Saturday, 14 July 2018 11:57

የኢትዮ- ኤርትራ አዲስ ምዕራፍ - በፕሮፌሰሩ ዕይታ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

  • በ10 አመት ውስጥ ኢትዮጵያና ኤርትራ በኮንፌደሬሽን ሊዋሃዱ ይችላሉ
     • በኢትዮጵያ አብዮት ሳይሆን ውስጣዊ የሥልጣን መቆራቆዝ እየተካሄደ ነው
     • ፕሬዚዳንት ኢሣያስ እንደዚያን ቀን ሲስቅ፣ ሲዝናና፣---አይቼው አላውቅም


    በተለያዩ ታላላቅ ዓለማቀፍ ዩኒቨርሲቲዎች በታሪክ ተመራማሪነትና መምህርነት ያገለገሉትና የኢትዮጵያ የሥልጣን ሁኔታና የገበሬዎች አመፅን የዳሰሱበትን “Ethiopian Power and Protest” እንዲሁም የኢትዮጵያ ኤርትራ ጦርነትን፣ በኢትዮጵያ የተደረገውን አብዮታዊ ለውጥ የቃኙበትን “The Ethiopian Revolution” የተሰኙ መፅሐፍትን ለንባብ ያበቁት ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ፤ በተለይ በኢትዮጵያና ኤርትራ ታሪካዊ ግንኙነት ላይ ሰፊ ጥናትና ምርምር በማድረግ ይታወቃሉ፡፡ ለመሆኑ ፕሮፌሰሩ፤ በሁለቱ አገራት መካከል በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመፍጠር የተቻለውን የሰላም ስምምነት እንዴት ይመለከቱታል? ከሰላም ስምምነቱስ አገራቱ የሚያገኟቸው ፋይዳዎች ምንድን ናቸው? በኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው የፖለቲካ ለውጥ እንቅስቃሴ ላይም አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ ከፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ ጋር ያደረገው ዘለግ ያለ ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡ እነሆ፡-

    በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የነበረውን ግንኙነት ታሪካዊ ዳራ ለማንሣት ያህል፣ ኤርትራ ነፃነቷን በተቀዳጀች ማግስት  ወደ ጦርነት የተገባበት ትክክለኛ ምክንያት ምን ነበር?
ለጦርነቱ እንደ ምክንያት የምትቆጠረው ባድመ ነች፡፡ ባድመ እንደ ምክንያት የግጭቱ መነሻ ለመሆኗ ደግሞ አፄ ምኒልክ ከጣሊያን ጋር በተፈራረሟቸው ውሎች መሠረት፤ በመሬት ላይ በተግባር ድንበሩን የማስመር ስራ አለመሠራቱ ነው፡፡ ኤርትራ ደግሞ ነፃነቷን ካገኘች በኋላ ሁለቱ ሃገራት ለሠባት ዓመታት ጥሩ ግንኙነቶች ነበሯቸው፡፡ ባህልን፣ አካባቢን፣ ትምህርትን፣ ኢኮኖሚን፣ ሳይንስን የሚመለከቱ ውሎችንም ሁለቱ መንግስታት ተዋውለው ነበር፡፡ በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ታምራት ላይኔ ናቸው፣ ውሎቹን የተፈራረሙት፡፡ በአቶ መለስና በአቶ ኢሣያስ መካከል ደግሞ ልዩ ወዳጅነት የተመሠረተ መስሎ የታየበት ጊዜ ነበር፡፡ ሁለቱን መሪዎች “የአፍሪካ አዲስ ተስፋዎች” በሚል የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ሳይቀሩ አሞካሽተዋቸው ነበር፡፡ ታዲያ ከሠባት ዓመታት በኋላ ባድመን እንደ ምክንያት አድርጎ የተፈጠረው ግጭት ምንድን ነው ብለን ስንጠይቅ፤ ዋነኛው መንስኤ የመሬት ጉዳይ ሳይሆን የኢኮኖሚ፣ የርዕዮተ ዓለም፣ የዜግነትና የማህበራዊ ጉዳይ ልዩነቶች ናቸው፡፡ ሁለቱ አካላት ፀረ-ደርግ ትግል አብረው ሲያደርጉ ለእነዚህ የልዩነት ምክንያቶች ትኩረት አልሠጧቸውም ነበር። ከደርግ ውድቀት በኋላ ኤርትራ ነፃነቷን ስታገኝ፣ ከኢትዮጵያ ልዩ ጥቅም ፈላጊ ሆነች። እንደውም በኢትዮጵያ እንደ ሁለተኛ መንግስት እስኪቆጠሩ ድረስ የፈለጉትን እየሠሩ፣ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ እና በመንግስት ጉዳይ እጃቸውን በረዥሙ እያስገቡ ነበር፡፡ በኢኮኖሚ ደግሞ ብዙ አሻጥር ይሠሩ ነበር፡፡ ያኔ አንድ የአሜሪካን ዶላር 5 ብር የነበረ ይመስለኛል፤ እነሱ ሆን ብለው ምንዛሬውን ከፍ አድርገው መሠብሠብ ጀመሩ። ኤርትራ ቡና አምራች አይደለችም፡፡ ከኢትዮጵያ በኮንትሮባንድና በተለያዩ መንገዶች እየወሠዱ፣ በድንገት ኤርትራ ቡና አምራች ሆና ብቅ አለች፡፡ ለውጭ ገበያ ቡና አቅራቢ ሆነች፡፡ ሌሎችም እንደ ሠሊጥና ጥራጥሬ ያሉትንም በተመሳሳይ እሷ ሣታመርት ከኢትዮጵያ እየወሠደች ለውጭ ገበያ ታቀርብ ነበር፡፡ የራሳቸውንም ናቅፋ የተባለውን ገንዘብ ያሳትሙ ነበር፡፡ በኋላ ብር እና ናቅፋ እኩል ዋጋ እንዲኖራቸው እንዲሁም  ግብይቱም በሁለቱ ገንዘብ እንዲሆን ይጠይቃሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ደግሞ አይሆንም፣ የምንገበያየው በዶላር ነው፤ ብር እና ናቅፋን እኩል አድርገን አንቀበልም የሚል ምላሽ ይሠጣል፡፡ በዚህ የተነሣ የኤርትራ መንግስት ተቆጣ፣ የተፈራረምናቸው ውሎች ተሸረሸሩ አለ፡፡ በዚህ ምክንያት ወደ ጦርነት ተገባ፡፡ የጦርነቱ ዋና ምክንያት ይህ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ  ደግሞ በፀረ ደርግ ትግሉ ወቅት ይዘውት የመጡት መቃቃር አለ፡፡ አፋፍ ላይ ደርሠው ነበር፡፡
በወቅቱ (1977) ጦርነት አፋፍ ላይ ያደረሳቸው ጉዳይ ምን ነበር?
በዚያን ጊዜ ሻዕቢያ ለብቻው ከደርግ ጋር የሠላም ድርድር ማድረግ ጀምሯል የሚል ወሬ ህወኃት ይሠማል፡፡ ይሄ ያስደነግጣቸዋል፡፡ ከመጀመርያውም ህወኃቶች፤ ኤርትራ የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ናት ብለው የተቀበሉት ለደህንነታቸው ሲሉ ነው፡፡ ገብሩ አስራትና አረጋዊ በርሄ እንደሚሉት፤ በወቅቱ ያለመብሰል ወይም ያለማገንዘብ ጉዳይ አይደለም። በወቅቱ እነሱ ኤርትራ በኢትዮጵያ ቅኝ ተገዝታለች ብለው ሲቀበሉ የስትራቴጂክ ምርጫ ነበር፡፡ ይህ ማለት የትግራይ ትግል ከኤርትራው ትግል ጋር ተያያዥ ነው፡፡ የኤርትራው ትግል ካልቀጠለ የህወኃት ትግል ህይወት እይኖረውም ብለው በማሠብ ነው፡፡ በእርግጥም የኤርትራ ትግል ጠቅሟቸዋል፡፡ ኢህአፓ በወቅቱ “የኤርትራ ትግል የቅኝ ግዛት ጉዳይ ነው ብለህ ተቀበል” ተብሎ ነበር፡፡ ኢህአፓ ግን ዝምታን ነበር የመረጠው። ህወኃት እና ሻዕቢያ በዚህ ተሣስረው ነው በመጨረሻ ለድል የበቁት፡፡ በ1977 ጦርነት አፋፍ ላይ ደርሠው የነበረውም ሻዕቢያ ከደርግ ጋር እየተደራደር ነው መባሉ ህወኃትን ያደናገጠ ጉዳይ በመሆኑ ነው። ሌላው እንዲሁ በወቅቱ ሁለቱ ፀረ ደርግ ታጋዮች የተስፋፉበት ጊዜ በመሆኑ፣ በ1977 የተከሠተውን ድርቅ ተከትሎ፣ ህወኃት ህዝቡን ከእልቂት ለማዳን ወደ ሱዳን ሊያሻግር ሲል ሻዕቢያ በሩን ዘግቶባቸው ነበር፡፡ እናንተ የቀበሮ ጉድጓድ ብቻ ተቀምጣችሁ ከህዝቡ ሳትቀላቀሉ፣ ህዝቡን ሳትቀሠቅሱ ድልን መቀዳጀት አትችሉም በሚል ህወኃት ሻዕቢያን ይተች ነበር፡፡ ሻዕቢያ ደግሞ ህወኃትን ይንቀው ነበር፡፡ መልስ አይሠጣቸውም ነበር። ሌላው የፀባቸው ምክንያት ህወኃት የሚያራምደው የብሄር ጉዳይ ነው፡፡ በኤርትራ ዘጠኝ ብሄሮች አሉ፤ ስለዚህ የብሄሮች መብት እስከ መገንጠል የሚለውን ተቀበሉ ይሏቸዋል ህወኃቶች። ሻዕቢያ ደግሞ እኛ ፀረ ቅኝ ግዛት ነው ትግላችን፤ በኛ ጉዳይ አያገባችሁም ይሏቸዋል፡፡ ኋላም ህወኃት-መራሹ ኢህአዴግ፤ አሁን ያለውን የፌደራል ስርአት ሲያቋቁም፣ በወቅቱ የኤርትራ መከላከያ ሚኒስትር የሆነው ጀነራል ስብሃት ኤፍሬምን ሁለት ጊዜ አግኝቼ አነጋግሬው ነበር፡፡ ህወኃት ሃገሪቱን በብሄር ማደራጀቱ ዞሮ ዞሮ እግራቸውን እንደሚቆርጣቸው ነግረናቸዋል፤ የጎሣ ፌደራሊዝም አይጠቅምም ብለናቸው ነበር ብሎኛል፡፡ እነዚህ እንግዲህ ሁለቱ በአንድ ተሰልፈው ደርግን የጣሉ ሃይሎች፣ ከነበራቸው ልዩነት ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ይህ ቁርሾ ወደ ሁለቱ ሃገራት ጦርነት ደረጃ ከፍ እንዳደረገው መገመት ይቻላል፡፡
እንግዲህ  ሁለቱ ሃገራት በጦርነት ከተለያዩ ከ20 ዓመት በኋላ ሠሞኑን አዲስ የሠላም ስምምነት ላይ ደርሰዋል…ይህንን የለውጥ ተስፋና ብርሃን እርስዎ  እንዴት አዩት?
በአግራሞትና በመደነቅ ነው ያየሁት፡፡ ምክንያቱም ሂደቱ በጣም ፈጣን ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አስመራ ሄደው ባለ በርካታ ነጥብ ስምምነት መፈራረም ያልተጠበቀና አስገራሚ፣ አንዳንዴም አስደንጋጭ ሆኖ አገኘዋለሁ፡፡ ይህ የሠላም ስምምነቱ የቀጠናውን ሁኔታ ይቀይረዋል የሚል ግምት አለኝ፡፡ የመሪዎቹን የግለሰብ ሁኔታ ስንመለከትም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ መጀመሪያ የአስመራን ምድር ከረገጡበት ጊዜ አንስቶ እስከ ምሽት የራት ግብዣው ድረስ ያለውን ሁኔታ ስንመለከት፤ ፕሬዚዳንት ኢሣያስ አፈወርቂ እንደዚያን ቀን ሲስቅ፣ ሲዝናና፣ ሲንቀሳቀስ አይቼው አላውቅም፡፡
ይህ የእርቅ ሂደት ለኤርትራውያንና ለፕሬዚዳንት ኢሣያስ አፈወርቂ ምን አንደምታ ይኖረዋል?
አንድ በኤርትራ ቲቪ አስተያየት የሰጠ ሠውም፤ “በትዕግስት ስንጠብቀው የነበረ መስዋዕት የከፈልንበት ነው፤ ውጤቱ የትዕግስትና የአቅል ነው” ብሏል፡፡ በዚህ አስተያየት ውስጥ የተገነዘብኩት፤ ኢሳያስ ጀግና ነው አለምን ገትሮ የያዘ ነው፤ ከአቋሙ ዝንፍ የማይል ነው ከሚለው በመነሳት፣ የአለመንበርከክነት ውጤት ሆኖ በደጋፊዎቻቸው እንደሚታይ ነው፡፡ ይህ የሠላም ጅምር በዚህ ሁኔታ የነበራቸውን የአለመንበርከክ ድጋፍ የሚያጠናክርላቸው ይመስለኛል፡፡ እንደሚታወቀው የኤርትራ መንግስት አፋኝ መንግስት ነው፡፡ ህገ መንግስት የሌላት፣ የዲሞክራሲ ፍንጭ ያልታየባት ሃገር ናት፡፡ በዚህ ምክንያት መድብለ ፓርቲ የሚባል ነገር የለም፡፡ በውጭ ሃገራት ሆነው የሚንቀሳቀሡ 19 ያህል ተቃዋሚ ድርጅቶች ቢኖሩም ያን ያህል ጠንካራ አይደሉም፡፡ ድርጅቶቹ ያላቸው ድክምት እንዳለ ሆኖ፣ ኢሣያስ ላይ የሚቀርቡ ተቃውሞዎች ለጊዜው በዚህ ሁኔታ ሊለዝቡ ይችላሉ፡፡ ሌላው ኤርትራ እንደሚታወቀው፤ ከአለም ማህበረሰብ ተገልላ የቆየች ሃገር ነች፡፡ ከኢጋድ አባልነት እንኳ የወጣች ሃገር ነች። ፕሬዝዳንት ኢሣያስም የአለም ባይተዋር ሆነው ነው የኖሩት፡፡ አሁን በ24 ሰዓት ውስጥ እንደ ሰሜን ኮርያው ኪም፣ በአንድ ጊዜ ወደ ዓለም መድረክ ነው የመጡት። በአንድ ጊዜ የዓለም መድረክ ላይ ቁጭ ነው ያሉት፡፡ ኤርትራም የአለም ህብረተሰብ አካል መሆን ወዲያው ጀምራለች፡፡ ለምሳሌ ከኢጋድ በፍቃዳቸው ነበር የወጡት፡፡ አሁን ኢጋድ የዶ/ር አብይን ብስለት አድንቆ፣ ኤርትራም ወደ ወጣችበት ማህበር እንድትመለስ ግብዣውን አስተላልፏል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደግሞ በኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንዲነሣ ጠይቀዋል። ማዕቀቡ ከተነሣ ለፕሬዚዳንት ኢሣያስ ትልቅ ትርፍ ነው፡፡ ይሄ ሁሉ በር የተከፋፈተው 48 ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ነው። እነዚህ በጎ ውጤቶች እንዳሉ ሆነው፣ ለፕሬዝዳንቱና መንግስታቸው የሚያሠጋ ነገርም አለ። ኤርትራ በሯ ተከፍቶ ወጣቱ፣ ዜጎች በአጠቃላይ ከሌላው አለም ጋር የሃሣብ መለዋወጥ ውስጥ ይገባሉ፤ ታስሮ ታፍኖ የነበረው ህዝብ ብዙ ልምድ ያገኛል፡፡ በዚህም ህዝቡ እንዳለፈው ጊዜ አፍነው የማይዙበት ደረጃ ይደርሳል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይህ ሲሆን ኢሣያስ አፈወርቂ ሁለት ምርጫ ይኖራቸዋል፡፡ አንደኛ፤ አስፈላጊውን ለውጥ አድርጎ፣ የለውጡን ፍላጎት ማስተናገድ ሲሆን ሌላኛው አማራጭ ደግሞ በሃይል ጨፍልቆ ማኖር ነው። ሁለተኛው በአሁን ዘመን የሚያዋጣ አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ ዶ/ር ዐቢይ የጀመሩ እንቅስቃሴ ለኤርትራ ህዝብ በጎ ውጤት አለው፤ አምባገነን  ለሆኑት ፕሬዚዳንት ኢሣያስ ደግሞ አደጋም ደቅኗል፡፡
ኢትዮጵያስ ከዚህ የእርቅና ሰላም ሂደት ምን ታተርፋለች?
ዶ/ር ዐቢይ ያደረጉት ነገር ድፍረትን እውቀትን የሚጠይቅ ነገር ነው፡፡ አንዱ ይህ ያለንበት የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደ አንቀሳቃሽ ሞተር የሚታዩበትን ሁኔታ የሚፈጥር ይመስላል። በጥልቀት የሚያስብ፣ ቃሉን አክብሮ የሚፈፅም መሪ የሚል ክብር ያስገኝላቸዋል፡፡ ይሄ አንዱ ትርፍ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ህዝብ አንፃር ደግሞ ይህ ሰውዬ መናገር ብቻ ሳይሆን የተግባር ሰው ነው የሚለውን ትርፍ ያስገኝላቸዋል፡፡ የተናገረውን የሚፈፅም ነው የሚል ተአማኒነት ያስገኝላቸዋል፡፡ በፖለቲካ ደግሞ አንድ መሪ ውጤታማ የሚሆነው ህዝብ ሲያምነው ሲተማመንበት ነው፡፡ እሳቸው በግላቸው ያተረፉት ነገር ይሄ ይመስለኛል፡፡
የእርቅ ሂደቱ ገና ብዙ አድካሚ ድርድር የሚጠይቅ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ከአድካሚው ድርድር በኋላ ግን የምስራቅ አፍሪካ አካባቢ አንቀሣቃሽ ዋነኛ ሃይል ኢትዮጵያና ኤርትራ እንደሚሆኑ ምንም ጥርጥር የለኝም። በአንድ በኩል ኢትዮጵያ በመልክዐ ምድሯ ስፋት፣ በህዝቧ ብዛት፣ በተፈጥሮ ሃብቷ፣ በኢኮኖሚ እድገቷ፣ በመከላከያ ብቃቷ የአፍሪካ ቀንድ እምብርት፤መልህቅ ነች፡፡ በዚህ ላይ ሁለቱን ወደቦችና ሠራተኛ ህዝብ ይዛ፣ ኤርትራ ስትጨመርና ሁለቱ ተስማምተው ሲሠሩ፣ ከአፍሪካ ቀንድ በመሻገር ታላቁን የምስራቅ አፍሪካ ቀንድ በመመስረት የአካባቢው ሞተር ይሆናሉ፡፡ ይህ ግምቴ ብቻ ሳይሆን ዘላቂ ሠላም ማስፈን እስከተቻለ ድረስ በትክክል የሚሆን ነው፡፡
ይህ የሁለቱ አገራት  እርቅ ለምን እስከ ዛሬ ዘገየ…? አሁንስ ለምን ሆነ? የሚል ጥያቄም ይነሣል---
አሁን ለምን ሆነ ለሚለው መልሱ፤ በኢህአዴግ አመራር ትልቅ ለውጥ መምጣቱ ነው፡፡ በብዙ ፍጭት ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመጡት፡፡ ከዚያ በፊት በቀላሉ ነበር አንድ ሰው ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሆነው፡፡ አቶ ለማ፤ “ተቆሣስለን ተፋጭተን ነው እዚህ የደረስነው” እንዳሉት፣ ዶ/ር ዐቢይ የመጡት፣ በዚህ መቆሳሰልና ፍትጊያ አልፈው ነው፡፡ ስለዚህ ይህ የአመራር ለውጥ መምጣቱ እርቁ አሁን ለመፈፀሙ ዋናው ምክንያት ነው፡፡ ሁለተኛው፤ በፕሬዚዳንት ኢሳያስ የሚመራው የኤርትራ መንግስት፣ የኢትዮጵያን መንግስት ኢህአዴግ ብሎ አይጠራውም፤ ወያኔ እያለ ነው የሚጠራው። ይህ ምንን ያመለክታል፣ ህወኃት ደንቃራ እንቅፋት ሆኖብኛል ብሎ የሚያምን መሆኑን ነው። አሁን ተንቀሳቃሽ፣ ደፋር መሪ መምጣቱንና የዶ/ር አብይን ቁርጠኝነት ሲያዩ፣ የእርቁን ፍላጎት ሃቀኝነት የተገነዘቡ ይመስለኛል፡፡ ህወኃት ተዳክሟል ዳግም አያንሠራራም፤ በዚህም የእርቁ በር ተከፍቷል የሚል እምነት እንዳደረባቸው ምንም ጥርጥር የለውም። የፕሬዚዳቱ አቀባበልም ይህን አመላካች ነው፡፡
ዶ/ር አብይ አስመራ በቆዩበት ጊዜም በሚያደርጓቸው ንግግሮች፣ በአቀራረባቸው ፕሬዚዳንቱን በጣም ነው ያስደመሟቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የነበራቸው አቀራረብ አስገራሚ ነበር፡፡ መፈራራቱን፣ መጠራጠሩን ሁሉ ነው በውስን ቃላት የሠባበሩት፡፡
“The Ethiopian Revolution” በተሠኘው መፅሐፍዎ፤ ለሁለቱ ሃገራት በኮንፌደሬሽን መተሣሠር ጠቃሚ እንደሆነ በሚገባ አስረድተዋል፡፡ እርስዎ የሚሉት አይነት ኮንፌደሬሽን ወደፊት የሚፈጠር ይመስልዎታል?
ከዚህ ቀደም በሸገር ሬድዮ ስጠየቅ፣ ከ25 ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በኮንፌደሬሽን ይጣመራሉ ማለቴን አስታውሳለሁ፡፡ ያኔ ይህን ስል በምኞት ነበር፡፡ አሁን ግን በአጭር ዓመታት ውስጥ እውነት እንደሚሆን ሙሉ እምነት አለኝ፡፡ የሁለቱ መሪዎች መቀራረብ ጥሩ ነው፡፡ በቀጣይ የሚደረገው ጠጣር ድርድር ሊያዘገየው ቢችል እንጂ ሁለቱ ሃገራት ከ10 ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ወደ ኮንፌደሬሽን የማይመጡበት ምክንያት አይታየኝም፡፡ በ10 አመት ውስጥ ኮንፌደሬሽኑ ይመጣል የሚል ተስፋ ሰንቄያለሁ፡፡
በዚሁ መፅሃፍዎ ላይ ምስራቅ አፍሪካ ሠላም የሚሆነው የኤርትራ፣ ኢትዮጵያና ሶማሊያ ትብብር እውን ሲሆን ነው ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደግሞ በሁለቱ አገራት መካከል  ጠንካራ ትስስር መፍጠር ይቻላል እያሉ ነው፡፡ ይሄን እንዴት ይመለከቱታል?
አሁን የተጀመረው እንቅስቃሴ ኢጋድን የሚያጠናክር ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ከዚያ አልፈን በተለይም ኤርትራ፣ ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲና ሶማሊያ የተጠናከረ ትብብር በመጀመሪያ በኢኮኖሚ ይመጣል የሚል ግምት አለኝ፡፡ ዶ/ር ዐቢይም የታያቸውና ለማድረግ የሚጥሩት ይሄ ይመስለኛል፡፡ ግሩም ስትራቴጂክ እርምጃ ነው እየወሠዱ ያለው፡፡ በአንድ በኩል ኢትዮጵያን በጎሣ፣ በአካባቢ ከመሻኮት አልፈው አካባቢያቸውን አድማሳቸውን እንዲያሠፉ የሚረዳ ነው፡፡ ይሄ ሲሆን ደግሞ ወደ ኮንፌደሬሽን ለማቅናት ሲሞከር፣ በመጀመሪያ በኢትዮጵያና በኤርትራ የሚጀምር ይመስለኛል፡፡ አንደኛ የ10 ዓመቱ የሁለቱ ሃገራት ፌደሬሽን ልምድ አለ፡፡ ከዚያ ውጪ የሺህ ዓመታት የህዝብ ለህዝብ ትስስሩ አለ፡፡ አሁን ደግሞ በአካል ተገናኝተው ሁለቱ መሪዎች መነጋገራቸው መተማመን ይፈጥራል፤ ቀጣዩን ሸካራ ድርድር የማለስለስ አቅም አለው፡፡ ከዚያ በኋላ ኮንፌደሬሽኑን ለመፍጠር ቀላል ይሆናል፡፡ የዚህ ሞተሩ  ምናልባት በኢህአዴግ ውስጥ ባለው ትርምስ ተጠልፈው ካልቀሩ ዶ/ር አብይ ይሆናሉ፡፡ አሁን የተጀመረው የሠላም ውይይት ጥሩ ውጤት እንደሚያመጣ ግን እተማመናለሁ፡፡
ጅቡቲ ሙሉ ለሙሉ ከፈረንሳይ እጅ አዙር አገዛዝ ባልተላቀቀችበት፣ ደቡብ ሱዳን የሃገር ምስረታዋን ባላጠናቀቀችበት፣ ሶማሊያ ከስርአት አልበኝነት (አናርኪዝም) ባልተላቀቀችበት፣ ኤርትራ የዲሞክራሲ ጅማሮ ውስጥ እንኳ ባልገባችበት፣ ኢትዮጵያ ገና የዴሞክራሲ ጥያቄዎችን ባልመለሰችበትና ብሄርተኝነት ባየለበት ሁኔታ እርስዎ የሚሉትን አይነት ቀጣናዊ ትስስር ፈጥሮ እስከ ኮንፌደሬሽን ሊያመራ የሚችል ነገር እንዴት መፈጠር ይችላል?
ስለ ኮንፌደሬሽን ስንነጋገር፣ እኔ በዋናነት ኢትዮጵያና ኤርትራ ነው ያልኩት፤ ዶ/ር አብይ ደግሞ እየሞከሩ ያሉት ሰፋ ባለ መልኩ ነው፡፡ አካባቢው በጣም አስቸጋሪ አካባቢ ነው፡፡ ገና ሠላም ያልሠፈነበት አካባቢ ነው፡፡ ሶማሊያ ተሰብስባ አላለቀችም፤ እንደተበተነች ናት፡፡ የደቡብ ሱዳን ሁኔታ ውጤቱንም ለመተንበይ አስቸጋሪ ነው፡፡ ኬንያም ብትሆን የጎሣ፣ የሃብት ክፍፍል ችግር አለበት፡፡ ቀጣናው በጣም ያልተረጋጋ ቀጣና ነው። ሠላም ለማስፈን በእያንዳንዱ ሃገር ያለውን ሠላም ማስፈን ያስፈልጋል፡፡ እንደኔ ግን ዋናው ነገር የኢጋድን እንቅስቃሴ ማጠናከር ነው፡፡ ወደ ኢትዮጵያና ኤርትራ ስንመለስ፤ ኤርትራ ነፃነቱን ቢቀዳጁትም ገና ብሄረ መንግስት ምስረታ ላይ ናቸው፡፡ የብሄረ መንግስት ምስረታቸው ከኢትዮጵያ ጋር የተፈጠረው ጦርነት አጓትቶባቸዋል፡፡ ሉአላዊት የምትባለው ድንበሯ የተከለለ፣ በአለም ደረጃ ታዋቂ ድንበሮች ያሏት፣ እውቅና ያላት ሃገር መሆኗን በአለማቀፍ ደረጃ ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ በዚህ ሉአላዊነት ኤርትራ ከተፈጠረች በኋላ ነው በእኩልነትና በፍቃደኝነት ከኢትዮጵያ ጋር በኮንፌዴሬሽን የመተሳሰሩ ነገር የሚመጣው፡፡ እኔ 10 ዓመት ባልበለጠ ብዬ አሣጠርኩት እንጂ ከዚያም ረዘም ሊል ይችላል፡፡ የኔ ተስፋ ግን በ10 ዓመት ውስጥ ይጠናቀቃል የሚል ነው፡፡ ይህ ግን የኤርትራ ብሄረ መንግስት ሳይጠናቀቅ የሚሆን አይደለም፡፡ መጀመሪያ ሉአላዊት ብሄረ መንግስትነቷ መጠናቀቅ አለበት፡፡
ሁለቱ አገሮች  የጀመሩት የእርቅ ሂደት በስኬት እንዲቋጭ ምን ማድረግ ይጠበቃል?
ህወኃት ያነሣቸው ነጥቦች አሉ፡፡ ህዝቡን ያላካተተ፣ ኢህአዴግ ያልተስማማበት የሚል ነገር አስቀምጠዋል። የኤርትራን ህዝብ አቀባበል በመግለጫቸው አደነቁ እንጂ የዶ/ር ዐቢይን ጥረት አልጠቀሡም፡፡ ይህ በትኩረት መታየት አለበት፡፡ ይሄ ተአቅቦ እንዳላቸው የሚያመላክት ነው፡፡ ገና የውስጥ መቆራቆዙ አልሠከነም፡፡ ከዚያ አንፃር እንቅፋት ሊፈጠር ይችላል፤ ስለዚህ ህዝቦች በሂደቱ መካፈል አለባቸው። ተቃዋሚዎችም ደካማም ሆኑ ጠንካራ እነሡም መሣተፍ አለባቸው፡፡ ዜጎች በመገናኛ ብዙሃን በጉዳዩ ላይ ያላቸውን ሃሳብ እንዲያቀርቡ ማበረታት ይገባል። ድንበር አካባቢ ያሉ ህዝቦች፣ በጉዳዩ ላይ መምከር አለባቸው፡፡ ከኢሮብ ህዝብ፣ ከባድመ ነዋሪዎች ጋር መነጋገር መወያየት ያስፈልጋል፡፡ የድንበር ተዋሣኝ ህዝቦች ጉዳዩ በቀጥታ ተፅዕኖ የሚያሳርፍባቸው በመሆኑ ሊወያዩበት ይገባል፡፡ ይሄ ጥንቃቄ መደረግ አለበት፡፡ ኢህአዴግም ወጥ አቋም በጉዳዩ ላይ ከወዲሁ መያዙን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ ሠላምና ፀጥታ ካላገኘች ከውጪ ሃገራት ጋር የምታደርገው ድርድር ሚዛን አይደፋም፡፡ ስለዚህ ሃገር ውስጥ ያሉ ችግሮችን ሙሉ ለሙሉ መፍታት ያስፈልጋል፡፡
እርስዎ ያሉት ኮንፌደሬሽን ባይሠምር የኢትዮጵያ የወደብ ጥያቄ በተለይ በአሠብ ላይ ያላት ጥያቄ እንዴት ነው ምላሽ ሊያገኝ የሚችለው?
ኮንፌደሬሽኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ካልመጣ የአሠብ ጉዳይ የሚወሠነው፣ በሁለቱ ሉአላዊ ሃገራት ነፃ መንግስታት መካከል በሚደረግ ድርድር ይሆናል ማለት ነው፡፡ አንዳንዶች የሄጉ ውሳኔና የአልጀርሱ ስምምነት ተሰርዞ፣ አዲስ ስምምነት መደረግ አለበት ይላሉ፡፡ ይሄ በሃሳብ ደረጃ ያለ እንጂ በቀላሉ የሚመጣ አይደለም። በእርግጥ በዚህ ጉዳይ የህግ አዋቂ ስላልሆንኩ ብዙ ማለት አልችልም፡፡ ስለዚህ የወደቡ ጉዳይ ከእንግዲህ በሁለቱ ነፃ መንግስታት ድርድር የሚፈታ ይመስለኛል። አሠብ ከኢትዮጵያ መሬት 60 ኪሎ ሜትር  ነው የምትርቀው፡፡ በዚህ ምናልባት የመሬት መለዋወጥ መፍትሄም ሊሆን ይችላል ይላሉ ደጃዝማች ዶ/ር ዘውዴ ገ/ስላሴ፤ የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ችግር መንስኤና መፍትሄ በሚለው መጽኃፋቸው፡፡ የአፋሮች ድምፅ ያለበት ውሳኔ ሊደረግ ይችላል፡፡ በመሬት ልውውጥ አሠብ የኢትዮጵያ የምትሆንበት ሁኔታ ቢፈለግ ጥሩ ነው፤ ይሄ ካልተቻለ በአለማቀፍ ደረጃ የኤርትራ ባለቤትነት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የኢትዮጵያ የተጠቃሚነት መብት የሚረጋገጥበት ህጋዊ ስምምነት መፈጠር አለበት፡፡ በነፃ የመጠቀሙ ጉዳይ ግን የኤርትራ መንግስትን ስምምነት ይጠይቃል፡፡ የሠላም ስምምነቱን ሻካራ ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል አንዱ የአሠብ ጉዳይ ይመስለኛል፡፡
ከኢትዮ-ኤርትራ ጉዳይ በመለስ፣ የዶ/ር ዐቢይን የለውጥ እንቅስቃሴ እንዴት ይመለከቱታል?
እስካሁን አስደናቂ ነው፡፡ ወሳኝነታቸውንና ፍጥነታቸውን እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ ወድጄዋለሁ። ግን አንዳንዴ ፍጥነቱ ከችኩልነት የማይለይበት ሁኔታ ይታየኛል፡፡ እዚህ ላይ አንዲት ምክንያት መግለፅ እችላለሁ፡፡ የፕራይቬታይዜሽን ጉዳዩን በተመለከተ በምን ጥናት ነው? ምን አይነት ውይይት ተካሄደ? ድጋፍና ተቃውሞስ ምን ያህል ቀረበበት? ስለሚለው የተነገረን ነገር የለም፡፡ ፕራይቬታይዜሽን አንዳንድ ሃገራትን አውድሟል፡፡ ከአፍሪካ በዚህ ተጠቅማለች የምትባለው ሞዛምቢክ ነች፡፡ ግን እሷ ጥሩ ምሳሌ መሆን አትችልም፡፡ ፕራይቬታይዜሽን ጎጂ ነው። በተለይ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ወደ ግል ጥቂት ድርሻም ቢሆን ለማዞር መወሠን ያስቆጫል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትራንስ ዎርልድ ኤርላየንስ በተሠኘው የአሜሪካ አየር መንገድ ድጋፍ የተቋቋመ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ኢትዮጵያውያን ሙሉ ለሙሉ ተቀብለው ነው ዛሬ ያለበት ገናና ደረጃ ያደረሱት፡፡ ፍጹም የተሟላ ስኬታማ ድርጅት ነው፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፡፡ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ለዘመናት የተሸከመ ነው፡፡ የማንነታችን መገለጫ የሆነ ተቋማችን ነው፡፡ ኩራታችን ነው፡፡ ይሄን ለሃገር ውስጥም ሆነ ለውጪ ባለሃብቶች ማስረከብ ዝቅጠት ነው፡፡ ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ይህን ነገር ለማስቆም መታገል አለባቸው የሚል አቋም አለኝ፡፡ ሁሉም ነገር በሳንቲም መተመን የለበትም፡፡ ለነገሩ ድርጅቱም በአትራፊነት አይታማም፡፡
አሁን በኢትዮጵያ የሚታየውን አጠቃላይ ለውጥ እንዴት ይገልጹታል?
አንዳንዶች አብዮት እየተካሄደ ነው ይላሉ፡፡ እኔ ደግሞ እንቅስቃሴ እንጂ አብዮት እተካሄደ አይደለም የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይህ እንቅስቃሴ ደግሞ በኢህአዴግ ውስጥ የሚካሄድ ነው፡፡
ዶ/ር ዐቢይ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ናቸው፡፡ ይሄ የለውጥ እንቅስቃሴ በኢህአዴግ ውስጥ በመካሄድ ላይ ያለ እንጂ ከዚያ ውጪ መዋቅር ያለው፣ ህዝባዊነት ያለው እንቅስቃሴ አይደለም፡፡ ወደ ተቋማት የወረደ እንቅስቃሴ አይታየኝም፡፡ ስለዚህ አብዮት እየተካሄደ አይደለም፤ እንቅስቃሴ ነው ያለው፡፡ አንዳንዶች እንደውም፣ ዶ/ር ዐቢይን ከሚኻኤል ጎርቫቾቭ ጋር የሚያነፃፅሩ አሉ፡፡ ይሄ የማልቀበለው ነው፤ አብዮት ሳይሆን ውስጣዊ የስልጣን ቁርቁዝ ነው እየተካሄደ ያለው፡፡ በኢህአዴግ ውስጥ ትርምስ አለ፡፡ ግን እኔ ዶ/ር ዐቢይ፣ የጎርቫቾቭ እድል እንደማያጋጥማቸው ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ለምን? ሚኻኤል ጎርቫቾቭ ባናፈሡት የዲሞክራሲ ሃሳብ፣ እሳቸው ከስልጣን ሲወርዱ የኮሚኒስት ፓርቲ አብሮ ተገለለ፡፡ ሶቭየት ህብረትም ተበታተነች፡፡ ዐቢይ ጎርቫቾቭ ሆኑ ማለት ከስልጣን ይወርዳሉ፣ ኢህአዴግ ይበታተናል፣ ኢትዮጵያም ትከፋፈላለች እንደ ማለት ነው፡፡ ንፅፅሩ ስለሚያስፈራኝ አልስማማበትም፡፡
አራቱ የኢህአዴግ ደርጅቶች የሚያራምዱት በዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የሚመራ ነው፡፡ ይሄ ከበረሃ ይዘወት የመጡት ነው፡፡ ከአቶ መለስ ህልፈት በኋላ ይሄ የርዕዮተ አለም አንድነት እየተሸረሸረ፣ እየተዳከመ መጥቷል፡፡ ስለሆነም በኔ እይታ፤ አብዮታዊ ዲሞክራሲ መርህ መቃብር ዳርቻ ላይ የደረሰ መስሎ ይታየኛል፡፡ ይሄ የሚያመጣው የራሱ አደጋ አለ። በቄሮዎችና በአርሶ አደሮች የተካሄደው አመፅ፣ እነ ለማ መገርሣ እንዲመጡ አደርጓል፡፡ ኦህዴድ አቋቋሙን እንዲፈትሽ አድርጎታል፡፡ ወጣት መሪዎች ሥልጣኑን ያዙ፡፡ ሥልጣኑን ከያዙ በኋላ ህወኃትን መጋፈጥ ይጀምራሉ። በአማራም በተመሳሳይ ወጣቱ ይንቀሳቀሳል፡፡ ይህ ኦህዴድና ብአዴንን ያቀራርባቸዋል፡፡ የእነሡ ጣምራ ጉዞ ህወኃትን ሙሉ ለሙሉ ከጨዋታው አስወርዶ ተራ አባል አድርጎታል። ከአሁን በኋላ ህወኃት አንሰራርቶ የመሪነቱን ቦታ ይይዛል የሚል ግምትም የለኝም፡፡ ከዚህ በኋላ የሡ ምዕራፍ አብቅቷል፡፡ አሁን ዶ/ር ዐቢይ የሚመሩት ኢህአዴግ ቅራኔዎች ያሉበት፣ ልዩነቶች ያሉት ደካማ ድርጅት ይመስለኛል፡፡ ከዚህ በኋላ የሚሻለው በመመካከር የኢህአዴግን ርዕዮተ አለም ከመቃብር አፋፍ መመለስ፣ ከግንባር ወደ ውህደት መሄድ አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ ይህ ለኢህአዴግ ብቻ ሳይሆን ለሃገሪቱም አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ ቢያንስ ቀጣይ ምርጫ እስኪደረግ የኢህአዴግ ልዩነቱን ማስታረቅ፣ለሃገሪቱ አንድነት አስፈላጊ ሊሆን ይችላል፡፡ ከእንግዲህ ያለው አማራጭም ወይ መተባበር አሊያም መበታተን ነው፡፡ የኋለኛው እንደማይሆን ተስፋ አለኝ፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀጣይ ፈተናዎች ምንድን ናቸው ይላሉ?
አሁን ኢህአዴግ የተዳከመበት ወቅት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጣብቂኝ ውስጥ ነው የገቡት፡፡ የመጀመሪያው አንቆ የሚይዛቸው የራሳቸው ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱ የፈጠረው በሠንሠለት የተሣሠረ፣ የሻገተ ቢሮክራሲ ነው ፈተናቸው፡፡ ያንን ቢሮክራሲ ለማፅዳት ኢህአዴግ ተጠናክሮ መውጣት ይኖርበታል። ይሄ ደግሞ በጥያቄ ውስጥ የገባበት፤ ርዕዮተ ዓለሙ መቃብር አፋፍ የደረሰበት ድርጅት ነው፡፡ ወጥሮ የሚይዛቸው የራሳቸው ድርጅት ነው የሚል እሳቤ ነው ያለኝ፡፡

Read 7430 times