Print this page
Sunday, 10 June 2018 00:00

“…ልጅ ሲያኮርፍ ምሣው ራት ይሆነዋል…?”

Written by 
Rate this item
(7 votes)

    ከዕታት አንድ ቀን፤ አንድ አንቱ የተባሉ፣ የደሩና የኮሩ የጥንት አርበኛ ፊታውራሪ፣ በአንድ የገጠር ከተማ ይኖሩ ነበር፡፡ እኒህ ሰው ጠላትን ባባረሩ ማግሥት የጀግንነት ተግባራቸው አልጠቅም ብሏቸው፤ ወደ ጫካ ወጣ ይሉና አደን ላይ ይሰማራሉ፡፡ ከርከሮ ካገኙ ከርከሮ፣ አውራሪስ ካገኙ አውራሪስ…ብቻ ያገኙትን የዱር እንስሳ አድነው ገድለው፣ ቢያጡ ቢያጡ ጅግራም ቢሆን ገድለው ወደ ቤት ይዘው ይመጣሉ፡፡ ይኼን ሁሉ ግዳይ ጥለው ቤተሰብ እንዲሰበሰብ ይደረግና በጋራ ገበታ ተቀርቦ ይበላል፡፡
ታዲያ እግረ መንገዳቸውን የእያንዳንዱን የሚታደን የዱር እንስሳ ባህሪ ያብራራሉ፡፡
“ነብር ስታድኑ፤ ይሄን ይሄን ጥንቃቄ አድርጉ… ከርከሮ ከሆነ አቁስሎ መተው አደገኛ ስለሆነ የገባበት ገብታችሁ መጨረስ አለባችሁ- ግሥላ ከከርከሮ ይብሳል… አልመህ መተኸውም አደገኛ ነው…” እያሉ በዝርዝር የታዳኞቹን አውሬዎች ባህሪና ጠባይ በደንብ ይገልፃሉ፡፡
ቤተሰቡም ጥያቄ ካለው እየተብራራለት ቁልጭ ያለ መግለጫ ያገኛል፡፡ ይሄ ሁሉ ሲሆን ገበታም የማይቀርብ፣ ማብራሪያም የማያዳምጥ፣ ሞገደኛና አባያ ልጅ አለ፡፡
ፊታውራሪ፤
“ያ፤ ካብ- አይገባ-ድንጋይ፣ ልጄ ዛሬ የት ሄዷል?” ይሉና ይጠይቃሉ፡፡
ቤተሠቡም፤
“በተደጋጋሚ ወደ ማዕዱ ቅረብ ብንለው አሻፈረኝ አለንኮ! በልመናም ሞከርነው፣ በጄ አላለንም። አሁንማ ጭራሽ ሁላችንንም አኩርፎ ቁጭ አለ!”
ፊት አውራሪም፤
“ተውት…ልጅ ሲያኮርፍ ምሳው ራቱ ይሆናል!” አሉ፡፡
ዕውነትም እንዳሉትም አልቀረ፣ ማታ ራበኝ አለና ቀን የተቀመጠውን በላ!
* * *
ህብረተሰብን በለውጥ-ወዳድ እና በለውጥ-ጠል ከፍሎ ማየት የሚቻል መስሎ አይታይም ነበር። የዚህ መሠረታዊ ምክኑ በእርምት-እንቅስቃሴ (Rectification)፣ እደሳ (Reform) እና ሥር ነቀል ለውጥ (Radical Change) መካከል፤ በፅንሰ-ሀሳብ ደረጃም ሆነ በአተገባበር መልኩ፣ የተወሰነ መቀራረብና መለያየት በመኖሩ ነው፡፡ በሀገራችን ቁርጥ ያለ፣ እንደ አብዮት ያለ ለውጥ እስካሁን የተለመደ ቅላፄና ዜማ ያለው ሆኖ በማየታችን፤ ከፅንፍ ፅንፍ ጥግ የያዘ መልክ (Polarized feature) በመሆኑ የምናወጣቸው ቅፅሎች፤ የምንሰነዝራቸው አቃቂሮች፣ የምንቀልማቸው ውዳሴዎች ጥርት ያሉ ቃላትን የተሸከሙ ነበሩ፡፡ ግልፅ ማብራሪያ ይሰጥበት ነበር፡፡ አድሃሪ፣ ተራማጅ፣ አስመሳይ፣ አድር ባይ፣ መሀል-ሠፋሪ፣ ወግ-አጥባቂ፣ ውዥንብር ፈጣሪ፣ ወዘተ በሚል ቅጥ-ባላቸው ቃላት እንገለገል ነበር፡፡ ዞሮ ዞሮ ቀዳማይ እና ድሃራይ የተሰኘው የኮርቻ ፊትና ኋላ በአብዮት ውስጥ፤ ወደ ፊት የመቅደምና ወደ ኋላ የመቅረት ባህሪ መገለጫ ሆነውን ነበር፡፡ ዛሬ የተያያዝነው ለውጥ ባህሪ ግን ፅንፈኝነት የሚያስተናግድ አይመስልም! እንደ ትራንስፎሜሽን ያለው ፅንሰ-ሀሳብ የዋዛ ክስተት አይደለም፡፡ ውጣ ውረዱ ብዙ ነው፡፡ ሂደቱ ረዥምና ጠመዝማዛ ነው! ጀሌነትና መንገኝነት ፋሺን (ዘዬ) የነበረበት ዘመን፤ ዛሬ ቀለሙ የፈዘዘ ነው! አፌ- ጮሌነት፣ ጤፍ የሚቆላ ምላስ ያለው አራዳ ጊዜ፣ ሁሉን ባፌ አመራዋለሁ ተብሎ የሚኩራሩበት ወቅት እያከተመ ይመስላል፡፡
ዛሬ በዐይናችን በብረቱ የምንመሰክረው፣ የምናውቀው ነባር ሥርዓት ቀስ በቀስ እየተናደ፣ መድረሻው በቁርጥ ወዳልታወቀ ግብ እየተጓዝን እንደሆነ ነው! እዚህ ላይ አንዳች ጥብቅ ጉዳይ መንፈሳችንን ሰቅዞ ይይዘናል፡፡ እስካሁን በፕሮግራም፣ በፖለቲካ ተጋግሮ፤ እንደ ንብርብር አለት ሁሉ በቀላጤ፣ በመመሪያ፣ በፈጣን ማስታወሻ ተደርቶ፣ ሥርዓቱን ለመመርመር እንኳ “በበላይ አካል”፣ “በሚመለከተው አካል፣” “በመዋቅሩ አቅጣጫ መሠረት”፣ “በግምገማ እንደ ተቀመጠው” ወዘተ በሚሉ ጠንካራ የቱሻ ገመዶች የተተበተበ የቢሮክራሲ ቀይ-ጥብጣብ (bureaucratic red-tape) የበዛበት ቅጥ-አምባሩ የጠፋ “የእኔ ብቻ አውቅልሃለሁ” ሥርዓት፤ አንኳር በአንኳር እየተናደ መሆኑን እያስተዋልን ነው! ይህ አንዱ የወቅቱ ገፅታ ሲሆን፣ ሌላው ገፅታው የሚሆነው የመልሶ መገንባቱ ሂደት ነው! ድሮ በነበረው ሥርዓተ-ፈርሳታ ወቅት፤ “ማፍረስ ቀላል ባይሆንም፤ መገንባት የበለጠ ከባድ ነው” የሚል መፈክር እንደነበር ልብ እንላለን፡፡
በዓለም ላይ የማፍረስ-መገንባትን ሂደት ያልቀመሰ ሥልጣኔ የለም! ከታዋቂው የአሜሪካን የርስ በርስ ውጊያ ጀምሮ፣ “ከእንግዲህ አንራብም!” ብለው እስከተነሱት አውሮፓውያን ድረስ፤ ፈርሰው ራሳቸውን የገነቡበትን ታሪክ አንብበናል፡፡ በተራችን ራሳችንን በመንፈም በአካልም የምንገነባበት ወቅት መከሰቱ የተስፋ ምሥራች ነው! በኢትዮጵያ አያሌ የለውጥ ነፋስ ያመጣቸውን አጋጣሚዎች በንዝህላልነት፣ በእልህ፣ እኔ የሌለሁበት አይሳካም የማለት ስሜት እና የነገን ራዕይ በብስለት ካለማጤን ዕድሉን አጥተናል፡፡ ከእንግዲህ ዐይናችንን እንክፈት አጋጣሚዎችን መዝለል የፀፀት እናት ነው!
(missed opportunities are mother of regretion) ይባላል፡፡ በተደጋጋሚ ፀፀት ውስጥ መውደቅ የለብንም! የመጣውን የለውጥ መንፈስ ላለመጋራት ማፈንገጥ፣ እምቢተኝነትን መቀፍቀፍና ማኩረፍ ነገ ያስከፍለናል፡፡ “ልጅ ሲያኮርፍ ምሣው ራት ይሆነዋል” የሚለው የአበው ብሂል፣ ይኸንኑ የሚመክረን ነው! ልብ ያለው ልብ ይበል!!

Read 4593 times
Administrator

Latest from Administrator