Saturday, 23 June 2018 11:52

የቀድሞ የእስልምና ጠ/ም/ቤት ፕሬዚዳንት ስለ መጅሊሱና የመንግስት ጣልቃ ገብነት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 • መንግስት ከሊባኖስና ከኢራን የአህባሽ አስተማሪዎችን አምጥቶ ነበር
  • የመንግስት ጣልቃ ገብነት የሙስሊሙን አንድነት ሸርሽሮታል
  • የመጅሊስ አመራሮች ለእምነቱ ብቻ እንዳይቆሙ ተደርጓል

    ሸይህ ኺያር ሙሃመድ አማን ይባላሉ፡፡ ከ2005 እስከ 2007 ዓ.ም የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት (መጅሊስ) ፕሬዚዳንት ነበሩ፡፡ በ2005 ዓ.ም በተካሄደው አወዛጋቢው የመጅሊሱ ፕሬዚዳንት ምርጫ፤ ለ5 ዓመት ለማገልገል የተመረጡት ሸይህ ኺያር ከሁለት አመት የስልጣን ቆይታ በኋላ ከስልጣን መነሳታቸውን በድንገት ከሬዲዮ መስማታቸውን ይናገራሉ፡፡ ለምን ከስልጣናቸው በድንገት ተነሡ?መንግስትና መጅሊሱ በወቅቱ የነበራቸውን ግንኙነት ያስረዳሉ፡፡ ለመሆኑ ግንኙነቱ ምን መልክ ነበረው? በመጅሊሱ አመራርነት ወቅት አጋጥመውኛል የሚሏቸው ፈተናዎች ምንድን ናቸው? ሸይህ ኺያር ሙሃመድ አማን ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡

   “የተዳፈነ የሙስሊሙ ሃቅ አለ” ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡ ለመሆኑ የተዳፈነው ሃቅ ምንድን ነው?
የሙስሊሙ ህብረተሰብ ጥያቄ ግልፅ ነው፤ ግን የተዳፈነ ነው፡፡ ጥያቄያችን ፍትህ ይሠጠን፤ እኛም እንደ ሌላው የዚህች ሃገር ዜጋ ነን፤ መብታችን በእኩል ይጠበቅ ነው፡፡ ይህ መብታችን ይጠበቅ የሚለው ጥያቄያችን፣ ከአፄዎቹ ጀምሮ ሲዳፈን እዚህ የደረሰ ነው፡፡
እርስዎ በ2005 በርካቶች ተቃውሞ ባቀረቡበት የመጅሊሱ ምርጫ ነው ወደ ስልጣን የመጡት?
በመጅሊሱ የመንግስት ጣልቃ ገብነት ከፍተኛ ነው፡፡ ቀደም ሲልም ሆነ አሁን ላይ ያሉት የመጅሊሱ አመራሮች፣ ምን ያህል የመንግስትን ዓላማ ብቻ አራማጅ እንደሆኑ ነው የተረዳሁት፡፡ የመጅሊስ አመራሮች፣ የመንግስትን ጉዳይ እንዲያስፈፅሙም ነው የሚፈለገው፡፡ በዚህም ታዛዥ መሆን አለባቸው። ለመንግስት አጎብድደው፣ ማንነታቸውን ረስተው፣ ፈጣሪን ረስተው፣ ሰውን ብቻ የሚፈሩ ሰዎች እንዲሆኑ ነው የሚፈለገው፡፡ ሃይማኖቴን ፈጣሪዬን መካድ የለብኝም ፤አላጎበድድም የሚሉ ሰዎች በቦታው እንዲቆዩ እንደማይፈለግ ነው የተረዳሁት፡፡ ትንሽ መንግስትን የሚፈታተኑ ከሆነ፣ በኛ ላይ የተፈፀመው ነገር ነው የሚያጋጥማቸው፤ ስለዚህ የመጅሊስ አመራሮች ለእምነቱ ብቻ እንዳይቆሙ ተደርጓል፡፡
በአወዛጋቢው የ2005 የመጅሊስ ምርጫ ተሳትፈዋል…ዛሬ ግን ወቃሽ ሆነዋል፡፡ በወቅቱ  ምርጫ እንዴት ሊሣተፉና በፕሬዚዳንትነት ሊመረጡ ቻሉ/ፈለጉ?
እኛ በወቅቱ አጋጣሚውን ለመጠቀም ነበር የፈለግነው፡፡ ትክክለኛ የሙስሊሙ ምሁራን ወደ መድረኩ መጥተው፣ የሙስሊሙን ችግር እንዲፈቱ በሚል ነው በምርጫው የተሣተፍነው፡፡ በወቅቱ እንደሚታወቀው፣ ግማሾቹ ታስረዋል፤ ግማሾቹ ከሃገር ተሠደዋል፡፡ እኛ ደግሞ ገብተን ይህን ነገር እንለውጥ፤ እድላችንን እንሞክር፤ ይሄን ሃይማኖት እናድን ብለን ነው ወደ ምርጫው የገባነው፡፡ እኔ በኦሮሚያ አርሲ ዞን ነው የተመረጥኩት፤ በኋላም በፕሬዚዳንትነት ተመርጫለሁ፡፡
እናንተ ስትመረጡ የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት እስር ቤት ነበሩ ---
በወቅቱ ወንድሞቻችን (የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት) ሊታሠሩ የቻሉበት ምክንያት አህባሽ የሚለው ልዩ አመለካከት፣ ከእስልምና መርህ ውጪ ነው በማለታቸው ነው፡፡ በዓለም ዙሪያ ማንኛውም ሙስሊም የሚመራው፤ በቁርአንና በሃዲስ ነው፡፡ ከዚህ አልፎ ቁርአንና ሃዲስን የሚተረጉሙ አራት የሃይማኖት አስተምህሮዎች አሉ፡፡ እኛ ከፈጣሪ ከተሠጠን ውጪ የምናመጣው አዲስ ሃይማኖት የለም ስንል፤ መንግስት ደግሞ ከሊባኖስና ከኢራን የአህባሽ አስተማሪዎችን በማምጣት፣ ይህ ነው ትክክለኛው፣ ለእናንተ የሚገባችሁ ለማለት ነው የፈለገው፡፡ ስንት የሃይማኖት ሊቃውንቶች፣ ኡለማዎች ባሉበት ሃገር፣ ከውጭ ማምጣት ምን ማለት ነው? ለምንድን ነው ከውጭ የምታመጡት ስንላቸው፣ የተሻሉ በመሆናቸው የሚል ነበር ምላሹ፡፡ ይህን ያደረገው መንግስት፣ ለራሱ ፖለቲካ የሚመቸውን ሁኔታ ለመፍጠር ነበር፡፡ በዚህ አካሄዱ በቀጥታ በኢትዮጵያ እስልምና ቲዎሎጂ ውስጥ ሳይቀር ነው መንግስት እጁን ያስገባው፡፡ ይሄን ደግሞ በወቅቱ ህዝቡ አልፈለገም ነበር፡፡ እኛም በመጅሊሱ አመራር ላይ ሆነን፣ ይህን ወንድሞቻችን የታሠሩበትን ጉዳይ ለመሞገት ጥረት ስናደርግ ነበር፡፡
በወቅቱ የትኛው የመንግስት አካል ነበር ጣልቃ ሲገባ የነበረው?
በቀጥታ ጣልቃ ገብቶ ይህን አድርጉ፣ ያንን አድርጉ ሲል የነበረው፣ የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ነው፡፡ ሚኒስትሩ እና ሚኒስትር ዴኤታው ናቸው፣ ይሄን ተፅዕኖ የሚደርጉት፡፡ በእርግጥ ሌላ እነሱንም የሚያዛቸው አካል እንዳለ ግልጽ ነው፡፡ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሚ/ር ዴኤታ የነበሩት አቶ ሽመልስ ከማልም በቀጥታ አህባሽ አስተምሮ በኢትዮጵያ መስፈን አለበት በሚል ተፅዕኖ ያደርጉብን ነበር፡፡ እኛ ደግሞ “ህዝቡ ከሚከተለው ሃይማኖት ውጪ ሌላ ነገር ማስተማር አንችልም፣መንግስት ከህገ መንግስቱ ውጪ፣ በጉዳያችን ጣልቃ እየገባ ነው” በሚል በመከራከራችን ነው  ጥርስ ውስጥ መግባት የጀመርነው፡፡
የኮሚቴው አባላት ሲታሠሩ፣ እናንተ ወደ ምርጫው የገባችሁት፣ ይህን ዓላማ ይዛችሁ ነው ማለት ነው?
አዎ! በዘዴ ገብተን ወገኖቻችንን፣ ህዝባችንን፣ እምነታችንን የምንታደግበትን መፍትሄ ለማቻቸት በሚል ነው፣ መንግስት በሚፈልገው መንገድ ወደ ምርጫው የገባነው፡፡ ውስጥ ሆነን ነገሮችን ለመለወጥ ነበር የገባነው፡፡ በእርግጥም በወቅቱ አጥልቀን ስለምንከራከር፣ ብዙዎች ከእስር ተርፈዋል፣ ከስደት ድነዋል፡፡
ከመንግስት ጋር ወደ አለመግባባት ደረጃ የደረሳችሁት እንዴት ነው?
መንግስት ትንሽ ቆይቶ፣ እነዚህማ የታሠሩት ሰዎች ደጋፊ ናቸው፡፡ መታሠር ይቁም፣ ፍትህ ይስፈን ይላሉ። ወንጀለኞች ናቸው ስልጣን ላይ የተቀመጡት፣ በሚል ወዲያው ፈረጀን፡፡
መንግስት በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ምን ያህል እጁን ያስገባል? ለዚህ በማሳያነት የሚጠቅሱት ተጨማሪ ምሳሌ አለ?
ምን እጁን ብቻ ጠቅላይ ሠውነቱን ነው በሃይማኖት ጉዳይ የሚያስገባው፡፡ በወቅቱ እኛ ሁለት አመት በአመራር ላይ ስንቆይ፣ መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ እጁን ማስገባት ብቻ ሳይሆን ሙሉ ለሙሉ ገብቶ እያቦካ እንደነበር ነው የተረዳነው፡፡ ስለ እምነት ጉዳይ ለሙስሊሙ አቅጣጫ የሚሰጠው መጅሊሱ፣ ሙሉ ለሙሉ ከመንግስት በሚመጣ አቅጣጫ ነበር የሚመራው፡፡ እኛንም ያጋጠመን ይህ ነው፡፡ በቀጥታ ትዕዛዝና መመሪያ ጭምር ይሰጡን ነበር፡፡ በህገ መንግስቱ ያለው ድንጋጌ የተረሣ ጉዳይ ነበር፡፡ ጣልቃ ገብነታቸው ምንም አይነት ወሰን አልነበረውም፡፡ አስተምህሮቶች ውስጥ ገብቶ፣ ለእናንተ አህባሽ ነው የሚያስፈልገው ማለቱ ግልፅ ማሣያ ነው፡፡
መንግስት በሁሉም ሃይማኖቶች እጁን አስረዝሞ እንደሚያስገባ፣ በኛ ላይ የደረሰው ማሣያ ነው፡፡
መንግስት የሃይማኖት ተቋማትን ለመቆጣጠር የፈለገው ለምን  ይመስልዎታል?
በእኛ እና በእነሡ (መንግስት) መሃል ያለው ትልቁ ፍትጊያ  የመብት ጉዳይ ነው፡፡ የህልውና ጉዳይ ነው። እነሡ ይሄ የፖለቲካ ጉዳይ ይመስላቸዋል፡፡ ስለዚህ አያምኑንም፡፡ ሙስሊሞች መንግስትን ገልብጠው፣ ስልጣን ይዘው፣ መንግስት የመሆን ህልም የላቸውም፡፡ የላቸውም ብቻ ሣይሆን ፈፅሞ የማይታሰብ የማይቻል ነገር ነው፡፡ ሃይማኖታችንም ሽብርን፣ ውጥረትን መፍጠር አይፈቅድም፡፡ የኛ ሃገር ሙስሊሞች እንኳን እንዲህ ሊያስቡ፣ ገና ወደ ሃገሪቱ ፖለቲካ ተሣትፎም ያልተጠጉ ናቸው፡፡ ከሃገሪቱ ፖለቲካዊ ተሳትፎ የተገፉ ናቸው፡፡ ጠየቁ ከተባለ ትልቁ የሚጠይቁት የመስጊድ ግንባታ ፍቃድ ነው፡፡
በውሃቢያ እና አህባሽ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?
እስልምና አንድ ነው፡፡ የእስልምና ሃይማኖት አንድ ቁርአን፣ አንድ ሃዲስ ያለው፣ መመሪያው አንድ የሆነ፣ አንድ ሃይማኖት ነው፡፡ ምናልባት በሚተገበርበት መንገድ ልዩነት ሊፈጠር ይችላል፡፡ ይሄ ውሃቢያ የሚባለው ነገር ግን በሃገራችንም ሆነ በአለም ላይ የለም፡፡ ውሃቢያ ነኝ የሚል ሙስሊምም የለም፡፡ እስልምና አንድ ነው፡፡ ውሃቢያ የሚለው የመጣው፣ ሰዎች እስልምናን እየረሱ፣ ወደ ባዕድ አምልኮ እየገቡ፣ ሃይማኖቱን ከባዕድ አምልኮ ጋር እየቀላቀሉ ሲጠቀሙ፣ ይሄ ነገር ከእስልምና ውጪ ነው ይቅር፣ በሚል አብዱሼክ አብዱልወሃብ የሚባል ምሁር ያስተምር ነበር፡፡ ወደ ሃይማኖቱ እንመለስ የሚል ምሁር ነበር፡፡ ይሄንን ነው ሃይማኖት ብለው የሚሉት፡፡  ይሄ ስህተት ነው፡፡ ውሃቢያ የሚባል የለም፡፡ አህባሽ ደግሞ ሃበሻ ከሚለው የመጣ ነው፡፡
አህባሽ የሚባለውስ ---?
ውሃቢያ አስቀድሜ እንዳብራራሁት ነው፤አህባሽ ደግሞ የቀላቀለ ነው፡፡ ለምሳሌ  ለመቃብር ቦታዎች የተለየ አምልኮ መስጠት፣ ለሰዎች ስእለት ማስገባት የመሣሠሉት በእስልምና ይከለከላል፡፡ በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነት ይሄ ነው፡፡ በእስልምና አስተምህሮ ግን ልዩነት የለም፡፡ እስልምና መሠረቱ ፈጣሪ አንድ ብቻ ነው የሚል ነው፤ ይህ ከሆነ ልዩነት የለውም ማለት ነው፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ  በሙስሊሙ መካከል ምን ያህል አንድነት አለ?
እንግዲህ በመንግስትም እንደ ወንጀል የተቆጠረው፣ ይህ “እስልምና አንድ ነው፤ አንድነት ያስፈልጋል” የሚለው አስተሳሰብ ነው፡፡ የሙስሊሙ አንድነት ጥያቄ የለውም፤ ግን ቅድም ባልኩት መሰረት የመንግስት ጣልቃ ገብነት፣ ይህን አንድነታችንን ሸርሽሮታል፡፡ ይህም ሆኖ ግን 80 በመቶ ህዝባችን አንድ ነው፡፡ አሁንም ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች አንድ ናቸው፡፡ አልተከፋፈሉም፡፡
እርስዎ ከስልጣን መነሣቴን የሠማሁት በሚዲያ ነው ብለዋል፡፡ በወቅቱ የተፈጠረው ነገር ምንድን ነው?
በ2005 ተመርጠን ሁለት አመት በብዙ ንትርክ ካሳለፍን በኋላ፣ በ2007 አመታዊ ጉባኤ እያዘጋጀን ባለበት ወቅት፣ መንግስት “እናንተ የማትታዘዙን ከሆነ ወይም የማታስተካክሉ ከሆነ ስልጣናችሁን ልቀቁ” ነው ያለን በቀጥታ፡፡ እኛ ደግሞ የሠራነው ጥፋት የለም፣ ለምንድን ነው የምንለቀው ስንል ቆየን፡፡ ደህንነቶች በየቀኑ እየመጡ ያስፈራሩኝ ነበር፡፡
ምን እያሉ ነበር የሚያስፈራሩት?
 በቃ ልቀቁ ነበር የሚሉን፤ መንግስት ካስቀመጠው አቅጣጫ ውጪ እየሄዳችሁ ነው፤ስለዚህ በአስቸኳይ ልቀቁ ነው የሚሉን፡፡ በህገ መንግስቱ፣ መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ አይገባም ብዬ ስከራከር፣”በቃ ይሄ የመንግስት አቅጣጫ ነው፤መንግስት አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ጣልቃ ይገባል” የሚል ምላሽ ነበር የሚሰጡን፡፡ በኋላ ያው በሬድዮ የሠማነው መፈንቅለ ስልጣን ነው የተደረገብን፡፡ እኛም ከስልጣን መነሳታችንን የሠማነው እንደ ማንኛውም ሰው በሬድዮ ነው፡፡
ምን ተብሎ ነው የተነገረው?
ያው በአመራሮቹ መካከል የተፈጠረን አለመግባባት ተከትሎ፣ ስልጣናቸውን በገዛ ፍቃዳቸው ለቀዋል የሚል ዜና ነው የተነገረን፡፡
በአመራሮች መካከል አለመግባባት ነበረ ማለት ነው?
ምን መሠለህ የኔ ምክትል የነበሩት ከኛ ጋር አይግባቡም ነበር፡፡ ለገዥው ፓርቲ ቅርበት አለኝ ስለሚሉ፣ እኔ ያልኩት ካልሆነ የሚል አቋም ነበራቸው፤ በኋላ እሳቸውን ከስልጣን አገድን፡፡ በኋላም ደህንነቶች “ወይ እሳቸውን ወደ ስልጣን ትመልሣለህ አሊያም አንተ ትነሳለህ” አሉኝ፡፡ እኔ ለሃይማኖቴ ተገዥ ነኝ፤ ፈፅሞ አልመልሳቸውም የሚል አቋም ያዝኩ፡፡ በኋላ የኛን አመራርና በእስር ላይ የሚገኙ የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትን ሁኔታ የሚከታተል፣ 22 አባላት ያሉት የእስልምና ምሁራን ያቋቋሙት ኮሚቴ ነበር፡፡ ለእነሱም ይሄን ጉዳይ አቅርበው፣ እኔን ከስልጣን እንድባረር ወይም ምክትሉ እንዲመለሱ እንዲደረግ ጠየቁ፡፡ በወቅቱ እኛ ሃይማኖታችንን አሣልፈን አንሠጥም በሚለው አቋም ፀናን፡፡ በዚህ መሃል መናገር የምፈልገው፤ በወቅቱ ከኢስላሚክ ባንክ የ7 መቶ ሚሊዮን ዶላር የልማት ፈንድ አግኝተን ነበር፡፡ ገንዘቡ ተዘዋዋሪ ፈንድ ነው፡፡ ለመንግስት ባለስልጣናት አሳወቅሁ፤ በሁኔታው ደስተኛ ነበሩ፡፡ በኋላም ለጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም በቀጥታ ስለተገኘው ፈንድና ማልማት ስለምንፈልገው ጉዳይ ነገርኳቸው። ደስ አላቸው፡፡ ለማንኛውም በጉዳዩ ላይ ፍቃድ ለመስጠት የሣምንት ጊዜ ስጠኝ አሉኝ፡፡ በሣምንቱ ቢሮአቸው ስሄድ፣ እባክህ ያልከው ነገር አልተቻለም አሉኝ፡፡ ከእርስዎ በላይ ማን ነው የሚወስነው ስላቸው፣”አይ ይሄ እዳ ውስጥ መግባት ነው፡፡” አሉኝ፡፡  ይሄ እኮ ተዘዋዋሪ ፈንድ ነው ብዬ ባስረዳቸውም፣”በቃ አልተቻለም ማለት አልተቻለም ነው” አሉኝ፡፡ ትንሽ ቆይቶ እንግዲህ ከስልጣናችን መነሳታችን ተነገረ ማለት ነው፡፡
በወቅቱ ታዲያ ለምን ለመገናኛ ብዙሃን እውነቱን አልተናገራችሁም?
የሚገርመው እኛ “ሣንድዊች” ነው የሆንነው፤ አጣብቂኝ ውስጥ ነው የገባነው፡፡ ህዝበ ሙስሊሙ “እነዚህ መንግስት ያመጣቸው ናቸው” ብሎ ርቆናል። በሌላ በኩል፤ መንግስት ደግሞ የታሠሩት ሰዎች አመለካከት አራማጆች ናቸው ይላል፡፡ በዚህ አጣብቂኝ መሃል ነው የገባነው፡፡ መንግስት እንደ ጠላት ነው የፈረጀን፡፡
ሚዲያዎች ሊቀርቡን አልፈለጉም፤ በወቅቱ እውነቱን ለመናገር ለተለያዩ ሚዲያዎች ሊቀርቡን አልፈለጉም፡፡ በወቅቱ እውነቱን ለመናገር፣ ለተለያዩ ሚዲያዎች “እረ ድምፃችንን ስሙ” ብለን ስንጮህ ማንም አልሠማንም ነበር፡፡ ጥሪያችንን አክብሮ መጥቶ፣ ጉዳያችንን የዘገበው፣ ብቸኛ ጋዜጣ “አዲስ አድማስ” ብቻ ነበር፡፡ በእውነት ለዚህ ተግባሩ ዛሬም ደግሜ አመሰግናለሁ፡፡ ጋዜጣው ያለብንን የመንግስት ጫና እያወቀ፣ ስለ ጉዳያችን የዘገበ ብቸኛ ሚዲያ ነው፡፡
እንግዲህ የሃይማኖት ተቋማት፣ ከመንግስት ጣልቃ ገብነት ነጻ መሆን እንዳለባቸው ህገ መንግስቱ ይደነግጋል፡፡ ከዚህ አንጻር ከአዲሱ የዶ/ር ዐቢይ አህመድ አስተዳደር ምን ይጠብቃሉ?
በነገራችን ላይ ዶ/ር አብይ፤ የሃገር ተስፋ ናቸው ብለን እንገምታለን፡፡ አሁንም ጭላንጭሎች እየታዩ ነው፡፡ ይህ ጭላንጭል ወደ ብርሃን እንዲቀየር፣ የሁላችንም ድጋፍና ተሣትፎ ያስፈልጋል፡፡ እሳቸው አንባቢ ናቸው፤ በግማሽ ጎናቸው ሙስሊም ናቸው፡፡ ስለዚህ በህዝብ ሙስሊሙ ላይ እየደረሠ ያለውን ነገር ሁሉ ያውቃሉ የሚል ግምት አለኝ፡፡ የህዝብ ሙስሊሙ መብት መከበር አለበት፡፡ መንግስት በህዝብ ሙስሊሙ ላይ ያለው ጫና፣ በእሳቸው ዘመን መነሣት አለበት። ይህ ይሆናል ብዬም እጠብቃለሁ፡፡ እሳቸው ፈጣሪ የመረጠልን ሰው ናቸው፡፡ የሚናገሩት ስለ ፍትህ፣ እኩልነት ነው፡፡ ስለ እነዚህ ጉዳዮች የሚናገር ሰው፤ ልቡ የሞቀ፣ አዕምሮው የሠከነ ሰው ነው፡፡
ለዚህ የሃይማኖት ችግር ዘላቂ መፍትሄ ይሠጡናል የሚል ሙሉ እምነት አለኝ፡፡ ግን ምላሻቸውን ተረጋግተን ነው የምንጠብቀው፤ አንቸኩልም፡፡

Read 4695 times