Saturday, 23 June 2018 11:45

መንግስት የዘጋቸውን 264 ድረ-ገጾች መክፈቱ ተነገረ

Written by 
Rate this item
(9 votes)

ኦኤምኤን ቴሌቪዥን ዛሬ ከአዲስ አበባ ስርጭቱን ይጀምራል

    መንግስት አገልግሎት እንዳይሰጡ ዘግቷቸው የነበሩ 264 የተለያዩ ድረ-ገጾችና የጦማርያን ገጾችን በመክፈት አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረጉን፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ሃላፊው አቶ ፍጹም አረጋ ትናንት በትዊተር ገጻቸው አስታውቀዋል፡፡
በአሜሪካ ፍቃዱን አግኝቶ የሚሰራጨው የኦሮሞ ሚዲያ ኔትዎርክ (OMN) ቴሌቪዥን፣ በዛሬው ዕለት ከአዲስ አበባ ሥርጭቱን እንደሚጀምር ታውቋል፡፡
ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ማረጋገጥ፣ ለሌሎች መብቶች መከበር መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን የገለጹት አቶ ፍጹም፤ በመስኩ የማሻሻያ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ የሚገኘው የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስት፣ ተዘግተው የነበሩ ድረ-ገጾችን በመክፈት፣ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረጉን አመልክተዋል፡፡
ነጻ የመረጃ ፍሰት እንዲኖር ማድረግ፣ በአገሩ ጉዳይ ተሳታፊና ሃላፊነት የሚሰማው ዜጋ ለመፍጠር ቁልፍ ሚና ይጫወታል ያሉት አቶ ፍጹም፤ መንግስት የተዘጉ ድረገጾችን ከመክፈት በተጨማሪ የኢሳትና የኦኤምኤን የቴሌቪዥን ስርጭቶች በነጻነት እንዲታዩ መፍቀዱንም ገልጸዋል፡፡    
አሶሼትድ ፕሬስ በበኩሉ፤ መንግስት ዘግቷቸው የነበሩት ብዙዎቹ ድረ-ገጾች በአሜሪካና በሌሎች ውጭ አገራት የተከፈቱ እንደሆኑ በመጠቆም፣ በአገሪቱ ታስረው የነበሩ ከሞላ ጎደል ሁሉም ጋዜጠኞችና ጦማሪያን በአዲሱ የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ መንግስት ከእስር መለቀቃቸውንና መንግስትን በመተቸት በሚታወቁ አክቲቪስቶች ላይ ተመስርተው የነበሩ ክሶች መቋረጣቸውን ዘግቧል፡፡

Read 10303 times