Saturday, 14 July 2018 12:00

“በራቸውን ሳይዘጉ ሌባ ሌባ ይላሉ” አለች ውሻ

Written by 
Rate this item
(21 votes)

 ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ገበሬ በሬው ይጠፋበታል፡፡ በሬውን ለመፈለግ የመንደሩን ህዝብ እርዳታ ጠየቀ፡፡ መንደሬው ተሰባስቦ ሊያፋልገው ወጣ፡፡ አገሩን አሰሱት፡፡ ከሰው ሁሉ አንድ ሰው ፍለጋው ላይ በጥብቅ የተሰማራ አለ፡፡ ፈልገው ፈልገው በሬው ታሥሮ የተደበቀበት በረት አጠገብ ሊደርሱ ሲሉ ያ ሰው ያከላክላል፡-
“አይ በዚህ በኩል እንኳ ከንቱ ድካም ነው፤ በሌላ በኩል እንሂድና እንፈልጋለን” ይላል፡፡ ፈላጊው ሁሉ ፊቱን በሌላ አቅጣጫ ያዞራል፡፡ አሁንም ፍለጋው በሌለ አቅጣጫ ይቀጥላል፡፡ ብዙ ከፈለጉ በኋላ እዚያው በሬው ያለበት በረት ጋ ይደርሳል፡፡
ያም ሰውዬ፤
“አይ! አሁን በዚህጋ ምን አለና ይፈለጋል?
ኧረ በሌላ በኩል እንሂድ፡፡ ዛሬ ሳናገኘው አንገባ!”
ሌላ አቅጣጫ ይቀየራል፡፡ ይዞሩ ይዞሩና እዚያው በረት ጋ ይደርሳሉ፡፡ በሦስተኛው ማዕዘን በኩል የተደረገውን ሙከራ ያው ሰው፤ “በዚህ በኩል ባንለፋ ጥሩ ነው” ብሎ ፍለጋውን ገታው፡፡
ይኸኔ በሬው የጠፋበት ሰው ነቃ!
ጥቂት እንደተራመዱ አንድ የሚያውቀው መንገደኛ ሰው ሌላው መንደር ይመጣና፤
“ወዳጄ በሬህ ተገኘ?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ባለ በሬውም፤ “አዝማሪ ያለውን አልሰማህም እንዴ”
“ምን አለ?” አለና ጠየቀው፤ መንገደኛው፡፡
“ነገሩስ ባልከፋ በሬውን መፈለግ
ግን ዳር እየደረስክ ከዐይንህ ሥር ሲሸሸግ
እንደምን ንብረትክን ልታገኘው አሰብክ
ከሰራቂህ ጋር ተሻርከህ እየዞርክ!”
ይሄኔ ያ አፈላጊ ነኝ እያለ አብሮ እሚዞር ሌባ፤ እንደተነቃበት ገብቶት ድራሹ ጠፋ!
* * *
ከሌቦች ጋር ተሆኖ ሌባ-ሻይ መሆን አይቻልም፡፡ ስለዚህ ውስጥን መመርመርና መፈተሽ የማናቸውም አዲስ የለውጥ ሥርዓት አሀዱ እርምጃ ነው፡፡ ሌብነት ከምዝበራና ከብዝበዛም ባሻገር፡- ሥራን  ማዳከምን፣ የቢሮክራሲውን ሞተር እንዳይሠራ አሻጥር ማድረግን፣ የተዛባ መረጃ መስጠትንና ህዝብን ማደናገርን፤ የነባር-አፍቃሪያንን ጎራ ምሉዕ- በኩለሄ (በሁሉም የተነካ) እንደነበረ የሚያሳይ ማስረጃ ማቅረብን ቅራኔው የማይታረቅ መሆኑ ይፋ እስኪወጣ ድረስ በጥድፊያ ውስጥ ውስጡን መርዝ መርጨትን፣ አዲስ መዋቅር ብቅ ካለ፣ አናት አናቱን መምታትን… ይጨምራል፡፡ በሩሲያ አብዮት ዘመን የፓርላማ ሰዓት አይሠራም ነበር- የክሬምሊን ደወል ከቆመ አገር ምን ዋጋ አላት? እያሉ ክፉኛ መፃረራቸውን ያንፀባርቁ ነበር፡፡  ልባምና ንቁ የሆነ ትውልድ ክፉና ደግ ለይቶ ህዝቡን በደጉ ወገን ማንቃትና ማገዝ አለበት፡፡፡ በአንዳንድ  ወቅት ስሜታዊነት  የህዝብ ጠላት ነው ይላሉ፤ አበው ፈላስፎች፡፡ በተለይም ጩኸትና ሆታ ሲበዛ “ግርግር ለሌባ ይመቻል” የሚለው ተረት ይሠራል፡፡ በዚህ ላይ የውስጥ ቦርቧሪ ከተጨመረበት አደጋና ሥጋት አረበበ ማለት ነው፡፡
“እኔስ መች ኖርኩ፣ እኔስ መች ተወለድኩ ከጠላቶቼ ጋር አብሬ እየዶለትኩ” ያለው ፎካሪ ወዶ አይደለም! ልብ ይሏል፡፡
ደራሲ ዘውዴ ረታ፤ “የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት” በሚለው መጽሐፋቸው፤
“ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤ በዚያን ዘመን የሥራ ትጋትና ብልህነት ከሚታይባቸው አንዱ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ ሆነው ስላገኟቸው፤ የማንንም ሀሳብ ሳይ ጠይቁ፤ ከውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ዋና ፀሐፊነት አንሥተው ለጥቂት፣ ወራት ልዩ ፀሐፊያቸው በማድረግ የሥራ ጠባያቸውን ካላመዷቸው በኋላ፣ በ1927 ዓ.ም የጽሕፈት ሚኒስቴር ዋና ዳይሬክተር ብለው ሾሟቸው፡፡”.. ለተሿሚው ኃ/ሥላሴ ባደረጉት ንግግር፡-
“ያሳደግኩትን አበባ እኔው ቆርጬ መጣሉ
ከሁሉ የበለጠ የሚያሳዝነኝ ስለሆነ፤
ይህ ሐዘን እንዳይደርስብኝ ተጠንቀቅ” ብለው ነበር፡፡
ከጃንሆይ ተግባርና ንግግር መማር እጅግ ትልቅ አስተውሎትን ያስጨብጣልና ልብ እንበለው! የምንሾማቸው ሰዎች የሥራ ትጋትና “ጨው ሆይ! ብትጣፍጥ ጣፍጥ፤ አለበለዚያ ድንጋይ ነው ብለው ይጥሉሃል” የሚለውን እናስገንዝባቸው፡፡
አሮጌን ሥርዓት ማፍረስ ቀላል ባይሆንም አዲስ ሥርዓት ማነፅ እጅግ ውስብስብ ነው፡፡ “ከአብሮ አደግህ አትሰደድ” የሚል አንደምታም አያጣም! ስለሆነም የሌት ተቀን ልፋትና መስዋዕትነት ጭምር ግድ ይሆናል! ከምንጠራ እስከ አጥር-አጠራ የመቶ ጀምበር ስራ ብቻ አይደል፡፡ “ትርፉን ነግሮ መከራውን ሳይነግረኝ” እንዳንል ውጣ-ወረዱን ከወዲሁ ማወቅ ይበጃል! ‹ሠንሠለቱን ለመበጠስ ከላላው ቀለበት ጀምር› የሚለውን ጥበባዊ መርህ አንዘንጋ፡፡ ደረጃ በደረጃ የምንሠራው ሥራ ደርዝና ብሰለት ይኖረዋል፡፡
እንደ ሩሲያው መሪ እንደ ጎርባቾቭ፤ የግልፅነት ክስተት (ግላስኖስት) ሁሉን በር በረጋግዶ አንድ መወርወሪያ መዝጊያ እንኳ ሳያበጁ  መቅረት ተገቢ አይሆንም፡፡ “ከተናገርክ ፍርጥ፣  ከመታህ ድርግም” ይላሉ የታክቲክ ጠበብት፡፡ አለበለዚያ እሷ ታስራ፣ በሩ ተከፍቶ ተትቶ፣ ሌባ ገብቶ ሲዘርፍ እንዳየችው ውሻ፤ “በራቸውን ሳይዘጉ ሌባ ሌባ ይላሉ” እንዳንል እንሰጋለን፡፡ ስለዚህም፤
“ላገሩ አልሆን ብሎ ሁኔታው ሲጠጥር
ጠጣሩ እንዲላላ የላላውን ወጥር!” እንላለን-ዛሬም ከገሞራው ጋር!

Read 8547 times