Saturday, 07 April 2018 00:00

“መካር የሌለው ንጉሥ አለ አንድ ዓመት አይነግስም”

Written by 
Rate this item
(5 votes)

“ሁሉም ነገር ይለወጣል፡- ከለውጥ ህግ በስተቀር”
ከዕለታት አንድ ቀን የፋሲካ እለት እናት፣ አባት፣ እንግዳና ልጅ ለመፈሰክ እየተዘጋጁ ነው፡፡ ልጁ እንግዳ ኖረም አልኖረም ከሰው ፊት እያነሳ የመብላት ልማድ አለው፡፡
እናትና አባት ተሳቀዋል! እንግዳ ስለ ልጁ ጠባይ አያውቅም፡፡ እናትና አባት ልጁን ቆጥ ላይ አውጥተው አሠሩት፡፡
ልጅ ማልቀስ ጀመረ!
እንግዳው ግራ ገባውና፤
“ምን አርጎ ነው ይህንን ልጅ ያሠራችሁት?” ሲል ጠየቀ፡፡
አባት፤
“አመል አለበት፤ ከሰው ፊት እያነሳ ስለሚበላ በልተን እስክንጨርስ ቢታሠር ይሻላል ብለን ነው”
እንግዳው፤ በሀፍረት፤
“ይሄ በዕውነቱ የማይገባ ነገር ነው፡፡ ነውር ነው! በሉ ፍቱትና መጥቶ አብሮን ይብላ፡፡ ልጅ‘ኮ ነው ምን ያውቃል?”
ባልና ሚስት የምንተ-እፍረታቸውን ልጁን ፈቱትና ገበታው ዘንድ እንዲቀርብ ተደረገ፡፡
ዶሮ ወጡ መጣ፡፡
ለባል ፈረሰኛ ወጣ፡፡
ለእንግዳ እግር ተሰጠ፡፡
ለሚስት መላላጫ ወጣለት፡፡
ለልጅ ዕንቁላል ቀረበለት፡፡
ወጡ ወጣና መቀመስ ተጀመረ፡፡
ይሄኔ ልጅ የእንግዳውን የዶሮ-እግር ላፍ አደረገ፡፡
አባት፤ “እንዴ ይሄ ባለጌ!”
እናት፤ “ይሄ አሳዳጊ የበደለው ልጅ!” አለች እናት
ልጁ ሌላ ቤት ያደገ ይመስላል፡፡ ሌላ እግር ለእንግዳው ወጣለት፡፡
ልጅ ከትንሽ ሰኮንድ በኋላ አሁንም የዶሮዋን ሥጋ ላፍ አደረጋት፡፡
እናት- “ኧረ ይሄ አሳዳጊ የበደለው ልጅ ምን ቢደረግ ይሻላል?”
አባት “ማጋጨት ነው የሚሻለው!” ብለው ብድግ አሉ፡፡
እንግዳው፤ “ኧረ ልጅ ነው ተውት፡፡ የኛ ልጆችኮ ድስቱን ራሱን ይዘው ነው የሚሮጡት።
አባት፤ ኮራ ብለው፡-
“አይ፤ ለሱስ ደህና አርገን ቀጥተነዋል!”
* * *
አስተዳደግ ከቤት ይጀመራል፡፡ ት/ቤት ይከተላል፡፡ ህብረተሰብ ይቀበለዋል፡፡ በዚህ ሶስት ማዕዘን ውስጥ ነው ትውልድ የሚቀረፀው፡፡ በሥነ-ስርዓት የተቀረፀ ወጣት ለወግ-ማዕረግ ይበቃል፡፡ አድጎ ተመንደጎ መልካም ዜጋ የመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ መልካም ወጣቶች ተረካቢ ትውልድ የመሆን ኃላፊነታቸው ለመወጣት ዝግጁ ይሆናሉ፡፡ ተስፋቸው ብርሃናማ ይሆናል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ለአደራ መብቃትን የመሰለ ነገር የለም፡፡ አንድ ገጣሚ እንዳለው፡-
“መፅሀፍ አንብቤ እፎይ ባልኩኝ ሰዓት
ምነው ዛፍ በሆንኩኝ እያልኩ እመኛለሁ   
ወይ ፍሬ አፈራለሁ
ወይ ጥላ እሆናለሁ
ቢያንስ አንዲት ወፍ በግል አምናኝ ተቀብላኝ
ጎጆ ቤትዋን ፈቅዳ እንደምትለግሠኝ፤ እተማመናለሁ፡፡
ያኔ በትክክል ለአደራ እበቃለሁ!” ማለት አግባብ ነው፡፡ እንደዚህ ያለ ሀሳብ ያለው መሪ ማግኘት መታደል ነው፡፡
ብዙ ቃል ተገብቶልን ላልተሳካልን ህዝቦች፤ ዛሬም ቃል ብርቃችን ነው፡፡ “ጊዜ የሥልጣን እጅ ነው!” እንዳለው ፀጋዬ ገ/መድህን፤ ጊዜን መጠበቅ በጎ ነው! ጊዜ የተግባር ፈተና ነውና! በሀገራችን በኢትዮጵያ አያሌ ያመለጡ ዕድሎች ነበሩ፡፡ በ1966 እና በ1983። ዛሬ ሌላኛው ዕድል የተከሰተ ይመስለናል፡፡ እንደገጠመኝ ሳይሆን እንደ ሂደት አስበን አጋጣሚውን መጠቀም ይጠበቅብናል! መሪዎች ምን ያደርጉልናል ከማለት ባሻገር እኛ በሀገራዊ ግዴታችን እንደዜጋ፣ እንደ ቡድን፣ እንደ ተቋም … ምን ዓይነት አዎንታዊ ሚና እንዲኖረን እናድርግ? እንበል፡፡ መሪዎችን ህዝቦች ሊቀርጿቸው እንደሚችሉ አንዘንጋ! ሁኔታዊ አስተዋፅዖዎች አያሌ ናቸው፡፡ ግብዓቶችን ፈልፍለን እንወቅ፡፡ ጊዜን በአግባቡ፣ እንጠቀምበት፡፡ የመደማመጥ ባህላችንን እናስፋ፡፡ ሥርዓትን በአግባቡ ለመለወጥ ተቋማዊ አቅም እንገንባ፡፡ ዲሞክራሲን በልካችን እንስፋ!
“ሁሉም ነገር ይለወጣል-ከለውጥ ህግ በስተቀር!” ለውጥን መውደድ እንጂ መፍራት አያስፈልግም፡፡ ትዕግሥትና ሆደ ሰፊነትን ማስፋት እንጂ “ትዕግሥት ፍርሃት አይደለም” እያሉ መፎከር አይበጅም፣
በጥንቃቄና በብልህነት አገርን ማደራጀት፣ በዙሪያችን ያሉ ወዳጆችን በሚገባ ማቀፍና የልዩነት ባለቤቶችን ማክበር፣ በቀና ልቦና ማነጋገር ወሳኝ ነው! አማካሪዎች የሥራ-ቦታ መፍጠሪያ አካላት መሆን የለባቸውም! በአገር- መውደድና ወገባቸውን ጠብቅ አድርገው የሚያሰሩ ሊሆን ይገባል! መልካም አማካሪዎችን ማግኘት ሰማኒያ በመቶ ሥራን ማገባደድ ነው! ለሀሳብ አክብሮትና ዋጋ መስጠት፣ ለትክክለኛ ግምትና ለሁነኛ ዕቅድ መሠረት የመጣል ያህል ነው! ከሁሉም በላይ፤ “መካር የሌለው ንጉሥ፣ ያለ አንድ ዓመት አይነግሥ” የሚለውን አንርሳ!

Read 3339 times