Sunday, 01 April 2018 00:00

“ሽቅብ መሳብ ቁልቁል መሳብ፤ ለአገር እድገት ሲባል”

Written by 
Rate this item
(11 votes)

  በሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን የአፄ ቴዎድሮስ ቴያትር ውስጥ ስለ አፄ ቴዎድሮስ መድፍ ስለ ሴቫስቶፖል የተነገረውና የተተወነው ታሪክ በጣም ደማቅ ነው፡፡
አፄ ቴዎድሮስ፤
“ሃያ ሺህ ጎበዝ መልምላችሁ መድፌን ሴቫስቶፖልን መቅደላ አፋፍ ድረስ አምጡልኝ” ብለው ባዘዙት መሰረት፣ መድፉ መጣላቸው፡፡
ያንን ቀጥ ያለ አቀበት፣ እጅግ ክብደት ያለውን መድፍ ይዞ መውጣት በዕውነትም ትልቅ ጉልበት የሚጠይቅ ነበር፡፡ ወደ ላይ ከወጣ በኋላ መልሶ ወደ ታች ይንሸራተታል፡፡ እንደገና ሽቅብ ይስቡታል፡፡ ደህና ወጥቶ ወጥቶ፣ መልሶ ቁልቁል ይወርዳል፡፡ ሽቅብ ይስቡታል፤ ቁልቁል ይሳባል፡፡ ለአገር አንድነት ሲሳብ፣ እስከ መጨረሻው ተደክሞበታል፡፡
በመከራ አፋፍ ድረስ ተጎትቶ መጥቶ፣ በመጨረሻ ደረሰና ተተኮሰ፡፡ ሆኖም የታሰበው ሳይሆን ያልታሰበው ተከሰተ!
እንደ ሎሬቱ አገላለፅ፤
“ሴቫስቶፖል መድፋችን የኋሊት ፈነዳ!”
ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ ቴዎድሮስ
“አየሽ አንቺ እማማ ኢትዮጵያ፣ አየሽ አንቺ እናት ዓለም ቃል የእምነት ዕዳ ነው እንጂ፤ የእናት የአባትኮ አይደለም!” ብለው ቃላቸውን የፈፀሙት!
“… እጅህን ስጥ አለኝ ፈረንጅ፣ እጅ ተይዞ ሊወሰድ … ምን እጅ አለው የእሳት ሰደድ … አያውቅም ክንዴ እንደሚያነድ!”
የሚሉት እንደ እሳት በሚንቀለቀል ወኔ ነው፡፡ ለሀገራቸው ህይወታቸውን የሰጡት ከዚህ ወዲያ ነው፡፡
“መቅደላ አፋፉ ላይ ጩኸት በረከተ
የሴቱን አናውቅም ወንድ አንድ ሰው ሞተ”
የተባለውና የተገጠመው ለዚህ ነበር፡፡
ገጣሚ መንግሥቱ ለማም በ“ባለካባና ባለዳባ” ቴያትራቸው ውስጥ “ቴዎድሮስ በህይወት ቢኖሩ ኖሮ ይሉታል” ብለው የሚያስቡትን እንዲህ ፅፈውታል፡-
“ቀማኛን መቀማት ከሌባ መስረቅ
ለማቅለል ከሆነ የድሆችን ጭንቅ
በእኔ ቤት ፅድቅ ነው አንድ ሰው ይሙት
አንድ መቶ ሺ ሰው ኪኖር በምፅዋት!”
ቀማኛን፣ ሙሰኛን መዋጋታቸው ነው፡፡ ድህነትን መፋለማቸው ነው፡፡ ለደሀ መቆማቸውን ማሳየታቸው ነው!!
*   *   *   *
የህዝብን አደራ መቀበልና ቃልን ማክበር፣ የመልካም መሪ የተቀደሰ ምግባር ነው፡፡ ራስን እስከ መስዋዕትነት ማዘጋጀትም በአርአያነት ተጠቃሽ የሆኑ ታላላቅ መሪዎች መልካም ተምሳሌት ነው፡፡ በተለይ እንደ እኛ አገር ያለች ድህነት ያቆራመዳት፣ አስተዳደር የራባት፣ ወገናዊነት ያጠጣባት፣ ዲሞክራሲ የተራቆተባት፤ ችግር ሲመጣ ብቻ ስብሰባና ግምገማ፣ ግርግርና መዋከብ የሚበዛባት፤ አገር ላይ ሹም መሆን አበሳው ብዙ ነው፡፡ ሥነ ልቦናዊም፣ ፖለቲካዊም፣ ማህበራዊም ዝግጅት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የልዩ አጋዥ ተቋማት መኖር ግድ ነው፡፡ የሲቪክ ማህበራትን መፍጠርና ያሉትንም ማጠናከር ያሻል። ለሀገር የሚበጅ ሀሳብን በአማራጭ እንዲያቀርቡ መንገዱን መጥረግ የጥበብ መጀመሪያ ነው፡፡ ሀሳብን አለመገደብ ልዩ ልዩ የዕድገት አማራጮችን እናይ ዘንድ ያግዘናል፡፡ ምንም ቢሆን ምንም፣ ለተስፋ መቁረጥ ቦታ አለመስጠት የጥንካሬያችን መፍለቂያ ነው፡፡ እፊታችን የተደቀኑ እልህ አስጨራሽ እንቅፋቶች ሊኖሩ መቻላቸው የማይታበል ሀቅ ነው፡፡ ቀበቶን ጠበቅ አድርጎ በዙሪያችን ያሉ ሰዎችን አጠናክሮ፣ በሆደ - ሰፊነት መስመር የጋራ ቤታችን የሆነችውን ሀገራችንን ከትናንት ወደተሻለ ነገ ለማሸጋገር ጥረት እናድርግ፡፡ ልዩነት የለም ብለን አናስብ፡፡ ይልቁንም እናጠበዋለን ብለን እንመን! ሁሉም መንገድ ወደ ድል ያደርሰናል ብለን አንገበዝ፡፡
“ህዝብ ያላማከረ ንጉሥ፣ አለአንድ ዓመት አይነግሥ” የሚለውን የአበው ብሂል አንዘንጋ!
“እንግዲህ ንጉሡ ምን እራስ አላቸው
ሁሉ በየአቅጣጫው እያደሙባቸው” የሚለውንም አንርሳ፡፡
ገጣሚው፤
“እንግዲህ ወገኔ ዳሩን እወቅና
መካከሉን ዳኘው በጥበብ ያዝና
አይፈለፈልም ደረቁ ባቄላ
እሳት አይገባውም፣ ርሶ ካልተበላ
አለቀ እምንለው ሰው አላቂ አይሆንም
ተሳፋሪው እንጂ አሳፋሪ አይወርድም!” የሚለውንም አንዘንጋ!
ከሁሉም በላይ ግን ረግጠን የመጣነውን መንገድ ሳንረሳ፣ የመሄጃችንን አውራ ጎዳናውንና መጋቢ - መንገዱን እንለይ! እንደ ጥንቱ ሚሲዮናውያን የኋሊት የሚፈነዳ መድፍ ሊሰሩልን የሚመኙትን ታላላቅ መንግሥታት በዐይነ - ቁራኛ እንይ!! ደግ - አሳቢ ነው ያልነው መቼ ክፉ - አሳቢ እንደሚሆን አይታወቅምና በተጠንቀቅ መጠበቅ ብልህነት ነው፡፡ ዮሐንስ ቤል እንዳለው፤ የሀገራችን ደወል “ፍርሃት … ብልሃት … ብልሃት … ፍርሃት …” እንደሚል ማዳመጥ መታደል ነው! “ሽቅብ መሳብ፣ ቁልቁል መሳብ፤ ለአገር አንድነት ሲባል” የሚለው እሳቤ ግን መቼም የማይሞት ነው! እያንዳንዱ ድል የራሱን መስዋዕትነት ይጠይቃልና!!    

Read 3998 times