Saturday, 07 April 2018 00:00

ንብ ባንክ ከኬፒኤምጂ ኩባንያ ጋር ውል ተፈራረመ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ለቀጣይ አምስት ዓመታት የሚያገለግለውን ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ለማዘጋጀት “ኬፒኤምጂ ኢስት አፍሪካ ሊሚትድ ኩባንያ ጋር ባለፈው ረቡዕ ከሰዓት በኋላ ቦሌ ደንበል ህንፃ ላይ በሚገኘው የባንኩ ዋና መሥሪያ ቤት ተፈራረመ፡፡
የባንኩ የዲሬክተሮች ቦርድ፣ የሥራ አስፈፃሚዎችና የኬፒኤምጂ ተወካዮች በተገኙበት በተፈፀመው የውል ስምምነት ሥነ - ሥርዓት ላይ የባንኩ ፕሬዚንት አቶ ብሩክ ፎንጃ እና የኬፒኤምጂ ኢስት አፍሪካ ሊሚትድ ኩባንያ ዳይሬክተር ሚስተር ዴቪድ ሌሂ ፊርማውን ፈፅመዋል፡፡
ስትራቴጂክ እቅዱን ለማሰራት ባንኩ ጨረታ ካወጣ በኋላ ለመወዳደር ጨረታውን ከወሰዱት 23 ድርጅቶች መካከል ስምንቱ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች መሆናቸውን በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ የተገለፀ ሲሆን በተደረገው የቴክኒክ ምርመራ ኬፒኤምጂ ኢስት አፍሪካ ሊሚትድ የተሻለ ውጤት በማግኘት፣ ጨረታውን አሸንፎ ለስምምነት መብቃቱም በዕለቱ ተገልጿል፡፡
ስትራቴጂካዊ ዕቅዱ የባንኩን ድርጅታዊ አወቃቀር ከዘመኑ ጋር እንዲዘምን በማድረግ ለሰራተኛውም ሆነ ለተገልጋዩ የተቀላጠፈ አሰራርና አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል፡፡
ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ፤ በአሁኑ ወቅት 25 ቢሊዮን ብር ጠቅላላ ሀብት ያለው ሲሆን ተቀማጩ 20 ቢ. ብር፣ በብድር የተሰጠ 13 ቢ. ብር፣ እንደደረሰ ጠቁሟል፡፡ 209 ቅርንጫፎችና እንዲሁም ከ4 ሺህ በላይ ሰራተኞች ያሉትና ከቀዳሚ የግል ባንኮች አንዱ እንደሆነም ተገልጿል፡፡

Read 3111 times