Sunday, 06 May 2012 14:41

ከአውሮፓ 4 ታላላቅ ሊጎች 2 ሻምፒዮኖች ታውቀዋል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

የ2011-12 የውድድር ዘመን በአውሮፓ ሊገባደድ አንድ ሰሞን ሲቀረው የጀርመን ቦንደስ ሊጋና የስፔን ላሊጋ ሻምፒዮኖች ሲታወቁ በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግና በጣሊያን ሴሪኤ የዋንጫ ፉክክሩ ነገ ወይንም ከሳምንት በኋላ ይለያል፡፡ ከአራቱ የአውሮፓ ሊጐች ምርጡ የትኛው ነው የሚለው ክርክርም እንደቀጠለ ነው፡፡ በገበያው በጣሊያን ሴሪኤ የዋንጫ ፉክክሩ ነገ ወይንም ከሳምንት በኋላ ይለያል፡፡ ከአራቱ የአውሮፓ ሊጐች ተፈላጊነት በየውድድር ዘመኑ 1 ቢሊዮን ፓውንድ የሚንቀሳቀስበትና በ211 አገራት በ572 ሚሊዮን ቤቶች ጨዋታዎቹ በቴሌቭዥን ስርጭት የሚታዩለት የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ የምድራችን ታላቅ ትርዒት መሆኑ ጐልቷል፡፡

የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ዋንጫን ያሸነፈ ሻምፒዮን ክለብ በገንዘብ ሽልማት ብቻ እስከ 18 ሚሊዮን ፓውንድ የሚያገኝ ሲሆን ይህ የሽልማት መጠን ሌሎቹ ሊጐች አይስተካከሉትም፡፡

በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ተወዳዳሪ የሆነ እያንዳንዱ ክለብ የሊጉ እኩሌታ የገቢ ድርሻ ሲኖረው በየውድድር ዘመኑ 20ዎቹ ክለቦች በዚህ መንገድ  እሰከ 13.82  ሚሊዮን ፓውንድለእያንዳንዳቸው ይታሰብላቸዋል፡፡ እያንዳንዱ ክለብ በቲቪ በመላው ዓለም ከሚኖረው ስርጭት በየጨዋታው 582090 ፓውንድ እየተከፈለው በዓመቱ መጨረሻ በ10 ጨዋታዎች ስርጭት እስከ 5.82 ሚሊዮን ፓውንድ ያገኛል፡፡

በአጠቃላይ የሊጉ ሻምፒዮን የሚሆን ክለብ በተለያዩ የገቢ ምንጮች እስከ 90 ሚሊዮን ዶላር ገቢ  ባንድ የውድድር ዘመን ሊኖረው ይችላል፡፡ ከሊጉ የሚወርዱ ክለቦች እንኳን የገቢ ምንጮቻቸው እስከ 45 ሚሊዮን ፓውንድ ያሳፍሳቸዋል፡፡

በስፔን ፕሪሚዬራ ሊጋ ሻምፒዮናነት የሚገኘው የገንዘብ ሽልማት እና ሌላ ገቢ ከ30 ሚሊዮን ፓውንድ አይበልጥም፡፡ ይህም ላሊጋው ከእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ያነሰ አቅም መያዙን ያመለክታል፡፡ ባርሴሎና በዘንድሮው የውድድር ዘመን በስፔንና በአውሮፓ ውድድሮች የበላይነቱ ቢገታም ኤስፒኤኤን ከስፖርት ኢንተለጀንስ ጋር በሰራው የዓለም ስፖርት የደሞዝ ጥናት ለተጨዋቾቹ በነፍስ ወከፍ በዓመት 8.7 ሚሊዮን ዶላር በመክፈል ለሁለተኛ ተከታታይ ዓመት በመሪነት ተቀምጧል፡፡ በደሞዝ ጥናቱ  በሰባት የስፖርት አይነቶች በ10 አገራት በሚገኙ 14 የሊግ ውድድሮች 278 ቡድኖችና 7925 አትሌቶች ክፍያ ተዳስሷል፡፡ በ2011 ለደሞዝ ወጭ የሆነው 15.7 ቢሊዮን ዶላር መሆኑም ተረጋግጧል፡፡ ባርሴሎና በየውድድር ዘመኑ ለተጨዋቾቹ በድምሩ 217.02 ሚሊዮን ዶላር በማውጣት አንደኛ ደረጃ ሲይዝ የላሊጋው ሻምፒዮን ሪያል ማድሪድ ለአንድ ተጨዋች በአማካይ 7.8 ሚሊዮን ዶላር ዓመታዊ ክፍያ በመፈፀም እስከ 195 ሚሊዮን ዶላር በአንድ የውድድር ዘመን በመክፈል ሁለተኛ ነው፡፡ ለአንድ ተጨዋች በአማካይ 7.4 ሚሊዮን ዶላር በመክፈል በየዓመቱ 185 ሚሊዮን ዶላር ወጭ የሚያደርገው ማንችስተር ሲቲ ሶስተኛ ደረጃ ይዟል፡፡ ቼልሲ ደግሞ ለአንድ ተጨዋች በአማካይ 6.8 ሚሊዮን ዶላር እየከፈለና በድምሩ እስከ 170 ሚሊዮን ዶላር ለደሞዝ እያወጣ አራተኛ ነው፡፡ ኤሲ ሚላን በ6.1 ሚሊዮን 7ኛ፤  ባየር ሙኒክ በ5.9 ሚሊዮን 8ኛ፤ ማንችስተር ዩናይትድ በ5.5 ሚሊዮን 11ኛ እንዲሁም የቦንደስ ሊጋው ሻምፒዮን ዶርትመንድ በ3.1 ሚሊዮን ዶላር አማካይ የ1 ተጨዋች ክፍያቸው ደረጃ ተሰጥቷቸዋል፡፡

20ኛው ፕሪሚዬር ሊግ የማንችስተር ነው

የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ በአዲስ መዋቅር ከተጀመረ ዘንድሮ 20ኛውን ዓመት ይዟል በውድድሩ ታሪክ  አስደናቂው የሻምፒዮናነት ፉክክር በሁለቱ የማንችስተር ከተማ ክለቦች የተደረገበት የሊግ ውድድር ከሳምንት በኋላ የሚጠናቀቅ ይሆናል፡፡ እስከ 36ኛ ሳምንት በተካሄዱት 360 ጨዋታዎች 1008 ጎሎች የተመዘገቡበት የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ በየጨዋታው በአማካይ 2.8 ጎሎች የሚገቡበት ሆኖ ቆይቷል፡፡ በኮከብ ግብ አግቢነት እየመራ ያለው የአርሰናሉ ሮቢን ቫንፒርሲ በ28 ጎሎች ሲሆን ሆላንዳዊው በፕሪሚዬር ሊግ ተጨዋቾች ማህበርና በስፖርት ጋዜጠኞች የዓመቱ የፕሪሚዬር ሊግ ኮከብ ተጨዋች ተብሎ ድርብ ሽልማቶችን አግኝቷል፡፡

ባለፈው ሰኞ የሊጉን ሻምፒዮን ይወስናል በተባለ የማንችስተር ደርቢ ማንችስተር ሲቲ በሜዳው ኢትሃድ ስታድዬም ማን ዩናይትድን 1ለ0 ካሸነፈ በኋላ 20ኛው የሊጉ ዋንጫ ማንቸስተር ከተማ መጥተው ተረጋግጧል፡፡ ማን ሲቲ ሊጉ በአዲስ መዋቅር ከተጀመረ ለመጀመርያው እንዲሁም በውድድሩ አጠቃላይ ታሪክ ከ44 ዓመት በኋላ የመጀመርያውን የሻምፒዮንነት ዋንጫ ለማንሳት የሚችልበትን እድል በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች በራሱ እንዲወሰን ማድረግ ችሏል፡፡ ማን ሲቲ ነገ ከዓመቱ አስደናቂ ቡድን ኒውካስትል ዩናይትድ ጋር የሚያደርገው የ37ኛ ሳምንት ጨዋታ በውድድሩ ዘመኑ ከባዱ ፍልሚያ ሲሆንበት ከዚህ ጨዋታ በፊት ሊጉን በ83 ነጥብና በ61 የግብ ክፍያ እየመራ ነው፡፡ ማን ዩናይትድ ተመሳሳይ ነጥብ ቢኖረውም በ8 የግብ ክፍያዎች ተበልጦ ሁለተኛ ነው፡፡ ሁለቱ የማንችስተር ክለቦች በቀሯቸው ሁለት ጨዋታዎች ድል ካደረጉ አሸናፊው በግብ ክፍያ በሚኖር ብልጫ ሊለይ ይችላል፡፡ የማንችስተር ከተማ ክለቦች የሊጉን ሻምፒዮናነት የሁለት ፈረሶች ሽቅድምድም አድርገው ለቀጣይ ዓመት የሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ማጣርያ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል፡፡ በሻምፒዮንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ማጣርያ ለመግባት በሚያስችለው ቀሪ የሁለት ክለቦች ኮታ ደግሞ ከ3 እሰከ 6ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት 3 የለንደን ክለቦችና ኒውካስትል ዩናይትድ ቀሪዎቹን የሁለት ዙር ጨዋታዎች በከፍተኛ ውጤት ለመጨረስ ይተናነቁበታል፡፡  በ66 ነጥብና በ24 የግብ ክፍያ አርሰናል፤ በ65 ነጥብና 23 የግብ ክፍያ ቶትንሃም፤ በ65 ነጥብና በ9 የግብ ክፍያ ኒውካስትል ዩናይትድ እንዲሁምበ61 ነጥብና በ21 የግብ ክፍያ ከ3 እስከ 6 ባለው ደረጃ ተቀምጠዋል፡፡ በወራጅ ቀጠና ዎልቨርሃምፕተን መውረዱን አስቀድሞ ያረጋገጠ ሲሆን  5 ክለቦችም በአጣብቂኝ ውስጥ ናቸው፡፡ በ36ጨዋታዎች 31 ነጥብ ያለው ብላክበርን ሮቨርስ፤ እኩል 34 ነጥብ ያላቸው ቦልተን ዎንድረርስ እና ኪውፒአር እንዲሁም በ37 ነጥብ 15ኛና 16ኛ የሆኑት አስቶንቪላና ዊጋን አደጋው እንዳንጃበባቸው ነው፡፡

ሁለቱ የማንችስተር ከተማ ክለቦች በቀጣይ የውድድር ዘመንም የበላይነት እንደሚኖራቸው ይጠበቃል፡፡ ዋንኛው ማስረጃም ሁለቱ ክለቦች እርስ በእርሳቸው የሚኖራቸውን ፉክክር ለመቀጠል በክረምቱ የዝውውር ገበያ ንቁ ተሳትፎ ማድረጋቸው ስለማይቀር ነው፡፡ በሁለቱም ክለቦች በክረምቱ የዝውውር ገበያ ከ250 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ በተጨዋቾች የዝውውር ገበያ ወጭ ሊደረግ ይችላል፡፡ ማንችስተር ሲቲ ኤዲን ሃዛርድ፤ ኤዲሰን ካቫኒንና ፈርናንዶ ሎረንቴን ለመግዛት እስከ 100 ሚሊዮን ፓውንድ ወጪ ለማድረግ ጥሪ እያቀረበ ነው፡፡ በማን. ዩናይትድም ለሰር አሌክስ ፈርጉሰን የአዳዲስ ተጨዋቾች ግዢ 100 ሚሊዮን ፓውንድ በጀት መደረጉ ሰሞኑን ተገልጿል፡፡

በቀሪ ሁለት የሊጉ ጨዋታዎች ሲቲ ከኒውካስትል እና ከኪውፒአር ጋር ሲገናኝ ዩናይትድ ደግሞ በደረጃው አማካይ ከሚገኙት ስዋንሲና ሰንደርላንድ ጋር ይፋለማል፡፡ ቼልሲ  በቀጣይ የውድድር ዘመን ለሻምፒዮንስ ሊግ ጥሎ ማለፍ ለመብቃት የነበረው እድል  የተሟጠጠ ሲሆን የቀረው ተስፋ ከ3 ሳምንት በኋላ በሻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ዋንጫ በመውሰድ ለውድድሩ መብቃት ነው፡፡ ካልሆነለት ግን ቼልሲን የሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ሲያመልጠው ከ10 ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ይሆናል፡፡

80ኛው  ሴሪኤ የጁቬ ወይም የኤሲ ሚላን ይሆናል

የጣሊያን ሴሪኤ ሊጠናቀቅ የ1 ሳምንት ጨዋታዎች እየቀረ ለስኩዴቶው ክብር በራሳቸው ውጤታማነት የሚወሰን እድል ይዘው ፉክክራቸውን የቀጠሉት ጁቬንትስና ኤሲ ሚላን ናቸው፡፡ በሴሪኤው እስከ 36ኛ ሳምንት በተደረጉ 360 ጨዋታዎች 915 ጎሎች ገብተው ሊጉ በየጨዋታው በአማካይ 2.54 ጎሎች እየተመዘገበበት ቆይቷል፡፡ በሴሪ ኤ ውድድር ሁለቱ የሚላን ከተማ ክለቦች ላለፉት 5 ዓመታት በነበራቸው የበላይነት ከዋንጫ ፉክክር ውጭ ሆኖ የቆየው እና በሙስና ቅሌት ሀብት የዋንጫ ክብሮቹን የተነጠቀው ጁቬንትስ ዘንድሮ ለሻምፒዮናነት ክብሩ ዋና ተቀናቃኝ ሆኗል፡፡ የአሮጊቷ ቡድን በ36 ጨዋታዎች ያለመሸነፍ ጥንካሬ በማሳየት ለስኩዴቶው ክብር ቅድሚያ ግምት አግኝቷል፡፡ እስከ 36ኛው ሳምንት ባደረጋቸው ጨዋታዎች ጁቬንትስ በ78 ነጥብ  በ44 የግብ ክፍያ ሴሪኤውን ሲመራ ኤሲ ሚላን በ77 ነጥብ  በ42 የግብ ክፍያ ተያይዞበታል፡፡ ጁቬና ኤሲ ሚላን ለቀጣይ ዓመት የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ማጣርያ በቀጥታ ማለፋቸውን ሲያረጋግጡ በ55 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ያለው ናፖሊ በቀሪ የጣሊያን ክለቦች ኮታ ለሻምፒዮንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ማጣርያ የሚኖረውን ተሳትፎ ጨብጧል፡፡ ሲዬና ኖቫራ ከሴሪኤው መውረዳቸውን ያረጋገጡ ሲሆን በቀረው አንድ የወራጅ ቦታ 39 ነጥብ ይዞ 17ኛ ደረጃ ላይ ያለው ጄኖዋና በ36 ነጥብ ከስሩ የሚገኘው ሊቼ አደጋው ውስጥ ናቸው፡፡

በኮከብ ግብ አግቢነቱ ፉክክር የኤሲ ሚላኑ ዝላታን ኢብራሞቪች በ26 ጎሎች እየመራ ሲሆን የናፖሊው ኤዲሰን ካቫኒ በ22 ጎሎች ይከተለዋል፡፡

የጁቬ የስኩዴቶ ድል ሊዘገይ የቻለው በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ከወረደው ሊቼ ጋር አቻ ተለያይቶ ሁለት ነጥብ በመጣሉ ነው፡፡ ቀጣይ የጁቬንትስ ጨዋታዎች ነገ ከካግሊያሪ ጋር ከሜዳ ውጭ የሚያደርገውና ከሳምንት በኋላ በሜዳው ከአትላንታ ጋር የሚገናኝባቸው ጨዋታዎች ሲሆን ግጥሚያዎችን በድል ከተወጣ ከ10 ዓመታት በፊት ኤሲ ሚላን ሳይሸነፍ የስኩዴቶን ክብር ካገኘበት ክብረወሰን ጋር ይስተካከላል፡፡ ኤሲ ሚላን የጁቬን ዋንጫ ለመንጠቅ ነገ በደርቢ ጨዋታ ከኢንተር ሚላን ጋር እንዲሁም ከሳምንት በኋላ ከወረደው ኖቫራ ጋር በሚያደርገው የመጨረሻ ጨዋታ ድል ማድረግ እና የጁሴን መሸነፍ መጠበቅ አለበት፡፡

81ኛው የስፔን ፕሪሚዬራ ሊጋ በርናባኦ ገብቷል

ሊጠናቀቅ የሁለት ዙር ጨዋታዎች ሲቀሩ ሪያል ማድሪድ በደረጃው መሪነት ተከታዩን ባርሴሎና በ7 ነጥብ በመብለጡ ለ32ኛ ግዜ የሻምፒዮናነት ክብሩን መውሰዱን ሰሞኑን አረጋግጧል፡፡ ሪያል ማድሪድ የላሊጋውን ሻምፒዮናነት ክብር ከ4 ዓመት በኋላ መልሶ ለማግኘት የቻለው ባለፈው ረቡእ አትሌቲኮ ቢልባኦን 3ለ0 በማሸነፉ ነው፡፡ የባርሴሎናቸው  ሊዮኔል ሜሲ ረቡእ በተደረገ ጨዋታ ባርሴሎና 6ለ1 ሲያሸንፍ ሃትሪክ በመስራቱ በላሊጋው የኮከብ ግብ አግቢዎች ፉክክር በ46 ጎሎች መሪነቱን ሲይዝ የማድሪዱ ሮናልዶ በ44 ጎሎች ዱካውን ይዞታል፡፡ ለኮከብ በረኞች በሚሸለመው የዛሞራ አዋርድ ላይ ዋና ተቀናቃኞቹ ቪክቶር ቫልዴዝና ኢከር ካሲያስ ናቸው፡፡ የባርሴሎናው ቫልዴዝ በላሊጋው በጨዋታ በአማካይ 0.76 ጎሎች እየገቡበት ሲመራ የማድሪዱ ኤከር ካስያስ 0.86 አስመዝግቦ ይከተለዋል፡፡ በላሊጋው የሁለት ዙር ጨዋታዎች እየቀሩ በተደረጉ 360 ጨዋታዎች 998  ጎሎች ከመረብ አርፈው ሊጉ በአንድ ጨዋታ በአማካይ 2.77 ጎሎች ሲመዘገብበት ቆይቷል፡፡ ሪያል ማድሪድ የሁለት ሳምንት ጨዋታዎች እየቀሩ ሻምፒዮን ሲሆን በ36 ጨዋታዎች 94 ነጥብና 85 የግብ ክፍያ አስመዝግቦ ነው፡፡ በቀጣይ ዓመት ለሚደረገው የሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ለምድብ ማጣርያ በቀጥታ ማለፋቸውን 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ የያዙት ሪያል ማድሪድና ባርሴሎና አረጋግጠዋል፡፡ ለሻምፒዮንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ውድድር ለማለፍ ደግሞ 3ኛ እና 4ኛ የሆኑት ቫሌንስያ እና ማላጋ እስከ ውድድር ዘመኑ መገባደጃ ይጠባበቃሉ፡፡ ሳንታንዴር መውረዱን ካረጋገጠ በኋላ 17ኛ ላይ በ40 ነጥብ የተቀመጠው ራዮ ቫላካኖ፤ በ37 ነጥብ 18ኛው ዛራጎዛ እና በ34 ነጥብ 19ኛ የሆነው ስፖርቲን ጊዮን በቀሪዎች ሁለት የወራጅ ኮታ ለመፈረጅ አደጋ ውስጥ ናቸው፡፡

የሜሲ እናሮናልዶ ከፍተኛ ግብ አግቢነት ሁለቱ የስፔን ክለቦች በአንድ ውድድር ዘመን ባገቡት በላሊጋው የታየው ጎል ክብረወሰን እንዲይዙ ምክንያት ሆኗል፡፡ ሊጋው ሊጠናቀቅ የሁለት ሳምንት ጨዋታዎች እየቀሩ ሪያል ማድሪድ በውድድር ዘመኑ በአጠቃላይ 115 ጎሎች በማስመዝገብ አዲስ ክብረወሰን ይዟል፡፡ ባርሴሎናም 108 ጎሎች አስመዝግቧል፡፡ ማድሪድ በቀሪዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ሙሉ ነጥብ ከወሰደ ባንድ የውድድር ዘመን ባርሴሎና በ99 ነጥብ የጨረሰበትን የከፍተኛ ነጥብ ክብረወሰን ሊሰብርም ይችላል፡፡ በአውሮፓ ሊጎች አጠቃላይ ኮከብ ግብ አግቢነት የወርቅ ጫማ ለመሸለም ፉክክሩም ቀጥሏል፡፡ በውድድር ዘመኑ 68 ጎሎች ያለው ሊዮኔል ሜሲ በገርድ ሙለር ከ32 ዓመታት በፊት በ67 ጎል የተመዘገበውን ሪኮርድ በማሻሻል በአንድ የውድድር ዘመን ከፍተኛውን የጎል ብዛት በማስመዝገብ አንደኛ ደረጃን ይዟል፡፡ ሊዮኔል ሜሲ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ በ14 ጎሎች ኮከብ ግብ አግቢነቱም እንደተጠበቀ ነው፡፡ ይህም በውድድሩ ታሪክ በአንድ አመት የተመዘገበ ከፍተኛው የጎል ብዛት ሆኖ ክብረወሰን ተፅፎለታል፡፡ 3 ገዜ የዓለም ኮከብ ተጨዋች የሆነው ሊዮኔል ሜሲ በባርሴሎና ክለብ በ326 ጨዋታዎች 248 ጎሎች በማስመዝገብ በክለቡ ታሪክ ከፍተኛው ግብ አግቢ በመሆንም ዘንድሮ አንደኛነቱን ጨብጦታል፡፡ በሁሉም ውድድሮች 58 ጎሎች በማስቆጠር ለወርቅ ጫማው 2ኛ ሆኖ ሜሲ የሚከተለው ሮናልዶ ነው፡፡ ለአውሮፓ የኮከብ ግብ አግቢነት  ያለው እድል እንዳልተሟጠጠና ማሸነፍ እንደሚፈልግ ሰሞኑን የተናገረው ሮናልዶ በዓለም ኮከብ ተጨዋችነት ዘንድሮ ለሶስተኛ ግዜ በመሸለም ከሜሲ ክብረወሰን ጋር ለመስተካከል አስባለሁ ብሏል፡፡

ሞውሪንሆ ማድሪድ ለ32ኛ ጊዜ የላሊጋው ሻምፒዮን ከሆነ በኋላ በሰጡት አስተያየት የስፔን ክለቦች ውድድር ዋንጫን ማሸነፍ በስራ ዘመናቸው ፈታኙ ብለውታል፡፡ በአራት ሊጎች 7 የሻምፒዮናነት ዋንጫዎችን በማንሳት ውጤታማናታቸውን የቀጠሉት የ49 ዓመቱ ሞውሪንሆ በፖርቶ ሁለቴ፤ በቼልሲ ሁለቴ እንዲሁም በኢንተር ሁለቴ የየሊጉ ሻምፒዮን ሆነው በሪያል ማድሪድ የመጀመርያውን ሻምፒዮናነት አግኝተዋል፡፡

49ኛውን የቦንደስ ሊጋ ዋንጫ ዶርትመንድ ወስዶታል

ለ49ኛ ግዜ የተካሄደው የጀርመን ቦንደስ ሊጋ ከሳምንት በፊት ያበቃ ሲሆን አምና ሻምፒዮን የነበረው ቦርስያ ዶርትመንድ ዘንድሮም በፍፁም የበላይነት ሊጉን በመቆጣጠር የውድድር ዘመን ከመገባደዱ ከአንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ሻምፒዮን መሆኑን አረጋግጧል፡፡ በሻምፒዮንስ ሊግ ለጀርመን ክለቦች በሚሰጠው 4 ኮታ ሻምፒዮኑ ዶርትመንድና ሁለተኛ ደረጃ ይዞ የጨረሰው ባየር ሙኒክ በቀጥታ ወደ ምድብ ማጣርያ ማለፍ ችለዋል፡፡ ሻልካ 04 እና ቦርስያ ሞንቼግላድባክ ለጥሎ ማለፍ ውድድር የሚያበቃቸውን የ3ኛና 4ኛ ደረጃ አግኝተዋል፡፡ በቦንደስ ሊጋው በተደረጉ 285 ጨዋታዎች 808 ጎሎች ተመዝግበው የሊግ ውድድሩ በአንድ ጨዋታ በአማካይ 2.84 ጎሎች ተመዝግቦበታል፡፡ የቦደስ ሊጋው ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ የጨረሰው የሻልካው ክላስ ያን ሁንትላር በ27 ጎሎች ሲሆን የባየር ሙኒኩ ማርዮ ጎሜዝ በ26 ጎሎቹ  በሁለተኛ ደረጃ ጨርሷል፡፡ በውድድሩ ዘመን በሊጉ ካደረጋቸው 33 ጨዋታዎች በ25 ሳይሸነፍ ከፍተኛ ጥንካሬ ያሳየው ዶርትመንድ ለሻምፒዮናነቱ 78 ነጥብና 51 የግብ ክፍያ አስመዝግቧል፡፡ ባየር ሙኒክ በ8 ነጥቦች ተበልጦ ሁለተኛ ሆኗል፡፡

 

 

 

 

Read 2564 times Last modified on Sunday, 06 May 2012 14:48