Saturday, 16 June 2018 12:42

‹‹…የሐሞት ጠጠር እና ሴቶች…››

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(3 votes)

 የሐሞት ጠጠር ከክርስቶስ ልደት በፈት በ1000/አመተ አለም ጀምሮ በተለይም በግብጽ ይታወቃል፡፡
ሴቶች በመውለድ እድሜ ላይ እያሉ ከወንዶች በእጥፍ ያህል የሐሞት ጠጠር የሚይዛቸው ሲሆን በተለይም እድሜያቸው በ50/ክልል ሲሆን መጠኑ ይጨምራል፡፡
የሐሞት ጠጠር ከወጣቶች ይልቅ በእድሜ በገፉ ሰዎች ከ4-10/ያህል ይበልጥ ይከሰታል፡፡
የሐሞት ጠጠር ወይንም ድንጋይ ማለት እንደ Simonsen, M. H. (2013) ሐሞት በሐሞት ከረጢት ውስጥ ሲጠራቀምና እዚያው እየደረቀ ሲሔድ የሚፈጠረው ድንጋይ መሰል ጠጣር ነገር ነው፡፡  ያ በሐሞት ከረጢት ውስጥ የሚገኘው ሐሞት የተባለው መራራ ፈሳሽ ሰውነት ስብ የሆነ ነገርን እንዲቃጠል ወይንም ከሰውነት እንዲዋሐድ ለማድረግ የሚያግዝ ነው፡፡ ይህ ሐሞት የተባለው መራራ ፈሳሽ የሚፈጠረው በጉበት ሲሆን ለአገልግሎት እስኪፈለግ ድረስ የሚቀመጠው ከጉበት ጋር በተያያዘው በሐሞት ከረጢት ውስጥ ይሆናል፡፡ ሰውነት እንዲፈጭ የሚፈልገው ስብ ነገር ሲኖር ደግሞ የሓሞት ከረጢትዋ እራስዋ እየተኮማተረችና እየተዘረጋች ፈሳሹን እየገፋች ወደ ትንሽዋ አንጀት በመላክ አገልግሎቱን ትሰጣለች፡፡ ይህ መልኩ ወደ አረንጉዋዴ የሚሔደው ሐሞት የተሰኘው መራራ ፈሳሽ በውስጡ ውሀ፤ cholesterol፤ ስብ፤ የሐሞት ጨው እና ከቀይ የደም ሴል የሚሰራ bilirubin የተሰኘ ንጥረ ነገርን ይይዛል፡፡ ሐሞት ከመጠን ያለፈ ኮለስትሮል በውስጡ ከያዘ ፈሳሹ ወደ ድንጋይነት እንዲለወጥ ምክንያት ይሆናል፡፡
ጥናት ከተደረገባቸው የአለም ሐገራት መረጃ ለምሳሌ ያህል ለንባብ ያልነው የአሜሪካንን ነው፡፡ በአሜሪካ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚጠቁመው እድ ሜያቸው ከ20-74 አመት የሚደርሱ ከ20/ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ማለትም 6.3/ ሚሊዮን ወንዶችና 14.2/ሚሊዮን ሴቶች በየአመቱ የሐሞት ጠጠር ታካሚዎች ናቸው፡፡ ከታካ ሚዎች መካከል ወደ 20% የሚሆኑት እድሜያቸው ከ40/አመት በላይ የሚሆኑ ናቸው፡፡ በንጽጽር ሲታይ ግን በአፍሪካ ያለው የሐሞት ጠጠር ታካሚዎች ቁጥር አነስ ያለ መሆኑን መረጃው ይጠቁማል፡፡   
ሴቶች የወር አበባ መቋረጥ ወይንም ሜኖፖዝ ሲደርሱ የሚከሰተውን ኢስትሮጂን የተባለ የሆርሞን እጥረት ለመተካት ሲባል የሚወሰደው መድሀኒት መጠኑ በልክ ወይንም አነስተኛ ካልሆነ በስተቀር በሐሞት ከረጢት ውስጥ ጠጠር እንዲፈጠር ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል፡፡ ሴቶች በእርግዝና ወቅት ከልክ በላይ ኢስትሮጂን ካመረቱ ወይንም እርግዝናን ለመከላከል የሚወሰዱ ኪኒኖች የሐሞት ከረጢት ጠጠርን ለመፍጠር አይነተኞቹ መንገዶች ናቸው፡፡ የስኩዋር ሕመም ያለባቸው ሴቶች ወይንም ኮለስትሮልን ለመቆጣጠር የሚወሰዱ ኪኒኖችም የሐሞት ከረጢት ጠጠርን ለመፍጠር በምክንያትነት ይጠቀሳሉ፡፡ የሐሞት ከረጢት ጠጠር ሕመም ስሜቱ ሳይኖር ለረጅም አመታት ሊቆይ ይችላል፡፡ ነገር ግን አንዴ ከተፈጠረ እየዋለ እያደረ እያደገ ስለሚሄድ ሕመሙም መሰማት ይጀምራል፡፡
የህመሙ አይነት፡-    
ባልታሰበ ወቅት እና እየጨመረ የሚመጣ ለተወሰነ ሰአት የሚቆይ ሕመም ፤
በላይኛው የሆድ እቃ በመካከለኛው ማለትም ከሁለት ጡት መካከል ከደረት አጥንት በስተግርጌ በስተቀኝ በኩል የሚሰማ ለተወሰነ ጊዜ የማያቋርጥ ሕመም፤
መቆም መቀመጥ የማያስችል የሆድ ሕመም፤
ከጀርባ በሁለቱ ትከሻዎች መካከል እንዲሁም ወደ አንገትና ደረት ወይም ጀርባ የሚሰማ ሕመም ፤
በቀኝ ትከሻ ከታች በኩል ሕመም፤
በአካባቢው የእብጠት ምልክት፤
ቆዳን እና አይንን ብጫ ማድረግ፤
ከፍተኛ ትኩሳት፤
ድምጽ እስኪሰማ ድረስ በአፍ በኩል ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ግሳት መኖር፤
የምግብ ፍላጎት መቀነስ ፤
ስብ ያለው ምግብ ለመመገብ ፍላጎት ማጣት፤
በሆድ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ አየር(ጋዝ) መኖር፤
ከላይ የተጠቀሱትና የመሳሰሉት ሕመሞች የሐሞት ጠጠር ለመኖሩ ምልክቶች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡በእርግጥ እነዚህ የህመም ምልክቶች በሌሎች ሕመሞች ምክንያት አይኖሩም ማለት አይደለም፡፡
ለሐሞት ጠጠር መከሰት ምክንያቶች ከሚባሉት ውስጥ የሰውነት ክብደት አንዱ ነው፡፡ ሴቶች ሰውነታቸው እጅግ በገዘፈ ቁጥር የሐሞት ጠጠር ችግርም ሊከሰት ይችላል፡፡ አለአግባብ የተከሰተን ክብደት ለመቀነስ ጥረት ማድረግ ምንም እንኩዋን ሕመሙን ሙሉ በሙሉ ያስወግደዋል ባይባልም ነገር ግን ከጠጠሩ መፈጠር ጋር ተያይዘው የሚመጡ የጤና ችግሮችን ለመቀነስ ይረዳል፡፡ ይሁን እንጂ ክብደትን ለመቀነስ ጥረት ሲደረግም ቀስ በቀስ ቢሆን ይመከራል፡፡
ሌላው ምክንያት ከቤተሰብ መወረስ መቻሉ ነው፡፡ የሐሞት ጠጠር ሕመም በቅርብ ቤተሰ ቦች የተለመደ ሕመም ከሆነ በዘር ሊተላለፍ ይችላል የሚሉ የባለሙያዎች እማኝነት አለ፡፡ ስለዚህም ይህ ከታወቀ ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠቅማል፡፡ ጥንቃቄ ከሚደረግ ባቸው መንገዶች አንዱ አመጋገብን ማስተካከል ነው፡፡ ለማንኛውም ሰው በተለይም ሴቶች ከወር አበባ መቋረጥ ጋር ተያይዞም ይሁን በማንኛውም ጊዜ የሐሞት ጠጠር ችግር ቢያጋ ጥማቸው ሕመሙ እንዳይባባስባቸው የሚከተሉትን ምግቦች ማስወገድ ይጠቅማቸዋል፡፡  
የማነቃቃት ተግባር ያላቸው ለምሳሌም…እንደ ቡናና ሻይ የመሳሰሉትን ምግቦች፤
ቸኮሌት ፤እንቁላል፤የወተት ተዋጽኦ (ቅቤ ፤አይስክሪም፤ ቺዝ)
ቅባት የበዛበትና በጣም የተቀቀለ ምግብ፤
የታሸጉ ምግቦች፤
ስብ የበዛበት ስጋ ፤
በቆሎ፤ባቄላ፤ለውዝ፤
ከላይ የተጠቀሱት እና የመሳሰሉት ሕመሙን እንደሚያባብሱት ተገልጾአል፡፡ከዚህ ይልቅ ሕመሙ የገጠማቸውም ይሁኑ ሌሎች ሴቶች የሚከተሉትን ምግቦች ቢያዘወትሩ ጤናማ የመሆን እድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡
አትክልትና ፍራፍሬ፤
እንደ (ስንዴ ፤ቡናማ ሩዝ ፤ገብስ፤ አጃ) ከመሳሰሉት እህሎች የተዘጋጁ ምግቦች፤
ስብ ያልበዛባቸው የወተት ውጤቶች፤
ስብ የሌለው ስጋ፤ ዶሮ ፤አሳ …ወዘተ…በአጠቃላይም ስብ ያልበዛበት እና ኮለስትሮል የሌለው መጠነኛ ካሎሪ እና ከፍተኛ ፋይበር ያለው ምግብ መመገብ ለማንኛውም ሰው ይጠቅማል፡፡
ሴቶች የሐሞት ጠጠር ሳይኖርባቸው የሐሞት ከረጢታቸው ስራውን በትክክል እንዲሰራ ለማድረግ አስቀድሞ አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰድ ይችላሉ፡፡ አመጋገብን በትንሽ በትን ሹ በቀን ከ5-6 ጊዜ ማድረግ ጥሩ ነው፡፡ በቀን 8/ብርጭቆ ውሀ መጠጣትም ለሁሉም ጤን ነት ይበጃል፡፡ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በተለያዩ መንገዶች ማድረግም ይመከ ራል፡፡ ሴቶች ከሐኪም ምክር በመቀጠል የአኑዋኑዋር ስልታቸውን በማስተካከል በራሳቸውም የተጠቀሱትን ጥንቃቄዎች ካደረጉ ወደፊት የሐሞት ጠጠር እንዳይይዛቸው ሁኔታውን አስቀድመው ማስተካከል ይችላሉ፡፡
ምንጭ ፡- Nigerian journal of surgery & Medicine Net.com


Read 6364 times