Saturday, 21 April 2018 13:49

ፀፀትና ህይወት!

Written by  አብይ ተስፋዬ አሳልፍ - (አተአ)
Rate this item
(7 votes)

ከከዋክብት ውስጥና ውጪ … የምትኖር ከዳመናዎች ሁሉ በላይ
ካንተ ከትንሷ እሳቤዬ ፈጣሪ  …ከአእምሮዬ ገንቢ መዳፍ ላይ
ተቀምጩ …
እንባዬን በከንፈሬ መጥጬ፣
…እንዲህ እላለሁ …
የሰማያትና የህዋዎች ሁሉ ገዢ … የጸሃይና የጨረቃ ባለቤት
አታይም ወይ … ምን እንዳለ ከኔ ቤት!?
ካየህስ ዘንዳ … ይህን ድብርት ከውስጤ ነቅለህ ጣልና
… ተመስገን ልበልህ ከእንደገና !
( አይመስልህም!? በልመና! )
*   *   *
ከራስጌ በኩል ረዘም አድርጌ ያንጠለጠልኩትን የመብራት ማብሪያ ማጥፊያ ቀጭ ቀጭ ቀጭ ቀጭ …. እያደረግሁ አይኖቼን ኮርኒስ ላይ ተክዬ እሁዴን ማጋመሴ ቆጨኝ፤ ቁርስ የለ፣ ቡና የለ  … ለብቻ ከመተከዝና ጀርባዬን ከመላጥ ብዬ … ለመነሳት ብዙ ግዜ ሞከርኩ፡፡ አልቻልኩም፡፡ ድክም ብሎኛል!
በህይወት ኡደት የማይደገም ምንድን ነው? ብዬ ራሴን መጠየቅ ከጀመርኩ ቀኔ በድብርት ይመሻል፡፡ የህይወት ድግግምን በማሰላሰል ሰልችቻለሁ፣ ትክት (ጠብቆ ይነበብ) ብሎኛልና። ህልቆ መሳፍርት ሀሳቦች በአንጎሌ ውስጥ እንደ ወጀብ ይነሱብኛል፣ ምንም መዳኛ የለኝም፡፡ መጠጥና ሱሳዊ ማደንዘዣ (!) አያስጥለኝም፡፡ ሀሳቤ ቀድሞ ያሰክረኛል፡፡
እናም ከዚህ ሁሉ ለመላቀቅ ብዬ ድንገት ከተጋደምኩበት ፍራሽ ላይ ዘልዬ ተነሳሁና ቱታ ነገር ደረብ አድርጌ ወጣሁ፡፡ በእግሬ እያቆራረጥኩ መሃል ፒያሳ ራሴን አገኘሁት፡፡ ግማሹን ሰው በትከሻ፣ ግማሹን ሰው በጎኔ እየገጨሁ ብዙ ይቅርታ እየጠየቅሁ፣ ብዙ ስድቦችን በድንዛዜ እያዳመጥኩ፣ በሰው መሃል ሽቅብ ቁልቁል ደጋግሜ እመላለሳለሁ፡፡ እንዲህ ሳደርግ ቀለል ይለኛል፡፡ ብዙ ግዜ እንዲህ ከዋልኩ ድክም ብሎኝ አካሌ ሲዝል፣ ወደ ቤቴ ተመልሼ እተኛለሁ፡፡
ለሁለተኛ ግዜ የምኒልክን ሐውልት ዞሬ ተመልሼ፣ ወደ ሲኒማ መታጠፊያ ስደርስ፣ ወደል መዳፍ ትከሻዬ ላይ ጨመደደኝ፡፡ ቀና ስል ለአመታት ያላየሁት ምናሴ ነበር! መጀመሪያ ተደነጋገርኩ (ነው ወይስ አይደለም! … ትልቅ መስሏልና!)፡፡ ተቃቀፍን፣ የናፍቆት ሰላምታ ተሰጣጥተን መጓዝ ጀመርን፡፡ ወደ ጣይቱ መንገድ ቁልቁል አዝግመን፣ ከአንዲቱ ቡና መሸጫ ቤት ተቀመጥን፡፡ መቀመጫን በሚያቅፉ ልስልስ ሶስት እግር መቀመጫዎች ላይ ተቀምጠን፣ ጥቂት ዝም ዝም ተባባልን፡፡ እሱ እንኳ ድሮም ዝምተኛ ነው…!
*   *   *
ክቡን መቀመጫ እያየሁ እንዲህ አስባለሁ፡- ሁሉም ይደገማል! ሁሉም የክቡን ጠርዝ እየዞረ ይጋጠማል! መነሻውና መድረሻው ይለያይ እንጂ ክብ የማይሰራ ነገር የለም፡፡ መጨረሻ ይደርስና ይጀምራል። ይኸው ምናሴ እንኳ ከጠፋበት መጣ፣ የጠፋ የተረሳ ይመጣል ደግሞም ይጠፋል። ከተያየን ቢያንስ አምስት ስድስት አመት ያልፋል፡፡ እነሆ ወጣቱ ልጅ፤ በጥቁር ዞማ ፀጉር የምናደንቀው ምናሴ፣ ነጭ ክር የተሸከመ ጀብሎ መስሎ መጣ፡፡ (… አንዷን የኑረት ክብ ገጠማት! ከልጅነት ተነስቶ ወደ ሙሉነት አዘገመ (ወደ ሙሉ አቀረባት!)፡፡ የተወለዱ አድገው ያረጃሉና፣ ያረጁም ደግሞ በልጆች ወደ ልጅነት ይመለሳሉና፣ የተወለዱ ደግሞ …  ስል አስባለሁ …)
‹‹… አልዓዛር … ውዴ! …›› ትከሻዬን በትልቅ መዳፉ ደጋግሞ ይተመትማል፡፡
‹‹ልጅ ምናሴ!… ምነው በሰላም! … በጣም ጠፋህ፣ ዘመናት አለፉ ከተያየን አይደል! በእርግጠኝነት አገር ውስጥ አልነበርክም!›› አፌ እንዳመጣልኝ አወራሁ፡፡ በሚበረብሩ አይኖቹ በዝምታ አስተዋለኝ፤ ቀስ ብሎ መዳፉን ከትከሻዬ እያወረደ፡፡
‹‹… አገባህ!? … ወለድክ? … መቼም ህጻን ልጅ በጣም ትወዳለህ አውቃለሁ--›› አለኝ፤ ትልልቅና ቀያይ አይኖቹ ላይ የእንባ መጋረጃ እየታየ፡፡ ይህን ጥያቄ የሚጠይቅ ሰው ሲደብረኝ አይጣል። ማግባትና መውለድ እንደ ሞባይል ካርድ ፋቅ ፋቅ አድርጎ መሙላት ነገር ነው እንዴ! ኸረ እሱም እንኳ የሚከብድበት ወቅት አለ፡፡
‹‹… አላገባሁም … አልወለድኩም … ይኸውልህ በዚህ ቀውጢ ከተማ መንነናል … አንተስ!?…›› ስል አከልኩበት፡፡
አፍንጫውን በነጭ ሱቲ መሃረብ ከጠራረገ በኋላ እንዲህ አለ፡-
‹‹… እንግዲያውስ እኔም ምንም አልቀረብኝማ!››
‹‹...እንዴት?! … ›› ፈገግ ለማለት እየሞከርኩ፡፡
‹‹…አልዓዛር ታስሬ በሰባት አመቴ መፈታቴ ነው … በ 24 ዓመቴ ገብቼ በሰላሳዎቹ መጀመሪያ የሃምሳ አመት ሰው መስዬ ወጣሁልህ…››
‹‹…አትቀልድ ባክህ…›› የያዝኩትን ስኒ ቀስ ብዬ እያስቀመጥኩ፡፡ ምናሴን የማውቀው የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳለን ነበር ፡፡ ከዚያ ከወጣንና ስራ ከጀመርን  በኋላ ድንገት ተሰወረ፡፡
‹‹…የወጣትነት ሰባት ዓመታቴን ግድግዳና ሰማይ እያየሁ አሳለፍኩ፡፡ አሁን ከወጣሁ አምስት ወር አለፈኝ፡፡ ይገርምሃል መንገደኛውን ፣ ሰውን ፣ አየሩን፣ መኪናውን፣ ህንፃውን፣ ግርግሩን  ….  አይቼ መጥገብ አቃተኝ፡፡ እናም ወደፊት ለመራመድ -- ሞመንተም ለማግኘት ከበደኝ፡፡ እስካሁን ድረስ እዚያው ከእስር የወጣሁ ዕለት የነበርኩበት የደስታ ስካር ላይ ነኝ!…››
‹‹…እንዴ! … ቆይ ቆይ … ምን አጥፍተህ፣ ምን ሰርተህ ነው? ሙስና ይሆን!?›› ለመቀለድ እየሞከርኩ፡፡ አላመንኩትም! ወደ ማዘጋጃ ገብቶ መሬት ሸጦ ይሆናል፣ ወይ ደሞ መንግስት ንብረት ግዢ ገብቶ ፈትፍቶ፣ ወይ ደሞ ጉምሩክ ገብቶ መንትፎ፤ ወይ ደግሞ ገቢዎች ገብቶ ተሞዳሙዶ፣ ወይ ደግሞ አየር መንገድ ገብቶ ዕቃዎችን አሳልጦ፣ … መላምት በጭንቅላቴ ውስጥ እንደ ጉድ ይተራመሳል፣ እንደ ተነገለ ጥቁር አፈር ይፈልሳል፡፡
‹‹…አልዓዛር፤ ድሮ በአስራዎቹ መጀመሪያ እድሜዬ፣ ከአገር ቤት ጠፍቼ ስወጣ ነፍስ አጥፍቼ ነበር!…›› ሁለቱን መንጋጋዎቹን በደንብ ገጥሞ አንቀራጨጫቸው፡፡
‹‹…ምን!…›› ድንጋጤዬን እንኳን ለመሸሸግ አቃተኝ (በሃሳቤ … ይህ ልጅ ሰው ገድሎ ነበርን! ማለቴ የነፍሰ ገዳይ ፊት ግን  የለውም … ስል አስባለሁ፡፡)
‹‹...ሳላስበውም ቢሆንም አሰቃቂ ነገር ነበር ያደረኩት፡፡ ልጅ ነበርኩ፡፡ በቁጣ ተሞልቼ ነበር። እና ተሳሳትኩ፡፡ የማይመለስ ነገር፣ ከአገሬም፣ ከዘመዶቼም ለዘልዓለም የሚያለያየኝ ነገር ነበር የሰራሁት…›› በሱቲ ጨርቋ በድጋሚ ፊቱን ሞዠቀ፡፡
 በማመን እና ባለማመን ውስጥ ሆኜ፣ አፌን ከፍቼ አዳምጣለሁ፡፡ ይህ ልጅ የሚያወራው እውነት ከሆነ ፀፀት አኝኮታል ማለት ነው፡፡ ትናንትናውንም ነገውንም ነጥቆታል፡፡ ይኸው ፊቱ የሌላ ሰው መስሏል፣ ፀጉሩ ተለውጧል፣ አስተሳሰቡ ድሮም አሪፍ ነበር … ሩህሩህና ደግ ነበር፣ እና እሱም የለ ይሆን! (ደግሞ ወዲህ  … የሆነ ፊልም ላይ ‹‹ እልም ያሉ ነፍሰ ገዳዮች ሩህሩህና ደግ ይመስላሉ!›› የሚል ሰምቼ ነበር ፡፡ እናም እሱን አሰላስላለሁ፡፡)
‹‹…ያደኩት ገጠር ነበር፡፡ አባት አልነበረኝም (ሞቶ!)  … ክፉ እንጀራ አባት ነበረኝ፡፡ እኔንና እህቴን የሚያሰቃይ፣ እናቴን የሚደበድብ። በዚያ ድርጊቱ በልጅነቴ ከፍተኛ ቁጣ ውስጥ ገባሁ። በቀል እያሰላሰልኩ አደኩ፡፡ በአንድ አመት የምትበልጠኝ ታላቅ እህቴ፣ በ15 ዓመቷ ዲቃላ ስትወልድ አገር ጉድ ብሎ ነበር፡፡ እናቴ በድብደባም ይሁን በትልልቅ ሰዎች ምክር ከማን እንደወለደች እንድትነግራት ብትለፋም አልሆነላትም። እኔ ግን አውቅ ነበር። ሰውየው እንደሚደፍራት በአይኖቼ አይቼ ነበር፡፡ (እንጀራ አባቴ!)…›› የእጆቹን መዳፍ ጨብጦ ከአይኖቹ የሚረግፉትን እንባዎች ይጠራርጋል። ውስጤ ተናወጠ። አለም ለሁላችን የተለያየ ብፌ ነው የምታቀርበው፤ በቀረበው ነገር የሚደሰትም የሚያዝንም አለ፡፡
 በአካባቢያችን ያሉ ሰዎች እንዳተኮሩብን ገብቶኛል፡፡ ምን ማድረግ ይቻላል! ፀጥ ብዬ ማዳመጤን ቀጠልኩ፡፡
‹‹…አንድ ዕለት እህቴ በወለደች በጥቂት ወራት ውስጥ የሚሆነውን ሁሉ እያየሁ መታገስ አቃተኝ። ሰውየውን በጉልበት መጋፈጥ አልችልም ነበር፤ ምክንያቱም በምግብ የተጎዳሁ ታዳጊ ነበርኩ፡፡ እንኳን ከሰው ልታገል ይቅርና የራሴ እግሮች ይከብዱኝ ነበር፡፡ እናም የመጨረሻዬ በነበረችው ዕለት፣ እኔ ክትምህርት ቤት ስመለስ አራስ የነበረችው እህቴን ሲያሰቃያት አገኘሁት። አበድኩ፡፡ አለቀስኩ፡፡ ወደ ጓሮ ሄጄ የግድያ እቅድ አውጥቼና አምሽቼ ስገባ፣ ሰውየው በዱላ ተቀበለኝ። ስራ ትተህ የት ጠፍተህ ነው ያመሸኸው ብሎ እንክት አድርጎ ቀጣኝ (እልሁን ነው የሚወጣብኝ … ያው እንዳልናገር ማስፈራሪያም ነው!)፡፡
በቃ የዚያን ዕለት ወሰንኩ፡፡ መጀመሪያ ፈርቼ ነበር ፤ ከድብደባው በኋላ ጨከንኩ፡፡ በስም ብቻ ወደማውቀው አዲስ አበባ ለመጥፋት አቀድኩ። ከጠፋሁ ደግሞ እሱን ገላግያቸው ብጠፋ ብዬ አሰብኩ…››
‹‹… የአይጥ መርዝ ከሚቀመጥበት ቦታ ፈልጌ አመጣሁና አዘጋጀሁ፡፡ ከዚያም በጣም በማለዳ ተነሳሁ፡፡ እናቴ ለእርሱ ብቻ ወጥ እየሰራች የምታንተከትክባት ትንሽዬ ድስት ከምድጃው ላይ ተጥዳለች፡፡ (መቼም እኛ ምናልባት በዓል ካልሆነ በቀር ከዚያች ድስት ጥራጊ እንኳ አንቀምስም ነበርና እርሱ ብቻ እንደሚበላት እርግጠኛ ነበርኩ!)፤ እናቴ በጧት ተነስታ ላም እያለበች እንደሆነ አውቃለሁ። ተነሳሁ፤ ቀስ ብዬ ምድጃው ላይ ያለችውን ድስት ስከፍታት የቅቤ ሽታ አወደኝ፡፡
የያዝኩትን መርዝ በሙሉ ድስቱ ውስጥ ከተትኩና አማስዬ ከድኜው ሔድኩ፡፡ ማለዳው ገና አልፈገገም፤ ቀስ ብዬ ከደሳሳ ጎጇችን ላልመለስ ወጣሁ (ለነገሩ እናቴ ብታየኝም ቤተክርስቲያን የምሔድ ነው የምመስላት። በወቅቱ ዲቁና እማር ነበርና በበዓላት ቀን በማለዳ ቤተክርስትያን እየሔድኩ አረፍዳለሁ!)፡፡ እናም በዚያች ማለዳ ጠፋሁ፡፡ ይገርምሃል አዲስ አበባ ለመድረስ ወራት ነበር የፈጀብኝ፡፡››
ለካ ለዚህ ነበር ሰው ቤት ተቀጥሮ እየሰራ የተማረው፡፡ ጋዜጣ አዟሪው፣ አትክልተኛውና  ባሬስታው … ምናሴ! (ስል አስባለሁ)
‹‹…ታዲያ እንዴት ተያዝክ!›› … ገረመኝ። ምንም አልተሰማኝም ነበር፡፡ አላዘንኩበትም። አልተደሰትኩበትም፡፡ ምንም የሆነ ስሜት ነበር የተሰማኝ፡፡ ብቻ ይህ ልጅ ነፍሰ ገዳይ የሆነው፣ በእድል እንጂ በገድል እንዳልሆነ በልቦናዬ እረዳለሁ፡፡ (…እኔ ብሆን ምን አደርግ ነበር! ብዬም አስባለሁ!)
*   *   *
ረዘም ያለ ትንፋሽ ከወሰደ በኋላ … ‹‹…እናቴ በጣም ስትናፍቀኝ ከተመረቅሁና ስራ ከጀመርኩ በኋላ ወደ ትውልድ መንደሬ ተመለስኩ (ጥቂት ብር ቋጥሬ፣ በአካልም ተለውጬ ነበር።) … እንግዲህ ሰውየው ከሞተ ጥሩ፣ ካልሞተም የመጣው ይምጣ ብዬ አስቤ ነበር፡፡  ያጋጠመኝ ነገር ግን ጥሩ አልነበረም፡፡ ሰው እንዳያገኘኝ ተጠንቅቄ ወደ መንደራችን ስቃረብ የቤታችን አካባቢ ጭር ብሏል፡፡ የቤታችንም ፍርስራሽ ዳዋ ለብሶ ነበር፡፡ ሰው የለበትም፡፡  
“ደንግጬ ትንሽ አሰብኩና … ጥቂት መንገድ ራቅ ብሎ ወዳለው የእናቴ አክስት ቤት አመራሁ። እናቴን እንደ ልጅ ያሳደገች የእናቷ ታላቅ እህት ነች፡፡ አርጅታ ማየት አትችልም ነበር፡፡ ቤቷ በር ደፍ ላይ ተቀምጣ፣ የተቀዳደደና የተጣጣፈ ጥቁር ልብስ ለብሳለች፤ ትንሽዬ ነጭ ጭራ እያወዛወዘች ዝንቦቿን ትዋጋለች፡፡ ከኋላዋ አንድ አመድ የመሰለ ጎረምሳ ልጅ ጥብቆውን እየጎተተ ብቅ ጥልቅ ይላል (ማስረሻ! …ብላ ስትጠራው ሰማሁ!)። እየተጠነቀቅሁ ተጠጋሁና ከሰላምታ በኋላ ጠየቅኋት (የቤቱ ባለቤቶች የት ገቡ ብዬ) እናም  ስለ ቤተሰቤ ሁሉንም ነገር ነገረችኝ፡፡ (…ለቅሶና ሳግ … !)
“ከቤት የጠፋሁ ዕለት በዓል ነበር (ግንቦት ልደታ!)፡፡ … እናም ቁርስ ላይ ሁሉም ቤተሰብ አንድ ማዕድ ቀርበው ነበር የተመገቡት፡፡ ሁሉም አንድ ላይ ነበሩ!…›› ረዘም ያለ ለቅሶ። እንደ ጎርፍ ያለ እንባ፣ እንደ መብረቅ ፊት ላይ ብልጭ ብሎ የሚታይ እናም በየሰከንዱ ታትሞ ፊት ላይ የሚቀር ፀፀት፣ እንደ ተራራ የከበደ የማይገለፅ ነገር …
‹ታዲያ?!›  … የምትል ቃል ከምላሴ ላይ ተንጠልጥላ ለመስፈንጠር ትፍጨረጨር ጀመር፡፡ ነከስኳት! (… ማን ተረፈ?… ማንስ ሞተ? ለማለት። ደሞ እንዴት ተያዝክ? ለማለት፡፡ ደግሞ እንዴት? … እያልኩ ለመቀጠል፡፡ አቃተኝ… አልቻልኩም!)
‹‹ይገርምሃል ድንገት … አንተ ድምጥህ የማውቀው ሰው ድምጥ ይመስላል፡፡ …. ምናሴ ነህ’ንዴ! … ስትል አክስቴ አስደነገጠችኝ፡፡ ዝም አልኩ፡፡ ደጋገመች፡፡ ኸረ አይደለሁም አልኩ፡፡ ጥቂት እንደቆየሁ ደህና ይዋሉ ብዬ ጉዞ ስጀምር.. ኡኡኡ … እያለች መጮህ ጀመረች›› … ጥቂት ፈገግታ፡፡
‹‹…መጀመሪያ መሮጥ ጀመርኩ፡፡ መሮጥና ከአካባቢው መጥፋት አሰብኩ፡፡ … ነገር ግን ድንገት ቆምኩና ነገሩን አሰብኩበት፡፡ እናም በቀስታ ተመለስኩ። ከዚህ ቦታ ሮጬ ማምለጥ እንደምችል ቢገባኝም ዝንት ዓለም እየሮጥኩና እየሸሸሁ ልኖረው የማልችለው ህሊና አለኝ አይደለምን! እንዲያ ነበር የተያዝኩት … ተመለስኩና ቁጭ አልኩ፡፡ የመንደሩ ሰው ሁሉ ተሰብስቦ ያስተውለኝ ጀመር፡፡››
ልቤ ጥልጥል አለች፡፡ ‹‹...ሁሉም ሞቱ ወይስ?…›› ብዬ …. መጠየቅ ፈለግሁ፡፡ ግና ድጋሚ ምላሴን ነከስኳት፡፡ ይቅር! ... (የታባቴ ምን ሊሰራልኝ! እኛ ከዳር የምንሰማ ሰዎች፣ በሰው ወንጀልና በሰው ጸጸት ራሳችንን የምናነሳና የምናነፃ ነን! )
አውቃለሁ፡፡ በዓለም ያለ ሃብትና ንብረት በሙሉ ቢሰበሰብ ትናንትናን ገዝቶ ሊያስመልስልን አይቻለውም፤ ከሰከንድ በፊትም ሆነ ትናንት የተናገርነውን መልሰን ልንውጠው አንችልም። በቃ! አይመለስም! አይደል! … አለምላሚም ሆነ ሰባሪ ቃላት ከአጥንት አልባው ምላሴ ላይ ተወናጭፎ ከተነሳ በኋላ ላስቀረውም አልችልም፡፡
በጊዜያዊ እብደት ወይም በልጓም አልባ ብስጭት ወይም በልጅነት አዕምሮ ተነሳስተህ የምትፈጽመው አንድ ድርጊትም ስህተት ከሆነ፣ ላልኖርክበት ነገ ፀፀት እንደሚያቀብልህ እርግጠኛ መሆን ይቻላል፡፡
ስለ ነገ መገመትም ይቻላል፡፡
‹‹… በደመና ተከልላም ይሁን ጥርት ባለ ሰማይ ላይ፣ ነገ ማለዳ በእርግጠኛነት ፀሃይ ትወጣለች። እኔ ግን ያው እንደምታየኝ … የቤተሰብ እዳ ተሸክሜ እዞራለሁ፡፡ አሁን ወደ ራሴ ለመመለስ ጥረት ላይ ነኝ፤ ተራራ የሚያክል ነገር ግን ልቤ ላይ ተጭኖኛል። ፀፀትና ብስጭት አስረጀኝ፤ ንዴትና ሃዘን ፀጉሬን ነጭ አደረገው፡፡ ከዚህ ሁሉ በኋላም ማንም የእኔ የምለው ሰው እንደሌለኝ ሳስብ ይቆጨኛል፡፡ ዘመድም ሆነ ጓደኛ ማግኘት አልቻልኩም፡፡›› … ከዚህ በኋላ ያለውን መግለጽ ከባድ ነበር፡፡
ብቻ አመሻሽ ላይ እቤቴ ተመልሼ ከፍራሼ ላይ ስጋደም፣ እንዲህ የሚል ፀሎት ማድረጌን ልነግራችሁ ይገባል! …
… አንተ በሩቅ ሰማይ ያለህ፣ እያለህ እንደሌለህ የሆንክ፤ አንተ በልጆች ህሊና፣ በታዳጊዎች ልቦና የተፃፍክ፣ በጎረምሶች ውበት፣ በወላጆች የልጆች ፍቅርና በአረጋውያን ብልሃት ውስጥ የምትታይ፡፡ የማትገለፅ፣ የማትገመት፣ የማትነገርና የማትተረጎም፣ የሰማያትና የህዋዎች ሁሉ ንጉስ ሆይ … ነገዬን በእርግጠኝነት ስለማላውቃት አመሰግንሃለሁ፡፡ ለነገ የሚያድር ግፍና ተንኮል፣ ስህተትና ክፋት ስላልሰራሁ አልመፃደቅም። ነገር ግን በደመና የተከለለችም ይሁን በነፃው ህዋ ላይ የምትንሳፈፍ፣ ፀሀይ ነገ እንደምትወጣ እርግጠኛ ነኝ፤ እናም እሞቃት ዘንድ ፍቀድልኝ፡፡ የሰራሁትን ስህተት እፀፀትበትና ይቅርታ እጠይቅበት ዘንድ አንዲት የይቅርታ ቀን ጨምርልኝ፡፡  አሜን! ( ፀሃይ ማታ ጠልቃ ጠዋት ትወጣ አይደለምን! … ክቧን መግጠሟ እርግጥ ነውና፡፡)
*   *   *
አሁን ወደ ኮርኒሴ ሳንጋጥጥ የማየው የተቀዳደ ጨርቅ አይደለም፡፡ ፀፀት አልባ የድሃ ነገን፣ እንዲሁም ጭጋግ አልባ ፀሃይና ጨረቃን ብቻ ነው!
ታዲያ እላለሁ፣ በሃሳብ ዘባተሎዬን ሳባትል ቆይቼ ድንገት እባንንና …. ተመስገን እላለሁ ከእንደገና !

Read 3422 times