Sunday, 10 June 2018 00:00

አዲሱ የኢኮኖሚ ሪፎርም - ተስፋና ስጋቶች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(11 votes)


• የህዝብን ሃብት መሸጥ ከተጀመረ፣ ወደ ድህነትና ኪሳራ እየሄድን ነው
• የእነዚህ ድርጅቶች አክሲዮን መሸጡ ብዙ ገንዘብ ያስገኛል
• ከቻይና ተበድረን ነው ቴሌኮም እያስፋፋን ያለነው


   ባለፈው ማክሰኞ ዶ/ር አብይ አህመድ በሊቀመንበርነት የሚመሩት የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ያካሄደ ሲሆን በስብሰባው ማብቂያ ባወጣው መግለጫ፤ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁሞ እንደ መብራት ሃይል፣ ቴሌ፣ አየር መንገድ፣ የባቡር ፕሮጀክቶች የሃይል ማመንጫዎች፣ የንግድ መርከብ የመሳሰሉት መንግስት ከፍተኛውን የባለቤትነት ድርሻ ይዞ፣ ለሃገር ውስጥና ለውጭ ባለሃብቶች በከፊል ለመሸጥ መወሰኑን አስታውቋል፡፡ ባለፉት 20 ዓመታት 200 ገደማ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ለግል ዘርፉ ተሸጠው መንግስት ብዙ ቢሊዮን ዶላር ማግኘቱን የጠቆሙ አንድ የኢኮኖሚ ባለሙያ፤ የሰሞኑ የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔ፣ አግባብ ያለውና ወቅታዊ ነው ብለዋል፡፡ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በበኩላቸው፤ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማነቃቃትና የሥራ ዕድል ለመፍጠር የኢኮኖሚ ሪፎርም መደረጉ ትልቅ ብሥራት መሆኑን ጠቁመው፤ የአክሲዮን ሽያጭ ሲካሄድ በብልሃትና በጥበብ ካልተመራ፣ በብዙ የአፍሪካ አገራት እንደታየው፣ ሌላ የሌብነት ማስፋፊያ ሊሆን እንደሚችል አሳስበዋል፡፡
ለብዙዎች ድንገተኛ የሆነው የኢኮኖሚ ሪፎርሙ አሁን መደረጉ ምን ያህል ተገቢ ነው? በኢኮኖሚው ላይ የሚያመጣው ተጽዕኖ ምንድን ነው? የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ተስፋና ስጋቶችስ ምንድን ናቸው? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ታዋቂ የኢኮኖሚ ባለሙያዎችን አነጋግሮ፣ አስተያየታቸው እንደሚከተለው አጠናቅሯል፡፡


               “ ትክክል ቢሆንም አፈፃፀሙ ላይ ጥንቃቄ ያስፈልጋል”
                   ዶ/ር ሰይድ ኑሩ (የኢኮኖሚ ምሁር)


     እንደሚታወቀው የጀመርናቸውን ትልልቅ ፕሮጀክቶች ለመጨረስ የውጭ ምንዛሬ እጥረት አለብን። በሃገር ውስጥም ታክስ ይጨመር ቢባል፣ ታክሱ በብር እንጂ በውጭ ምንዛሬ ስለማይከፈል ችግሩን አይፈታውም፡፡ እነዚህን ፕሮጀክቶች ደግሞ ያለ ውጭ ምንዛሬ ማስቀጠል አይቻልም፡፡ የእነዚህ ፕሮጀክቶች ማለቅ አለመቻል መውደቅ ነው እንደሚባለው ነው፡፡ ለትራንስፎርሜሽን ብለን የጀመርናቸው ፕሮጀክቶች ካልተሳኩ ትራንስፎርሜሽን የለም ማለት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ቁልፉ ችግር የውጭ ምንዛሬ እጥረት ነው፡፡ የተጀመሩትን ፕሮጀክቶች ማስጨረሻ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ደግሞ ተቋማቱን ለሃገር ውስጥና ለውጭ ባለሀብቶች መሸጡ ጠቃሚ ነው፡፡
ከመጀመሪያውኑ አቅሙ ሳይኖረን እነዚህን ፕሮጀክቶች በራስ አቅም ብለን መጀመራችን ስህተት ነበር፡፡ አሁን የተወሰነው ጥሩ ነው፡፡ በሌላ በኩል ትልልቆቹን መሸጥ ለምን አስፈለገ የሚለው ነው። አሁንም የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለማስታገስ ይመስለኛል፡፡ ሌላው ሃገሪቱ እዳ ተጭኗታል የሚለውን ገፅታም ለመቀየር የታሰበ ይመስላል፡፡ ይህን ማድረጓ በአበዳሪዎችም በለጋሾችም እንደ መልካም እርምጃ ስለሚቆጠር፣ ገፅታ ላይ የተወሰነ ነገር ይፈጥራል፤ ግን በዋናነት የውጭ ምንዛሬ ማግኘት መቻሉ ነው፡፡ ለሃገር ውስጥ ብቻ የሚሸጥ ቢሆን ኖሮ፣ የውጭ ምንዛሬ ማምጣት አይችልም ነበር፡፡ ለውጪ ባለሀብቶችም ክፍት መደረጉ ከዚህ አንፃር ጠቃሚ ነው፡፡ ትልቁ እጥረት ብር ሳይሆን የውጭ ምንዛሬ ነው፤ ስለዚህ ከዚህ የተቋማት ድርሻ ሽያጭ የውጭ ምንዛሬ መገኘት አለበት፡፡
እርግጥ ነው በዚህ ሂደት የምናገኘው የውጭ ምንዛሬ ዘላቂ አይሆንም፡፡ አንዴ ከሸጥናቸው ሁል ጊዜ የውጭ ምንዛሬ እንደማያስገኙ ይታወቃል፡፡ ለምሳሌ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድን መሸጥ ምን እንደሚጨምር ግልፅ አይደለም፡፡ አሁንም የውጭ ምንዛሬ እያስገኘ ነው፡፡ ቴሌኮምን በተመለከተ ብዙም የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝ አይደለም፡፡ ራሱም ምንዛሬ ፈላጊ ነው። መብራት ኃይልም የውጭ ምንዛሬ ይፈልጋል፡፡ ፕራይቬታይዝ ስናደርግ የምናገኘው ገቢ አንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ገንዘቡን በአግባቡ ተጠቅሞ፣ ሌሎች መደላድሎችን መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ገንዘብ በሁለት እግራችን መቆም መቻል አለብን፡፡ ከዚህ አንፃር እርምጃው ትክክለኛ ቢሆንም አፈፃፀሙ ላይ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡
አንደኛ፤ ገዥ አመራረጥ ላይ ጥሩ ምንዛሬ ማግኘት የምንችልበት መሆን አለበት። ሌላው ደግሞ ከገባንበት ቅርቃር ወጥተን፣ በሁለት እግራችን ለመቆም የመጨረሻው አማራጭ መሆን ይኖርበታል፡፡


---------------              “እነዚህን ድርጅቶች መሸጥ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል”
                አቶ ክቡር ገና (ምሁርና የቢዝነስ ባለሙያ)


    አንድ ድርጅት ከመንግስት ወደ ግል የሚተላለፈው አንደኛ፤ መንግስት ከአቅሙ በላይ ሲሆንና ድርጅቱ ወጪ እንጂ ገቢ ከሌለውና ለሃገርም ለልማትም የሚያመጣው ውጤት ውስን ሲሆን ነው፡፡ ሌላው መንግስት የማስተዳደር ችሎታው ደካማ ሲሆን ነው። አንዳንድ ደግሞ ስልታዊ ናቸው ተብሎ በመንግስት ተይዘው የሚቆዩ አሉ፡፡ አሁን የተወሰደው እርምጃ ምክንያቱ ግልፅ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ስለ አየር መንገድ መርሳት የሌለብን ነገር፣ ብዙ ሰው በሀገር ፍቅር እየሰራ መስዋዕትነት ከፍሎበታል፡፡ አንድ ፓይለት አሁን ለሀገሩ ስለሆነ በቀን 18 ሰዓት ስራ ቢባል ይሰራል። የስራ አድማ የሚባል ነገር ተሰምቶ አይታወቅም። ይሄ ሁሉ የሆነው ሰራተኛው ለሃገሩ እንደሚሰራ ስለሚያምን ነው፡፡
ከሃገር ፍቅር በመነጨ ስሜት ነው የሚሰሩት። አሁን ወደ ግል ይዞታ በከፊል ይዛወራል ሲባል ግን በሚሰራው ስራ ልክ እንዲከፈላቸው ይፈልጋሉ። በተለይ አየር መንገድ እንደ ሌሎች ድርጅቶች አይደለም፡፡ ሁሉም የኔ ነው የሚለው ነው። ይሄን መሸጥ ምንድን ነው ትርጉሙ? አየር መንገዱ’ኮ 100 አውሮፕላን ካለው፣ 80ው በብድር ነው የተገዛው። ታዲያ ምኑ ነው የሚሸጠው?
ሌላው መብራት ኃይልን ብንመለከት፣ በአብዛኛው የህዝብ መገልገያ ነው፡፡ አሁን ለግል ሲሸጥ ኩባንያው በፈለገው ዋጋ ኤሌክትሪክ ይሸጣል ማለት ነው፡፡ እነዚህ የህዝብ ንብረቶችን መንካት ምንድን ነው ትርጉሙ? እነዚህን ድርጅቶች ለመሸጥ ገበያ ላይ ማውጣት፣ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ እነዚህ ድርጅቶች የኢህአዴግ አይደሉም፡፡ ከእነሱ በፊት የተገነቡ የህዝብ ሃብቶች ናቸው፡፡ እኔ ውሳኔው ግራ ነው ያጋባኝ፡፡ እነዚህን ድርጅቶች መሸጥ ለምን አስፈለገ? እዳ ለመክፈል ነው ከተባለ፣ እዳ ተከፍሎ ቁጭ ነው የሚባለው ማለት ነው? መሸጥ በየጊዜው የሚገኝን ገቢ ነው የሚያሳጣው፡፡ ስለዚህ ለኔ ይሄ እንደ ስጋት ነው የሚታየኝ፡፡ የህዝብን ሃብት መሸጥ ከተጀመረ፣ ወደ ድህነትና ኪሳራ እየሄድን ነው ማለት ነው፡፡  


------------                  “ውሳኔው ለአገሪቱ በእጅጉ ጠቃሚ ነው”
                    ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በርሄ (የኢኮኖሚ ምሁር)

     ይሄ ውሳኔ መወሰኑ ለሃገሪቱ በእጅጉ ጠቃሚ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሃገራት ብድር እያገኘችና ከዳያስፖራ የሚመጣ ገንዘብ በመጠቀም፣ ብዙ መሠረተ ልማቶችን ስትገነባ ቆይታለች፡፡ አሁን ግን ሃገሪቱ ያለባትን እዳ መክፈል የማትችልበት ደረጃ ነው የደረሰችው፡፡ እዳ መክፈል ቀርቶ ለፋብሪካዎች ግብአት ለማምጣትና መድኃኒት ለመግዛት እንኳ ተቸግራለች። ከዚህ ችግር ለመውጣት ቢያንስ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ብዙ የውጭ ምንዛሬ ሊያስገኝ ይችላል። ንግድ መርከብም ትልቅ ድርጅት ነው፡፡ የአፍሪካ ትልቁ የንግድ መርከብ፣ የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ነው ግን፤ ሀገሪቷ ወደብ የላትም፡፡ ስለዚህ የእነዚህ ድርጅቶች አክሲዮን መሸጡ ብዙ ገንዘብ ያስገኛል። በዚህም እዳችንን መክፈል እንችላለን፡፡ መሰረተ ልማቶች፣ ኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ ማዳበሪያ ፋብሪካዎችን ለመስራት የሚያስችል ገንዘብም ሊገኝበት ይችላል፡፡
ሌላው ከውጭ የምናመጣው፣ ከብረትና ከነዳጅ ቀጥሎ የቢራ ብቅልና የምግብ ሸቀጦች ናቸው፡፡ ማዳበሪያ፣ ስንዴ፣ ዘይት፣ ስኳር ወዘተ --- በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እያስገባን ያለነው፡፡ እነዚህ ግን እዚሁ ሃገር ቤት ማብቀል የምንችላቸው ናቸው፡፡ 72 ሚሊዮን ሄክታር የሚታረስ መሬት ያላት ሃገርና 122 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ይዘው የሚፈሱ ወንዞች እያሉን፣ ምግብ ከውጭ ማስገባት የለብንም፡፡ ወተት ሳይቀር ነው በውጭ ምንዛሬ እያስገባን ያለነው፡፡ አሁን እነ ቴሌኮም፣ መብራት ኃይል በከፊል ቢሸጡ ይሄ ይቀየራል ማለት ነው፡፡ እኔ የተባበሩት መንግስታትን ወክዬ ናይጄሪያ በምሰራበት ወቅት፣ በ2000 እ.ኤ.አ ነው ኢኮኖሚውን ሊበራላይዝ ያደረግነው፡፡ በወቅቱ በዓመት 250 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ነው ያገኘችው። በአንድ ዓመት ውስጥ መንግስት ከግሉ ዘርፍ የሚያገኘው፣ 2.8 ቢሊዮን ዶላር ነው ያደገው፡፡
ኬንያ በሞባይል ስልክ ብቻ 30 ቢሊዮን ዶላር ነው አክሲዮን ሸጣ ያገኘችው፡፡ እኛ ከቻይና ተበድረን ነው ቴሌኮም እያስፋፋን ያለነው፡፡ እሱም ብዙ ጉድለቶች አሉት፡፡ አሁን አክሲዮን ሲሸጥ ከሚገኘው ካፒታል ባሻገር አገልግሎቱም የተሻለ ይሆናል፡፡ በዚህ ዘመን ኢንተርኔት በአግባቡ ካልሰራ ሌላውን መስራት አይቻልም፡፡ ከዚህ አንፃርም ሊበራላይዜሽኑ ጠቃሚ ነው፡፡
በዚህ መሃል ግን ፕራይቬታይዜሽኑ አሁን ባሉት የመንግስት መዋቅሮችና ሰራተኞች ይሰራ ከተባለ አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለ ሙስና፣ መልካም አስተዳደር ችግሮች እያወራን ባለበት፣ እንደገና ይሄ ሲጨመር ከባድ ይሆናል፡፡ ለዚህ አማራጩ ብቃት ያላቸው ሃገር ወዳድ፣ ገቢያቸውና ደሞዛቸው ለሙስና የማይጋብዛቸው ሰዎች አሉ፤ እነሱ ይሄን ቢሰሩ ይመረጣል፡፡ ለምሳሌ አምስቱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምክትል አስፈፃሚዎች ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡
ዶ/ር ቴዎድሮስ አድኃኖም (WHO)፣ ዶ/ት ተገን ጌጡ (UNDP)፣ አቶ ጌታቸው እንግዱ (UNISCO) እና ሌሎችም አሉ፡፡ እንዲህ ያሉ ትልልቅ ድርጅቶችን የሚመሩ ኢትዮጵያውያን በእውቀትና በንፅህና ቢሰሩት የተሻለ ውጤት ያመጣል፡፡ በዚህ ረገድ መንግስት፣ ሃገር ለበለጠ ሌብነት እንዳትዳረግ መጠንቀቅ አለበት፡፡

----------             “ሃገራዊ ባለሃብቶች ምን ያህል የመግዛት አቅም አላቸው?”
               አቶ ሞሼ ሠሙ (ፖለቲከኛና የኢኮኖሚ ባለሙያ)


    እኔ የፕሮግረሲቭ ሊበራል አስተሳሰብ አራማጅ እንደመሆኔ፣ ይሄ አስተሳሰብ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሰርፅ፣ ከ1992 ጀምሮ፣ በፊት የነበርኩበት ፓርቲዬ ሲተባልበት የኖረ ሃሣብ ነው፡፡  መንግስት በኢኮኖሚው ውስጥ ሊኖረው የሚገባው ሚና የተገደበ መሆን አለበት፡፡ የያዛቸው ትልልቅ ኢንቨስትመንቶች በሂደት ለባለሃብቶች እየለቀቀ፣ ከኢኮኖሚው የሚወጣበትን ሁኔታ ማመቻቸት አለበት፡፡ ከዚህ አኳያ እርምጃው ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ እንደሚታወቀው እስካሁን ድረስ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ውስጥ ኢትዮጵያዊው ባለሃብት የመሣተፍ እድል የለውም፡፡  ሃገራዊ ባለሃብቱ በአብዛኛው እቃ ከውጭ እያስመጣ በመሸጥ ላይ የተወሰነ ነው፡፡ ትንሽ ደፈር ብለው ወደ አምራችነት የገቡት በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር ይህ እርምጃ ሃገራዊ ባለሃብቱን አዲስ ነገር በማለማመድ ረገድ ጠቀሜታ አለው፡፡
 ሌላው መንግስት ፖለቲካውን፣ ኢኮኖሚውን ይዞ ዲሞክራሲን ለመገንባት የሚደረገው ጥረት የመጨናገፍ እድሉ ሠፊ ነው፡፡ በታዳጊ ሃገራት ያሉ መንግስታት፣ ኢኮኖሚውን በመቆጣጠር፣ ሲመቻቸው የስራ እድል በመክፈት፣ የሰውን የፖለቲካ ተሣትፎ ያቀጭጩታል፡፡ ከዚህ አንፃር ይህ እርምጃ ለዲሞክራሲ ሂደቱም አጋዥ ይሆናል፡፡
መንግስት የሞባይል ካርድና የመብራት አገልግሎት አየቸረቸረ መኖር የለበትም፡፡ መንግስት ቀስ በቀስ ከዚህ ወጥቶ ፖሊሲ ወደማመንጨቱና ማሠራቱ ነው መሄድ ያለበት። እርግጥ እንደ አየር መንገድና መብራት ሃይል፣ ቴሌና ባቡር የመሳሰሉት ለአንድ መንግስት የጀርባ አጥንት ናቸው፡፡ መንግስት አሁን እነዚህን በከፊል ለመሸጥ መነሣቱ፣ በሌሎች ሥራዎች ላይ ትኩረቱን እንዲያደርግ ያግዘዋል፡፡ በመንግስት ሥር ያሉ ፕሮጀክቶች፣ ሁልጊዜ የሚዝረከረኩት በሃላፊነት የሚሠራ ስለማይኖር ነው። ባለሃብቱ ግን ከራሱ ላይ አይሠርቅም፤ በሃላፊነትም ይሠራል፡፡፡ ሃብትና ትርፍ ለማግኘት ስለሚጥር ዘመናዊ አሠራር እየመጣ፣ ሁልጊዜ ራሱን ለማበልፀግ ሲጥር፣ በቀጥታ ተገልጋዩንም ይጠቅማል ማለት ነው፡፡ መንግስት በአብዛኛው እነዚህን ተቋማት፣ የሥራ እድል መፍጠሪያ አድርጎ ስለሚጠቀምባቸው፣ አግባብ ያለው ባለሙያ፣ አግባብ ካለው ስራ ጋር አይገናኝም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ አባላቱን የሥራ እድል መጥቀሚያ ነው የሚያደርጋቸው፡፡ በቂ ምርት ሣይኖርም በኪሣራ ደሞዝ ይከፍላል፡፡
ሌላው የፕራይቬታይዜሽኑ ጠቀሜታ ለባለሃብቶች በተለይ ለውጭ ኢንቨስተሮች መተማመን ይፈጥራል። በሌላ በኩል፤ እነዚህን ግዙፍ ተቋማት፣ ወደ ግል ለማዞር ሲወሰን ጥናት ተደርጓይ ወይ? በቀጣይስ የመንግስት ሚና ምን ይሆናል? ለእነዚህ ጥናት ያስፈልጋል፡፡ ሌላው ስጋት ለምሣሌ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ድርሻ መግዛት የሚችለው የትኛው ኢትዮጵያዊ ባለሃብት ነው? አቅም ያለው ባለሃብት  ተፈጥሯል ወይ? ሌሎችንም ለመግዛት በቂ እቅም ያለው ሃገራዊ ባለ ሃብት ተፈጥሯል? እነዚህ ምን ያህል ተጠንተዋል?
አቅም ያለው ሃገራዊ ባለሃብት ከሌለ ደግሞ አሁን ሃገሪቱ ላይ አቅም ያላቸው የፓርቲ ኩባንያ የሆኑት እነ ኤፈርት፣ ጥረት ወዘተ-- ድርጅቶቹን የሚገዙት ከሆነ፣ የባሠ ወድቀት ነው፡፡ የበለጠ ኢኮኖሚው በአንድ እጅ ተሰባስቦ፣ መሣሪያውም ፖለቲካውም ኢኮኖሚውም በአንድ ቡድን እጅ ይወድቃል፡፡
ድርጅቶቹ የሚገዙት ከሆነ፣ ሃገሪቱ የፓርቲዎቹ ልትሆን ነው ማለት ነው። በሌላ በኩል የውጭ ሃገር ባለሃብቶች፤ እንደ ሃገራዊ ባለሃብት ሃላፊነት አይሰማቸውም፡፡ ስለዚህ የኔ ስጋት፣ እንዴት ነው ሃገራዊ ባለሃብቶች አቅም ሣይፈጥሩ፣ ድርጅቶቹን በዚህ ሠዓት ወደ ግል ለማዞር የተፈለገው የሚለው ነው? እነዚህን ድርጅቶች ለመሸጥ ሲወሰን፣ ህዝብ ምን ያህል ተወያይቶበታል? የህዝብ ተወካዮች ም/ቤትስ? የሚለው መጠየቅ ያለበት ነው። እኔ ፕራይቬታይዝሽኑን ብደግፈውም፣ እነዚህ ነገሮች ትኩረት ሊያገኙ ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡

Read 3874 times