Saturday, 21 April 2018 11:17

‹‹…ሕጻናትን ከጎጂ ኬሚካል ለመከላከል…››

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

 ሕጻናት ተገቢውን የጤናና የእድገት ሁኔታ እንዲያገኙ በተለያዩ መንገዶች ጥንቃቄ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡ በተለይም ሕጻናቱ በቅርብ ከሚያገኙዋቸው መጫወቻዎቻቸውና መመገቢያዎቻቸው የሚያገኙዋቸው ጎጂ ኬሚካሎች የተሟላ ጤና እንዳይኖራቸው ስለሚያደርግ ጥንቃቄን ይሻል፡፡
ለህጻናት መጨወቻ እንዲሆኑ በተለይም ከፕላስቲክ  የሚሰሩ አሻንጉሊቶች ለረጅም ጊዜ በጥቅም ላይ መዋላቸው ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው እንደሚያመዝን ጥናቶች ይፋ አድርገዋል፡፡ ጥናቱን ያደረገው በእንግሊዝ የሚገኝ Plymouth University የተባለ ሲሆን በ Environmental Science and Technology journal ለንባብ ይፋ አድርጎ ታል፡፡የብሪትሽ ሳይንቲስቶች ባደረጉት ምርምር ወደ 197/አንድ መቶ ዘጠና ሰባት  የሚሆኑ አዲስ ያልሆኑ (ሳልቫጅ) አሻንጉሊቶች ከመኖሪያ ቤቶች፤ ከሕጻናት ማቆያዎች እንዲሁም ከእርዳታ ድርጅቶች ተሰብስበው ፍተሻ ተደርጎባቸው ነበር፡፡ ጥናት አድራጊዎቹ እንዳረጋገጡት ከሆነ አሻንጉሊቶቹ ከአንድ ጊዜ ጥቅም በሁዋላ ሲያረጁ ወይንም ሳልቫጅ ሲሆኑ ሊወገዱ እንደሚገባ የሚያሳዩ የተለያዩ መርዛማ ኬሚካሎችን እንደያዙ ተጠቁሞአል። መርዛማ ከተባሉት ኬሚካ ሎችም (arsenic, barium, cadmium, chromium, lead, antimony and selenium) የመሳሰሉት ናቸው፡፡ cadmium, chromium, የተባሉት በተለይም ወደሰውነት ውስጥ ከገቡ ምን ያህል አደገኞች እንደሆኑና በተለይም ቀለማቸው ቀይ እና ቢጫ እንዲሁም እንደ አልማዝ ወይም እንቁ መሳይ ነጠብጣቦች ያሉዋቸው እንዲሁም በእንስሳ መልክ የተሰሩ አሻንጉሊቶች አገልግሎታቸው ሲያበቃ መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል ጎጂ መሆኑን ያሳያል የዳሰሳ ጥናቱ፡፡ አብዛኞቹ አሻንጉሊቶች ከእነዚህ ከተጠቀሱት መርዛማ ኬሚካሎች ቢያንስ አንዱ እንዳለባቸው ታውቆአል፡፡ በተለይም በእድሜያቸው ከፍ ያሉ ሕጻናት አሻንጉሊቶቹንም ይሁን ሌሎች ነገሮች ወደአፋቸው ማድረግ ስለሚቀናቸው ለጉዳት ሊዳረጉ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ኬሚካሎች በጤናና እደገት ላይ ችግር የሚፈጥሩ በመሆ ናቸው ያረጁ አሻንጉሊቶች ወደ ሕጻናቱ እጅ እንዳይገቡ ልዩ ጥንቃቄና ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል እንደ ጥናት አቅራቢዎቹ ምስክርነት፡፡
ጥናቱ በሚደረግበት ወቅት ወደ 200/ የሚሆኑ ከፕላስቲክ የተሰሩ አሻንጉሊቶች ሆነው በሁለተኛ ደረጃ የሚታዩ ወይንም ሳልቫጅ የሆኑትን ከተለያዩ ቦታዎች ማለትም ከሱቆች፤ ከትምህርት ቤቶች፤ ከህጻናት ማቆያዎች፤ ከመኖሪያ ቤቶች ተሰብስበው በኤክስሬይ ማለትም በራጅ መሳሪያ ወይንም መብራት ማለትም ወደ 9/ የሚሆኑት ጎጂ ኬሚካሎች መጠንና አይነት ለመለየት በሚያስችል ሁኔታ ምርምር ተደርጎባቸዋል፡፡በዚህም ውጤት ምናልባትም አሻን ጉሊቶቹ ቢታኘኩ ወይንም ወደ ሆድ ቢዋጡ የሕጻናቱን ሆድ ምን ያህል በባክቴሪያ ይመርዛሉ የሚለውን ለማወቅም ወደ 26/የሚሆኑትን አሻንጉሊቶች በመለየት ፍተሸ አድርገዋል፡፡ የኬሚ ካሉን መጠን ለማወቅም የፕላስቲክ አሻንጉሊቶቹን ክብደትና ውፍረት በመለካት ከኤክስሬይ መሳሪያው ከሚገኘው ውጤት ጋር ማመዛዘን አንዱ መንገድ ነበር፡፡
የምርምሩም ውጤት እንደሚከተለው ነው፡፡
ለምርምር ከቀረቡት ሳልቫጅ ወይንም ያረጁ አሻንጉሊቶች መካከል 31/የሚሆኑት ቢያንስ አንዱ አይነት ጎጂ ኬሚካል ተገኝቶባቸዋል፡፡
የተቀሩት ማለትም ለረጅም ጊዜ አገልግሎት ላይ የዋሉ አሻንጉሊቶች የተለያዩ ኬሚካ ሎች ለምሳሌም ቢያንስ ሁለት አይነት መርዛማ ኬሚካሎችን የያዙ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ሳልቫጅ ወይንም ለረጅም ጊዜ ከጥቅም ላይ የዋሉ ወይንም ከአንዱ አገልግሎት ወደሌላው የሚሸጋገሩ እድሜ ጠገብ የሆኑት አሻንጉሊቶች (bromine, cadmium), (lead and antimony,)  (cadmium and selenium) (or chromium and antimony.) የተባሉት መርዛማ ኬሚካሎች እንዳለባቸው ተረጋግጦአል፡፡
ወደ 26 ሚሆኑት አሻንጎሊቶች ማለትም ሳልቫጅ በሚለው ደረጃ ከተቀመጡት 4/ የሚሆኑት የህጻናቱን ደህንነት ለመጠበቅ የማይመቹ ሆነው የተገኙ ሲሆን ይህም ከአመራረት ደረጃቸው ወይንም ለአገልግሎት ከተጠቀሙባቸው እቃዎች ጋር የተያያዘ እንደሚሆን መረጃው ይጠቁማል፡፡
ጥናት አቅራቢዎቹ እንደሚሉት የጥናቱ ውጤት እንደሚያሳየው ለሕጻናቱ ጤንነት ይበጃል የሚለውን ማለትም በየሀገራቱ የተቀመጡትን ገደቦች የአሻንጉሊት አምራቾቹም ሆን ወላጆች ወይንም መምህራን ቢያንስ ያገለገሉ አሻንጉሊቶችን ከአንዱ ወደአንዱ በመቀባበል ሊጥሱዋቸው አይገባም፡፡ የእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች፤ ሱቆች ወይንም ለሕጸናት ማቆያዎች የሚደረጉ እርዳታ ዎች ወይንም ግዢዎች፤ ሆስፒታሎች እንዲሁም ትምህርት ቤቶች ሁሉ ልብ ሊሉአቸው ይገባል፡፡
አጥኚዎቹ እንደሚመሰክሩት በተለይም በብጫ እና ቀይ ቀለም የተሰሩት አሻንጉሊቶች ሲያረጁ በከፍተኛ ሁኔታ cadmium and lead-based pigments ይገኝባቸዋል፡፡ ፈካ ባለ ከለር የተሰሩትም ቢሆኑ በጥንቃቄ ከጥቅም ላይ ሊውሉ የሚገባቸው ናቸው፡፡   
ጥናቱን ያደረጉት ባለሙያዎች እንደሰጡት ማጠቃለያ ከሆነ ፡-
አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች ወይንም የህጻናት መቆያዎች እና ወላጆችም ቢሆኑ የፕላስቲክ አሻንጉሊቶች ለረጅም ጊዜ የሚያገለግሉና የማይበላሹ እንዲሁም ሊታጠቡ የሚችሉ ናቸው ከሚል ሌላ አዲስ አሻንጉሊት ከመግዛት ይልቅ ሌሎች ልጆች የተጠቀሙባቸውን በነጻ ወይንም ረከስ ባለዋጋ ማግኘት ሊያስደስታቸው ይችላል፡፡  
ከፕላስቲክ የተሰሩ አሻንጉሊቶችን በጥቅም ላይ ማዋልን ምናልባትም መጠነኛ እና ቀላል ነው ከሚል የተለመደ አጠቃቀም በመሆን እየተለመደ የመጣ ይመስላል፡፡
ነገር ግን የእነዚህ አሻንጉሊቶች ውጤት በጥናቱ እንደተገለጸው ከሆነ ሲያረጁ መወገድ እንጂ አንዱ ልጅ ሲያድግ ለሌላው እየተላለፉ ከጥቅም ላይ መዋል የለባቸውም፡፡  
በእርግጥ ልጅዎ በአረጀ የፕላስቲክ ስሪት የሆነ አሻንጉሊት እየተጫወተ የሚገኝ ከሆነ ወዲያውኑ በማስፈራራት ሊነጥቁትም አይገባም፡፡ ምክንያቱም ለጊዜው ልጅዎ ይህንን አሻንጉሊት የማኘክ እና ምራቁንም ወደሆዱ የማስገባቱን ነገር መከታተል ስለሚያስ ፈልግ እና ምናልባትም አሻንጉሊቱ ከምርምር ደረጃ ደርሶ እንደዚህ ያለው ጎጂ ኬሚካል አለበት ስለአልተባለ ነው፡፡ በሂደት ግን እንደዚህ ያሉ አሻንጉሊቶችን ከጥቅም ማስወገድ እንደሚገባ እንዳይዘነጉ፡፡
በእርግጥ ጥናቱ የተሟላ ነው ማለት እንደማይቻል ትንተናውን የሰጡት ባለሙያ ያረጋግጣሉ፡፡
ምክንያቱም ለምርምር የተሰበሰቡት አሮጌ አሻንጉሊቶች ምን ያህል በልጆቹ እጆች ያሉትን አሻንጉሊቶች ይወክላሉ የሚለው አንዱ መመለስ ያለበት ጥያቄ ስለሆነ ነው፡፡ ሌላው ነገር የተሰበሰቡት አሻንጉሊቶች በትክክል ምን ያህል እድሜ እንዳስቆጠሩ አለመታወቁ ነው፡፡ በዚህ ምክንያትም ይኼኛው አሻንጉሊት አገልግሎት መስጠት ይችላል…ይኼኛው ግን መወገድ አለበት ለማለት ያስቸግራል፡፡
አጥኚዎቹ ለወላጆች ያስተላለፉት መልእክት የሚከተለው ነው፡፡
በተቻለ መጠን አሻንጉሊቶች መጠናቸውና ቅርጻቸው ልጆቹ ወደአፋቸው ሊያስገቡአቸው የማይችሉት ቢሆን ይመረጣል፡፡
በተቻለ መጠንም ከፕላስቲክ የተሰሩ አሻንጉሊቶች አዲስ ካልሆኑ በስተቀር ለልጆች ባይሰጡና አዲስ ቢሆኑም እንኩዋን ለምን ያህል ጊዜ መጠቀም የሚለውን ከግምት ውስጥ ማስገባቱ ሕጻናቱን ከጎጂ ኬሚካል ለመከላከል ያስችላል፡፡    

Read 1871 times