Saturday, 23 June 2018 11:44

የወላይታ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ግንባር የሃዋሳውን ግጭት አወገዘ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

 - ጠ/ሚኒስትሩ ህዝብ የሚያፈናቅሉ ከስልጣናቸው እንዲወርዱ አሳሰቡ
   - ሲዳማ፣ ወላይታ፣ ጉራጌ ዞን ራሣቸውን ችለው ክልል እንዲሆኑ ጥያቄ ቀርቧል


     የወላይታ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ግንባርን ሠሞኑን በአዋሣ በወላይታና በሲዳማ ብሄር ተወላጆች መካከል የተፈጠረውን ግጭት በፅኑ አውግዞ፣ አጥፊዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠይቋል፡፡
“ትርጉም አልባ ድርጊት” በማለት ግጭቱን ያወገዘው ፓርቲው፤ “ክስተቱ በወላይታና በሲዳማ ህዝብ መካከል ያለውን ወንድማማችነት የማይወክል ነው፤ ለወደፊቱ የሁለቱ ህዝቦች ወንድማማችነት እየተጠናከረ እንጂ እየላላ አይሄድም” ብሏል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ፣ ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው በሃዋሳ እና በሶዶ ህዝቡን በማነጋገር ላደረጉት የማረጋጋት ስራ ምስጋናውን የገለፀው ፓርቲው፤ በሃገሪቱ የሚታዩ የብሄር ግጭቶች በመላው ህዝብ መወገዝ አለበት ብሏል፡፡
የወላይታ ህዝብ የሚተዳደርበት የግብርና ኢኮኖሚ አካባቢው ካለበት የመሬት ጥበትና የህዝብ ብዛት አንፃር እየተጣጣመ አለመምጣቱ፣ የአካባቢው ተወላጆች ስራ ፍለጋ ወደ ሌላ ቦታ እንዲንቀሣቀሱ ማስገደዱን የጠቆመው ፓርቲው፤ በቀጣይ በአካባቢው ያለው ፖሊሲ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ተኮር መሸጋገር እንደሚገባው ገልጿል፡፡
በወላይታ ለአንድ አርሶ አደር የሚደርሠው መሬት በአማካይ ከ0.13 ሄክታር በታች መሆኑን የጠቀሠው መግለጫው፤ በትንሹ ሶስት ልጆች ያሉት አባወራ፣ ቤተሠቡን መቀለብ እንኳ አይችልም ብሏል፡፡
ለዚህ መፍትሄው የወላይታ ህዝብ ራስን ችሎ በክልል እንዲተዳደር ማድረግና በአካባቢው ኢንዱስትሪ መር ፖሊሲን መተግበር ነው ብሏል፡፡
ፓርቲው ግጭቱን ባወገዘበት መግለጫው፤ ህይወት ያጠፉ በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡ፣ የተፈናቀሉ ወደ ቦታቸው እንዲመለሱና ሃብት ለወደመባቸው ተገቢ ካሣ እንዲከፈላቸው ጠይቋል፡፡
ከዚሁ ጉዳዩ ጋር በተያያዘ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ፤ ከሠኞ እስከ ረቡዕ በሃዋሣ፣ በወላይታ ሶዶና በወልቂጤ ከተማ ባጋጠሙ ግጭቶች ላይ ከህዝብ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸው ወቅት ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል በሶስቱም ዞኖች “ራሳችንን ችለን ክልል እንሁን” የሚለው ይገኝበታል፡፡ በሲዳማ፣ በወላይታና በጉራጌ ማህበረሠቦች ራሣችን ችለን ክልል እንሁን የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄው ህጋዊ መሆኑን ጠቅሠው በቅርቡ አጠቃላይ የሃገሪቱ የወሠንና የክልሎችን ጉዳይ ፈትሾ፣ መፍትሄ የሚያበጀ ኮሚሽን ይቋቋማል ብለዋል።
በየወረዳውና ዞኖቹ ግጭቶቹ ሲከሠቱና የሠው ህይወት ሲጠፋ በቸልታ የተመለከቱ አመራሮችም በገዛ ፍቃዳቸው ስልጣን መልቀቅ እንዳለባቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሣስበዋል፡፡
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የአማራ ክልል ተወላጆችን ያፈናቀሉ ባለስልጣናትም ለህግ እንደሚቀርቡ የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የክልሉ ፕሬዚዳንት እኒህን አመራሮች ከስልጣን ያወርዳሉ ብለው እንደሚያምኑ አስታውቀዋል፡፡
ይህን የጠቅላይ ሚኒስትሩን የስልጣን ልቀቁ ጥያቄ ተከትሎ የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ እና ምክትላቸው ጨምሮ አምስት ከፍተኛ ባለስልጣናት በገዛ ፍቃዳቸው ስልጣን ለቀዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ስልጣን መልቀቃቸው ተገቢ እና አርአያነት ያለው ነው ሌሎችም ይለቃሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል፡፡
ሃዋሳ ላይ በተፈጠረው ግጭት 10 ሰዎች መሞታቸው እና በሺዎች መፈናቀላቸው እንዲሁም በወልቂጤ 5 ሰዎች መሞታቸው መገለፁ ይታወቃል፡፡

Read 8199 times