Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 28 April 2012 14:47

የፖስታ ድርጅት ሃላፊ፤ “ፖስታ ጊዜ አልፎበታል” አሉ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በየወሩ አንድ ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ እየደረሰበት የሚገኘው የአሜሪካ ፖስታ አገልግሎት፤ በሺ የሚቆጠሩ ፖስታ ቤቶችን ለመዝጋት ያወጣው እቅድ እንቅፋት ገጥሞታል። ንብረትነቱ የመንግስት የሆነው የፖስታ ድርጅት፤ ኪሳራውን ለመቀነስ 3700 ፖስታ ቤቶችን እንዲሁም 250 ዋና ማእከላትን ለመዝጋት እቅድ አውጥቷል። የአሜሪካ ፖስታ ድርጅት ከ220 አመት በላይ ያስቆጠረ አንጋፋና ግዙፍ ድርጅት ከመሆኑም በተጨማሪ፤ በአለማችን በጣም “ዘመናዊ” ከሚባሉት መካከል የሚመደብ ነው። በቀን 500 ሚሊዮን መልእክቶችን ያስተላልፋል ወይም ያደርሳል። ክፍያዎችንና የገንዘብ ልውውጦችን (የሃዋላ አገልግሎቶችን) ይሰጣል። እንዲያም ሆኖ፤ እንደ ማንኛውም የመንግስት ቢዝነስ፤ የአሜሪካ ፖስታ ድርጅትም “ወደ ኋላ” እየቀረ ተዳክሟል።

ለምን ብትሉ፤ አንጋፋው የፖስታ ድርጅት፤ ከግል ቢዝነስ ጋር እኩል መራመድና መወዳደር አልቻለም። ዛሬ አብዛኛው የመልእክት ልውውጥ... በሞባይል ስልክና በኢንተርኔት ሆኗል። እነ ጉግል፣ ያሁ እና መሰል የግል ኩባንያዎች ከማስታወቂያ በቢሊዮን የሚቆጠር ትርፍ የሚያገኙት ለምን ሆነና? በኢንተርኔት ነፃ የመልእክት ልውውጥ አገልግሎት በመስጠት ነው። በቀጥታ የሚከናወን የፅሁፍ ምልልስ ወይም ወሬ (ቻት) ... ይሄም በነፃ ነው። የገንዘብ ክፍያዎችን በፖስታ ድርጅት በኩል ማስተላለፍም እየቀረ መጥቷል። ክፍያዎችና የገንዘብ ልውውጦች በኢንተርኔት ወይም በሞባይል ይከናወናሉ።

የግል ቢዝነስ ሁሌም፤ አዲስና የተሻለ፣ ቀላልና ወጪ ቆጣቢ የአሰራር ዘዴ ወይም የመሳሪያ ቴክኖሎጂ ከመፍጠር አይቦዝኑም። መፍጠር ያልቻሉ ቢዝነሶችም እጃቸውን አጣጥፈው አይቀመጡም። ከሌሎች ኩባንያዎች ትምህርት ይቀስማሉ፤ ራሳቸውን ያሻሽላሉ። አለበለዚያማ፤ ለደንበኞች ጥሩ ምርትና አገልግሎት በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ ያቅታቸዋል፤ ገበያ ውስጥ መወዳደር ይሳናቸውና ይከስራሉ። የመንግስት ድርጅት ግን፤ ይሄን ሁሉ “ጣጣ” አያውቅም። የመንግስት ቢዝነስ ማለት ባለቤት የሌለው ቢዝነስ እንደማለት ነው።

የመንግስት ድርጅት ሃላፊ ብሆን ብላችሁ አስቡት። የድርጅቱን አሰራር ለማሻሻልና ትርፋማ ለመሆን መጣጣር አያስፈልጋችሁም። ድርጅቱ አትራፊ ቢሆንኮ፤ ገንዘቡ ኪሳችሁ ውስጥ አይገባም። ድርጅቱ መወዳደር እንዳያቅተውና እንዳይከስር መስጋት አይኖርባችሁም። ቢከስር ምን ቸገራችሁ? የራሳችሁ ንብረት አይደለም፤ ከኪሳችሁ የሚጎድል ነገር አይኖርም።

በእርግጥ የድርጅቱ ሃላፊዎችና ሰራተኞች፤ ከጫፍ እስከ ጫፍ ግድየለሽ ይሆናሉ ማለት አይደለም። በተለይ፤ የግል ቢዝነስና የታታሪነት ባህል በተስፋፋበት በአሜሪካ፤ የመንግስት ድርጅቶችም የዚሁ ባህል ተቋዳሽ መሆናቸው አይቀርም። እናም፤ ብዙዎቹ ሃላፊዎችና ሰራተኞች ግድየለሽ አይሆኑም። ነገር ግን፤ የግል ቢዝነስ ውስጥ የሚታየውን ያህል ጠንቃቃነትና ታታሪነት፤ በመንግስት ድርጅት ውስጥ ሊሰፍን አይችልም። እናም በፍጥነት ባይሞቱ እንኳ፤ ቀስ በቀስ ወደ ኋላ እየቀሩና እየደከሙ ይሄዳሉ። የቱንም ያህል ድጎማ ቢያገኙ፤ የቱንም ያህል የሞኖፖል ስልጣን ቢያገኙ፤ የኋላ ኋላ ከመውደቅ አይተርፉም። በተንዛዛ ቢሮክራሲ እየተተበተቡ፣ በማይሻሻል አሰራር እየተዝረከረኩ፣ በሃብት ብክነት እየተራቆቱ ይዳከማሉ። የአሜሪካ ፖስታ ድርጅትም፣ ከዚህ “እጣ ፈንታ” አላመለጠም። እና ምን ተሻለ?

ድርጅቱን የሚመሩት ፓትሪክ ዶናሆ እና የበላይ ተቆጣጣሪዎቹ የቦርድ አባላት፤ በአንድ የመፍትሄ ሃሳብ ተስማምተዋል - ወጪዎችን የመቀነስ ሃሳብ። በዚህ ሃሳብ መሰረትም በርካታ ውሳኔዎችን አሳልፈዋል። ለምሳሌ፤ የስራ ቀናትን ለመቀነስ ወስነዋል። የፖስታ ደብዳቤዎች ወደየቤቱና ወደየቦታው የሚዳረሰው ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ነበር። አሁን የቅዳሜውን ስራ ብናስቀረው ወጪዎችን ለመቀነስ ይረዳናል በማለት የድርጅቱ ሃላፊዎች ወስነዋል።

ዋናው የወጪ ቅነሳ ውሳኔ ግን ሌላ ነው - 7300 ፖስታ ቤቶችን መዝጋት። ከዚህም በተጨማሪ ትልልቅ የፖስታ ማእከላት አሉ። ከየአካባቢው የሚመጡ ፖስታዎችና መልእክቶች ተሰብስበው፣ እንደየአድራሻቸውም ተለይተው ወደየአቅጣጫው የሚሰራጩት በእነዚህ ማእከላት አማካኝነት ነው። ከእነዚህ ውስጥ 250 ያህሉን ለመዝጋት የተቋማቱን ዝርዝር አዘጋጅተዋል -  የድርጅቱ ሃላፊ።

ሃላፊው ፓትሪክ ዶናሆ እንደሚሉት፤ በአጠቃላይ በአመት 6.5 ቢ. ዶላር ያህል ወጪ ለመቀነስ ነው ያቀዱት። ነገር ግን፤ እቅዳቸው አንድ ስንዝር አልተራመደም። በመሃል፣ የአሜሪካ ምክር ቤቶች (ኮንግረስና ሰኔት) የፓትሪክ ዶናሆን እቅድ በአጭር የሚያስቀር ህግ አርቅቀዋል። የሰኔት አባላት ለደርዘን ያህል ጊዜ፤ ረቂቅ ህጉን ሲከልሱ፣ አንቀፅ ሲለውጡ፣ አረፍተነገር ሲቀይሩ ቆይተው ባለፈው ረቡእ እለት ህጉን አፅድቀውታል - 62 ለ37 በሆነ አብላጫ ድምፅ። በፀደቀው ህግ ያልተደሰቱት ፓትሪክ ዶናሆ፤ አላስፈላጊና ያልተገባ ህግ ነው በማለት ተቃውመውታል።ላይ ላዩን ሲታይ፤ ፓትሪክ ዶናሆ ህጉን የሚቃወሙበት ምክንያት ያለ አይመስልም። በኪሳራ ለተዳከመው የፖስታ ድርጅት 11 ቢ. ዶላር ድጎማ ከመንግስት እንዲመደብለት በህጉ ተደንግጓል። ኪሳራውን የሚያካክስለት ገንዘብ ከተገኘ፤ ምን ችግር አለ? ችግርማ አለ። ገንዘቡ ከሰማይ አይዘንብም። ከዜጎች የሚሰበሰብ ቀረጥ ነው። ብዙዎቹ አሜሪካዊያን ደግሞ፤ የቀረጥ ነገር አማርሯቸዋል። በዚያ ላይ፤ ህጉ ሌሎች ተጨማሪ አንቀፆችንም ይዟል። አንደኛ፤ እንዲዘጉ ከተወሰነባቸው 250 የፖስታ ማእከላት መካከል 125ቱ መዘጋት እንደሌለባቸው በህጉ ገደብ ተጥሏል። ሁለተኛ፤ 7300 ፖስታ ቤቶችን ለመዝጋት የወጣው እቅድ፤ በመጪው ህዳር ወር ጠቅላላ ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ መዘግየት እንዳለበት በህጉ ተጠቅሷል። ሶስተኛ፤ በህጉ መሰረት፤ ከህዳር ወር በኋላም ቢሆን፤ ጥቂቶቹ ፖስታ ቤቶች ብቻ ናቸው ስራ እንዲያቆሙ ማድረግ የሚቻለው።

በአንድ በኩል፣ የድርጅቱን ኪሳራ ለማቃለል ይረዳል በሚል የድጎማ ገንዘብ እንዲመደብ፤ በሌላ በኩል ደግሞ አክሳሪ ሆነዋል የተባሉት ፖስታ ቤቶችና ማእከላት እንዳይዘጉ ይደነግጋል - ህጉ። በሌላ አነጋገር፤ ፓትሪክ ዶናሆ፤ በአመት 6.5 ቢ ዶላር ያህል ወጪ ለመቀነስ ያወጡት እቅድ በአብዛኛው ተግባራዊ አይሆንም ማለት ነው። የወጪ ቅነሳ እቅዶችን የሚያሰናክል የ11 ቢ. ዶላር ድጎማ፤ የድርጅቱን ችግር ሊያቃልል አይችልም የሚሉት ፓትሪክ ዶናሆ፤ ብዙዎቹ ፖስታ ቤቶች ምንም ደብዳቤ ሳያስተናግዱ አፋቸውን ከፍተው የሚውሉ እንደሆኑ ተናግረዋል። አገሪቱ በኢኮኖሚ ቀውስ እየተጎዳች ባለችበት ወቅት፤ ምንም የማይሰሩ ፖስታ ቤቶችን አዝለን ለመሄድ ድጎማ መመደብ ጨርሶ ተገቢ አይደለም ብለዋል - የድርጅቱ ሃላፊ።የ12 ቢ. ብር እዳ የተሸከመው የፖስታ ድርጅት በአመት ውስጥ የ14 ቢ. ዶላር ኪሳራ ይገጥመዋል ተብሎ ይጠበቃል። በሰኔት የፀደቀው ህግ፤ በኮንግረስም ተቀባይነት ቢያገኝ፤ በፕሬዚዳንቱም ቢፀድቅ እንኳ ዋጋ የለውም። የ11 ቢ. ዶላር ድጎማ፤ ብዙም አያዘልቀውም። ያው፤ እንደገና ድጎማ ለመጠየቅ ወደ ምክር ቤቶቹ ተመልሰን መምጣታችን አይቀርም ሲሉ የድርጅቱ ሃላፊ ተናግረዋል።

የድርጅቱ አሰራሮች እንዳይሻሻሉና የወጪ ቅነሳ እቅዶቹ እንዳይተገበሩ ከተደረገ፤ በአመት የድርጅቱ ኪሳራ ወደ 21 ቢ. ዶላር ሊያሻቅብ እንደሚችልም ገልፀዋል። ለመልእክት ልውውጥም ሆነ ለተለያዩ የገንዘብ ክፍያዎች የፖስታ አገልግሎትን ይጠቀሙ የነበሩ ሰዎች፣ ከአመት አመት ፊታቸውን ወደ ኢንተርኔት እያዞሩ እንደሆነ የተናገሩት የፖስታ ድርጅት ሃላፊ፤ በዚህም ምክንያት በርካታ ፖስታ ቤቶች አላስፈላጊና ምንም የማይሰሩ ሆነዋል ብለዋል።

 

 

 

 

 

 

Read 3509 times Last modified on Saturday, 28 April 2012 15:02