Sunday, 06 May 2012 14:54

ቱፓክ በሆሎግራም ቴክኖሎጂ ነፍስ ዘራ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ከሦስት ሳምንት በፊት በካሊፎርንያ ግዛት ኢንድዮ ከተማ በተደረገው የኮቼላ የሙዚቃ ፌስቲቫል፤ ሟቹ ራፐር ቱፓክ ሻኩር፤ ከእነ ስኑፕ ዶግ ጋር በአንድ መድረክ ላይ ሲሰራ መታየቱ እያነጋገረ ነው፡፡ በሙዚቃ ፌስቲቫሉ ላይ ቱፓክ ሻኩር ነፍስ የዘራው ስኑፕ ዶግና ዶር ድሬ ባመነጩት ሃሳብ ሲሆን ትዕይንቱ በሆሎግራም ቴክኖሎጂ በመታገዝ ነበር የቀረበው፡፡ የቱፓክ ምስል ከስኑፕ ዶግ ጋር ለ5 ደቂቃ መጫወቱን የገለፀው “ዘ ሂንዱስታን ታይምስ”፤ በትኬት ሽያጭ እና በዱቤ ካርዶች አጠቃቀም ተወስኖ የነበረው የሆሎግራም ቴክኖሎጂ በአዲስ ምእራፍ ላይ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡

ቱፓክ መድረኩ ላይ ለስኑፕ ዶግ አጃቢ ሆኖ የራፕ ዘፈኖችን በመጫወት ታዳሚውን ማዝናናቱን ያወሳው ዋሽንግተን ፖስት፤ ሙከራው ታላቅ ድምፃዊያን በነበሩበት ዘመን ላልተወለዱና ህፃን ለነበሩት ሁሉ የማያውቋቸውን ታላላቅ አርቲስቶች የሚያስተዋውቅ ድንቅ ፈጠራ ብሎታል፡፡ ከዘመኑ እውቅ ራፐሮች አንዱ የሆነው ናስ ከሟቹ ቱፓክ ሻኩር ጋር ጠበኛ ቢሆንም በሆሎግራም መድረክ ላይ ለመጫወት የቻለበትን ሁኔታ በይፋ አድንቋል፡፡ ዊዝ ካሊፋ፣ ጄይዚ እና ሌሎች ዝነኛ ራፐሮቹም በፈጠራው እንደተማረኩ ተናግረዋል፡፡ በሆሎግራም ቅንብር የቱፓክ ዳግም መነሳት ዶር ድሬ እና ስኑፕ ዶግ ለራፕ ሙዚቃ ፈጠራ ዛሬም ቢሆን እየደከሙ መሆናቸውን ያሳያል ብለዋል ራፐሮቹ፡፡ የመድረክ ቅንብሩን “የራፐሮች ድምቀት” በሚል ርእስ አድንቆ የፃፈው “ዎል ስትሪት ጆርናል” በበኩሉ፤ ከ15 ዓመት በፊት የሞተው ቱፓክ በዚህ የቴክኖሎጂ ቅንብር መመለሱ ምናልባትም ለሌሎች ተመሳሳይ ስራዎች መነቃቃትን ይፈጥራል ብሏል - የቢትልስ የሙዚቃ ቡድን በሞት የተለያቸውን አባላቸውን ጆን ሌነን፤ የጃክሰን ወንድማማቾች ማይክል ጃክሰንን እንዲሁም ጂሚ ሄንድሪክስ፣ ዊትኒ ሂውስተንና ሌሎች ሟች ሙዚቀኞች እንደቱፓክ በሆሎግራም ቴክኖሎጂ ኮንሰርት የሚያቀርቡበት መድረክ እንደሚፈጠር በመጥቀስ፡፡

 

የቱፓክ ሻኩር የሆሎግራም ቅንብርን ለመስራት አራት ወራት የፈጀ ሲሆን 400ሺ ዶላር ገደማ ወጪ እንደፈጀ ተገልጿል፡፡ ቅንብሩን የሰራው ዲጅታል ዶሜን ግሩፕ የተባለ ኩባንያ ሲሆን የመድረክ ላይ ትእይንቱ በዩቲውብ መታየቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አድናቂዎች እንዲመለከቱት እድል ፈጥሯል ተብሏል፡፡ ኩባንያው ሌሎች የሞቱ ዝነኛ የዓለም አርቲስቶችን ሥራዎች በተመሳሳይ መንገድ ለማሰራት እቅድ ነድፎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ታውቋል፡፡

 

 

Read 3194 times Last modified on Sunday, 06 May 2012 15:00