በተያያዘ ዜና ቶም ክሩዝ የሚተውንበት የ”ሚሽን ኢምፖሲብል” 5ኛ ክፍል ሊሰራ እንደሚችል ታውቋል፡፡ አምና የዱባይን ትልቁን ፎቅ ቡርጃ ካሊፋን በመንጠላለጠል አስገራሚ ትወና በማሳየቱ የተደነቀው ቶም ክሩዝ የ”ሚሽን ኢምፖሲብል” 4ኛ ክፍል የሆነውና “ዘ ጎስት ፕሮቶኮል” በሚል ንዑስ ርእስ በቀረበው በዚህ ፊልሙ በመላው ዓለም የተሰበሰበው ገቢ 694 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ በሌላ በኩል በብሮድዌይ ከሦስት ሳምንት በፊት መታየት በጀመረው “ሮክ ኦፍ ኤጅስ” በተባለ ሙዚቃዊ ቲያትር ላይ የሚተውነው ቶም ክሩዝ፤ በአተዋወን ብቃቱ አድናቆትን እንዳተረፈ “ዘ ሃፊንገተን ፖስት” ዘግቧል፡፡ በሙዚቃዊ ቲያትሩ ላይ ቶም ክሩዝ የሮክ ሙዚቀኛ ሆኖ የሚጫወት ሲሆን አሌክ ባልድዊንና ራስል ብራንድ አብረውት እንደሚተውኑ ታውቋል፡፡ ቶም ክሩዝ ከ30 በላይ ፊልሞች ላይ የሰራ ድንቅ የሆሊውድ ኮከብ ነው፡፡