቱ የፋይናንስ ጫና ያሣርፋል የሚል ስጋት ነበር፡፡ ይሄን ስጋት በሚቀርፍ መልኩ ደግሞ የተለያዩ ሃገራት መንግስታትና ተቋማት “እኛ እንመጣላችኋለን፤ እናንተ ግቡ” ብለውን ነበር፡፡ ሣኡዲ አረቢያ ሳትቀር  “ገንዘብ እንሠጣችኋለን፤ እናንተ አስተዳደሩን ተረከቡ” ብለውን ነበር፡፡
ከእስር  ከተፈቱ በኋላ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎ ምን ይመስላል?
ታስሬ ከተፈታሁ በኋላ ፈፅሞ ወደ ፖለቲካው አልተመለስኩም፡፡ በወቅቱ በጣም ብዙ ችግሮች ገጥመውኛል፡፡ መቼስ የኢህአዴግ መንግስት ያላደረሰብኝ ነገር የለም፡፡ ቤተሠቤን በትኗል፡፡ ትዳሬ ፈርሷል፡፡ ቤቴን ሸጬ ገንዘቡን ባንክ ሳላስገባ ማታውኑ ታርጋ በሌለው መኪና መጥተው ገንዘቡን ሙሉ ለሙሉ ተዘርፌያለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ኑሮዬ ተመሰቃቅሏል፡፡ በየቦታው እየዞርኩ ነው የምኖረው። ለደህንነቴ ስለምፈራ በየቦታው እየተዘዋወርኩ ነው የምኖረው፡፡ ካገኙኝ ከመግደል አይመለሱም፡፡ ዘንድሮ እንኳ ህዳር 16 ቀን 2010 ደብድበውኝ፣ ሞቷል ብለው ጥለውኝ ሄደዋል፡፡
እስቲ በወቅቱ የተፈጠረውን ይንገሩኝ?
በወቅቱ ሌሊት ለሰላት ወደ ፒያሣ ቤኒን መስጊድ እየመጣሁ ነበር (ቃለ ምልልሱ የተደረገው በመስጊዱ ግቢ ውስጥ ነው)፡፡ ለአስራ አንድ ሰዓት ሃያ ጉዳይ ነበር። ቸርችል ጎዳና ፣ ጥቁር አንበሳ ት/ቤት ጋ ስደርስ፣ አንዱ የስፖርት ቱታ የለበሰ ሮጦ አልፎኝ ሄደ፡፡ ከዚያ ትራኮን ህንፃ ጋ ሲደርስ ከአይኔ ተሠወረ፡፡ ይሄ ሰው ምን ውስጥ ገባ እያልኩ መንገዴን ቀጠልኩ፡፡ ከኋላዬም የስፖርት ቱታ የለበሱ ነበሩ፡፡ በመጨረሻ ከፊትም ከኋላም መጥተው አነቁኝ፡፡ በኋላ ራሴን ሳትኩ፡፡ በኪሴ ውስጥ የነበረ መታወቂያ፣ መንጃ ፍቃድና ወረቀቶችን በሙሉ ወሰዱ፡፡ አንድ ብጣሽ ወረቀት እንኳን አላስቀሩልኝም። 500 ብር እና ሣንቲሞች በኪሴ ነበር፤ ሳንቲሞቹ  እንኳ አልቀሩልኝም፡፡ ከዚያም ሞቷል ብለው ወንዝ ዳር ወስደው ጣሉኝ፡፡ ለ1 ሰዓት 25 ጉዳይ ነው ራሴን ያወቅሁት፡፡ በዚህ ምክንያት ይገድሉኛል የሚለው ስጋቴ ጨምሯል፡፡ በዕለቱ ስለደረሠብኝ ጥቃት ለፖሊስ ለማመልከት ሞክሬ ነበር፡፡ ነገር ግን ጉዳዬን የዕለት ሁኔታ ላይ እንኳ አልመዘገቡልኝም፡፡ ፖሊስ ጣቢያ ሆኜ 2 ሺህ ብር ተዘርፌያለሁ ያለ ቻይናዊ ጉዳይ የዕለት ሁኔታ ላይ ሲመዘገብ፣ የኔን ግን ሊመዘግቡልኝ እንኳ አልፈለጉም፡፡ በዚህ ምክንያት ዛሬም ህይወቴ አደጋ ላይ እንዳለ ነው የሚሰማኝ፡፡ በየቦታው ክትትል ይደረግብኛል፡፡ ትልቅ ስጋት ላይ ነኝ፡፡ ለዚህ ነው ሸሽቼ ተደብቄ መኖር የመረጥኩት፡፡ ትንሽ አሁን የተወሰነ ለውጥ ከመጣ በኋላ ስጋቱ ቢቀንስልኝም፣ አሁንም አስተማማኝ ደህንነት አይሠማኝም፡፡ ከዚያ በመለስ ግን በፖለቲካው ከመሳተፍ የገደበኝ እውነተኛ ፓርቲ አለመኖሩ ነው፡፡ በዋናነት ደግሞ ሀሳብን በነፃ የመግለጽ፣ የመደራጀት፣ የመንቀሳቀስ መብት በታገደበት ሁኔታ፣ የይስሙላ ምርጫ በሚካሄድበት ሁኔታ፣ በፓርቲ ፖለቲካ መንቀሳቀስ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ ለፖለቲካውም አይጠቅምም፡፡ ዛሬ የመጣው ለውጥ በኦሮሞ ወጣቶች፣ በአማራ ወጣቶች ተጋድሎ እንጂ በፓርቲ ፖለቲካ አይደለም፡፡ ይሄ መንግስት ሊፈርስ የሚችለው በሁለት መንገድ ብቻ ነው ብዬ አስብ ነበር፡፡ አንደኛ፤ በኢህአዴግ መሃል ክፍፍል ሲፈጠር። ሁለተኛው፤ ኦሮሞና አማራ አንድ ላይ የተንቀሳቀሱ ጊዜ ነው  እል ነበር፡፡ ይህ እምነቴ ነው አሁን እውን ሆኖ ያየሁት፡፡ ለውጡ አንደኛ በፈጣሪ፣ ሁለተኛ በኦሮሞና አማራ ህዝብ ትግል፣ ሦስተኛ በአሜሪካ መንግስት ግፊት የመጣ ነው፡፡
ቋሚ የመኖሪያ አድራሻ የለኝም ብለዋል፡፡ ለምንድን ነው?
ስለምፈራ ነው፡፡ የሆነ ሰዓት ይገድሉኛል የሚል ስጋት አለኝ፡፡
አሁን በምን ገቢ ነው የሚተዳደሩት?
የተለያዩ አቅሜ የሚፈቅዱ ስራዎችን እሠራለሁ። ልጆቼንም አስተምራለሁ፡፡ በአቅሜ በየቦታው እየተዘዋወርኩ ቤት እየተከራየሁ ነው የምኖረው፡፡ እውነቱን ለመናገር በፖለቲካው ምክንያት የደረሠብኝን ችግርና ጉዳት ሰዎችን በሚያሳዝን መልኩ መናገር አልፈልግም፤ ከሚዲያ ተደብቄ የኖርኩትም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ መቼም ይሄ ቀን ማለፉ አይቀርም፡፡ ሌላ ሥርአት መምጣቱ አይቀርም በሚል ተስፋ ነው፣ ሁሉንም ነገር እንዳመጣጡ ሳስተናግድ  የቆየሁት፡፡
ከእስር እንደተፈቱ ወደ አሜሪካ ሄደው አልነበር?
በ2000 ዓ.ም ከእስር እንደተፈታሁ ወደ አሜሪካ ሄጄ ነበር፡፡ እዚያ ለወራት ከቆየሁ በኋላ፣ ሸሽቼ ከሃገሬ አልወጣም ብዬ ነው የተመለስኩት፡፡ እኔ የተመለስኩት ቢያንስ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ በማሰብ ነበር፤ ነገር ግን ሰው በፍርሃት ተውጦ ነበር፡፡ ይሄን በፍርሃት የተዋጠ ህዝብ ማስተባበር ከባድ ነበር፡፡ ፓርቲ ለመመስረት ሞክሬም አልተሳካልኝም፡፡ ለዚህ ነው ራሴን ከማህበረሰቡ አግልዬ የኖርኩት፡፡ እዚህ መስጊድ ስመላለስ ማንም ሰው አያውቀኝም ነበር፡፡ ምክንያቱም ከስቻለሁ፡፡ በኋላ “እባክህ ራስህን ደብቀህ አትኑር፤ ያለህበትን ሁኔታ ቢያንስ ለህዝቡ አሣውቅ” የሚል ግፊት ሲመጣ ነው፣ ለእናንተም ቃለ ምልልስ የሠጠሁት እንጂ አልፈልግም ነበር፡፡ እውነቴን ነው የምልህ፣ የዚህ መንግስት ደህንነቶች መሄጃ መቀመጫ ነው ያሣጡኝ፡፡ እስከ ዛሬም አልተውኝም፡፡ እያሣለፍኩ ያለሁት ጊዜ ከባድ ነው፡፡ እኔ የደረሠብኝን ለሰው መናገር አልፈለግሁም ነበር፤ ለፈጣሪዬ ነግሬው ነው የተውኩት፡፡
ከዚህ በኋላ ወደ ፖለቲካው የመመለስ እቅድ የለዎትም?
እንግዲህ ከ1997 በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ ምርጫ አልነበረም፡፡ ምርጫ በሌለበት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ማድረግ አዋጭ አይደለም፡፡ ምናልባት አሁን የጀመረው የዲሞክራሲ ፍንጣቂ ተጠናክሮ ከመጣ፣ እሰየው ብዬ ፖለቲካ ውስጥ  መሣተፍ እፈልጋለሁ፡፡ እኔ ቦክሰኛ አይደለሁም፤ በጉልበት መግጠም አልችልም፡፡ በሃሳብ የሚገጠምበት ዕድል ከተፈጠረ ግን በዝረራ ለማሸነፍ ወደ ፖለቲካው እገባለሁ፡፡ 97 ምርጫ ላይ ዘርሬ ነው ያሸነፍኩት፡፡ እኔ 36 ሺህ ድምፅ ሣገኝ፣ የኢህአዴግ ተወካይ 2 ሺህ ነው ያገኘው፤ዘርሬ ነው ያሸነፍኳቸው። በፍ/ቤትም ዘርሬ ነው ያሸነፍኳቸው፡፡ ነገር ግን በጡንቻና በመሣሪያ ተዘርሬአለሁ፡፡ ስለዚህ ዲሞክራሲ የሚሠፍንበት ስርአት ሲመጣ አፈር እስኪጫነኝ ድረስ በፖለቲካ ውስጥ ለመሳተፍ ዝግጁ ነኝ፡፡ ፖለቲካ ጡንቻ ሳይሆን ጭንቅላት ነው የሚጠይቀው፡፡ ቢያንስ ያንን ጭንቅላት በመጠቀም፣ አንድን ሰው ከበደል ማዳን ትልቅ ነገር ነው፡፡
አሁን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያደርጉትን የለውጥ እንቅስቃሴ እንዴት ይመለከቱታል?
አሁንም የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ አለ፤ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ኢህአዴግ አለ፡፡ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዲሞክራሲ ፍንጭ እያሣዩ ነው፡፡ እኔም በዚህ ተስፋ አድርጌ ነው ወደ ፖለቲካው ለመምጣት ፍላጎት ያደረብኝ፡፡ በአፈና ውስጥ ነው የኖርኩት፡፡ ምናልባት ለብዙዎች ይሄ ግልፅ ላይሆን ይችላል፡፡ የኔ አጎት እኮ ከቤት ታፍኖ ተወስዶ የት እንዳለ እንኳ አናውቅም፡፡ በዚህ አፈና ውስጥ ነው ያለፍነው፡፡ ከዚህ አንፃር ዶ/ር ዐቢይ የሚያደርገው ተስፋ የሚሰጥ ነው፡፡ ነገር ግን አሁንም ኢህአዴግ አለ፡፡ እኔ የምፈልገው ለውጥ ጥገናዊ አይደለም፡፡ ከእነ ግንዱ ተቆርጦ የሚወድቅ ለውጥ ነው የምፈልገው፡፡ ቅርንጫፉ ብቻ መልኩን መቀየሩ ዋጋ የለውም፡፡ ቅርንጫፍ በክረምት ይለመልማል፣ በበጋ ይደርቃል፣ ደርቆም ይረግፋል፤ ስለዚህ ለውጡ ከግንዱ ነው መሆን ያለበት፡፡ እውነተኛ ዲሞክራሲ አለ የምለው፣ እነዚህ እውን ሲሆኑ ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ላየነው የዲሞክራሲ ጭላንጭል ግን የኦሮሞ ወጣቶች፣ የአማራ ወጣቶች፣ የአሜሪካ መንግስት እና ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ምስጋና ይገባቸዋል፡፡

Read 4296 times