Saturday, 28 April 2012 14:48

ባየር ሙኒክና ቼልሲ የኤልክላሲኮ ግልባጭ አላቸው

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

57ኛው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ከ15 ቀናት በኋላ ባየር ሙኒክና ቼልሲን የሚያፋጥጥ ሆነ፡፡ ዓለም በጉጉት የጠበቀው የኤልክላሲኮ ፍፃሜ በ2ቱ ክለቦች ከሽፏል፡፡ ሻምፒዮንስ ሊግ በአዲስ መዋቅር ከተጀመረ ወዲህ በሜዳው ለፍፃሜ ጨዋታ የቀረበ ብቸኛው ክለብ ባየር ሙኒክ ሲሆን ቼልሲ በበኩሉ በታሪክ ለመጀመርያ ግዜ በውድድሩ ሻምፒዮን ለመሆን የሻምፒዮንስ ሊጉን ዋንጫ አይታ ለማታውቀው ለንደን ከተማ የምስራች ለማምጣት ይቀርባል፡፡  ከሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ጋር በሽልማትና በገበያ ድርሻ ሻምፒዮን ክለብ እስከ 80 ሚሊዮን ዶላር ያገኛል፡፡ 2ኛው ደግሞ 70 ሚሊዮን ዶላር ድረስ ይሰበሰባል፡፡ ለግማሽ ፍፃሜ የሚደርሱ ክለቦች ደግሞ ድርሻቸው እስከ 60 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ለሩብ ፍፃሜ የደረሱ ክለቦች ገቢያቸው በአማካይ ከ25 ሚሊዮን ዶላር በላይ ነው፡፡

ባየር ሙኒክ ለአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የዋንጫ ጨዋታ ሲበቃ ባለፈው ሶስት የውድድር ዘመን ለሁለተኛ ግዜ ሲሆን ዘንድሮ ፍፃሜ ጨዋታው በሜዳው አሊያንዝ አሬና መደረጉ በታሪኩ 5ኛውን የአውሮፓ የሻምፒዮናነት ክብር ለመጎናፀፍ ያለውን ተስፋ ያጠናክርለታል፡፡

ባየር ሙኒክና ቼልሲ በ2004/05 በሻምፒዮንስ ሊግ ሩብ ፍፃሜ ተገናኝተው ነበር፡፡ በዚህ ወቅት በመጀመርያው ጨዋታ ቼልሲ 4ለ2 በስታምፎርድ ብሪጅ አሸነፈ፡፡ በመልስ ጨዋታው ደግሞ አሊያንዝ አሬና ላይ ባየር ሙኒክ 3ለ2 ረታ፡፡ በድምር ውጤት ግን ቼልሲ 6ለ5 ባየርን በመርታት ለግማሽ ፍፃሜ ሊያልፍ ችሎ ነበር፡፡ ባየር ሙኒክ በሻምፒዮንስ ለግ የተሳትፎ ታሪክ እንግሊዝን ከወከሉ ክለቦች ጋር 35 ጊዜ ተገናኝቶ በ13 ድል አድርጎ በ12 አቻ  ወጥቶ እንዲሁም በ10 ሽንፈት አስተናግዷል፡፡  ቼልሲ ደግሞ ከጀርመን ክለቦች ጋር 13 ጊዜ ተገናኝቶ 7 ግዜ ድል አድርጎ በ2 አቻ ወጥቶና በ4 የተሸነፈበትን ታሪክ አስመዝግቧል፡፡ ቼልሲ ወደ ጀርመን ተጉዞ ካደረጋቸው 6 ጨዋታዎች አንድ ግዜ ብቻ ስቱትጋርትን 1ለ0 አሸንፏል፡፡

ሁለቱም ክለቦች በዋንጫ ጨዋታው ወሳኝ የሚባሉ ተሰላፊዎቻቸውን በቢጫ ካርድ ቅጣት አያሰልፉም፡፡ በቼልሲ በኩል ቴሪ፤ ሜሪሌስ፤ራሚሬስና ኢቫኖቪች እንዲሁም በባየር ሙኒክ በኩል አላባ፤ ባድስታበርና ጉስታቮ ፍፃሜው ያመልጣቸዋል፡፡

ባየር ሙኒክ በውድድር ታሪኩ ለ9ኛ ግዜ ለዋንጫ ሲቀርብ ቼልሲ ገና 2ኛው የዋንጫ ጨዋታ ነው፡፡ አራት ግዜ የአውሮፓ ሻምፒዮን የሆነው ባየር ሙኒክ በውድድሩ ታሪክ በ5ኛ ደረጃ የተመዘገበ ውጤት ያለው ሲሆን ቼልሲ ግን ገና ቶፕ 20 ውስጥ አልገባም፡፡

በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ታሪክ የፍፃሜውን ጨዋታ በሜዳው ወይም በአገሩ ያሸነፈ ክለብ ሁለቴ አጋጥሟል፡፡ በ1957 ማድሪድ በበርናባኦ በ1965 ደግሞ ኢንተርሚላን በሳንሲሮ ዋንጫውን በደጋፊያቸው ፊት አስቀርተዋል፡፡ ባየር ሙኒክ ውድድሩ በአዲስ መዋቅር ከተጀመረ ወዲህ በሜዳው ዋንጫውን በማስቀረት ታሪክ ሊሰራም ይችላል፡፡ከወር በኋላ የዋንጫ ጨዋታው የሚስተናገድበት የሙኒክ ከተማ በውድደሩ ታሪክ ያልተጠበቁ ውጤቶች ተከስተውለል፡፡ በተለይ ሁለት የጣሊያን ሃያል ክለቦች በሙኒክ የዋንጫ ድል ሳይሆንላቸው ቀርቷል፡፡

የመጨረሻው ፍፃሜ ከ15 ዓመት በፊት ቦርስያ ዶርትመንድ ሻምፒዮናነቱን ሊያስጠብቅ የቀረበውን ጁቬንትስ 3ለ1 የረታበት ነው

ከ18 ዓመት በፊት ደግሞ ኦሎምፒክ ማርሴይ 1ለ0 ኤሲሚላንን አሸንፏል፡፡

የእንግሊዙ ኖቲንግሃም ፎረስት ደግሞ የስዊድኑን ክለብ ማላሞ ኤፍኤፍ 1ለ0 በመርታት ዋንጫ አንስቶበታል፡፡ የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ በውድድሩ የ57 ዓመታት ታሪክ ለስድስተኛ ጊዜ ዲዛይኑ የተሰራለት ነው፡፡73.5 ሴሜ የሚረዝመውና 8.5 ኪግ የሚመዝነው የአሁኑ ዋንጫ ከ6 ዓመት በፊት ተሰርቶ መሸለም የጀመረ ነው፡፡ ዋንጫዎቹ ተደጋግመው ሊሰሩ የቻሉት ከ50 ዓመት በፊት የውድድሩን በተከታታይ 3 ዓመታት አከታትሎ የወሰደና 5 ዋንጫ የወሰደ ክለብ እንዲያስቀር በመፈቀዱ ነው፡፡

ስለሆነም 9 ያሸነፈው ሪያል ማድሪድ፤ 7 ያሸነፈው ኤሲ ሚላን፤ በድሮው ሻምፒዮንስ ለገ ከወሰዷቸው የአውሮፓ ሻምፒዮንነት ክብሮች በሶስት የውድድር ዘመናት ክብራቸውን ያስጠበቁት አያክስ እና ባየር ሙኒክ ኦርጅናል ዋንጫውን ለዘላለም ወስደዋል፡፡

ባየር ሙኒክና ቼልሲ በአጨዋወታቸው ይመሳሰላሉ፡፡ ሁለቱም ክለቦች የትኛውን የዓለም ክለብ መቋቋም በሚችል የተከላካይ መስመር የተገነቡ ናቸው፡፡ በማጥቃት ጨዋታቸው በመልሶ ማጥቃት የሚጫወቱት ሁለቱ ክለቦች በፊት መስመራቸው ሰፋ አድርጎ የሚጫወት ግዙፍ ሰውነት ያለው አጥቂ በማሰለፍ ይለያሉ፡፡ በሁለቱም ክለቦች ያለው ልምድ ቀላ አይባልም፡፡ ሽዋንስታይገር፣ሪበሪ፣ሩበንና ፊሊፕ ላሃም ከባየርንሙኒክ፤ ድሮግባ፣ ቴሪ፣ ቼክ፣ ኢስዬንና አሽሊ ኮል ከቼልሲ በሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ባለፈው 10 ዓመት ከታዩ ተጨዋቾች ምርጦቹ ናቸው፡፡ የሚገርመው ሁሉም ለዋንጫው ድል ያበቁ መሆናቸው ነው፡፡ ሌላው የክለቦቹ ጥንካሬ ዛሬ በዓለም እግር ኳስ ምርጥ የተባሉትን ሁለት በረኞች መያዛቸው ነው ፒተር ቼክና ማኑኤል ኒውዬርን፡፡

 

 

 

 

 

Read 3064 times Last modified on Saturday, 28 April 2012 14:51