Monday, 07 May 2018 09:51

የቻይና የንግድ ሳምንት እየተካሄደ ነው

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

 የቻይናው ኩባንያ (MIE events DMCC) እና አገር በቀሉ ፕራና ኢቨንትስ በጋራ ትብብር ያዘጋጁት ሁለተኛው የቻይና የንግድ ሳምንት፣ ከትናንት በስቲያ በሚሊኒየም አዳራሽ የተከፈተ ሲሆን የንግድ ሳምንቱ በዛሬው ዕለት ይጠናቀቃል።
በዘንድሮው የንግድ ትርዒቴ ላይ የኮንስትራክሽን ግብአቶችና ማሽነሪዎች፣ የኤሌክትሪክ ቁሳቁስና ኤሌክትሮኒክሶች፣ የመብራትና የኢነርጂ መሳሪያዎች፣ የግብርና ማሽነሪዎች፣ ለማዕድን ሥራ የሚያገለግሉ መሳሪያዎች፣ የምግብ ማቀነባበሪያ ማሽኖች፣ የሆቴል እንጨት ሥራዎች፣ ለዕለት ተዕለት ፍላጎት የሚውሉ ዕቃዎች፣ የእንስሳት መኖ ቴክኖሎጂና የጤና መጠበቂያዎችን ያካተተ መሆኑን አዘጋጆቹ ገልፀዋል፡፡
የኤምአይኢ ኢቬንትስ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሚ/ር ዴቪድ ዋንግ፤ “የቻይና የተለያዩ ምርቶችን ለማስመጣት፣ እንደዚሁም ልዩ ልዩ አገልግሎቶችን ለማግኘት፣ የኢትዮጵያ አምራቾችና ነጋዴዎች ከቻይና ኩባንያዎች ጋር ጠንካራ የንግድ ግንኙነት እንዲኖራቸው ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ማድረግ በመቻላችን የላቀ ደስታ ይሰማናል” ብለዋል፡፡
ከቻይና ጋር በጋራ በመስራቱ በኩል ከዚህ ቀደም ምንም ዓይነት እድሉ የሌላቸው፤ እንደዚሁም ሥራውን ከየት እንደሚጀምሩ ምንም ዓይነት ፍንጩ ለሌላቸው የኤግዚቢሽኑ ጎብኚዎች በምን መልኩ ከቻይና ጋር የንግድ ልውውጥ ማድረግ እንደሚችሉ መረጃ የሚሰጥ ሴሚናር በሦስቱ ቀናት ኤግዚቢሽን እንደሚካሄድ ታውቋል።
ኤም እይ ኢ ዓለም አቀፉ የሁነቶች (Events) ዳይሬክተር ሚ/ስ ሚሸል ሜይሪክ በሰጡት ማብራሪያ የሴሚናሮቹ ዋነኛ ዓላማ “የቻይና ምርቶች ዝቅተኛ የጥራት ደረጃ አላቸው” የሚለውን የተሳሳተ አመለካከት ለመለወጥ መሆኑን ጠቁመው፤ “እንደዚህ ዓይነቱ አመለካከት እንደ አጋጣሚ ሆኖ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በበርካታ ሃገራት ያለ በመሆኑ መሰል ሴሚናርም የኢትዮጵያ ኩባንያዎች በሚከፍሉት የተሻለ የክፍያ መጠን የተሻለ ጥራት ያለው ምርትን ከቻይና የሚያገኙ መሆኑን ግንዛቤ ለማስጨበጥ ይጠቅማል” ብለዋል፡፡
የቻይና የንግድ ሳምንት ማንም ሰው በነፃ ከኢንተርኔት ላይ አውርዶ ሊጠቀምበት የሚችል የራሱ የሆነ ኢንተርኔት መተግበሪያ ወይም አፕልኬሽን ያለው ሲሆን ጎብኚዎች ስለ ኤግዚቢሽኑ ተሳታፊዎች ወቅታዊ መረጃን እንዲያገኙ እንደሚደረግና ከተሳታፊዎች ጋር በቀጥታ ኦንላይን የሃሳብ ልውውጥ ማድረግ፣ በሴሚናሩ ንግግር አድራጊዎች ዙሪያ መረጃ ማግኘት፣ ብሎም በቻይና የንግድ ሳምንት 80 ሺ ተሳታፊ ከሚደርሱ በቻይና የንግድ ሳምንት ተሳታፊ ኩባንያዎች ጋር የሚገናኙበት እድልም ይፈጠርላቸዋል ሲሉ አዘጋጆቹ አመልክተዋል፡፡   

Read 2483 times